ህግን ያልተከተለ አሰራር ያማረው ጉባኤው ወይስ ቅሬታ አቅራቢዎቹ?

Wednesday, 09 May 2018 13:35

ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነን ሰንደቅ ጋዜጣ ሚያዝያ 24 ቀን 2010 የረቡዕ ዕትሙ በዜናና በዓምድ ዘገባው ያሰፈረው “የፌዴራል ዳኞች ምልመላ ቅሬታ አስከተለ” የሚለው የተሳሳተ ዘገባ ነው። ጋዜጣው ቅሬታ አቀረቡልኝ ያላቸውን አቤቱታ አቅራቢዎች ጠቅሶ እንደዘገበው የፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ለሶስቱም የፌደራል ፍ/ቤቶች ዕጩ ዳኞችን ለመመልመል በቅርቡ ያካሄደው የማጣሪያ ምልመላ “ህግን ያልተከተለ አድልኦና መገለል ያለበት አሰራር ነው” በማለት ያትታል። ቅሬታ አቅራቢዎቹ ይህንን አስመልክተው ለኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ያቀረቡት ማመልከቻም ጋዜጣው በዚሁ እትሙ ማውጣቱ ይታወቃል። ወደ ጉዳዩ ከመግባታቸው በፊት አንድ ቅሬታ የቀረበበት ጉዳይ ቅሬታውን መርምሮ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ አቤቱታው የቀረበለት “ቅሬታ ሰሚ አካል” በኩል በቀረበለት ጉዳይ ላይ ውሳኔውን ከማሳወቁ በፊት (ጉዳዩ የቀረበለት አካል ቅሬታውን በይግባኝ የማየት በህግ የተሰጠው ግልፅ ስልጣን አለው የሚለውን ግምት ወስደን) ቅሬታ አቅራቢውም ሆነ አንድ የፕሬስ ውጤት በእንጥልጥል ላይ ያለን ጉዳይ ያውም ክስ የቀረበበት አካል ሳይጠየቅና ምላሹን ሳይሰጥ በሚዲያ ማሰራጨት ተገቢ ነው ወይ? በቅሬታ ሰሚው ላይ ከወዲሁ ተፅዕኖ ለማሳደር ወይም የምልመላ ሂደቱን ለማደናቀፍና ብዥታ ለመፍጠር ታስቦ የተወጠነ አይመስልም ወይ? የሚሉትን ጥያቄዎች እንደምንመለስበት ታሳቢ በማድረግ በቀጥታ ወደ ጉዳዩ እንግባ። ከሁሉም በፊት አንባቢ በተነሳው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ተገቢ ግንዛቤ እንዲኖረው በማሰብ ስለ ፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ስልጣንና ተግባር እንዲሁም የእጩ ዳኞች የምልመላ ስርዓት ትንሽ ማለቱ ተገቢ ይሆናል።

በኢትዮጵያ ታሪክ ትኩረት ተነፍጓቸው ተዳክመውና ተልፈስፍሰው ከቆዩት መንግስታዊ ተቋማት መካከል ፍ/ቤቶች በመጀመሪያ ረድፍ ይሰለፋሉ ቢባል ማጋነን አይሆንም። ዘመናዊ ዳኝነት በኢትዮጵያ ከተዘረጋ ከ1934 ጀምሮ ለሁሉም ዜጎች ክፍት የሆነ፣ አሳታፊ፣ ግልጽነት የተላበሰና በብቃት ላይ የተመሰረተ የአሿሿም ስርዓትና በሚታወቅ ዝርዝር መስፈርት የተመሰረተ የዳኝነት የምልመላ ስርዓት እንዳልነበረ ለማንም የተሰወረ አይደለም። ለዳኛ የሚያበቁ ግልጽ መስፈርቶች ወጥተው መስፈርቱን እናሟላለን የሚሉ ዜጎች እንዲወዳደሩ የተሰጠ ዕድል አልነበረም። ዳኛ የመመልመልና የመሾም ወይም የማሾም ሙሉ ስልጣኑ የአስፈፃሚ ከመሆኑም በላይ አንድ ሰው በየደረጃው ላሉ ፍ/ቤቶች እንዴት በዳኝነት እንደሚሾም፤ ከተሾመ በኋላ ያለውን ነፃነትና የተጠያቂነት ስርዓት በዝርዝር የህግ ማዕቀፍ የተደገፈ ስርዓትም ሆነ የዳኝነት አካሉን ከምልመላው ጀምሮ የስራ አፈፃፀሙን የመከታተልና የመቆጣጠር ስልጣን ያለው ገለልተኛ አካል አልነበረም ማለት ይቻላል።

