አድዋ የደም ቀለበት

Wednesday, 21 March 2018 13:14


በአድዋ ዋዜማ በጾመ ሁዳዴ ሰሞን ቀን ቀን መዝሙር ከሚደመጥባቸው የአዲስ አበባ ምሽት ቤቶች መካከል በአንዱ እኔ እና ጓደኞቼ አንድ ሁለት እየቀማመስን አዳዲስ በሚወጡ ዘፈኖች እራሳችንን ደስ ለማሰኜት በደመወዝ ቀን ማግስት ከቤት ኪራይ እና ሌሎች ወጭዎቻችን ያተረፍናትን ሳንቲም ቋጥረን ተገናኝተን ነበር።


እናም እንደተለመደው መጠጡን እየቀማመስን እግረ መንገዳችንም ስለ ሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ፣ ስለኑሮ ውድነቱ ስለ ጠቅላይ ሚኒስተሩ በገዛ ፈቃዳቸው ስልጣናቸውን ስለመልቀቃቸው ስለ ቀጣዩ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስተር ስለ ሌሎችም ጉዳዮች በመጠጡ ሞቅታ ተገፋፍተን ያለፍርሃትና ያለመከልከል አወጋን።


ከመካከላችን በተለየ የህይወት ፍልስፍና የሚታወቀው ወዳጃችን አንዱ ‹‹የሰው ልጅ በቃኝ ማለትን ካልተማረ በቀር በታወቁና ስመጥር ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ገብቶ የሚቀስማቸው እውቀቶችና ልምዶች ሰላምና ሙሉ ደስታን አያስገኙለትም።


አለማችን ለደረሰችበት ቁሳዊ እድገት ሳይንስ ትልቅ ሚና ቢጫወትም ቅሉ ትውልዱ ለሚገኝበት ሞራላዊ ውድቀት ምላሽ አላስገኝም›› አለ
‹‹ትምህርት ባይኖር ምን እንሆን ነበር›› በሚል ርዕስ የመወያያ ሀሳብ ተነስቶ


‹‹በመሰረቱ የሚባለው ዘመናዊ ትምህርት ባይኖር የሰው ልጆች እጣ ፈንታ ምን ይመስል ነበር? ነው በመባል ያለበት። በእኔ እምነት ትምህርት በሰው ልጆች የህይወት ጉዞ ውስጥ የማይጠፋ ነገር ነው። ህፃናት እንደተወለዱ ለዚህ ምድር በቂ እውቀት ይዘው አይመጡም። ለዚህ ይመስለኛል ትምህርት ሒደታዊ ነው›› የሚባለው። አለ ሽመልስ የተባለው ወዳጄ
ጨለማ በብርሃን ብንርሃንም በጨለማ በሚተካኩበት የጊዜ ሒደት ውስጥ የሰው ልጅ ራሱን በህይወት ለማቆየት ሲል በብዙ ውጣውረድ ውስጥ ያልፋል። ለሀገርና ለወገን የሚተርፍ ሰናይ ተግባርን ፈፅሞ፣ መልካም ስምን በሚሊዮኖች ልብ ውስጥ ተክሎ ከሚያልፈው ሌላ በራሱ የህይወት ምህዋር የሚሽከረከር ደስታን በመጠጥና ጫት በመቃም እንዲሁም በሌሎች የመዝናኛ መንገዶች የሚፈልጋት ለተቸገሩ ድጋፍና እርዳታ በማድረግ ላጡትና ለነጡት በመዘርጋት ከሚገኝ እርካታ ይልቅ ራስን ብቻ ማዕከል ባደረገ የህይወት ልምምድ ውስጥ ከሚመላለሱ ወጣቶች መካከል አንዱ ወዳጄ ሽመልስ ነው።


