ተፈናቃዮችን ወደ ሌላ አካባቢ ወስዶ ለማስፈር የሚደረገው እንቅስቃሴ ሕገ-ወጥ ስለሆነ መቆም አለበት!”

Wednesday, 28 March 2018 12:45

(ከኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት /መድረክ/ የተሰጠ መግለጫ)

 

ለዘመናት ኑሮአቸውን መስርተውና ማህበራዊ ትስስር ፈጥረው ከሚኖሩባቸው አከባቢዎች በመሳሪያ ኃይል ተገደው የተፈናቀሉ ዜጎችን መብት በማስከበር መንግሥት ወደ ቀዬአቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙ ማድረግ ሲገባው፣ ሕገ መንግሥቱን የማስከበር ጉዳይ እንደዋዛ ወደ ጎን በመተው፣ የተፈናቃዮን ይዞታና ንብረት ለአፈናቃዮቹ ተትቶ፣ ተፈናቃዮቹን ወደ ማያውቋቸው ሩቅ አካባቢዎች ወስዶ የማስፈር ዕቅድ መንግሥት ይዞ ሲንቀሳቀስ በትዝብት እያየነው ነው። የዚህ እርምጃ እንደምታው ብዙ እና ለሀገራችን አንድነትና ለህዝቦቻችንም አብሮነት አደጋ ያለው ነው።


በዚህ ረገድ፣ በያዝነው ዓመት፣ በተለይም በምሥራቁ የአገራችን ክፍል በድንበር ጥያቄ ሰበብ በኢትዮጵያ ሱማሌና በኦሮሞ ክልሎች መካከል ባለው አለመስማማት መንስኤነት ከ700ሺህ በላይ የሚገመቱ ወገኖች የጦር መሣሪያ በታጠቀ አስገዳጅ ኃይል እርምጃ የመፈናቀል አደጋ እንደደረሰባቸው በመንግሥት ጭምር ይፋ ተደርጓል። በአሁኑ ጊዜም የተፈናቃይ ወገኖች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቶ አንደ ሚሊዮን እንደ ደረሰ ከተለያዩ ምንጮች በሚሰጡ መግለጫዎች ለማረጋገጥ ተችሏል። የሚገርመው ደግሞ ከተፈናቃዮቹ መካከል የሚበልጡት “የድንበር ጥያቄ” አለው ከሚባበት ከገጠሩ ሳይሆን የትላልቅ ከተማዎች ነዋሪዎች ጭምር መሆናቸው ነው።


በየደረጃው በዚህ ጉዳይ እጃቸው ያለበት የፌዴራልና የክልል መንግሥታዊ አካላት በተናጠልም ሆነ በጋራ ተጠያቂዎች እንደሚሆኑና ወደ ህግ ፊት እንደሚቀርቡ፣ የተፈናቀሉት ዜጎች ደግሞ ቀድሞ ወደ ነበሩበት ቀዬአቸው እንዲመለሱ ይደረጋል ተብሎ ነበር። በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት አንቀጽ 32.1 “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ… በመረጠው የአገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖርያ ቦታ የመመሥረት፣ እንዲሁም በፈለገው ጊዜ ከሀገር የመውጣት ነፃነት አለው” ተብሎ በተደነገገው መሠረት፣ በአገሪቱ ውስጥ በየትኛው ክልል መብታቸው ተጠብቆ የመኖርና ሀብት የማፍራት ሕገ መንግሥታዊ መብት ያላቸው ናቸው።


