ውዳሴ ዘ ንጉሡ ጥላሁን!!!

Wednesday, 07 February 2018 13:23

 

 

በአንድነት ቶኩማ

 

አንድ ወቅት አቶ ንጉሱ ጥላሁን ‹‹የአማራና የትግራይ ሕዝቦች አብረው ታግለዋል ሞተዋል፣ በአንድ ጉድጓድ ተቀብረዋል›› ያሉትን ቃለ መጠይቃቸውን አንብቤ ብደሰትም የፖለቲካ ፍጆታ መስሎ ስለተሰማኝ አድንቄ ሳላደንቅ ሰነበትኩ። ወድጄ እንዳይመስላችሁ። በኢህአዴግ እቅፍ ስር ያሉት ሁሉ አሽንፈው ማማውን መቆናጠጥ ስለሆነ ዋናው ግባቸው ሁልጊዜ ይጠረጠራሉ። መጠራጠራችንን እሳቸው እንዳሉት ‹‹ከጉም አልዘገነውም›› ኢህአዴጎችን ስለምናውቃቸው ያገኘነው ነው። ሌላ አይደለም። እሳቸውም ከዚያው መንደር ስለሆኑ ከማመን በፊት መጠርጠርን እንድንመርጥ ያደርገናልና። ያልጠረጠረ ተመነጠረ ይባል የለ?


ለምሳሌ ያክል አቶ ንጉሱ የወልቃይትን ጥያቄ ትክክለኛ እና የመልካም አስተዳደር እጦት ያመጣው ጥያቄ ነው ብለው ለሰንደቅ ጋዜጣ ተናግረው ነበር። መናገር፣ መሰብሰብ፣ ሃሳብን በነጻነት መግለጽ ተገቢና ትክክለኛ መንገድ ነው ሲሉ በጊዜው የነበረውን የጎንደርን እና የባህርዳሩን ሰልፍ አድንቀዋል። የተለመደው ተቃዋሚዎችን፣ ሻቢያን እና ግንቦት ሰባትን ዋና ምክንያት ማድረጉንና በተለመደው መንገድ መክሰሱ እንዳለ ሆኖ።


አቶ ንጉሱ ንጉሱ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እየነጠረ የመጣው ሰብዕናቸው ከሁሉም በላይ እውነቱን መናገር መጀመራቸው ሕዝቡን ማስደነቅ ጀመረ። ለምሳሌ በሁለት የመገናኛ ብዙሃን የተላለፈውን ‹‹የኦሮሞ ሕዝብ የአማራን ሕዝብ እያረደ›› ነው የሚለውን ጫጫታ በአሁኑ ሰዓት የኦሮሞ ሕዝብ አማራን ለማረድ ይፈልጋል ብለን አናምንም ሲሉ ውሃ ቸለሱበት። ተደነቅን!!! ወንጀሉን የሰራው አካል አለ እናጣራለን ሲሉም ተደመጡ። በዚህም ምክንያት ተጠመዱ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን በአንክሮ እና በመጠነኛ የልብ መክፈት ተቀበላቸው። ጥርጣሬው እንዳለ ሆኖ። ያም ሆነ ይህ ግልጽ ለመሆን ከሞከሩት አንደበት ርቱዕ ተናጋሪ ተርታ የሚመደቡ ናቸው። ስለ ትግራይ ሕዝብና ሰለ አማራ ሕዝብ የተናገሩት ቢሆንም አስገራሚ ነበር።


ታዲያ አቶ ንጉሱ ምንም እንኳ በገዥው ፓርቲ የተሾሙ ቢሆንም ጥቅል ምንደኛ ሆነው የአባቶቻቸውን ደም እና አጥንት የተከሰከሰበትን ምክንያት እና ዓላማ ዘንግተው በባንዳዊ ስሌት ሕዝባቸውን ለመካድ ህሊናቸው አልፈቅድ ብሎ ሲሞግታቸው ሰሞኑን አየን። ‹‹መኰንን ሐሰተኛ ነገርን ቢያደምጥ፥ ከእርሱ በታች ያሉት ሁሉ ዓመፅኞች ይሆናሉ።›› (ምሳሌ 29:12) የሚለው ገበቷቸው ይመስላል ሃሰተኛ ነገር ያንገሸገሻቸው እና ከእውነት ጋር ለመጣበቅ የወሰኑት።


