ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ማረሚያ ቤቶችን የመዝጋት ምኞትና ተግባሩ

Wednesday, 18 April 2018 13:22

 

በግርማቸው መሪጌታ

በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚታተመው ዕለታዊው የኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 15/2018 (የካቲት 8 ቀን 2010 ዓ.ም) ዕትሙ ለአማራ ክልል ወልድያ ከተማ እና ጭልጋ ከተሞች የማረሚያ ቤት ሕንጻ ግንባታ ጨረታ ይዞ መውጣቱ ለዚህ ጽሁፌ መነሻ ሆኗል። የዚህ ማረሚያ ቤት ግንባታ ጨረታ የወጣው የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እስካሁን በሀገራችን ለተፈጠሩ ፖለቲካዊ ቀውሶች ኃላፊነቱን እንደሚወስድ ቃል በገባበት ወቅት መሆኑ የተለየ ያደርገዋል። የግንባሩ ቅርብ ጊዜ መግለጫው በጠራራ ፀሐይ በሕግ ማስከበር ስም ሰብዓዊ መብት የሚረገጥበትን የፌዴራል ወንጀል ምርመራ በቀድሞ አጠራሩ ማዕከላዊ ዘግቶ ወደሙዚየምነት ለመቀየር መወሰኑን ይፋ አድርጓል። ይህንንም ውሳኔ ተከትሎ ከሳምንት በፊት ማዕከላዊ ተዘግቷል። ኢህአዴግ ማዕከላዊን ለመዝጋት የወሰነው እስርና የሰብዓዊ መብት ረገጣ በዚህች ሀገር እንደማይቀጥል ለማመላከት እንጂ ሙዚየም ማሳያ ህንፃ በማጣቱ አይደለም። እናም በቅድሚያ ህንፃውን ከመዝጋቱ አስቀድሞ የአመራሩ ሥነ ልቦና ውስጥ የበቀለው የእስር አባዜ ዶሴ መዘጋት ነበረበት። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ረሀብተኞች፣ በአካባቢያዊ ግጭቶች የተፈናቀሉ ወገኖች በበዙበት ሀገር እስረኛ ማሰሪያ (ማጎሪያ) ቤቶችን ማስፋፋት ዘመኑ የሚፈቅደው አስተሳሰብም አይደለም። የዲሞክራሲያዊ መንገድ እከተላለሁ የሚል መንግስት ባህርይም አይደለም።

እስርን በተመለከተ የአገራችን ሰው ሲመርቅ “የታሰሩትን ያስፈታልን!” ወይም “በወህኒ ቤት ለሚገኙት ወገኖቻችን የምህረት ጊዜ ይምጣ!” ይላል። ዛሬ በአገራችን “ማረሚያ ቤት” የሚባሉት “እስር ቤቶችን” ወይም “ወህኒ ቤቶችን” በተመለከተ ቀደም ሲል ከነበረው በቁጥር እየበዙ መምጣታቸው እጅግ የሚገርም ነው። “በወህኒ ቤትነት” ሳይሆን “በማቆያነት” አገልግሎት የሚሰጡ (የሚታወቁ” “እስረ ቤቶች ተለይተው ባለመታወቃቸው የተነሳ “ማን የት እንደታሰረ?” ፈልጎ ለማግኘት ከቂሊንጦ ወደቃሊቲ ከዚያም ወደዝዋይ ካልሆነም ሸዋ ሮቢት መሄድ ግድ ይላል። በተለምዶ “ከርቸሌ” እና “ዓለም በቃኝ!” የሚባለው ቦታ ወደ ቃሊቲ ሲሸጋገር አሁን “ቂሊንጦ” የሚባለውን ቦታ ወልዶ በዚህም ሳይወሰን የታሳሪው ቁጥር ሲበዛ ወደ “ሸዋ ሮቢት” እና “ዝዋይ” ከዚያም ባለፈ በየማሰልጠኛ ጣቢያው (ዲዴሳ እና ብላቴን) ወይም ብርሸለቆ ድረስ እስር ቤት የመሆናቸው ጉዳይ የአገራችንን ፖለቲካዊ ሁኔታ ያሳያል ዛሬ እነዚህ ቦታዎች ታሳሪ ባይኖርባቸውም ሁሉንም የአገራችንን እስር ቤቶች በተመለከተ ወደ አገልግሎት ሰጭነት ወይም የማሰልጠኛ ተቋም በማድረግ ገፅታቸውን መለወጥ ይገባል።