ጥንት አዳም ከቦት ነበረውን ምቾት የተገነዘበው ከውድቀቱ በኋላ ነበር ክፉንና ደጉን የሚያሳውቀውን ፍሬ እንደበሉ አዳምም ሆነ ተጣማሪው ሄዋን በመጀመሪያ የተገነዘቡት እራቁት መሆናቸውን ነበር። ወዳጄ በአሁኑ ሰዓት በሳይንስ አለምን እንለውጣለን ከሚሉት ምዕራባዉያን ይልቅ እውነት ሆይ ሽንቁርሽ የት አለ ሳይሉ ምድሪቷን አምነው ዘር ዘርተው አጭደው የእለት ጉርሳቸውን የሚያገኙባት የአላዋቂነትን ሸማ ደርበው እርቃናቸውን የሸፈኑት ናቸው። ክልላቸውን በታንክ ያጠሩት እና የአለምን ተለዋዋጭ ሁኔታ ተከታትሎ ምላሽ ለመስጠት ብቃቱ አለን የሚሉት፣ ፍርሃት የተጋረዱበትን የብልፅግና መጋረጃ ቀድዶ ለብርድ ያጋለጣቸው ምስኪን የምዕራብ ሀገር ሰውች አይደሉምን?


ፈሪዎች ዘወትር ለሚያሳስባቸው ጉዳይ መፍትሔ በማፈላለግ ላይ ይጠመዳሉ። ጀግኖች ግን ያለምንም መጨነቅ ህይወታቸውን በሙሉ ደስታ ይኖራሉ።


ቢላ ቤት ቢኖርህ ውድ የሚባል መኪና ብትነዳ ሌሎች ሀብቶችን ብታፈራ ምንም ያክል ዝነኛ ብትሆን የቱንም ያክል ብትማር እርቃኑን ከነበረው አዳም ይልቅ አንተኑ ይበርድሀል።


ተማርኩ ስትል የሚገባህ ብዙ እንደማታውቅ ነው። ታዲያ ብዙ አለማወቅህ ምቾት ይነሳህና ክፍተትህን ለመሙላት ሌላ ውጥን ትጀምራለህ። ዳሩ ግን በእውቀት ጎዳና ውስጥ የምታጎድለው እንጂ የምትሞላው ክፍተት ባለመኖሩ ባለህ ነገር መደሰት ያቅትሀል። ምንአልባት እንደፈላስፋው ‹እኔ የማውቀው አለማወቄን ነው› ለማለት ትገዳድ ይሆናል። ታዲያ ይሄንን እውነታ መቀበል አቅቶህ የፈለከውን ደስታ አያስገኝልህም። የእድሜህ ፀሀይ ማቆልቆል ስትጀምር እርጅና ልጅነት ሚባል የደስተኝነት መገኛ እንደነበር ያሳይሀል።


በእድሜ ዘመንህ ሁሉ ያካበትከው እውቀት እንደ እምቧይ ካብ ተንዶ ወገብህ ጎብጦ አይኖችህ ደብዝዘው እንኳን ምግቤን አጉርሱኝ ጨርቄን አልብሱኝ ስትል ሁሉን መርሳት ስትጀምር እንደልጅነትህ ዘመን ሳይኮለኩሉህ ትስቅ ይሆናል። በጉብዝናህ ወራት ብዙ ወርደህ ወጥተህ ሀብት ስታፈራ ከእጅህ ላይ የሌለው ነገር ያባብልሀል። የሌለህን ለማግኜት ስትል የማትፈነቅለው ድንጋይ አይኖርም ከፊት ለፊትህ የቆመውን ሁሉ ትጨፈልቃለህ ልዩ ልዩ ስልቶችን ትነድፋለህ በአቋራጭ ለመበልፀግ የትኛውንም አይነት አጋጣሚ ለመጠቀም ትዘጋጃለህ ሀብት የሚባለው ኮተት ብቻውን ደስታን ሊሰጥህ እንደማይችል እስካልገባህ ድረስ በእጅህ ያለውን ነገር ለመጠቀም እድል ፈንታ አይኖርህም›› ነበር ያለው ሽመልስ።


መክበብ የተባለው ወጣት በበኩሉ በሽመልስ ሀሳብ እንደማይስማማ ገልጾ ኋላ ቀርነት እና መሀይምነት ለሰው ልጆች የማይበጅ በመሆኑ ራስን በማሰልጠን ከዚህ እንቅልፍና ድንዛዜ መንቃት እንደሚያስፈልግ አብራርቶ ለጥቆም አንዲህ አለ።


