ማብራሪያ፡- ስለ ኮንዶሚኒየም ተመዝጋቢዎች ከከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር

Wednesday, 28 March 2018 12:40

 

የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር በከተሞች የሚታየውን የቤት እጥረት ለመቅረፍ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ ፕሮግራም በ1996 ዓ.ም ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች 384 ሺህ በላይ ቤቶች ሲገነቡ፣ ከ248 ሺህ በላይ ቤቶች ለተጠቃዎች መተላለፋቸውን፣ 136ሺህ የሚሆኑት ደግሞ በመገንባት ላይ መሆናቸው ይታወቃል። የመጠለያ ችግርን ከመቅረፍ በተጨማሪ የቤቶች ግንባታ ሂደቱ በየአመቱ ከ60ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል የፈጠረ፣ ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ማደግ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረከተ እና የቁጠባ ባህልን ከማዳበር አንፃር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተ በዚህም በዓለማቀፍ ደረጃ ለሀገራችን እውቅና ያስገኘ መርሃ ግባር ሲሆን በእነዚህ ስራዎች አበረታች ውጤት የታየባቸው ቢሆንም አሁንም ትልቅ ርብርብ ልናደርግበት የሚገባን ወሳኝ የልማት ዘርፍ ነው። በአዲስ አበባ ብቻ መንግስት በ10 ቢሊዮን የሚቆጠር በጀት መድቦ (ቦንድ) ከ132 ሺህ ቤቶች በላይ አሁንም በግንባታ ላይ ይገኛሉ።

 

የልማቱን ተጠቃሚዎች በተመለከተ በ2005 ዓ.ም በ40/60 የቤት ልማት ፕሮግራም የተመዝጋቢዎች የቁጠባ ሁኔታ እስከ ጥር 30 ቀን 2010 ዓ.ም ያለው መረጃ ስንመለከት በ40/60 ፕሮግራም ጠቅላላ የተመዘገቡ ነዋሪዎች ብዛት 166ሺህ288 ሰዎች እስካሁን እየቆጠቡ በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ ነዋሪዎች 133ሺህ013 ሰዎች ናቸው። 972 ነዋሪዎች ደግሞ በ11ኛው ዙር ዕጣው የደረሳቸው ባለዕድለኞች ናቸው። የተወሰኑት ያቋረጡትም በምዝገባ ወቅት አቅማቸውን በሚመጥናቸው ደረጃ ያለመመዝገብ ዋናው ችግር ሲሆን በተለያዩ በግል ችግሮችና ሌሎች የቤት አማራም በማየት ነው።
በሌላ በኩል በ2005 ዓ.ም በ10/90 እና 20/80 የቤት ልማት ፕሮግራም የተመዝጋቢዎች ብዛት 780ሺህ473 ሲሆኑ ከእነዚህ ውስጥ ቅድመ ክፍያ ሙሉ በሙሉ ያጠናቀቁ ተመዝጋቢዎች ብዛት 53ሺህ022 ሲሆኑ ከቅድመ ክፍያ በታች በየወሩ እየቆጠቡ ያሉ 41ሺህ185፣ በማቆራረጥም ቢሆን ቁጠባቸውን በመፈፀም ላይ ያሉ 624ሺህ970 ሲሆኑ ባጠቃላይ በመቆጠብ ላይ ያሉ ደግሞ 719ሺህ177 ናቸው። 719ሺህ177 እየቆጠቡ ከነበሩት ውስጥ በ10ኛውና በ11ኛው ዙር ዕጣ የወጣላቸው ባለ እድለኞች 65,178 ነዋሪዎች ሲሆኑ እስካሁን እየቆጠቡ በመጠባበቅ ላይ ያሉ ነዋሪዎች 653ሺህ999 መሆናቸውን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።


እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ አንዳንድ ፀረ ልማት የሚዲያ ተቋማት በሬ ወለደ አይነት መረጃ ለህብረተሰቡ በማድረስ ህዝቡን እያወናበዱ ይገኛሉ። በተለይ ኢሳት 30/06/2010 ዓ.ም ሪፖርተር ጋዜጣን በምንጭነት በመጥቀስ ከ900ሺህ ዜጎች በላይ ቤት ፈላጊዎች የባንክ አካውንት ከፍተው ቁጠባ ቢጀምሩም፣ 624ሺ ተመዝጋቢዎች ቁጠባ ማቆማቸውን የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ዶ/ር አምባቸው መኮንን ገለፁ በማለት ከእውነት የራቀ የውሸት ዘገባ አቅርቧል። ይህንን በተመለከተም የተዛባ መረጃ ላስተላለፈው ሚዲያ ምላሽ ለመስጠት ሳይሆን በቀጣይ ለሚኖሩ ተመሳሳይ ጉዳዮችም ከመንግስት ከሙንኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ጋር ተመሳሳይ መረጃ ሊኖረን ስለሚገባ ጥሬ ሀቁን ማቅረብ አስፈልጓል።


