የጫካው ገዥ እምነ ነገደ አናብስት ንጉስ ነገስት ቀዳማዊ

Wednesday, 21 February 2018 11:55

 

ልጅ አምበራ

 

ባንድ ወቅት የዱር እንስሳት በሆዳቸው ከሚሳቡት በእግሮቻችው ከሚራመዱት፣ በክንፎቻቸው ከሚበሩት ሳርና ቅጠል በሎች፣ ስጋ ተመጋቢዎች እንዲሁም ያገኙትን ከሚመገቡት መካከል ከየዘሮቻቸው የተወጣጡና ሐሳባችሁ ሐሳባችን ነው፣ ልሳናቸሁ ልሳናቸው ነው። ጉዳያቸሁ ጉዳያችን ነው ተብለው የተመረጡት ተወካዮች በተገኙበት በተዘጋጀው ውይይት ላይ ልዩነታቸውን አጥብበው የጋራ በሚያደርጓቸው ጉዳዮች ላይ እንዴት መተባበር እንዳለባቸው እንስሳቱ ሲመክሩ ዋሉ።


‹‹ምድረቱን እንድንገዛት ምን እናድርግ። በሠው ልጆች የተወሰደብንን ብልጫ እንዴት እንቀልብስ›› የሚል ከጀንዳ ተይዞ ውይይት ተካሔደ። በውይይቱ የተለያዩ ሐሳቦች ተሠነዘሩ።
‹‹በእኔ ግምት የሠው ልጆች አኗኗር ሳይሆን የፍትሃዊነትና የእኩልነት ጉዳይ ነው ችግራችን›› አለች ከጦጣዎች የተወከለችው እንስሳ።


‹‹የለም የለም በጫካው ሠላም እንዲነግስ ከተፈለገ አንዳችን የሌላችን ጠላት መሆናችን ያብቃ›› አለ ዝንጀሮ ለጥቆም ጅብ የተባለው እንስሳ ስጋ ተመጋቢ ወዳጆቻችን በሠው ልጆች ደባና ሸፍጥ የተነሳ ምግባቸውን እያሳጡብን ይገኛሉ። ደኖች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጨፈጫፉ ነው። ይኸ ሁኔታ በተዘዋዋሪ እኛን የሚመለከት ሁኖ ሥላገኘነው የችግሩን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ከመቸውም ጊዜ ይልቅ የጫካውን ደህንነት ለማስከበር ውሳኔ ላይ ደርሰናል።›› ሲል

አንበሳም በበኩሉ ‹‹እኔ በበኩሌ በአያ ጀቦ ሃሳብ እስማማለሁ የሠው ልጆች መስፋፋት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እኛንም የሚጐዳ በመሆኑ ድርጊቱን አጥብቄ እቀዋመዋለሁ›› አለ
‹‹በስጋ በል ወንድሞቻችን ጥቃት በአፋጣኝ እንዲያስቆምልንና በሕይወት የመኖር ነፃነታችን እንዲከበርልን ጉባኤውን እጠይቃለሁ›› አለች ሚዳቋ።


‹‹ሁላችንም በሕይወት የመኖር ዋስትናችን የሚወሰነው ባለን ጥንካሬ ልከነው። በዱር አለም የኔ የሚባል ግዛት የግል የሚባል ክልል የለም። ሁሉም ነገር የሁላችን ነው። ማናችንም ብንሆን እንኳን የራሳችን አይደለንም። ትጋትና ጥንካሬ ከሌለን በሕይወት የመኖር መብታችን እናጣለን›› አለ”ች ተኩላ።


‹‹ጉባኤው ከግራም ከቀኝም ሐሳቦች እየተንሸራሸሩበት በእንስሳቱ አለም የሥጋት ምንጭ የሚባሉት ተለይተው የመፍትሔ አቅጣጫ ተሠጥቶባቸው በአንዳንድ ሥጋ በልና ተሳቢ እንስሳት ላይ በተለየ ሁኔታ ምክክር ተደርጐባቸው ተመጣጣኝ የሚባል ቅጣት ተጣለባቸው። በነገሩ ግራ የተጋባችውና ስብሠባው ለሳር በልና ደካማ የዱር እንስሳት ዋስትና ለሕይወታቸው የሚሠጥ ሳይሆን ሌሎች ተጨማሪ ሥጋቶችን የፈጠረ መሆኑን የበላይ እምባ ጠባቂ ተደርገው የተሾሙት እንስሳት ራሳቸውን እንኳን ከአዳኞቻቸው ወጥመድ የሚያስጥል ጥንካሬ እንደ ሌላቸው ሚዳቋ ሐሳብ ሠጠች።