የአፍሪካ ሀገራት የእርስ በእርስ ግንኙነት በጠንካራ ወዳጅነት ላይ የተመሰረተ ሳይሆን በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖሎቲካዊ ትብብሮሽን ከማዳበር ይልቅ በጥርጣሬ አይን የሚተያዩ እና እስከ አሁን ድረስ በይዞታ ይገባኛል ውዝግብ ውስጥ የማይታጡ ናቸው። እነዚህ እህት አገራት ታዲያ በድንበር ግጭቶች ደም የሚፋሰሱት እራሳቸው በፈጠሩት ችግር አይደለም።


የወቅቱ ሀገራችን ችግር ሳይቀር የምዕሪብ ሀገራት የጎነጎኑት ሴራ ውጤት ነው። ጣሊያኖች በመሳሪያ ያልጨረሱትን ህዝብ እርስበእርሱ እንዲተላለቅ የሚያደርግ ዘረኝነት የሚባል ፈንጅ ነው በሀገሪቱ ዜጎች ዘንድ ቀብረው የሔዱት። እኛ አፍሪካዊያን የትውልድ ዘር ሀረግ እየጠቀስን በብሔርና በጎሳ እየተከፋፈልን አንድነት የሚሰጠውን ብርታት አጥተን በድህነት እንድንማቅቅ ለተደረግንበት በደል አውሮፓ ካሳ ልትከፍለን አትችልም።


ሀገራት በሀገራት ላይ እየተነሱ በግፍ ላፈሰሱት ደም ካሳ ቢከፍሉም ለወረወሩት ፈንጅ እንጂ ቅኝ በገዙት ሀገር ላይ ላጠመዱት ስውር ወጥመድ ፀፀት አይሰማቸውም።


እባካችሁ ዲሞክራሲን ገንቡ የሰብአዊ መብት አያያዛችሁ ይሸሻል ይሉናል። ነገር ግን ለዴሞክራሲ እጦትም ሆነ ለሰብዓዊ መብት አያያዝ ችግር ምክንያቶቹ እነርሱ ናቸው። ለግፈኛ መሪዎች መሳሪያ ያስታጥቃሉ ተገፋን፣ ተበደልን ለሚለውም ቡድን መትረጊስ ይሸልማሉ። በዚህ ትይንት መካከል አስታራቂ ሆነው በሽምግልና ወንበር ላይ እራሳቸውን ይሾማሉ። በአፋቸው ፍትህን እየሰበኩ በልባቸው የሚያገኙትን ፖለቲካዊ ትርፍ ያወራርዳሉ። በዜና ማሰራጫወቻችው እከሌ የሚባል ቡድን በእከሌ ቡድን በደል ደረሰበት ይሉናል የብሔር ታርጋ እየለጠፉ።


እኛም መንቃት አቅቶናል አፍሪካ በማያባራ እንቅልፍ ውስጥ ናት መሪዎቿም ቅዥት ውስጥ ወድቀዋል። ለህዝባቸው ሚሆን የማንቂያ ደወል የላቸውም የሚመሩትን ህዝብ ፍላጎት አያጤኑም። የራሳቸውን ምቾት ለማቆየት ሲሉ ለውጥን ይፈራሉ።


ለሀገራቸው የሚበጅ የአመራር ብልህትን ከመከተል ይልቅ የአደጉ ሀገራትን አስተዳደር ብልሃትን እየተከተሉ ህዝባቸው ከሚያስፈልገው ትክክለኛ መፍትሄ አርቀዋል። አንድ ሀኪም ለተለያዩ በሽታዎች ተመሳሳይ የህክምና መንገድን አይከተልም። ተመሳሳይ ላልሆነ በሽታ አንድ አይነት መድሀኒት አይሰጥም።


እኛ አፍሪካዊያን እንቅልፍ በቃን ማለትን መጀመር አለብን። በእንቅልፍ ልብ ከመዳከር ወጥተን ያለ አሜሪካ ድጋፍ ለመራመድ መጨከን አለብን።