በኢትዮጵያ ታሪክ በዳኞች ምልመላና አሿሿም ላይ መሰረታዊ ለውጥ የመጣው የፌዴራል የዳኝነቱ አካሉን በገለልተኛ አካል ማስተዳደር ከተጀመረ በኋላ ነው። የተሻሻለው የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ አዋጅ ቁጥር 684/2002 ለዚህ ተጠቃሽ ነው። በዚህ አዋጅ የዳኝነት ነፃነትና ገለልተኝነትን ለመጠበቅ ሲባል የጉባኤው አባላት ስብጥር ከአስፈፃሚው ውጭ ተደርጓል። (ጉባኤው ከፌደራል የዳኝነት አካል አምስት፣ ከህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ሶስት፣ ከአስፈፃሚ አንድ፣ ከጠበቆች ማህበር አንድ፣ ከዩኒቨርስቲ የህግ ተቋም አንድ፣ ከታዋቂ ሰው አንድ ያቀፈ ሆኖ የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት የጉባኤው ሰብሳቢ ናቸው። አዋጁ የፌዴራል ፍ/ቤቶች ዳኞችን የመመመልመል ሥልጣን ለጉባዔው ይሰጣል። ጉባዔው አዋጁን ለማስፈፀም ደንብ ወይም መመሪያ ሊያወጣ እንደሚችል በአዋጁ አንቀጽ 14 በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት በ2003 ዓ.ም የፌዴራል ፍ/ቤቶች ዕጩ ዳኞች ምልመላ ሥርዓት አፈፃፀም መመሪያ አውጥቶ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል።

ይኸው አሳታፊ ግልፅነት የተላበሰና በኢትዮጵያ የዳኝነት ታሪክ እንደ አንድ እመርታዊ ለውጥ የሚታየው የምልመላ ሥርዓት የተወዳዳሪዎች የምዝገባ ሂደት፣ የማስታወቂያ አገላለፅና የማጣሪያ ሥርዓቶች፣ እንዲሁም ውጤት አገላለጽ ግልጽነት ባለው መንገድ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ እኩል ዕድል በሚሰጥ አቅጣጫ እየተመራ ይገኛል። የምልመላ ስርዓቱ ግልጽነት ለተወዳዳሪዎች ብቻ ሳይሆን ሂደቱን መከታተል ለሚፈልግ ሶስተኛ ወገንም ሆነ ለሕዝብ ተደራሽ እንዲሆን በማሰብ በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች ጭምር በመጠቀም ሂደቱን አሳታፊና ግልፅነት የተላበሰ ለማድረግ የተጓዘው ርቀት ቀላል የሚባል አይደለም። ስለሆነም የጉባኤው የዳኞች የምልመላና የአሿሿም ስርዓቱ ለሌሎች ተቋማት እንደ አንድ የጥሩ ተሞክሮ ማዕከል ሆኖ ያገለግል እንደሆነ እንጂ የሚያስወቅሰው አይሆንም። እያንዳንዱ የምልመላ ሂደት ከተወዳዳሪዎች ጥሪ ማስታወቂያ ጀምሮ የምዝገባ፣ የቅድመ ማጣሪያ፣ የፅሁፍ ፈተና፣ የቃለ መጠይቅ ሂደቱም ሆነ በመጨረሻም በዚህ መንገድ የተመለመሉትን ዕጩ ዳኞች ለሹመት ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ከመቅረባቸው በፊት ሥነ-ምግባራቸው ለሕግና ለሕገ-መንግሥቱ ያላቸው ተገዢነትና እምነት በተመለከተ በሕዝብ አስተያየት እንዲሰጥባቸው ይደረጋል። ስለሆነም በጉባኤው የሚመራው የፌዴራል ዳኞች የምልመላ ሥርዓት ከማንም ተቋም በላይ በግልፅ መስፈርት ተመስርቶ የሚከወን አሳታፊና በግልጽነት የተሞላ ብቻ ሳይሆን በሂደቱ ቅሬታ ያለው አካል ቅሬታውን የሚያቀርብበትና ምላሽ የሚያገኝበት ስርዓት ዘርግቶ የሚካሄድ መሆኑ ሂደቱን ሙሉዕ ያደርገዋል።