ኢህአዴግ “ራሴን ፈትሼ የአመራር ድክመት ነበረብኝ በማለት ጥልቅ ተሀድሶ” ባደረገ ማግስት “ማዕከላዊ ምርመራ” እንዲዘጋ ወስኗል። ሙዚየም እንደሚሆንም ተገልጿል። ቦታው እንደ “ዓለም በቃኝ!” ለተሻለ ህዝባዊ አገልግሎት እንዲበቃ ማድረግ ደግሞ የበለጠ ጠቀሜታ እንደሚያስገኝ ይታመናል። “ዓለም በቃኝ!” የሚባለው እስር ቤት ሙሉ ሉሙሉ እንዲፈርስ ተደርጎ ቦታው አህጉራዊ ድርጅት የሆነው የአፍሪካ ህብረት (AU) ዋና ጽ/ቤት ተገንብቶበት ለአገልግሎት በመብቃቱ አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት ዋና መቀመጫና የአፍሪካ መዲና በመሆን አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ትኩረት ማግኘቷ በአንድ በኩል የከተማውንና የአገራችንን ገፅታ ከመገንባት በተጨማሪ በኮንፍረንስ ቱሪዝም ተጠቃሚ መሆን ተችሏል። ይህ እውነት አሁን በአገራችን የሚገኙ እስርቤቶች (ወህኒቤቶች) ወይም ማረሚያ ቤቶችን ቁጥር (ብዛት) በመቀነስ ለህዝባዊና ለተሻሉ አገልግሎቶች እንዲውሉ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው። ደርግ በራሱ መስመር “ማዕከላዊ ምርመራ” እና “ቤርሙዳ” ከሚባሉ ቦታዎች በተጨማሪ የተለያዩ መመርመሪያና ማሰቃያ ቦታዎች እንደነበሩት ሁሉ ኢህአዴግ ያንን ተቀብሎ በማጠናከር በተለያዩ ከተሞች ጭምር ማጎሪያዎች እና እስር ቤቶች ማብዛቱ “ትሻልን ትቼ ትብስን…” ሆኗል። በየጊዜው ከሚነሱ ፖለቲካዊ ጥያቄዎችና ተቃውሞዎች ጋር ተያይዞ በርካታ ዜጎች በተለይም ወጣቶች በተለያዩ አካባቢዎች በእስር ቆይተው አሁን ባለው ሁኔታ ከእስር እንዲለቀቁ መደረጉ በበጎ ጎኑ ተቀባይነት ያለው ቢሆንም የእስር ቤቶቹ (ማቆያ ቦታዎቹ) ግን እንዳሉ አሉ። (ከማዕከላዊ ምርመራ መዘጋት በስተቀር)።

በእርግጥም ሰዎች በሕግ ተጠያቂ ሲሆኑ ወንጀል ሲፈፅሙ እንደጥፋታቸው ዓይነት ፍርድ እየተሰጣቸው ወደእስር ቤት እንደሚገቡ ይታወቃል። በዚህ መልኩ የሚታሰሩ ሰዎች የተወሰነባቸውን ቅጣት አጠናቀው እስኪወጡ ድረስ የሚቆዩበት (የሚታሰሩበት) ቦታ መኖር ግድ ቢልም እነዚህን ቦታዎች በተሻለ ሁኔታ በማዘመን “እስረኛው” ከጥፋቱ የሚታረምበት በተለየ ሙያ ብቁ ሆኖ የሚወጣበት ቦታ ሆነው ቢዘጋጁ “በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ” እንደማለት ነው። ይህ አዳዲስ እስርቤቶች (ወህኒቤቶች) በመገንባት ሳይሆን ያሉትን በተሻለ የእስረኛ አያያዝ የመማሪያና የመታረሚያ ቦታ በማድረግ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል።