በአባትዋ የምታላግጥን የእናትዋንም ትእዛዝ የምትንቅን ዓይን የሸለቆ ቍራዎች ይጐጠጕጡአታል፥ አሞራዎችም ይበሉአታል። (ምሳሌ 30:17) የሚለውን ያነበቡ ይመስል በአባታቸው ለመደራደር አልፈለጉም። ጥሩ ነው። ምንም ክፋት የለበትም። ክብር እንጂ።


ታሪክን መማር የማይሹ ቱባ ባስልጣናት የታወቁትን ስመ ጥር አርበኛ የአማራ ራዲዮ ማንሳት አልነበረበትም ብለው ሲገመግሟቸው ያሳዩት ጽናትና ለኢትጵያ ሕዝብ አባቶች ያሳዩት ተቆረቋሪነት ያስደንቃል። በእውነት ከባንዳዊ ተላላኪነት ይልቅ የአባቶች ተከላካይ ሆነው መገኘታቸው በእውነት የልጥፍ ማንነት ውጤት ነው ለማለት አይቻልም። ይህ ንጹህ አቋማቸው ነው ለማለት ያስደፍራል።


አቶ ንጉሱ እወነትም ሲሳይ ሆነው ታይተዋል። የኢትዮጵያ ሲሳይ ። ወይም የሕዝቦች ጥላ። ስማቸውስ ጥላሁን የሚል ቃል አለበት አይደል። ዛሬ ለሕዝብ ታሪክ ጥላ ካልሆኑ መቼ ሊሆኑ ነው ከሞቱ በኋላ? በተለይ እውነት ለሚሻ ሕዝብ ዘብ ነበሩ ማለት ይቻላል።


በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን የውይይት መድረክ ላይ የአማራና የኦሮሞ ዘጋቢዎችን ሆን ተብሎ እንዳይጠሩ ከተደረጉ በኋላ ግምገማ ሊደርግ እንደሆነ የተገነዘቡት አቶ ንጉሱ በሸፍጡ ይገረሙና የአማራን ዘጋቢዎች በስብሰባው ላይ በራሳቸው ውሳኔ እንዲገኙ አድርገዋል። በዚህም ሳይቆጠቡ ለምን የአማራና የኦሮሞ ዘጋቢዎች እንዳይገኙ እንደተደረገ ሲገልጹ ‹‹የቤትና የእንጀራ ልጅ የለም›› ብለው በአደባባይ ሞግተዋል። በዚህ አነጋጋር ለስብሰባው በክብር የተጠሩት የቤት ልጆች ያልተጠሩት የእንጀራ ልጆች ነበሩ ማለታቸው ነው። የሰውየው ድፍረት ያስገርማል። ‹‹ሲባዛ ማርም ይመራል›› ያሉ ነው የሚመስለው።


የሚያስገርመው አቶ ንጉሱ ከተከሰሱበት አንዱ ምክንያት በትግራይ የተዘገበን ሥራ የአማራ ቲቪ አላስተላለፈም ተብሎ ነው። ቲቪው ተላላኪነቱን አቁሟል መሰለኝ። ተደጋግፈው ቢሰሩ እሰየው ያስብላል። ሆኖም ግን ታማኒነቱን አረጋግጦ ማቅረብ ይገባል። አንዱ ላኪ አንዱ ተላኪ ሊሆን አይገባም። መመጋገብ እንጂ። እሱማ ጠቃሚ ሆኖ ሲገኝ ከሲኤን ኤን፣ ቢቢሲ፣ አልጄዚራስ ይወሰድ የለ?


‹‹ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ›› እንዲሉ ሌላው የተከሰሱት ለምን የተለያዩ ምሁራንን ለውይይት በአማራ ቲቪ አቀረባችሁ በሚል ነበር። ንጉሱ መች የዋዛ ሆኑና። ለዚህ ክስ መልስ ሲሰጡ ልሂቃንን አቅርበን ማወያየታችን ትክክል ነበር። ትክክልም ነው ብለዋል። የታሪክ ጀግኖችን በማውሳቱም የአማራ ቲቪ ተከሷል። ለምን አማራ ናቸዋ የተነሱት። ስለ ኃየሎም ሲነሳ ማን ምን አለ እና ነው ጣሊያንን ያርበደበደው አባ ገስጥ ወይም ራስ አበበ አረጋይ ሲነሳ ችግር የሚሆነው? ተው እንጂ። ደግነቱ አቶ ንጉሱ መች የዋዛ ሆኑ መንፈሳቸው ተቆጣ። አያትን ማስቀማት ወይም ማዋረድን የሚቀበሉ ሆነው አልተገኙም። ወይ ተላላኪነታቸውን ትተዋል ወይም ከመጀመሪያውም ተላላኪ አልነበሩም ማለት ነው።


