ለክቡራን የመንግሥት ወኪሎች

Wednesday, 04 April 2018 14:10

 

ከአሰፋ አደፍርስ

 

መንግሥት ይሠራሉ ብሎ የገመታቸውን በየመስኩ ያሰማራል፤ የተሰማሩት ደግሞ ለተመደቡበት ቦታ ኃላፊነት የመወጣት ግዴታ አለባቸው። በተመደቡበት ቦታ ግዴታቸውን መወጣት በማይችሉበት ጊዜ ተወቃሹ ወይንም ተጠያቂው መንግሥት መሆኑ ነው።


መንግሥት ይህንን ሳያሟላ፤ ይህንን ሳይሠራና በግድየለሽነት ተቸገርን፤ ተራብን ተጠማንና ተራቆትን የመሳሰሉት ወቀሳዎች የሚወርድበት በመንግሥት ላይ መሆኑ የታወቀ ነው።


መንግሥት የማይታይና የማይጨበጥ ጉዑዝ ቢሆንም እንደ ሕዝብ መሪ አካልና አምሳል ሆኖ ወኪሎቹን ሰይሞ በስሙ የሚከበርና የሚታመን ያንድ አገር መመሪያ አውጭ የበላይ አካል ነው።


ታዲያ አንዳንድ ስልጣኑን የያዙት እንደማይደፈርና እንደማይነካ አካል በመሆን በማን አለብኝነትና በእንዝህላልነት በሚፈጽሙት፤ ሥራቸውን በተገቢው ሥነሥርዓት ባለመፈጸማቸው መንግሥትን ያስወቅሳሉ፤ ተገልጋዩንም ሕዝብ ይጎዳሉ፤ ይበድላሉ፤ አገርንም ከልማት ወደኋላ ይጎትታሉ፤ ተረጂውንም ሕዝብ እጅ እግሩን አስረው እንዳይቀሳቀስ ያደርጉታል። ይህንን የሚከታተል ጠንካራ ወኪል ሊያየውና ሊያቃና የሚችልም መኖር አለበት። ይህ ካልሆነ፤ ሁሉ ቃልቻ ማን ይሸከም ስልቻ ይሆንና ከንቱ ልፋት፤ ከንፈር መምጠጥና የአሽሙር አደባባይ ወደ መሆን ተለውጦ ያገርንና የሕዝብን ርምጃ ወደኋላ ጎትቶ የበይ ተመልካች ያደርጋል። እላይ የዘበዘብኳቸውን ተወት ላድርግና ወደ ተነሳሁበት መለስ ብዬ አስተያየቴን ሰጥቼ ስሚ ባገኝ መልካም፤ ጆሮ ዳባ ከተባለም ይህ አስተያየት ለትዝብትና ለታሪክ እንዲቀመጥ በማለት አስተያየቴን ተስፋ ሳልቆርጥ እቀጥላለሁ።


ቀደም ሲል በየጋዜጦች ስለትራፊክ ጋጠ ወጥነት፤ ስለሴቶች መብት ኢትዮጵያ ቀደምት እንደነበረችና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያሉ አስተያየትቶችን ማስመዝገቤን ያነበባችሁ ትኖሩ ይሆናል። ይሆናል ያልኩበት ትችትም ሆነ አስተያየት ተሰንዝሮ ባለማየቴ ነው።


ዛሬ ለማሳሰብ የተነሳሁት ስለከተማ ማስተር ፕላን ስለ መረን የለቀቀ የአነዳድ ሥርዓትን የተመለከተ ይሆናል። የከተማን ፕላን አስተካክሎ ለመቀየስም ሆነ መስመር አስይዞና በሰለጠነው መልክ ለማሰራትም ሆነ ለመሥራት የከተማውን ከንቲባ ጥንካሬና ወሳኝ ክትትልን፤ ቁርጠኝነትና በሳምንትም ይሁን በሁለት ሳምንት የሚያስተዳድረውን ከተማ የተቻለውን ያህል በእግር፤ በመኪናና ከተቻለም በሄሊኮፕተር ተዘዋውሮ የከተማውን ውበት፤ በሚገባ መሠራቱን፤ መስመር መያዙንና ጠቅላላ ሁኔታውን ዞሮና ተዘዋውሮ ወደ አንድ ግንዛቤ ላይ ለመድረስ ብችል በራሱ ስልጣንና ከበላዩ ጋር በመመካር ተገቢውን ሁሉ ለማድረግ እንኳ ባይችል የተቻለውን ለሕብረተሰቡ በማስገንዘብ የበኩሉን ድርሻ መወጣት ይገባዋል።


