የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል

Wednesday, 11 April 2018 14:30

 

ይህ ደብዳቤ በቀጥታ የተጻፈው በአድራሻ ለተመለከቱት አካላት ቢሆንም በአዲስአበባ ጤና ቢሮ ውስጥ በከፍተኛ አመራሩ የታገዘ የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባር የቱን ያህል ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ጥቆማ ይሰጣል። በሌሎች መሰል መንግሥታዊ መ/ቤቶችም የሚካሄደውን የጸረ ሙስናና የጸረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል ያነቃቃል በሚል በዚህ ገጽ ላይ አስፍረነዋል። (በደብዳቤው ላይ አንዳንድ ስሞች ማስቀረታችንን ለውድ አንባቢያን እንገልጻለን።)

 

* * *

 

 

~ ለክቡር ዶ/ር አቢይ አህመድ
የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የኢህአዴግ ሊቀመንበር
ለክቡር አቶ ድሪባ ኩማ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ
አዲስ አበባ

 

ጉዳዩ፡- እኛ የአዲስ አበባ ጤና ሴክተር ሠራተኞች በሴክተራችን ውስጥ የሚታየውን የከፍተኛ አመራር የሙስና፣ ብልሹ አሠራርና የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባር እንዲስተካከል አመራር ለመጠየቅ የቀረበ ጥቆማ፣


በቅድሚያ ለዚህ ታሪካዊ ኃላፊነት በመብቃትዎ እንደማንኛውም ዜጋ የተሰማንን ደስታ እንገልጻለን።


ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር


በሙስናና ብልሹ አሠራር ላይ በያዙት ጽኑ አቋም በመነሳሳት ጉዳዩን ስናቀርብ አስቸኳይ ምላሽ እንደሚሰጡን በመተማመን ነው።
የአዲስአበባ ጤና ቢሮ ከፍተኛ የመንግሥት እና የዓለም አቀፍ ረጂ ድርጅቶች ገንዘብና ሐብት ከሚንቀሳቀስባቸው ተቋማት ግንባር ቀደም መሆኑ ይታወቃል። ቢሮው የመንግሥትን የአምስት ዓመት መርሃ ግብር እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት የምዕተዓመቱ የጤና ግብ እንዲሳካ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሎ ተስፋ ከተጣለባቸው ተቋማት ግንባር ቀደሙ መሆኑም ይታወቃል።
ይህን ትልቅና ድርብ ኃላፊነትና ግብ የያዘ ተቋም በጥቂት የግል ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ በሚሯሯጡ አመራሮች እየተደፈቀ ያለበትን ተጨባጭ ሁኔታ እንደሚከተለው እናቀርባለን።

ክቡርነትዎ
ይህን ደብዳቤ ለእርስዎ ለመጻፍ የተገደድነው በአዲስ አበባ ጤና ምክትል ቢሮ ኃላፊ የሚመራው ቡድን ከሰባት አመታት በላይ በአዲስ አበባ ኤች አይ ቪ ጽ/ቤት፤ በከነማ ፋርማሲ፣ በአዲስአበባ የጤና ተቋማት፣ በጤና ቢሮው ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት እየጨመረ መሆኑና ንፁሐን ሠራተኞችና አመራሮች በተለያየ ጊዜ ከስራ ውጪ እየሆኑ በመሆኑ፤ ችግሩን በተመለከተ በተደጋጋሚ ለመንግስታዊ መዋቅር የሚቀርቡ አቤቱታዎች ሰሚ ባለማግኘቱ መሆኑን በቅድሚያ እናስታውሳለን።

 