በዚሁ መሰረት ባለፉት ሰባት ዓመታት ለሶስቱም የፌደራል ፍ/ቤቶች የተደረገው የዕጩ ዳኞች ምልመላ ስርዓት (በ2004፣2006 እና 2008) ለተወዳዳሪዎች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ዜጋ ግልፅ አሳታፊ፣ ተደራሽና ተአማኒ እና ብቃት ላይ በተመሰረተ መንገድ መፈፀም ተችሏል።

በ2010 እየተካሄደ ያለው የፌዴራል ፍ/ቤቶች የዕጩ ዳኞች የምልመላ ሂደትም ከላይ የተጠቀሱትን የህግ ማዕቀፎችና መስፈርቶች ተከትሎ እየተከናወነ ይገኛል። ጉባዔው ለሶስቱ ፍ/ቤቶች ዳኞችን መመልመል እንደሚፈልግ ተደራሽ በሆኑ የህትመትና የኤሌክትሮኒክ ሚዲያዎች፣ በፍ/ቤቱ ማህበራዊ ሚዲያ እንዲሁም በክልልና በፌዴራል ፍ/ቤቶች በመለጠፍ ለሁሉም ጥሪ አድርጓል። በዚህ መንገድ በወጣው የቅድመ ዕጩ ዳኝነት ምዝገባ ማስታወቂያ መሰረት ለሶስቱም ፍ/ቤቶች 3330 አመልካቾች ተመዝግበዋል። ይህ ቁጥር ጉባኤው ከዚህ በፊት በስድስት ዓመታት ካካሄዳቸው ሶስት የፌዴራል ዳኞች የምልመላ ሂደቶች በተመዝጋቢ ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ልብ ማለት ይገባል። ጉባኤው በአዋጁና በመመሪያው በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት ከአመልካቾቹ መካከል የተሻለ ብቃትና የስራ ልምድ ያላቸውን በጥንቃቄ በመለየትና በማጣራት ለፅሁፍ ፈተና ያለፉ አመልካቾች ስም ዝርዝር በፍ/ቤቱ ማህበራዊ ሚዲያ ጭምር ይፋ ሆኗል። ይህንን ተከትሎም ሚያዝያ 13 ቀን 2010 በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ የፅሁፍ ፈተናው እንዲሰጥ አድርጓል።

ለፅሁፍ ፈተና ያለፉትን በፍ/ቤቱ ድረ-ገፅ ይፋ ከተደረገ በኋላ ለሶስቱም የፌዴራል ፍ/ቤቶች ለዕጩ ዳኝነት ካመለከቱት መካከል ጥቂቶቹ የተዘረጋውን የአቤቱታ አቀራረብ ስርዓት በመጠቀም ቅሬታቸውን ለጉባኤው ጽ/ቤት በፅሁፍ አቅርበዋል። የጉባዔው ጽ/ቤት አቤቱታቸውን መርምሮ ምላሽ ሰጥቷል። በጽ/ቤቱ ምላሽ ያልረኩ ወገኖች ቅሬታቸውን በይግባኝ መልክ ለጉባዔው ሰብሳቢ አቅርበው ጉዳያቸውና ማስረጃቸው በመመርመር ውሣኔ ተሰጥቷቸዋል።

ጉባኤው የዘረጋው ይህ አይነቱ ግልጽነት የተላበሰ ስርዓት በመታገዝ በጽሁፍና በአካል ጭምር ግልጽና አሳማኝ ምላሽ ከተሰጣቸው ከነዚህ አካላት መካከል ጥቂት ለፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የቀረቡት የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ዳኞች አመልካቾች (በ2006 ዳኛ የሆኑ ናቸው) በሰንደቅ ጋዜጣ ቀርበው ሕግን ባልተከተለና አድልኦ በተሞላበት ሁኔታ ከሂደቱ ተገልለናል በማለት ቅሬታ ያቀረቡት። እነዚህ አቤቱታ አለን የሚሉት ዳኞች ጉባዔው በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ያቀረቡትን የዳኝነት የሥራ ልምድ ከሌሎች ተወዳዳሪዎቻቸው ያነሰ በመሆኑ ማጣሪያውን ማለፍ እንዳልቻሉ ያቀረቡትን ማስረጃ በማገናዘብ ምላሽ የተሰጣቸው መሆናቸውን አንባቢው ሊገነዘብልን ይገባል።