ለምሳሌ ቀደምቶቹን ከንቲባዎች ብንመለከት፤ ከከንቲባ ዘውዴ በላይነህ፤ ከንቲባ ዘውዴ ገብረሥላሴ፤ ከንቲባ ዘውዴ ገብረሕይወትንና ከንቲባ ኃይለጊዮርጊስ ወርቅነህን ብንወስድ፤ በሙሉ ጊዜያቸውን በማጥፋት ምክትሎቻቸውን እንደነ ም/ከንቲባ ሙሉጌታ ሥነጊዮርጊስ ያሉት ካኪያቸውን ግጥም አድርገው ከመንደር መንደር ከቀዬዬ በመዘዋወር ያነሳውን በመመልከት፤ የጎደለውን በማሟላት በኋላ ቀር ቴክኖሎጂ የተቻላቸውን ሠርተው ወገናቸውን አገራቸውን አገልግለው ለመጪው አስረክበው አለፉ።


ምናልባት፤ የትኛውን ፎቅ ሠሩ የምትሉ ትኖሩ ይሆናል። እነርሱ እኮ ከምንም ተነስተው ነው። ዛሬ ድንክዬ የሆነችው በሰንጋ ተራ ወይንም በንግድ ትምህርት ቤት አካባቢ የምትታየዋ የአውራ ጎዳን ሕንፃ ሰማይ ጠቀስ ተብላ ከየጠቅላይ ግዛቱ ወጣት ተማሪዎች ጉድ እንዲያዩ የተጋበዝንበት ዘመን ነበር። ስለዚህ ከምንም ተነስተው ዛሬ ክቡር ከንቲባዎቻችን የተቀመጡበትን ታላቁን ሕንፃ፤ የብሔራዊ ባንክን ሕንፃ፤ የአዲስ አበባን (የቀ.ኃ.ሥን) ዩኒቨርሲቲ፤ የንግድ ምክር ቤትን ሕንፃና የመሳሰሉትን ሥልጣኔያችን ከጀመረበት ከ1933 ዓ,ም እስከ 1966 ድረስ ከምንም ተነስተው በ33 ዓመታት ውስጥ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን የትምህርት ቤቶችና አነስተኛ ግን በጥራታቸው ከኦክስፎድ ሐርቫርድ ጋር የሚያወዳደሩ ዩኒቨርሲቲዎች ሠርተውልን ነው እንዳልሠሩ ደርግ ስማቸውን በማጥፋት ያፈረሳቸው። ከንቲባዎቹ እምብዛም በየዩኒቨርሲቲው ዞረው ተመራቂዎችን ጋዎን ለብሰው ለመመረቅ ጊዜም አልነበራቸውም። ዛሬ እንደምንመለከተው የግንባታ ፈቃድ ሰጪው ስለከተማ ፕላን እውቀት ሳይሆን ባለፈበትም ያለፈ የማይመስል ነው። ያሳዝናል።


ሰው እንደያቅሙ በፕላን ሊሠራ ይችላል፤ ግን አድርግ ብሎ የሚመራው የከተማ አስተዳደር ያለ አይመስልም። በጥሩ ፕላን የተሠራን ፕላን ሲያበላሹ ነው የሚታየው። ለዚህም ነው የከንቲባው ከተማውን ዞሮ ማየት ጠቃሚነቱ። በዚህ ጉዳይ በጣም ይቆጨኛል፤ ለምን? ትናንትና የተነሳች ሩዋንዳ ቀድማ ስትሄድ እኛ ምን ይሆን የጎደለን? ክቡር ከንቲባው በዚህ ጉዳይ ቢያስቡበት መልካም ይሆናል።