‹‹አባቱን የሚረግም፥ እናቱንም የማይባርክ ትውልድ አለ።


ለራሱ ንጹሕ የሆነ የሚመስለው ከርኵሰቱ ያልጠራ ትውልድ አለ።›› (ምሳሌ 30፡11-12) የሚለው ምሳሌ የተከሰተላቸውና አባታቸውን ለመርገም ያልፈቀዱ ሆነው ተገኙ።


አቶ ንጉሱ አንዱ የተከሰሱበት የቴዲ አፍሮን ‹‹አሮጌ ባንዲራ›› ደግፈሃል ተብለው ነበር። ቴዲ መቼ አሮጌ ባንዲራ እንዳሰራ አለወቅሁም። ልጁ ወጣት በመሆኑ አዲስ እንጂ አሮጌ ባንዲራ ሊኖረው እንዴት እንደቻለ አልገባኝም። እንደመሰለኝ ከሆነ ምልክት ያልተቀመጠበትን የድሮውን አረንጋዴ፣ ቢጫ እና ቀይ የተባለውን ባንዲራ ሳይሆን አይቀርም። ጨርቅ ነው የተባለውን ማለቴ ነው።


መቼም እሳቸው ቂል አይደሉም አሮጌ የተባለውን ወይም ጨርቅ ነው የተባለውን የአባታቸውን ባንዲራ አያነሱም። ቢያነሱም ችግር የነበረው አልመሰለኝም። ቴዲን ለምን ጋበዛችሁ መሰለኝ ዋናው ድብቁ ጠብ። በሌሎች ሰዎች አዕምሮ የተቀመጠን ሃሳብ ያንተ ነው ብሎ ሰውን ለማሸማቀቅ መሞከር ለአርበኛው ልጅ ለንጉሱ አልተዋጠላቸውም። ከሳሾቻቸውን የምን ማምታታ ነው ሲል ሞገቷቸው። የአዲሱ ዘመን ትውልድ እና የአረበኞቹ ሕብር አዕምሯቸውን ወጥሮ ይዞት እንዴት ዝም ይበሉ?


አታስዋሹኝና ስብሰባው ግርሻ የተባለውን ባንዳ አቡነ ጴጥሮስን ሲሞግት ያቀረበውን ታሪክ ነው ያስታወሰኝ። ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን ነው የደረሰው። ‹‹ጴጥሮስ ያችን ሰዓት›› ትሰኛለች። ግርሻ የተባለው ባንዳ አቡነ ጴጥሮስ በአባቶቻቸው እንዲያፍሩ የተናገረውን ሙግት የሰበሩትን ካህኑን መሰሉኝ። የአያቶቻቸውን ታሪክ ሲከላከሉ አቶ ንጉሱ በአጸደ ስጋ ላሉት የሕያዋን ካህን ነበሩ። ‹‹ደብተራ ዘ አማራ›› ወይም ‹‹ካህነ ኢትዮጵያ››ነበሩ። በእውነት የአማራ ቲቪን መክሰስ ነበርን ዋና ግቡ? ሌላ የነበረው ይመስለኛል። አቶ ንጉሱ እንደ ባንዳዎቹ ‹‹እኔ እኮ እኔነቴን ብቻ ነኝ አባቴ (አለቆቼ)። እነሱ በጊዜአቸው ሕይወታቸውን ኖረው ሞታቸውን ሞተዋል። እኔስ የጊዜዬን ሕይወት ኖሬ የጊዜዬን ሞት እንድሞት አይፈቀድልኝም?›› አላሉም።