በጋዜጣው ላይ ቅሬታቸውን ያቀረቡት እነዚህ ወገኖች ለአቤቱታቸው መነሻ ሆነን ያሉትን የህግና የአሰራር ጥሰት እያነሳን እውነታውን ወደ መመልከት እንግባ። እንደ አቤቱታ አቅራቢዎቹ አገላለፅ ጉባዔው ባደረገልን የማስታወቂያ ጥሪ መሰረት ከተመዘገብን በኋላ ወደ ቀጣዩ የፅሑፍ ፈተና የሚቀርቡትን ለመለየት ያካሄደው የማጣራት ሥራ በአዋጅ 684/2002 አንቀጽ 11 ስለ ፌደራል ዳኞች አሿሿም የተዘረጋው ስርዓት የጣሰና ሕግን ያልተከተለ ነው ይላል። ቀጠል በማድረግም “ዕውቅና ካለው ከፍተኛ ትምህርት ተቋም በሕግ ትምህርት ቢያንስ የመጀመሪያ ዲግሪ በከፍተኛ ውጤት የተመረቀ/ች/ የሚጠይቅ ሆኖ እያለ ከምዝገባ በኋላ ጉባዔው ይህንን የሚፃረር አዲስ መስፈርት አውጥቷል” በማለት ጉባዔውን ወንጅለውታል። እዚህ ላይ አንባቢ እንዲገነዘብልን የምንፈልገው በጋዜጣው የተገለፀው መስፈርት ዝቅተኛ ተፈላጊ ችሎታ እንጂ ከዚህ በላይ ብቃትና ልምድ ያላቸውን እንዳይመረጡ የሚከለክል ህጋዊ መሰረት የለም ብቻ ሳይሆን የተሻለ የዳኝነት ልምድ ያላቸው ከማንም ተወዳዳሪ በላይ የተሻለ የመመረጥ እድል አላቸው።

ዳኛ ሆኖ ለመሾም ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንዳሉት በአዋጁ አንቀጽ 11/1/ከሀ እስከ ረ የተዘረዘሩ ዝቅተኛ ተፈላጊ መስፈርቶች ማሟላት እንዳለበት ይዘረዝራል። ይህ አንቀጽ አንድ ለቅድመ ዕጩነት የሚቀርብ አመልካች ወይም ተወዳዳሪ ዝቅተኛ የተፈላጊ ችሎታ መስፈርት እንጂ ወደ ማጣሪያ ለማለፍ ከተጠቀሰው በላይ የካበተ የስራ ልምድ ያላቸው ተወዳዳሪዎች እንዳይመረጡ የሚከለክል ሕግም ሆነ በሕግ የተደገፈ ምክንያት የለም። በአዋጁ መንፈስ መሰረት ማድረጉ የማይቻለው የተጠቀሱት አስገዳጅ ዝቅተኛ መስፈርቶችን የማያሟላ አመልካች ለጽሁፍ ፈተና ማቅረብ የማይቻል መሆኑ ነው። በማጣረያ ሂደት አስገዳጅ የሆነውን ዝቅተኛ ተፈላጊ መስፈርቱን በሚያሟሉ መካከል በማበላለጥ መምረጥ የተለመደ አሰራርና የህግ ድጋፍ ያለው ነው። የሚፈለገው የዕጩ ዳኞ ብዛት ከቀረቡት ተወዳዳሪዎች ብዛት እያመዛዘነ መመሪያውን ተግባራዊ የማድረግ ኃላፊነት ለጉባኤው የተሰጠ ስልጣን መሆኑ መገንዘብ ያስፈልጋል።

አዋጁን ተንተርሶ በ2003 የወጣው የፌዴራል ፍ/ቤቶች ዕጩ ዳኞች ምልመላ ስርዓት አፈፃፀም መመሪያ በአንቀጽ 15/2/ እንዲህ በማለት ይገልፀዋል። “እንደሚፈለገው የተወዳዳሪዎች ብዛት እየታየም የተሻለ የሥራ ልምድ ያላቸው ተወዳዳሪዎች ቅድሚያ እንዲያገኙ ሊደረግ ይቻላል” ይላል። ጉባዔው ያደረገውም ይህንኑ ነው። ዘንድሮ ከፍተኛ ብዛት ያለው አመልካች ስለቀረበ ወደ ፅሁፍ ፈተና የሚቀርቡትን ለማጣራት ለስራ ልምድ በተለይ ለዳኝነት የስራ ልምድ ትኩረት እንዲሰጥ ጉባኤው ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት የተፈፀመ ህጋዊ አሰራር ነው። ከዚህ ውጭ ጉባዔው ያሻሻለው አዲስ መመሪያ የለም። ሥራ ላይ ያለውን መመሪያ የአዋጁን መንፈስና ዓላማ በተከተለ መንገድ ለማስፈፀም የተሰጠውን ሥልጣን መሠረት ተደርጎ የተከናወነ ተግባር ነው። ጉባኤው ቅሬታ አቅራቢዎቹ “መስፈርቱን ባናሟላም ቅድሚያ ልትሰጡን ይገባል” በማለት ሕግን ያልተከተለና ሚዛናዊነት የጎደለው ጥያቄያቸውን ባለማስተናገዱ የጉባዔውን ሥርዓት የተከተለ አሰራር ማጥላላት ተገቢም አይደለም፤ በህግም ያስጠይቃል።