ወደ ውጥንቅጡ የወጣበት የትራፊክ ጉዳይ ልግባና ቢወደድም ቢጠላ ትንሽ አስተያየት ልስጥ። የዚህ ተጠያቂ እንደሚመስለኝ በመጀመሪያ ፈቃድ ሰጭው ክፍል በሁለተኛ ደረጃ የጋጠ ወጥ ነጂዎች አሰልጣኞች ግን ለማሰልጠንስ ፈቃድ ማን ሰጠውና? አሁንም ተጠያቂ ፈቃድ ሰጪ ክፍል ከመሆን አያልፍም።


ስለሁኔታው መዘዘር አያሻም እንጂ ብዙ፤ ብዙ ማለት ይቻላል፤ ግን እንዲሁ ሾላ በድፍኑ እንለፈው። የየክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነሮች ሳያሰለጥኑ የትራፊክ ፖሊሶችን በየመንገዱ የመደቡት?


በ1960ቹ በኢትዮጵያ ከግራ አነዳድ ወደ ቀኝ በተዘወረችበት ዘመን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አልነበረም። በዘመኑ የነበረ ራድዮና ጋዜጣ ብቻ ነበሩ። በነኝህ የመገናኛ ዘዴዎች ተለፍፎ ያለአንዳች አደጋ ነበር ሁሉም መስመሩን ይዞ ሥርዓትን ጠብቆ ይነዳ የነበረው። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የአነዳድ ሕጉ በግራ ይሁን በቀኝ አይታወቅም። በየደረስኩበት መኪናዬን አቁሜ ፖሊሶችን ስጠይቅ በጨዋ ደምብ ነው የሚመልሱልኝ፤ ይህንን አድርጉ አታድርጉ አልተባልንም፤ አደጋ ሲፈጠር አደጋው የደረሰበትም ሆነ አደጋውን ያደረሰ በአስቸኳይ ቀለም አምጥቶ ፖሊስም ከጣቢያ አምጥቶ ነው የአደጋው ሁኔታ የሚለካው፡፡ በብዛት ስልክ የሚነጋግገርና ቀበቶ ያላሰረን ነው የምንከታተለው የሚል መልስ ነው የማገኘው። ታዲያ የማን ጥፋት ነው? ያጠፋ እንዳላጠፋም የሚፈረጅበትም ጊዜ አለ። ይህንንም እጅ ከፍንጅ በተያዘ ማስረጃ ለማቅረብ ይቻላል።


የአዲስ አበባ ፖሊስ ም/ኮሚሽነር በተሌቪዥን ኢንተርቪው ሲሰጡ ቢሮዬ ለወገኔ ባለጉዳይ ሁልጊዜ ክፍት ነው ብለው ነበር፤ በርግጥም ክፍት ነው፤ እርሳቸውን ማግኘት ግን ያን ያህል ቀላል አይደለም።


ይህ ሁሉ የጋራ ጉዳያችን ስለሆነ ተደፈርኩ ሳይሆን ይህንን ጉዳይ እንዴት ልናሻሻል እንችላለን ብለን ካልተነሳን፤ ይህንን የጻፈውን አግኝቼው በተበቀልኩት ሳይሆን በርግጥ ያላቸው ሁሉ ትክክለኛ ይሆኑ ብሎ አጣርቶና አረጋግጦ ተገቢውን ርምጃ መውሰዱ ለሁላችንም ጥቅም ይኖረዋል።


በመስኩ ያልሰለጠኑትን መመደቡ ያንድን ሰው ጥቅም ቢያሟላም አገርና ይጎዳል፤ ውጥንቅጣችንን ያባብሰዋልና እናስብበት። በንግድ ሚኒስቴር፤ በጉምሩክ፤ በፍርድ ቤቶች በኩል ያየሁትን ጉድ በሚቀጥለው ለመንግሥታችን እንዲመለከተውና የማያዳግ እርምጃ እንዲወስድ ለማቅረብ ዝግጁ ነኝ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
110 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 832 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us