አቶ ንጉሱ አኮቴት ይገባቸዋል የምለው የአያቶቻቸውን እና የአሁኑን ዘመን ትውልዶች ለማዳን ፍርሃትን አውልቀው ጥለው ስላየሁ ነው። ‹‹…ግን ልጄ እኔ-እኔ የሚለው የአንተነትህን አካል ያለበስከው እኮ ያው እናት አባትህ የሰጠሁን ሥጋና ደም ነው። ከነሱ ስጋና ደም ተካፈልክ እንጂ ይህን አንተነትህን አንተ አልፈጠረከውም።›› የሚለው የጸጋዬ ገብረመድህን ‹‹ጴጥሮስ ያችን ሰዓት›› ሙግት በገጽ 25 ላይ ያቀረቡትን የፈተና ማርከሻ ፍልስፍና የተቀበለ ይመስላሉ።


አገራቸውን ወይም ሕዝባቸውን አሰድበው በየትኛው ማንነት ሊቆሙ? ይልቁንም ‹‹ታዲያ ይኽን ከወላጆችህ በውርስ ተቀብለህ፣ በልደት ተቀጥላ፣ ያጎለመስከው አንተነትክን፣ ይኸ በፍርሃት እያኮላሸ፣ በሽኩሹክታ እያስጎለበተ፣ እንደ ድመት ግልገል በጥርስ የሚያሰቅል፣ በጥሻ የሚያስሸሽግ፣ መታሰቢያነታቸውን የሚያረክስና የሚያስወግዝ፣ መዝለቅ የምትለው ዘለቄታህ፣ እውነተስ ከዚህች ከድፍን ሌሊት ባሻገር፣ ከዚች ከብኩን ዘመንና ከመቃብራቸው በሻገር፣ የዘለዓለም ወቀሳቸው አያስከትልብህ ይመስልሃልን?›› የሚለው መነባንብ ገብቷቸው አቶ ንጉሱ ለእወነት ቆመው አየናቸው። ከዚህ በኋላ ቢቀመጡ እንኳ ታሪክ አቁሟቸዋል እና ቆመው ይኖራሉ። የአማራ እና የኦሮሞ ቲቪ አባቶቹን እንዳያነሳ እገዳ ሊጥልበት ያሰበ ኀይል አየን እኮ እባካችሁ!። ልክ አይደለም።


ነውር ተወደደሳ!! ችግር መኖሩን ያሳያል። አቶ ንጉሱ አንዱ የተተቹበት በቴዲ ዘፈን ኮንሰርት ነው። ጥያቄው ቴዲ ህገ መንግስት የማያከብር ሆኖ ከተገኘ ለምን እሱ ሙሉ ሰው ነው እና አይጠየቅም? ‹‹ሊበሏት የፈለጓትን…›› ሆኖ ነው እንጂ ነገሩ። የኦሮሞው ዘፋኝም ለኦሮሞ ቲቪ ጣጣ አምጥቷል። ‹‹ጅብን ሲወጉ በአህያ ይጠጉ›› እንዲሉ ሆኖ ነው እንጂ።


አቶ ንጉሱ ተቆርቋሪነታቸው ከእንጀራ ናፍቆት የፈለቀ አልመሰለኝም። አልተለጎሙማ። ‹‹ከመውግዝ ከመአርዮስ›› ሲባሉ ውግዘቱን በራሳቸው ድፍረት ፈተው የአባቶቻቸውን መንፈስ ተውሰው በአደባባይ ድርጅታቸውን ሞግተው እርቃኑን አወጡት እንጂ። በመፍራት እና ባለመፍራት መንታ መንገድ አልቆዩም። አያቶቻቸው ለእውነት ሲቆሙ እስከሞት መሆኑ ታወሳቸውና እስከ መናገር ደፈሩ። ውሸትና ሸፍጥ ሁልጊዜ እየተማጉ መኖር ሰለቻቸዋ!!!ምን ያድረጉ የወከሉትን ሕዝብ ማሴጠን(demonizing) አንገሸገሻቸው። በዚህ ምክንያት እውነትን ደፍረው መናገር ፈለጉ አደረጉትም። እጅ እንነሳለን!!! ውለታዎን አንረሳውም። ታሪክ ሁልጊዜ በትዝታዋ ማህደር ታኖረዎታለች። ሁሉም ካድሬዎች ከቻሉ ከእርስዎ ይማሩ።


