የአዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ሹመት አስመልክቶ ከኢራፓ የተሰጠ መግለጫ

Wednesday, 04 April 2018 14:07

 

የሃሳዊ ነቢያት፣ የዕኩይ ራዕይ ጥማት፣
ለአገራችን ሥጋት፣ ለሕዝባችን ጥፋት፤

 

ሕወሃት መራሹ ኢሕአዴግ የምኒሊክ ቤተ-መንግሥትን በአፈ-ሙዝ ከተቆጣጠረበት ማግሥት አንስቶ፣ በማናቸውም መስፈርቶች አንዳች ቅቡልነት ያልነበራቸው አስገራሚ የተሰኙ የምርጫ ቴአትሮችን ሲተውን ቆይቷል። በተለይም በ5ኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ‘በዴሞክራሲያዊ መንገድ በአብላጫ የሕዝብ ድምፅ ተመርጫለሁ’ በሚል ፈሊጥ፣ የመንግሥት ሥልጣንን በምርጫ ሽፋን ተቆናጥጦ፣ መቶ በመቶ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎችን በመቆጣጠር አቻ ያልተገኘለት ትወናውን ቀጥሏል።


ከሕወሓት/ኢሕአዴግ እኩይ ራዕይና አምባገነናዊ ግብሩ በመነጩ የሩብ መቶ ክፍለ-ዘመን አገራዊ ግፍና ሕዝባዊ በደል የተነሳ፣ አንዴ ጋም አንዴ ድንብሽ እያለ ተዳፍኖ የከረመው ሕዝባዊ ብሶት፣ ልክና ደርዝ አጥቶ እንደ ኢትዮጵያዊ ተቋቁሞ ሊታለፍ ከማይቻልበት አንገፍጋፊ የብሶት ጫፍ ላይ በመድረሱ፣ ዛሬ ላይ በመላው ኢትዮጵያዊ ሠላማዊና ሕጋዊ የሥርነቀል የሥርዓት ለውጥ ሕዝባዊ ጥያቄና፣ በተጓዳኝ በተነሳው መንግሥታዊ የጥገና መላላጥና የባሩድ አባዜ ሳቢያ፣ አገራችንና ሕዝቧ በሞት ሽረት ትግል አልቂትና ውድመት ማዕበል መናጣችን ሳያንስ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተሰኘ የአፈሙዝ እመቃ ተሸብበን እንገኛለን።


ከአገራዊና ሕዝባዊ ህልውና ይልቅ ድርጅታዊና መስመራዊ ህልውናው ከምንምና ከማንም በላይ የሞት ያህል የሚያስጨንቀው አብዮታዊ ግንባር፣ የምልዓተ ሕዝቡን ፍፁም ሠላማዊ እምቢተኝነት መቋቋም ሲሳነው፣ ‘ጥልቅ ተሃድሶ’ በተሰኘ የውስጠ ድርጅት ተሞዳማጅ እርብትብት ትርምሱ ማግስት፣ በአጥፊነት ኑዛዜ፣ በፀፀት ትካዜ፣ በይቅርታ ንስሃ፣ በእርምት ግዝት፣ በእድል ስጡን ተማጽኖ ድርጅታዊ መግለጫው የዕኩይ ራዕይ ባለቤትነቱንና አስፈጻሚነቱን ያለ አንዳች እፍረት ለዓለም በይፋ አረጋግጧል።


‘ራዕይ አስፈፃሚዎቻቸው ነን’ ባይ ሃሳዊ ነቢያቶቻቸው ቢክዱንም ቅሉ፣ የግንባሩ ቁንጮ ‘ባለራዕይ’ ተብዬዎች ድርጅታቸው ከአናቱ መበስበሱንና ከውስጥ መንቀዙን ደጋግመው ያበሰሩን ሃቅ እውን ሆኖ ገሃድ በመውጣቱ፣ የኢሕአዴግ ድርጅታዊ ህልውና ከመሠረቱ ተናግቶ እነሆ ዛሬ ላይ ሊቀመናብርቱን የተማሪዎች የክፍል አለቃ ያህል እንኳ ማፅናት ተስኖት፣ ‘ሥልጣኔን በፈቃዴ ለቀቅሁ’ ባሉት ሥዩመ-ሕወሃት ጠቅላይ ሚኒስትር ፈንታ፣ በተለመደው የጥገናዊ ለውጥ እሳቤ በመመራት ሰኞ፣ መጋቢት 24 ቀን፣ 2010 ዓ.ም ዶክተር ዓብይ አህመድን ሹመው ለመሸለም በቅተዋል።