በቢሮው የሚታዩ ችግሮች እንደማሳያ ፡-
1. ቡድንተኝነት


በምክትል ቢሮ ኃላፊው የሚመራ ሕገወጥ ቡድን ከላይ እስከታች መዋቅሩን የዘረጋ ሲሆን እንቅፋት ወይንም የጸረ ሙስና ትግል ሲገጥመው ሠራተኞችንና ባለሙያዎች በተለያዩ ጥቅማጥቅም በመደለል፣ በማስፈራራት፣ በማባረር የሚፈልጋቸውን ሕገወጥ ተግባራት በመፈጸም ላይ ይገኛል። ምክትል ቢሮ ኃላፊው በዘረጉት የቡድንተኝነት ኔትወርክ አማካይነት ከአዲስአበባ ኤችአይቪ ጽ/ቤት ወደ አዲስአበባ ጤና ቢሮ ተመድበው የመጡ ሲሆን በቢሮው ሥራ ከጀመሩ በኋላም ሕግና ሥርዓትን ባልተከተለ መንገድ ቀስ በቀስ የራሳቸው ሰዎች በዝውውር እያመጡ በቢሮው ውስጥ በቁልፍ የኃላፊነት ቦታዎች መድበዋል። በአዲስአበባ ሆስፒታሎች ቡድናቸው በማስፋት ለኪራይ ሰብሳቢነት አላማ የሚያመች አመራር በመመደብ የጤና ሴክተሩን እንደ ሸረሪት ድር የራሳቸውን መረብ በመዘርጋት ድብቅ አላማቸውን በማካሄድ ላይ ናቸው። ሙስናና ብልሹ አሠራርን ከየጊዜው የተቃወሙ ሠራተኞችና አመራሮች ጭምር የመባረር ዕጣ ገጥሟቸዋል።


ምክትል ቢሮ ኃላፊው ከፍተኛ ገንዘብ የሚንቀሳቀስባቸው የሲዲሲ ፕሮጀክት እና ሌሎች ፕሮግራሞችን የሚመራውን የምክትል ቢሮ ኃላፊ ዘርፍ ለመቆጣጠር በኔትወርኩ ሲሰራ በነበረው ስም የማጥፋት ዘመቻና እንቅስቃሴ ለሴራቸው ያልተመቹ ሁለት ምክትል ቢሮ ኃላፊዎች በሐሰት በመወንጀል ከስራቸው እንዲሰናበቱ ሆነዋል። ዋና የቢሮ ኃላፊ የነበሩት ለዝርፊያ ቡድኑ የማይመቹ ሆነው ስለተገኙ በተሀድሶ ስም ንጹህ ግለሰብ እንዲሰናበቱ ተደርገዋል። በቅርቡም ምክትል ቢሮ ኃላፊው በራሱ ፈቃድ ራሱ በራሱ የበሽታ መከላከል ምክትል ቢሮ ኃላፊ አድርጎ ሾሟል። ይህም የሆነበት ምክንያት በፕሮግራሞቹ የተመደቡ ከፍተኛ በጀት ሆን ተብሎ በሕገወጥ መንገድ ጥቅም ላይ ለማዋልና ለመመዝበር ታቅዶ የተከናወነ ነው ብለን እንገምታን።

የሲዲሲ ፕሮጀክት የተቀነባበረ ዘረፋ፣


በቢሮው ውስጥ በዓመት ከ100 ሚሊየን ብር በላይ የሚንቀሳቀስበት የሲዲሲ ፕሮጀክት አለ። ይህን ፕሮጀክት በኔትወርክ ለመያዝና ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት አድርገው የፕሮጀክት ዋና ዋና የሥራ ቦታዎችን በራሳቸው ኔትወርክ አጠናክረዋል።


የጤና ተቋማቶችን ለማጠናከር በፕሮጀክቱ በብዙ ሚሊየን ብሮች የሚገዙ የሕክምና መሳሪያዎች ግዥ ከተፈጸመ በኋላ ለታቀደላቸው ተቋማት ሳይደርስ አየር በአየር የሚጠፉበት ተጨባጭ ክስተት አጋጥሟል። ለአብነት ያህል በቅርቡ ከመድሃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ ከ19 ሚሊየን ብር በላይ የተገዙ የሕክምና መሳሪያዎች ለቢሮው ገቢ ሳይሆኑ የት እንደገቡ ሳይታወቅ ቀርቷል።


በዚሁ ፕሮጀክት በሀገር ውስጥ እና በሀገር ውጭ የሙያ ልምድ ልውውጥ ፕሮግራሞች ቢኖሩም በተጨባጭ የሚሳተፉት የቢሮው ሙያተኞች ሳይሆኑ ግለሰቡ ያዋቀረው ኔትወርክ ቡድን አባላትና ወደፊት ለመመልመል የሚታሰቡ ግለሰቦች ማማለያ ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው። በዚህም ኢ- ፍትሐዊ አሠራር አብዛኛው የቢሮው ባለሙያ ከፍተኛ ቅሬታውን በቀጥታም በተዘዋዋሪም እያቀረበ ይገኛል።