የንግግር ብዝሃነትን ሰበኩ። ንግግርዎ ሲጣፍጥ። ‹‹multitudes of ideas›› መስተናገድ አለበት አሉ። ጎሽ እንዲህ ነው እንጂ በራስ መተማመን።
አቶ ንጉሱ ያነሱት ሃሳብ በተለይ ስለ ሁለት ሚዲያዎች መሳጭ ሙግት ነበር። ‹‹በጌታዋ የተማመነች በግ ላቷን ውጭ ታሳድራለች›› የሚለውን ስነ ቃል ያስታውሳል። ኦሮሞ አማራን አረደው ብለው ዜና የዘገቡትን ወቅሰው ሕዝብን ከሕዝብ ለማስተላለቅ የተላከ የጥፋት መልክት ሰባኪዎች እንደሆኑ ስለ አመኑ አጥብቀው ኮንነዋል። ይህን ያደረጉት ደግሞ መሰለኛቸውን አክለው ‹‹በብሮድ ካሰቲንግ ባለስልጣን ተማምነው ነው›› ብለዋል። እግዚአብሔር ፈጽሞ የሚጠላውን ነገር ኮንነዋል።
‹‹እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች ናቸው፥ ሰባትንም ነፍሱ አጥብቃ ትጸየፈዋለች፤
ትዕቢተኛ ዓይን፥ ሐሰተኛ ምላስ፥ ንጹሕን ደም የምታፈስስ እጅ፥ ክፉ አሳብን የሚያበቅል ልብ፥ ወደ ክፉ የምትሮጥ እግር፥ በሐሰት የሚናገር ሐሰተኛ ምስክር በወንድማማች መካከልም ጠብን የሚዘራ።›› (ምሳሌ 6፡16-18) የሚለውን አስታወሰኝ። ልክ ነው። አገር የሚመራው በብስለት እና በመተራረም በመሆኑ፤ ሲሆን ሰውን ከሰው ጋር ማቀራረብ ነው እንጂ ማናጨት ምን ይጠቅማል ሲሉ ነው የሞገቱት።


ይህን አይተው እና ሰምተው ዝም ያላሉት ሞገደኛው አቶ ንጉሱ እነዚህን ሚዲያዎችን ጠቅሰው የብሮድካስቲንግ ሆኑ የፌዴራል ኮሙኒኬሽን ባለስልጣናት ስልጣን መልቀቅ ነበረባቸው ብለዋል። በኢህአዴግ ዘመን አንድ ባለስልጣን ‹‹ሕዝብን ይቅርታ ጠይቆ አጥፊው ባለስልጣን ሥልጣን መልቀቅ አለበት›› ሲሉ እና እኔ ስሰማ የመጀመሪያዬ ነው። ቀደም ሲል በሙስና የተጠረጠሩት እና ለሥልጣን አስጊ የሆኑት መልቀቃቸው እውነት ነው። የኢህአዴግ ባለስልጣን የኢህአዴግን ባለስልጣንን ‹‹ስልጣን መልቀቅ›› ነበረበት ሲል ስሰማ ትንግርት ሆነብኝ። በእውነት አድኖቆቴን ልነፍገዎ አልችልም።


ባልሳሳት በሌላ አገር ቢሆን ስልጣን ያስለቅቃል ነው ያሉት። በእኛ አገር ጉደኛው ይሾማል። በወንድማማች መካከል ጠብን የሚዘራ ይሸለማል። የሚሳደብ ያድጋል። ምክንያቱም ሕዝብ የማይወደው ለአጼዎች ጥሩ ባሪያ ይሆናል የሚል ስንኩል አስተሳሰብ ስላለ ነው።


ስለ አገር መገንባት እና በጥንቃቄ መምራት የሰጡት ገለጻ ሰውየው እንዴት በብስለት አደባባይ የሰነበቱ አርቆ አስተዋይ ሰው መሆናቸውን ያሳያል። ዘገባ በከፍተኛ ጥንቃቄ ነው መዘገብ ያለበት ሲሉ ነው የሚነሱት። ግለሰቡ የአማራ ቲቪ ስህተትም አምነዋል። ይሁን እንጂ በጊዜው የተደረገው ግምገማ ልክም አይደለም ብለዋል። ለይቶ ማጥቃት ነው ሲሉ ነው የሞገቱት። የግምገማ አካሄዱም ልክ አይደለም ብለዋል። ሁለቱን ቲቪ ለመቀጥቀጥ የተቀመጠ ቀመራዊ ሴራ ነው የሚል አስተያየትም የሰጡ ይመስላል። ነገሩ