ዛሬ “ማረሚያ ቤት” የሚባለው ቦታ በእርግጥም ሰዎች የሚታረሙበት ስለመሆኑ ምንም የተካሄደ ጥናት የለም። ያ! ቢሆንና በእርግጥም የሚታረሙበት ቦታ ቢሆን ኖሮ በተደጋጋሚ በመታሰር የሚታወቁ ወንጀለኞች ባልኖሩ ነበር ስያሜው “ወህኒ ቤት” “ከርቸሌ” እስር ቤት “ማረሚያ ቤት” መባሉ እንዳለ ሆኖ በእንግሊዘኛው “ፕሪዝን (prison) “እስር፣ እስረኛ” ስለሆነ እስር ቤት ማለት ይበቃል።

ስለ እስር ቤት ህይወት ሲገለፅ “ከመታሰር ይሰውረን!” እንጂ በተለያዩ እስር ቤቶች ያለው እውነታ እንደእስረኛው ዓይነት ከመለያየቱም በላይ በግንብ አጥር ውስጥ ሆኖ ሰማይን ከማየት በስተቀር የሰው ናፍቆቱ የበዛ ነው። የታሰረ ሰው ጠያቂ ይፈልጋል፣ ሰው ይናፍቃል። ማዕከላዊ አሁን ተዘጋ እንጂ አራት በአራት በሆነ ክፍል ከ12 ሰዎች በላይ አንድ ላይ ታጉሮ ሙሉለሙሉ ብረት በሆነ በር በትልቅ የጓጉንቸር ቁልፍ ተቆልፎባቸው ከተለያዩ ስቃይና ግርፋቶች ጋር ማሳለፍ እጅግ ዘግናኝ ነው። ያ!እውነት ለታሪክ ይቀመጥ።

በከርቸሌ (ወህኒ ቤት) በተለይ አቃቂና ቂሊንጦ የታሰረ ሰው ደግሞ የራሱ ገጠመኝ አለው። በከርቸሌ “ደቦቃ” የሚባለው ቦታ አንዱ ሰው በሌላ ሰው ሰውነት የሚደበቅበት፣ በአንድ ጎን ብቻ የሚተኛበት፤ ሁለት ሰዎች ጆንያ የሚደረድሩ ይመስል የሌላውን እስረኛ እጅና እግር በማንጠልጠል በተጋደመ ሰው ሰውነት ላይ በመለጠፍ አንዱ ሰው የሌላውን እግር እየተንተራሰ በጎን በኩል በመደርደር መገላበጥ ጨርሶ በማይታሰብበት ሁኔታ መሽቶ የሚነጋበት ሁኔታ የበዛ ነው። የእስረኛው ክስ ግን በአያያዝ ጭምር የተለያየበት አሰራር አንዳንዱ ከፍተኛ ተፅዕኖ በመፍጠር መንገላታት የሚታይበት ነው።

የእስር ቤት ህይወት አሳዛኝ አስከፊና አስገራሚ የመሆኑን ያህል አስደሳች የሚሆንበት ወቅትም አለ። በመታሰራቸው ሞራላቸው የተነኩ በማይጠበቅ ሁኔታ ብርቱ የሚሆኑበት፣ ትልቁ የሚያንስበት፣ ትንሹ ትልቅ የሚሆንበት አጋጣሚ በርካታ ነው። የታመቁ እውነቶች ድብቅ ሀሳቦች በድንገት ሕይወት ዘርተው በመውጣት ለሌላውም አስተማሪ የሚሆኑ ልምዶችና ተሞክሮዎች የሚገኝበት ነው። እውነቱ ሰፊና በርካታ በመሆኑ በእስር ቤት ህይወት ጉዳይ ወደፊት በዝርዝር ለማቅረብ ይቻላል።

ወደዋናው ጉዳይ ስንመለስ ግን አሁን የምንገኝበት የአገራችን ሁኔታ እስር ቤቶች (ወህኒቤቶች) የሚገነቡበት ባለመሆኑ ያሉትን እስርቤቶችንም ጭምር ወደልማት ማዕከላት ለመለወጥ መስራት ያስፈልጋል። አዲስ ወህኒቤት ለመገንባት የተያዘ በጀት ካለም ወደሌላ የህዝባዊ አገልግሎት ተቋም ግንባታ በመቀየር እንደትምህርት ቤት ወይም የጤና ተቋማት (ሆስፒታል) በመገንባት ወደልማት ሥራ እንግባ። አሁን በግልፅ የሚታወቁትንና የማይታወቁትን እስር ቤቶች ቁጥር በመቀነስ ጭምር (በመዝጋት) ከእስረኛነት እንላቀቅ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
98 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 921 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us