ፕሮጀክቱ ገንዘብ አወጣጥ ግልጽነት የጎደለውና ሥራውን ፈጻሚ ክፍሎች እንዳያውቁት ተደርጎ ጭምር፣ በጀቱን በፈለጉት መልክ እያዘዋወሩ ግልጽ የዘረፋ ሥራቸውን በማከናወን ላይ ይገኛሉ።
የሲዲሲ ፕሮጀክት በአገር አቀፍ ደረጃ ጠቀሜታው እጅግ የላቀ መሆኑ የሚዘነጋ ባይሆንም በተለይ በጤና ቢሮው በሰፈነው የኪራይ ሰብሳቢ አመለካከትና ተግባር ጋር ተያይዞ የግጭትና የአመራር አለመረጋጋት ምንጭ መሆኑ ቢሮው የተጣለበትን ከፍተኛ አገራዊ ኃላፊነት በአግባቡ እንዳይወጣ እንቅፋት ሆኖ ይገኛል።

 

2. የግንባታ ፕሮጀክቶችን በተመለከተ፣


በአሁኑ ወቅት በቢሮው ስር ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የጤና ጣቢያ ግንባታዎች እና በግምት ከስድስት ቢሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የሶስት ሆስፒታል ግንባታዎች ዕቅድና ተግባር በቢሮው መኖሩ ይታወቃል። በተለይ የተጀመሩ የጤና ተቋማት ግንባታ አፈጻጸም ለሙስናና ብልሹ አሠራር የተጋለጠ ስለመሆኑ በየጊዜው ከሠራተኞች የሚሰጠው አስተያየትና ጥቆማ ቡድንተኛው አመራር ተቀብሎ የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ ፈቃደኛ አልሆነም።


ከግንባታው ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ግዥ የሚፈጸምባቸው ጨረታዎች ሒደት ለሙስናና ብልሹ አሠራር በኔትወርኩ ሙሉ በሙሉ የተያዘ ነው።
እነዚህ የግንባታና የግዥ ሒደቶች ሆን ተብሎ ለኪራይ ሰብሳቢነት በከፍተኛ ደረጃ በመጋለጣቸውና ይህንንም ተከትሎም የዝርፊያ ቡድንተኝነት መንሰራፋት ምክንያት የቢሮው ሠራተኞች ተረጋግተው የተጣለባቸውን ሃላፊነት በየደረጃው እንዳይወጡ ከፍተኛ ማነቆ ሆኗል።


3. አላስፈላጊ ስብሰባዎች በማድረግ ተጠቃሚ ለመሆን መሞከርን በተመለከተ በስፋት የሚታይ ነው። በቢሮው ስብሰባዎች ይቸረቸራሉ። ይህም ማለት ሰብሰብ ተደርጎ አንድ ላይ መከናወን ያለባቸውን ስብሰባዎች በክፍለከተሞች ጭምር በመቆራረጥ በዛ ያሉ ሰብሰባዎች እንዲከናወኑ ይደረጋል። ይህ ዓይነቱ አሠራር የሐብት ብክነትን ከማስከተሉ ባሻገር የሥራ ጊዜንም የሚሻማ ነው። በዚህ አጋጣሚ አንዳንድ ባለሙያዎችና የቢሮው ኃላፊዎች በቀን ውስጥ ሁለትና ሶስት ስብሰባዎች እየዞሩ የአበል ክፍያዎችን የሚወስዱበት አሠራር የተለመደና ሕጋዊ መልክ እየያዘ መጥቷል።