‹‹አውጪ አውጪኝ
ሁላችን ተቀምጠን
ምነው ጪን ብቻ መረጡ
የ‹‹ጠን›› ቤት ረሱ
‹‹ጣን›› እየዘነጉ
አውጪ አውጫጪኝ
አውጪ ብቻ አሉ። (አውጫጪ፡- የሸንበቆ ባህር ገጽ 76) የምትለዋን ግጥም አስታወሰኝ።


ግለሰቡ በግልጽ ታሪክን ማስተማር ተገቢ ነው ሲሉ ባልሰማም የታሪክን ትምህርት አስፈላጊነት ያውቃሉ። አማራና ኦሮሞ ተዋልዶ በአንድነት የኖረ ሕዝብ ነው ብለዋል። ታሪክ አዋቂነታቸውን ያሳያል። ታዲያ ድፍረቱ ከየት መጣ ከዚህ እውቀት ነው። የትግራይ ሕዝብና የአማራ ሕዝብ የረጅም ጊዜ ታሪክ አላቸው ብለዋል ይህም የታሪክ ሊቅ ያደርጋቸዋል።


ደረቅ ታሪክ ግን አይደለም ያነሱት። በጋብቻ፣ በሃይማኖት፣ በጂኦግራፊ እና በኢኮኖሚ የታሳሰሩ ሕዝቦች መሆናቸው ተገልጾላቸው ነው። በዚህ ሃሳባቸው ‹‹ከያለፍኩበት›› መጽሐፍ ጸሐፊ ከዶ/ር ፍስሐ አስፋው ጋር ይመሳሰላሉ። ‹‹የአሰበ ተፈሪ ትምህርት ቤት የታሪክ አስተማሪዬ የነበሩትን መሪጌታ ሳስታውስ ሁልጊዜ የሚነግሩንን ‹ታሪክን ማወቅ ኩራት ነው። ክብር ነው። የማንነት መገለጫ ሰነድ ነው። ታሪክ የሌለው…ከእንስሳ ተራ ከመፈረጅ ባሻገር ክብርም ሆነ አለኝታ ያጣ ተገዥ ነው የሚለውን ቃላቸውን አብሬ አስታውሳለሁ።›› (ገጽ 16)እንዳሉት ነው። የግንቦት 20ን ታሪክ እየተናገሩ ሌላው የሕዝባቸውን ታሪክ እንዳይናገሩ ለምን ለመከልከል ተፈለገ? እንስሳ ለማድረግ ነውን? ወይስ ቀጥቅጦ ለመግዛት? ለማንኛውም ቲቪው ታሪክ ያስተምር ዘንድ እናበረታታለን። ታዲያ የቲቪው ሰራተኞች


‹‹አንኮበር የአምሃየስ በር
አድማስ ፈጠር ኬላ ሰበር
አንኮበር የእምባ ላይ አገር።›› ሳይሉ እንዲኖሩ ተፈለጎ ነውን? ጸጋዬ ገ/ መድህን አንኮበር እሳት ወይ አበባ ገጽ 106) ይኼን መቼም አታደርጉትም።


አቶ ንጉሱ የመንግስት ሚዲያን ተዓማኒነት አንስተዋል። አነስተኛ መሆኑንም አክለው ገልጸዋል። ልክ ነው ሚዲያው ተአማኒነቱ የወደቀ ነው። ቅቡልነቱን ለማሻሻል ምን ይደረግ የሚለውን ሲያብራሩም ሕዝባዊ ወገንተኝነቱን ማሳየት እንደሚኖርበት ሳይጠቁሙ አላለፉም። የተአማኒነቱ ምንጭ ደግሞ እውነትን መዘገብ እና የሕዝብ ተወካዮችን በነጻነት ያለ ፍርሃት ማቅረብ ነው። ‹‹ምላሱን ከሚያጣፍጥ ይልቅ ሰውን የሚገሥጽ በኋላ ሞገስ ያገኛል።›› እንዲሉ። ለማንኛውም ደፍረው ስለገሰጹ አይደለምን ስለ እርስዎ ያወሳነው። ይበርቱ! ከፍትህ አደባባይ ፈጥነው አይውረዱ!!! ከቻሉ እዚያው ይሰንብቱ። ውዳሴውን እንደማንነሳዎ ቃል እንገባለን። ለጊዜው ውዳሴውን ያጣጥሙ የመንፈስ ስንቅ ይሆነዎታል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
156 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1011 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us