የአፍሪካ ሀገራት ዓመት እየጠበቁ ከቀኝ ገዥዎቻቸው ቀንበር ነፃ የወጡበት ቀን ብሔራዊ በዓል አድርገው የሚያስቡት ቢሆንም፡- በእጅ አዙር በተግባር ከተፈተኑበት የግፍ አገዛዝ ያልተላለቁ ናቸው። በዚህ እረገድ ሀገራችን ኢትዮጵያም ለሌሎችም የቀድሞው ቅኝ ተገዥ ሀገራት ምሳሌ ለመሆን የበቃችበት የሚያኮራ ታሪክ ባለቤት ትሁንም እንጂ አባቶች በየሚዲያ ተቋሙ ጀግኖች የዚያ ዘመን ትውልዶች ስለ አስመዘገቡት ድል ሲናገሩ የሚደመጥ ቢሆንም አድዋ የጥቁር ህዝቦች ሁሉ የሚጋሩት ታሪክ የተገለጠበት የኩራት ካፓን የደረበልን የነፃነታችን አርማ ቢሆንም


በሀይማኖት በጎሳ፣ በቋንቋ ተካፋፈለን ልንኖር ከሻትን በእውነት ከጣሊያን ቅኝ አገዛዝ አልወጣንም። አድዋ በደም የተነሳሰርበት የቃል ኪዳን ቀለበት ጭምር እንጂ ባርንትን ያሽቀነጠርንበት፣ ሉዓላዊነታችን ያስከበርንበት የታሪክ ማህደር፣ የድል ውሎ ማስታወሻ ብታች አይደለም።


አድዋ በአንድ ወቅት ገድል የተፈጸመበት ግዑዝ ተራራ አይደለም። አድዋ እኛ ኢትዮጵያዊያን ላንለያይ የተሰናሰልንበት የደም ቀለበት ነው።


አድዋ ብርቱ ክንዱን ትምክት ያደረገውን ወራሪ ሀይል በአለም ህዝቦች ፊት አዋርደን የመለሰንበት ታሪክ ብቻ አይደለም።


የመከፋፈል አደጋ በመካከላችን እንዳይኖር የጨከንበት አንድነታችን ከብረት አጥር የጠነከረ መሆኑን ያሳየንበት ነው። እኛ ኢትዮጵያዊያን ከእንቅልፋችን ልንነቃ ይገበናል ከተደገሰልን የክፋት ወጥመድ ልናመልጥ የምንችለው ዘረኝነትን እምቢ ስንል ብቻ ነው።


ሁላችንም በምሽት ቤቱ ውስጥ ከሚካሄደው ሁኔታ ፍጹም ርቀን በመጠጡ መተ ሞቅታ ተንቃቅታን ከሚሴንቆው ጥዑም ዜማ ርቀን ድምፃቸን ከፍ አድርገን ስናወራ ሀሳብ ስንለዋወጥ አምሽተን ተለያየን። በእለቱ አንዳችን በሌላችን ሀሳብ ላይ ተንተርሰን ሀሳብ ስንሰጥ ምክንያትን በምክንያት ስንሸር፣ አንዳችን የሌላችንን ትኩረት ለማግኘት ስንል ባለን እውቀት በተለያየ ርዕሰ ጉዳዮች መላ ምት ስናስቀምጥ፣ የልብ የልባችንን ስናወጋ ቆይተን ለሌላ ቀን ተቀጣጥረን ተለያየን።


‹‹ዛሬ ከትናንቱ የሚሻል የመረቆዘ ቁስልን የሚያለዝብ፣ የተሰበረ ልብን የሚጠግን ምክር ታጥቷል። ልክ ካልሆነ፣ ጉዞ ከተንጋደደ አካሄድ የሚመልስ ጠፍቷል። ፍቅር በጥላቻ ተሽሮ ንግግሩ ሁሉ ሽሙጥ ሆኗል›› ሲል አንዱ ሌላኛው ‹‹ኤድያ ባሁኑ ዘመን በውይይት መግባባት ይከብዳል ሁሉም መስማት በሚፈልገው እውቀት ተሞልቷል። መስማት ከሚፈልገው በቀር የሚያዳምጥ የለም›› ይባባላሉ፤ በቅርብ እርቀት በምሽት ቤቱ ለደንበኞች በተዘጋጁ ወንበሮች ላይ ተሰይመው ንግግሮቻችን በትኩረት የሚከታተሉት እና በውይይታችን የተሳቡ ሁለት ጎልማሶች።

 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
83 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 415 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us