4. የከነማ ፋርማሲዎችን አስደንጋጭ የሙስና ሁኔታ በተመለከተ፣


በአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ሥር በድምሩ 16 የከነማ ፋርማሲዎችና ሁለት መደብሮች ያሉ መሆኑ ይታወቃል። ፋርማሲዎቹ ለህብረተሰቡ ጥራት ያለው መድሃኒት በተመጣጣኝ ዋጋ የማቅረብ ተልዕኮ ያላቸው መሆኑም የሚዘነጋ አይደለም። በከነማ ፋርማሲዎች የሚታዩ የሙስናና የብልሹ አሠራር በተደጋጋሚ የተጠና ቢሆንም በጤና ቢሮውም ሆነ በከተማ አስተዳደሩ በኩል የተወሰደ የማስተካከያ እርምጃ ባለመኖሩ ችግሩ ቀጥሏል። ጉዳዩን በተጨባጭ መረጃ ለማቅረብ ያህል ድርጅቱ ላይ ያሉ ችግሮች እንዲጣሩ ኮምቴ ተዋቅሮ ግኝቱን ይፋ ያደረገው የመጀመሪያው በ2005 ቀጥሎ በታህሳስ ወር 2009 ዓ.ም ነበር። በዚህ ኮምቴ እዚህ ልንጠቅሰው የማንችለው እጅግ አስደንጋጭ ግኝት አግኝቷል። ይህ ከሕግ ብቻ ሳይሆን ከሞራልም አንጻር እጅግ አሳፋሪ ተግባር ሲሆን ከሪፖርቱ በኋላ ባለው አንድ ዓመት የተጠጋ ጊዜ ተገቢውን እርምት የተወሰደበት አለመሆኑ ሰሚውን ሁሉ ግራ የሚያጋባ ሆኗል። እንዲህ ዓይነቱ የከፋ ሙስና «አስቀድሞ መከላከል» የሚለውን የጤና ፖሊሲያችንን የሚጎዳና የህብረተሰብን ጤና የከፋ አደጋ ላይ የሚጥል፣ የመንግሥትና የሕዝብ መልካም ግንኙነት ጥርጣሬ ላይ የሚከት መሆኑ ግልጽ ነው።

5. የኤች አይ ቪ ጽ/ቤት የሙስና ሁኔታ በተመለከተ፣


· በአሁኑ ወቅት የጤና ቢሮው ምክትል ሀላፊ ቀደም ሲል ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ የኤች አይ ቪ ጽ/ቤት ኃላፊ ሆነው ሲሰሩ የኮንደም ግዥ ጋር በተያያዘ እንዲሁም ቫይረሱ በደማቸው ካለ ወገኖች ማህበር አንዳንድ አመራር አባላት ጋር በመመሳጠር በእጅ አዙር የተደረገ የገንዘብ ምዝበራ መኖሩ መረጃዎች አሉን፣

 

6. ኪራይ ሰብሳቢው ኃይል የከፍተኛ የመንግሥት አመራሮችን ስም፤ ለሕገወጥ ተግባሩ ማስፈጸሚያ በይፋ እየተጠቀመ ስለመሆኑ፣


ኪራይ ሰብሳቢው ኃይል በግልጽ « ከንቲባው ጓደኛዬ ነው፤ ምክትል ከንቲባው ጓደኛዬ ብቻ ሳይሆን አማካሪዬ ነው፣….» እና መሰል ወሬዎችን በማውራትና በማስወራት ሠራተኞችና አንዳንድ ሕገወጥ አሠራሮችን የሚቃወሙ አመራሮችን ለማሸማቀቅ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። በተጨማሪም አንዳንድ መድረኮችን ጓደኛዬ የሚሏቸው ከፍተኛ አመራሮች ስብሰባውን እንዲከፍቱ በማድረግ ስብሰባው የማይመለከታቸውን ሠራተኞች በሙሉ እንዲገኙ ጭምር በማድረግ፣ እግረመንገድ ጓደኝነትንና ተክለስብዕናን መገንቢያ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።