ይሁን እንጂ ገዥው ፓርቲና መንግሥት ይህን የዜጎችን ሕገ መንግሥታዊ መብት ድንጋጌ ለማስከበር ጥረት ሲያደርግ አይታይም። የማፈናቀሉን እርምጃ የወሰዱትም ወንጀለኞች በህግ ቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው ሲጣራ አይታይም። የተፈናቀሉ ዜጎች መብታቸው ተጠብቆ፣ ወደ ቀዬአቸው ቢመለሱ “አደጋ ይደርስባቸዋል” የሚል ተልካሻ ሰበብ፣ መንግሥት ቁሞ ባለበት ሀገር እየቀረበ በመሆኑ፣ በየክልል “የዘር ማጽዳት” እርምጃ ለመውሰድ ለሚንቀሳቀሱ ካድሬዎች “አይዞአችሁ፣ በርቱ” ከማለት የተለየ መልእክት አይሰጣቸውም! ለዚህም ማስረጃው መንግስት ተፈናቃዮቹን በመጠለያ ውስጥ ለወራት ያህል አጉሮ በማቆየት፣ በማያውቋቸው የገጠር አካባቢዎችና በየከተሞቹ ዙሪያ በቋሚነት የማስፈር ተግባር እያከናወነ መሆኑ ነው። ይህ እርምጃ በዚሁ ከቀጠለ፣ ማንም ይሁን ማን በሕገ ወጥነት ዜጎችን ከቀዬአቸው እያፈናቀለ የሚያባርር ይሆንና፣ ዜጎች በኢትዮጵያዊነት ተከብረው በፈለጉበት ክልል የመኖር ህገመንግስታዊ መብታቸው እየተጣሰ፣ ሀገራዊ አንድነት ግንባታው አደጋ ላይ ይወድቃል። ስለሆነም መንግስት ህግን በማስከበር የዜጎችን መብት ማስጠበቅና አፈናቃዮችን ወደ ህግ ፊት በማቅረብ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ አለበት እንጂ ከዚህ ውጪ ሌላ የሰፈራ ፕሮግራም ማካሄድ መጀመሩ፣ ከየክልሉ “ዘር የማጽዳት” እርምጃ ዕቅድ እንዳለው ያስመስልበታል።


በሌላው አንጻር፣ በወገኖቻቸው ላይ የደረሰውን የመፈናቀል አደጋ ለመቋቋም ዜጎች በግልም ሆነ በቡድን እያደረጉ ያሉት ዕርዳታ ሁሉ የሚደነቅ ቢሆንም፣ የተገኘው ዕርዳታ ተፈናቃዮቹን እንደወጡ የሚያስቀር ሳይሆን ወደ ተፈናቀሉበት አካባቢ ተመልሰው የሚቋቋሙበት መሆን ይኖርበታል። ሌላው መሆን ያለበትና ተገቢ የሚሆነው እርምጃ፣ ይህንን ህገወጥ ድርጊት በሰላማዊ ዜጎች ላይ የፈፀሙትን አካላት ሕግ ፊት ማቅረብ መሆን ነበረበት እንጂ ዜጎችን ያፈናቀሉት ወገኖች ድርጊት እንደ ቀላልና ተራ ድርጊት ታይቶ፣ ጉዳዩን ወደ ጎን በመተው ለተፈናቃይ ወገኖች የመልሶ ማቋቋሚያ ኮሚቴ አቋቁሞ ከወገን እርጥባን በማሰባሰብ የተለየ ሠፈራ ፕሮግራም መንደፍና ማካሄድ፣ ለወደፊት ዜጎች በፈለጉበት የአገሪቷ የአስተዳደር ክልሎች ውስጥ ተዘዋውረው እንዳይኖሩና ቤት ንብረት እንዳያበጁ፣ ካለምንም ስጋት ከቦታ ወደ ቦታ ተዘዋውረው ሰርተው እንዳይኖሩና ሀብትና ንብረት እንዳያፈሩ የሚያደርግ አደገኛ እርምጃ ከመሆኑም በላይ፣ የዜጎችንም ህገ መንግስታዊ መብት የሚጥስ ነው። በመሆኑም በየክልሎቹ በህገወጥ ባለሥልጣናትና ካድሬዎች እርምጃ ለተፈናቀሉት ወገኖች የሚደረገው የተሳሳተ የሰፈራ ፕሮግራምና እንቅስቃሴ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ የሚያስከትል ከመሆኑም በላይ ወደፊትም ከፍተኛ ሀገራዊ ችግር የሚያስከትል ስለሆነ መድረክ አጥብቆ ይቃወማል።