የሪፖርተር ጋዜጣን የካቲት 25/06/2010 ዓ.ም በዜና አምዱ ላይ ያስነበበው እውነታው ግን የሚከተለው ነበር። “የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ዶ/ር አምባቸው መኮንን ረቡዕ የካቲት 21 ቀን 2010 ዓ.ም ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ 624 ሺ ተመዝጋቢዎች ቁጠባቸውን እያቆራረጡ መሆኑንና ቁጠባቸውን በትክክል በምዝገባ ወቅት ከሚጠበቀው መቶ በመቶ እየቆጠቡ የሚገኙት ደግሞ ከ100 ሺ እንደማይበልጡ ተናግረው፣ ሕጉ ለስድስት ወራት ቁጠባቸውን ያቋረጡ ይሰረዛሉ ስለሚል ተመዝጋቢዎች በአግባቡ እንዲቆጥቡ ማሳሰባቸውን ዶ/ር አምባቸው መኮንን ተናግረዋል” በማለት አስነብቧል።


ነገር ግን ኢሳት የካቲት 30/06/2010 ዓ.ም ሪፖርተር ጋዜጣን በመጥቀስ ያሰራጨው ዘገባ “ከ900 ሺ ዜጎች በላይ ቤት ፈላጊዎች የባንክ አካውንት ከፍተው ቁጠባ ቢጀምሩም፣ 624 ሺ ተመዝጋቢዎች ቁጠባ ማቆማቸውን የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ዶ/ር አምባቸው መኮንን ገለፁ።” በማለት ዘግቧል። “ቁጠባቸው እያቆራረጡ” እና “ቁጠባ ማቆማቸውን” የሚሉ ቃላቶች በጣም የተለያዩ ትርጉም ነው ያላቸው። ቁጠባቸውን እያቆራረጡ የሚከፍሉ ማለት በሚቆራረጥ ቁጠባቸውን በመፈፀም ላይ ያሉ ማለት ሲሆን ቁጠባቸውን ያቆሙ ማለት ደግሞ ክፍያ አቋርጠው ሂሳባቸው የተዘጋ ማለት ነው።


በዚህ መሰረት የኢሳት ዘገባ 624ሺ ተመዝጋቢዎች ቁጠባ ማቆማቸውን በሚል የተዘገበው በይዘትም በትርጉምም የውሸት ዘገባ መሆኑን እና እንደ መረጃ ምንጭ የተጠቀመውም ሪፖርተር ጋዜጣም ቢሆንም ሪፖርተር ጋዜጣ ከላይ የተጠቀሰውን የተሳሳተ ዘገባ አለመዘገቡን መረዳት ይቻላል።


ይሁን እንጂ ሪፖርተር ጋዜጣም በእሁድ የካቲት 25 ቀን 2010 ዓ.ም በርዕሰ አንቀፁ “በርካታ የኮንዶሚኒየም ተመዝጋቢዎች ቁጠባቸውን እያቋረጡ ነው” ብሎ ማቅረቡ በራሱ ትክክል አለመሆኑን ያቋረጡ ሰዎች በጣም ጥቂት መሆናቸው፣ ለቀጣዩም የህዝብ መሰረታዊ ጥያቄ የሆነው የቤት ልማት በፖሊሲያችን በተቀመጠው ከ5 ዓይነት በላይ የቤት አቅርቦት አማራጮች ለመፍታትና ላለፉት 100 ዓመታት የተከማቸው የቤት እጥረት ለመፍታት ልማታዊ መንግስታችን በየዓመቱ ከ15 እስከ 20 ቢሊዮን ብር በጀትና የቦንድ ብድር እያመቻቸ በመንግስት አቅም ግዙፍ ልማት እየተከናወነ ይገኛል። ማንም ድሃ አገር በአሁኑ ሰዓት ያልደፈረውን የቤት ችግር በመስራት ላይ ሲሆን ይህንን አጠናክረን እንቀጥላለን።


የመቆጠብ አቅማቸው ዝቅተኛ ለሆኑ የተቀረፀው የ10/90 ፕሮግራም ለተመዘገቡ መቶ በመቶ ቤቱን አዲስ አበባ ገንብቶ ያስረከበ ሲሆን ቀጣይም በመቆጠብ የቤት ባለቤት ለመሆን ለተመዘገቡትም ሌት ከቀን እየተሰራ ነው። የተከማቸው የቤት ፍላጎት በርካታ በመሆኑ ምክንያት አሁን ከደረስንበት የሀገሪቱ የገንዘብ አቅምና የመገንባት አቅም ጋር ሲነፃፀር አሁንም በርካታ ፍላጎቶች በመኖራቸው በተለያዩ አማራጮች ግንባታውን ተጠናክሮ ስለሚቀጥል የተመዘገባችሁና መስፈርቱን በማሟላት ቁጠባችሁን አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ እያሳሰብን ፀረ ልማት ኃይሎች የጀመርነውን ልማት ማጥላላትና የበሬ ወለደ ውሸት የተለመደና የሚጠበቅ በመሆኑ ለዚህ አይነቱ የተሳሳተ ሃሳብ ቦታ ሳንሰጥ በልማቱ ስራ ላይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ ተቀናጅተን እንድንሰራ ደግመን መግለፅ እንፈልጋለን።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
531 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 449 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us