የመድረኩ መሪ የሆነው እንስሳ አያ አንበሴ በበከሉ የሳርበል እንስሳትን ነፃነት ለመጠበቅ ሥጋ በሎችን መሾም ፍትሃዊነት ታማኝነት እንደሌለው በመግለፅ ከዚህ ይልቅ የሜዳ አህዮች ቆርኪዎችን፣ ደኩላዎች ዝሆኖችና ቀጭኔዎች ሌሎችም ሳር በል የሚያመሰኩትና የማያመሳኩት ሾክና ያላቸውና የሌላቸው እንስሳት ራሳቸውን ከጠላት የመከላከል አቅማቸውን በማጐልበት በወዳጆቻቸው የተጣለባቸውን ሐላፊነት በታማኝነትና በቅንነት እንዲወጡ ጉባኤው መወሰኑ መልካም መሆኑን አስረዱ። ለጥቀውም በመፈራራት ላይ የተመሠረተ አንድነት አላማቸውን ከግብ ለማድረስ እንደማይረዳቸው አስረዱ።


በዚህ ጉባኤ በአመዛኙ ትኩረት የተሠጠበት ጉዳይ የሳር በሉ እንስሳት የሕልውና ጉዳይ በመሆኑ በቀነ ቀጠሮው የተያዘው አጀንዳ ተርስቶ ነበር ማለት ይቻላል። በመሆኑም በሐቅም ሆነ በብልሃት ራስን ከጠላት አደጋ ለመከላከል ሲባል የእምባ ጠባቂ ተቋም ይመሰረት የሚለው የበራሪ እንስሳት ሐሳብ ከቁብ በመቆጠሩ ምላሽ አገኘ። በዚህ ሁኔታ መላዎች ዘዴዎች ተሠናድተው ሕጐችና ደንቦች ረቀው በጉዳዩ ላይ ሐሳብ እንዲሠጥበት ሲደረግ አያጅቦ የተባለው እንስሳ ስብሠባው ሥጋ በሎችን ያገለለ ለሳርና ቅጠል በሉ ወገን ብቻ ያደላ እንጂ የሥጋ በሉ የወደፊት እጣፈንታ እንዳልታሠበበት፣ በሥጋ በሉ ላይ የተሰናዳ ሸፍጥና ደባ መሆኑን፣ ይኼም ሁኔታ ከዘር ማጥፋት ወንጀል እንዳማይተናነስ ‹‹አድናችሁ አትብሉ መባሉ›› ‹‹በራችሁን ዘግታችሁ ሙቱ›› እንደ ማለት እንደሚቆጠር እና ጉባኤውም ተሠሚነትንና ዝናን ለማትረፍ ሲባል ሕቡዕ ፍላጐትን ያዘለ እና የእንስሳቱን ዘር ከማቀራረብ ይልቅ በልዩነት ውስጥ ያለውን አንድነት የሚጐዳ መሆኑን አስረዳ።


ቀጭኔ የተባለችው ሳርና ቅጠል በል እንሳስ በበኩሏ በአያጅቦ ሐሳብ እንደምትሰማማ ገልፃ በሥጋ በሉ እንስሳት የደረሠውን በደል ሳር በል እንስሳቱ በጉባኤ እንዲያስረዱ መደረጉ አግባብነት እንደሌለውና ለሌሎች አዳኝ እንስሳት ልምድን የሠጠና በምን አይነት ብልሀት ታዳኝን ማጥመድ እንደሚቻል ተሞክሮ የሠጠ በመሆኑ በጉባኤው የተደረሠባቸው ሥምምንነቶች በቀጭኔው ማኀበር እንስሳ ዘንድ ተቀባይነት እንደማይኖረው አስረዳች።


ለጥቃም ሁኔታዎችን ከላይ ሆኖ ለመከታተል የሚያስችል ቁመና ባለቤት እንደሆነች ሁሉ የነገሮችን ሥር መሠረትም ከምንጩ ለመገንዘብ የሚያስችል አእምሮ እንዳላት ገልፃ ይኼ ጉባኤ የአደባባይን አደን የከለከለ ሥውር ወጥመድ መሆኑን ገለፀች።