እንደዚሁም በቅርብ ጊዜ በምስራቅና በምዕራብ ሀረርጌ በጨለንቆ፣ በአወዳይ፣ በሐማሬሳና በወልዲያ ላይ በበርካታ ዜጎች ላይ ግድያ ተፈፅሟል። ሰሞኑን ደግሞ በሞያሌ ከተማ በበርካታ ሰላማዊ ዜጎች ላይ በመከላከያ ሠራዊቱ አባላት የተፈፀመው ዘግናኝ ግድያ በጣም አሳዛኝና የሚወገዝ ወንጀል ነው። በሌሎች አካባቢዎችም፣ በምስራቅና በምዕራብ ወለጋ፣ በቀለም ወለጋ፣ በምዕራብ ሸዋ የዜጎች ሕይወት በአሳዛኝ ሁኔታ ቀጥፏል። በትግራይ ክልልም በተምቤን ዞን በርካታ የአረና ትግራይ አባላትና ደጋፊዎች፣ እንዲሁም በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት በሲአን አባላትና ደጋፊዎች ላይ እስራት እየተካሄደ ነው። በአዲስ አበባ ከተማም በየክ/ከተማው በሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎች በርካታ ወጣቶች በአሰሳ እየተያዙ መታሰራቸው ታውቋል።


ስለሆነም መድረክ ቀደም ሲል በተደጋጋሚ በሰጣቸው መግለጫዎች ሀገራችን የተረጋጋችና ሰላም የሰፈነባት እንድትሆን፣ ህዝቦቿም በሰላም ወጥተው በሰላም መግባት እንዲችሉ መፍትሔ ሊሆኑ ይችላሉ ብሎ ባመነባቸው ጉዳዮች የበኩሉን አማራጭ ሲያቀርብ ቆይቷል። አሁንም የሀገራችንን ወቅታዊና መሠረታዊ ፖለቲካዊ ችግሮች መፍታት እንዲቻል፡-


1. መንግሥት ከሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ውጭ ከየክልሉ የተፈናቀሉትንና የተሰደዱ ዜጎችን በሌላ አካባቢ አሰፍራለሁ የሚለውን እንቅስቃሴ አቁሞ፣ የደረሰባቸውን በደል ግምት ውስጥ በማስገባት፣ የሚገባቸውን ካሳ ከፍሎ ተፈናቃዮቹን ወደነበሩበት መኖሪያ ቀዬአቸው መልሶ እንዲያቋቁማቸው፣


2. በሀገሪቷ ዜጎች ላይ በሰበብ አስባቡ እየተፈፀመ ያለው ሕገ ወጥ እስራት፣ ማዋከብና ግድያ በአስቸኳይ ቆሞ፣ በጥፋተኛነት የተጠረጠሩ ዜጎች ቢኖሩ ጉዳያቸው በሕግ አግባብ እንዲታይ፣
3. ቀደም ሲል የታሰሩና አሁንም እየታሰሩ ያሉ የፖለቲካ እስረኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ፣


4. በሀገሪቷ ላይ ለተከሰቱት መሠረታዊ ፖለቲካዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለመፈለግ፣ ኢህአዴግና መንግስት ከመድረክና ሌሎች ሀቀኛ ተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ጋር የውይይትና የድርድር ሂደት በአስቸኳይ እንዲከፍትና ተዓማኒ ምርጫ ተካሂዶ ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት የሚሆንበት ሁኔታ እንዲፈጠር መድረክ አጥብቆ ይጠይቃል።


የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ
መጋቢት 14 ቀን 2010 ዓ.ም
አዲስ አበባ

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
114 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 464 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us