7. ፀረ-ዲሞክራሲያዊነት ፍጹም አምባገነንት፣


በጤናው ዘርፍ በአጠቃላይ ከፍተኛ አመራሩ በሕግና በሥርዓት አለመመራት፣ ግልጽነት አለመኖር፣ አለማሳተፍ፣ ለሚነሱ ችግሮች በቀናነት ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ግለሰቦችን ማሳደድ የመንግሥት ስልጣን ያለ አመለካከት የተዛባ መሆንና ለግል ሐብትና ጥቅም ማስጠበቂያ ማዋል፣ የተቋሙ የሕዝብ ጤና ጥበቃ መሆኑ ቀርቶ ለጥቂት ግለሰቦች ጥቅም ጋር በተያያዘ የሕዝብን ጤና የሚጎዳና አደጋ ላይ የሚጥል፣ በረዥም ጊዜ ውጤቱም በመንግሥትና በሕዝብ መካከል መተማመንን የሚንድ ሆኗል። በተጨማሪም ኪራይ ሰብሳቢው ኃይል የመንግስትን ሥልጣን በተደራጀ መንገድ በቡድንተኝነት መሳሳብ ይዞ የግል ጥቅሙን ለማስጠበቅ ሲል ሐቀኛ ሠራተኞችን ለይቶ የማጥቃት ተግባሩን አጠንክሮ ገፍቶበታል። ለሕገወጥ ተግባራቸው የማይተባበሩ ሠራተኞችንና ሙያተኞችን ማሸማቀቅ፣ ከሥራ ማሰናበት፣ ጥቅምና ዕድገት መከልከል ሥራዎችን በማከናወን ሰፊው ሠራተኛ እንዲጎዳ፣ በሥራው ተስፋ እንዲቆርጥ በማድረግ የሕዝብ አገልግሎት እንዲበደል ትልቁን አፍራሽ ሚና ተወጥቷል፣ እየተወጣም ይገኛል። እንደአንድ አብነት ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ የጤና ሴክተር አመራር መረጋጋት ማጣቱን ማንሳት ይቻላል። ከቡድኑ ጋር ባለመተባበራቸው ወይንም ባለመወገናቸው ብቻ ከጤና ቢሮ የተባረሩና መሯቸው እንዲሄዱ የተደረጉ ሶስት ሴት እና ሁለት ወንድ አመራሮች በተከታታይ ይታሰቡ፤ የኋላ ታሪካቸውም ይጠና። ከእነዚህ አመራሮች መካከል ሁለቱ በቢሮ ኃላፊነትና በምክትል ቢሮ ኃላፊነት ደረጃ የነበሩ ናቸው።


በአጠቃላይ በኪራይ ሰብሳቢነት በተቋሙ መንሰራፋት ተቋሙ የተጣለበትን የመንግስትና የህዝብ ኋላፊነት መወጣት ከማይችልበት ደረጃ እንዲደርስ አድርጎታል። በሰራተኛውና በማኔጅመንቱ መካከል ከፍተኛ ቅራኔ በመፈጠሩ ምክንያት መተማመን የማይቻልበት ሁኔታ ተደርሷል። በብልሹ አሰራር የተዘፈቀው አመራር ራሱን ለመከላከል በሚወስዳቸው እርምጃዎች ሠራተኛው ተሸማቆ እንዲኖር አድርጓል። ትልቅ ራዕይና ዓላማ ያለው ተቋም በዚህ ሁኔታ ተሸመድምዶ በኪራይ ሰብሳቢዎች ሙሉ ቁጥጥር ሥር ወድቋል።

 

ክቡርነትዎ


መንግሥታችን ከአንድ ዓመት በፊት ባስቀመጠው ጥልቅ ተሀድሶ መሠረት በሴክተራችን ውስጥ የመንግስት ሥልጣን ለግል ጥቅማቸው እያዋሉ የሚገኙ እና ላለፉት ዓመታት በምክትል ቢሮው ኃላፊው የተደራጀውን ኔትወርክ ለመበጣጠስ ሰፊው የሴክተር ሠራተኛ በተዋረደ በተገኘበት ግልጽ የሆነ የተሀድሶ መድረክ እንዲመቻችና በግምገማው ውጤት መሠረት ተገቢውን ማስረጃና መረጃ ተሰብስቦ አጥፊዎች በሕግ እንዲጠየቁ ተገቢውን አመራር እንዲሰጡልን እንጠይቃለን።


ከዚህ በላይ ላቀረብነው አቤቱታ የሰውና የሰነድ ደጋፊ ማስረጃ በተጠየቅን ጊዜ ማቅረብ የምንችል መሆኑን እየገለጽን አቤቱታችን ተገቢውን ማጣራት ተደርጎበት በአዲስአበባ ጤና ቢሮ የተንሰራፋው ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ሙስናና ብልሹ አሠራር ላይ የማጥራት እርምጃ እንደሚወሰድበት እንተማመናለን።

ኪራይ ሰብሳቢነት በትግላችን ይደፈቃል!

ከሠላምታ ጋር
ከአዲስ አበባ ጤና ሴክተር ሠራተኞች
ቀንና ፊርማ አለው

 

ግልባጭ
- ለክቡር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፤ የኢህአዴግ ምክርቤት ጽ/ቤት ኃላፊ
- ለክቡር አቶ ተወልደ ገ/ጻድቃን፤የአዲስ አበባ ኢህአዴግ ጽ/ቤት ኃላፊ

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
101 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 923 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us