ተኩላ የሚባለው ሥጋ በል እንስሶ በበኩሉ የአያጅቦን ሐሳብ እንደሚደግፍ ከገለፀ በኋላ በእንስሳቱ መካከል ያንጃበበውን ፍርሀት ለመናድ እና በእውነተኛ ወዳጅነት ላይ የተመሠረተ አንድነት ለመመስረት ብቸኛው መንገድ አንደኛው የእንስሳ ዘር በሌላኛው የመኖር ሕልውና ላይ የተመሠረተ እንደሆነ አምኖ መቀበል መሆኑን አስረዳ።


የሳርና ቅጠል በሉን እንስሳት ስጋቶች ምላሽ ለመስጠት ከሚደረግ ስብሰባ ይልቅ እነዚህን ተፈጥሮአዊ ልዩነቶች እውቅና ለመስጠት ጥረት ማድረግና በማህበረ እንስሳቱ ዘንድ ይህን የማይታበይ እውነታ ማስገንዘብ ያስፈልጋል አለ።
አያነብሮ በበኩሉ “ባልደረቦቼ በሠነዘሩት ሐሳብ እስማማለሁ። እንደዚህ አይነት የተከፋፈሉ ልዩነቶችን ይዘን ምድሪቷን ተቆጣጥረን፣ የሠው ልጆችን መግዛት የምንችልበትን አቅም አናገኝም። ዳሩ ግን በሕይወት ለመቆየት የሚሆን ብልሀት ተፈጥሮ አዘጋጀታልናለች። ሁላችንም ውስጥ ጅብነት አለ። ምክንያቱም ከወዴት አቅጣጫ እንዲሆኑ የማናውቃቸው ሥጋቶች አሉብን። ሁላችንም ሚዳቋዎችን ነን፤ ሕልውናችንን ለማስረዘም ያለመተካት መሮጥ አለብንና ነው። ሁላችንም ጐሾችን በሕይወት ለመቆየት እንዋጋለንና ነው።


አንዳችን ያላንዳችን እንዳንኖር ሁነን ተፈጥረናል። ጅብ ያለሚዳቋ መኖር አይችልም። ዛሬ የምንመክርባቸው የሠው ልጆች ምንም እንኳን ተፈጥሮ የሰጠቻቸውን ሠብዓዊ አንድነት ድንበር እየፈጠሩ ሚስጥር እየመሠጠሩ፣ በፈጠሩት ሐይማኖትና ቋንቋ እየተከፋፈሉ ቢንዱትም የሚጠሉትን ጅብ ለአንድ ነገር አጥብቀው ይፈልጉታል።


እርሡም የበሏቸውን እንስሳት ቅሪቶች እንዲወገዱላቸው ሲሉ ጅብን አጥብቀው ይፈልጉታል። ያለ ጅብ ያለ ውሻ ሠዎች ኑራቸው ከቆሻሻ ጋር ይሆን ነበር ማለት ይቻላል።
በኔ እምነት ሥጋ በሎች በሳርና ቅጠል በሎች መንደር ድርሻ አይበሉ የሚል ሐሳብ መሠንዘር ቅጥፈት ነው። ይህንን ሁኔታ ከሥልጣን ፈላጊነት ለይተን አናየውም። ባንድነት ጫካውን መግዛት ይኖርብናል፤ ገዥነትን ለአንበሳ ብቻ አንተውም። ሥጋ የመብላት ግብር በምርጫ የተቀበልነው እጣ ሳይሆን ተፈጥሮ የጣለችብን ግዴታ ነው። የትኛውም ሳር በል በዱር በገደሉ ተንከራትቶ ሆዱን ከመሙላት ራስን ለመከላከል ሲባል በሚደረግ ውጊያ ሕይወቱን ከማጣት ቅጠል በል መሆን ይሻለኛል ብሎ ቅጠል በል ልሁን ብሎ የሆነ የለም።


ይልቁንስ ለሥጋ በል ወገኖቼ የሚሆን ምክር በዚህ አጋጣሚ መስጠት እፈልጋለሁ። ሳር በልና ቅጠል በል እንስሳቱ በዛፍ ላይ የሚንጠለጠሉት፣ በእግሮቻቸው የሚራመዱት በሰማይ በአክናፎቻቸው የሚበሩት ወገኖቻቸን ሕይወቶቻችን ናቸው። ልንከባከባቸው ይገባል። ሥናድን ቆጥበን ልንመገብ ይገባል። የምግብ እጥረት እንዳይገጥማቸው ደኖችን ከሠው ልጆች ጥፋት ልንጠብቅ ይገባናል። እነርሱን መጠበቅ ራሳችን መንከባከብ ነው።”