በራዕይ ፓርቲ እምነት የጥገና ለውጥ ጊዜው ባለፈበትና፤ ሠላማዊ የሥርዓት ለውጥ የማይታለፍ ብቸኛ አማራጭ ሆኖ በወጣባት አገራችን፣ ከኢሕአዴግ ተፈጥሮአዊ ባህርይ በመነሳት የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሹመት፣ የ‘ጉልቻ ቢቀያየር’ አይነት ተረት እንዳይሆን ስጋቱን ከወዲሁ ይገልፃል።


ሆኖም ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ የ21ኛው ክፍለ-ዘመን የአዲስ ትውልድ ተወካይ እና ምሑር ሲሆኑ፣ በግል ሕይወታቸውም ካካበቱት ልምድና ተሞክሮ አንፃር ሲመዘኑና፣ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተጣለባቸው ተስፋ፣ በኢሕአዴግ ውስጥ ሆነው ተራማጅ አስተሳሰብ ያላቸውን አመራር ግለሰቦች በከፍተኛ ጥንቃቄ ከጎናቸው በማሰለፍ፣ የሕዝብን መሠረታዊ ጥያቄ በብቃት ከመወጣት አኳያ፣ በእጃቸው የገባውን ታሪካዊ ወርቃማ እድል በአግባቡ በመጠቀም እስከ ሥርዓቱ ሪፎርሜሽን፣ ወይንም መሠረታዊ ለውጥ የሚያደርሰንን ታሪካዊ ጉዞ በእምነት፣ በቅንነት፣ በግልፅነትና በቆራጥነት ያለማወላወል በጊዜውና በቦታው እንዲወጡ።

 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተሰጣቸው የሥልጣንና ኃላፊነት ዘመናቸው፡-


1ኛ. ከድርጅታዊ ህልውናና ‘ዘልዓለማዊ’ የሥልጣን ጥማት በዘለለ፣ ለአገርና ለሕዝብ የቅንና የታማኝ አገልጋይነት ብቃታቸውን እንዲያስመሰክሩ፤
2ኛ. በሕገ-መንግሥቱ የተቀመጠውን የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣንና ኃላፊነት ያለ አንዳች ጣልቃ ገብነት በሙሉ መብትና አቅማቸው መገልገላቸውን እንዲያረጋግጡ፤
3ኛ. እንደ አገርና እንደ ሕዝብ ከፊት ለፊታችን የተጋረጠብንን በህልውና የመቀጠል ሥጋታችንን ለመቅረፍ፣ ብቸኛ አማራጭ ለሆነው ‘አግላይ ያልሆነ ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ መግባባት’ የአፋጣኝ ግብረ መልስ አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁነታቸውን በተግባር እንዲተረጉሙ፤ በታላቅ ትህትና እየጠየቅን፤


ኢራፓ እንደ ባለ ራዕይ ፓርቲ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመፃዒ የሥራ ዘመናቸው ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት ሊያበረክቱ በሚችሉት አዎንታዊ አስተዋጽኦ ልክ፣ ፓርቲአችን ከአገራዊና ሕዝባዊ ወሳኝ አጀንዳዎች ዙሪያ ሠላማዊ የመፍትሄ አማራጮች፣ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰቦችና አሠራሮች ጎን የመሰለፍ ብቃቱን ከወዲሁ እያረጋገጠ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ መልካም የሥራ ዘመን እንዲገጥማቸው ያለንን ምኞት በሙሉ ልባዊ ፍቅር ለመግለጽ እንወዳለን።

 

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
122 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1034 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us