ጉማሬ የተባለው የውሃ ውስጥ እንስሳ በበኩሉ አስታራቂ ሐሳብ እንደያዘ ተናግሮ “እዩኝ እኔ ውብነኝ። በሥራዬም የምደጎም ታታሪ ነኝ። በሕይወት ለመቆየት የማንንም ፍቃድ አልጠብቅም፣ ነገር ግን ከራሴ ጋር ታርቄ የምኖር በመሆኔ ውሃውን ያለፍርሃት መኖሪያ ሁነኝ ብዬ የብሡንም ማዕዴ ነህ ብየው በእምነት በፍፁም ደስታ እኖራለሁ። ነገር ግን ግዙፍ ነኝ፣ ደግሞም ውብነኝ፣ የትኛውም አይነት እንስሳት ከእነምግቡ የተፈጠረ ቢሆንም እንኳን ማዕዱን የማክበር ግዴታ አለበት።


ታዳኞችም ቢሆን እራሳቸውን እንደተጠቂና እንደ ተጐጂ ከመቁጠር ይልቅ ያለ እነሡ ሊኖሩ የማይችሉ ደካማ ፍጥረት እንዳሏቸው መቁጠር አለባቸው። በመስዋዕትነት ውስጥ ያለውን ደስታ ለማጣጣም መሞከር አለባቸው። እኔ የሕይወት እንጀራ ነኝ ማለትን መማር አለባቸው። የሕይወት እንጀራውን በንቀት የሚመለከት ማንም ቢኖር ግን የተረገመ ነው። በመካከላችን ያለው ሠፊ ልዩነት እንዲጠብ ከተፈለገ በፍርሀት እና በጥርጣሪ ከመተያየት ይልቅ ፍፁም በጠነከረ አንድነት በሠላምና በፍቅር ጫካውን ለመጋራት ካስፈለገ የአዳኝነት እና የታዳኝነት ሥሜት ጠፍቶ የምግብና የተመጋቢነት ግንኙነት በመካከላችን ሊኖር ይገባል።


ለሳር በልና ቅጠል በል ወገኖች የምለው ምክር አለኝ። እኛ በሌሎች እጣፈንታ ላይ ወሳኞች አይደለንም። ነገር ግን አንዳችን ለሌላችን አስፈላጊዎች ነን። የተገዥነት እና የገዥነት መደብ በመካከላችን እንዲኖር መፍቀድ የለብንም። የእምባ ጠባቂም ሆነ ደንብ አስከባሪ አያስፈልገንም “ሲል ጭብጨባና ፉጨት በመድረኩ አስተጋባ። አያ አንበሴ ሕቡዕ ሐሳቡ ስለተደረሠበት እና ባመዛኙ በእንስሳቱ መካከል የመቀበልና የመደማመጥ አዝማሚያ የበላይነቱን እንደይነጠቅ ሥጋት ገባው። ማኀበረ እንስሳ ዘም ነገዶ አናብስት ንጉሰ ነገስት ተብሎ በጫካው የእንስሳት ዘር በሁሉም ዘንድ በሐይሉና በክንዱ ብርታት ተከብሮና ታፍሮ የኖረባቸው ዘመናት እንዳያልቁ እጅግ ፈራ “አንድነት የማይፈረካክሠው አለት የለም፣ መለያየት ግን ጥንካሬን ያሳጣል” ነበር ያለው። አያ ዝንጀሮ ታዲያ በእንስሳቱ ዓለም በንጉሱ አያ አንበሴ አሠባሣቢነት የተደረገው ውይይት በብዙ መግባባቶች ሲጠናቀቅ የፈላጭ ቆራጭነቱን ድርሻ ለሚወስዱትና በገዥነት መደብ ለሚፈረጁት ሌላ ሥጋትን የወለደ መሆኑ አልቀረም።


በሁለተኛው ቀነ ቀጠሯቸው እንስሳቱ በሌሎች ሐሳቦች ዙሪያ ለመነጋገር ወስነው አጨብጭበው ሲለያዩ በቀጣይ ውይይታቸው የቤት እንስሳቱን ሁሉ ያካተተ ለማድረግ ቃል በመግባት ነበር።
ቀጣዩ ዘመን ብሩህ ነው። ያረጀና ያፈጀ የተባለው ወግና ልማድ ባዲሱ የአስተሳሰብ መርህ ይተካል። ምናልባት በክንዶቻቸው ብርታት ትምክህት ያደረጉ በተባበሩት መዳፎች ስር አንድ ቀን ይወድቁ ይሆናል። ጊዜ ለኩሉ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
115 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 447 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us