ጋዜጣው ቅሬታ አቅራቢዎቹን ጠቅሶ እንደዘገበው ጉባኤው ያደረገው የማጣራት ሂደት ለዳኝነት የሥራ ልምድ ልዩ ትኩረት መስጠቱ ተገቢ አይደለም የሚል አስገራሚ ትችትም አስደምጦናል። ዳኝነትን ለመሰለ በሰው ህይወት፣ ነፃነትና ንብረት ላይ አስገዳጅ ውሳኔ የሚወስን ሙያዊ መንግሥታዊና ህዝባዊ ሹመትን ያጣመረ ከባድ ኃላፊነት የተሸከመ ስራ ይቅርና ለማንኛውም የአገልግሎት ሰጪ ተቋም የወጣ የተፈላጊ የሥራ መደብ ማስታወቂያ ለሚፈለገው የሥራ ኃላፊነት የተሻለ ቅርበት ያለው ባለሙያ ቅድሚያ እንደሚሰጠው ቅሬታ አቅራቢዎቹ የህግ ባለሙያዎች ስለሆኑ ለቀባሪ ማርዳት ሊሆን ይችላል። በዳኝነት ለሚሰራ ዕጩ ዳኛን ለመመልመል በዳኝነት የተሻለ አገልግሎት ላለው ተወዳዳሪ ቅድሚያ መስጠት ተገቢ ብቻ ሳይሆን ቅቡልነት ያለው ሕጋዊ አሰራር ነው። ሌክቸረር ለመቅጠር የፈለገ አንድ የዩኒቨርስቲ ተቋም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የማስተማር ልምድ ያውን መምህር ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚቀጥር ሁሉ ዐቃቤ ሕግ ለመሾም የፈለገ የፍትህ ተቋም የዐቃቤ ሕግነት የሥራ ልምድ ያለውን ቅድሚያ ሰጥቶ ማጣሪያውን እንዲያልፍ እንደሚመርጠው ሁሉ ዳኛ ለመመልመል በዳኝነት በርከት ላሉ ዓመታት ለሰሩት ቅድሚያ መስጠቱ ሃጢያቱ የቱ ላይ ነው? ለነገሩ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ሌክቸረሮችን፣ ዓቃቢያን ህግን ሌሎች የህግ ባለሙያዎች ከምልመላው ተገልለዋል የሚል ስሞታ ያቀረቡት ለተነሱበት ሕገወጥ ዓላማ ከጎናቸው ለማሰለፍ ታስቦ እንጂ ስለሌሎቹ ተወዳዳሪዎች አስጨንቋቸው እንዳልሆነ ለማንም ግልፅ ይመስለናል። ጉባዔው ቀደም ሲል ያወጣው የፌዴራል ፍ/ቤቶች ዕጩ ዳኞች የምልመላ ሥርዓት አፈፃፀም መመሪያ በሕግ ዕውቀታቸው ብቻ ሳይሆን በዳኝነት ልምዳቸው የተሻለ አገልግሎት ያላቸውን ቅድሚያ እንዲሰጥ ከማንም በላይ እነሱ ጠንቅቀው ያውቁታል።

በነገራችን ላይ የዳኝነት አካሉ ባለድርሻ አካላት ከሆኑት ጠበቆች፣ ዓቃቢያነ ህግ፣ ነገረፈጆችና ሌሎች ተገልጋዮች ከሚያቀርቧቸው ቅሬታዎች መካከል ዋነኛው በየደረጃው ለሚገኙ ፍ/ቤቶች የምትሾሟቸው ዳኞች መካከል ቀላል የማይባል ቁጥር በቂ የዳኝነት የሥራ ልምድ ስለሌላቸው በችሎት አመራርና በፍርድ ጥራት ላይ ሰፊ ክፍተት እየተፈጠረ መሆኑን ሲገልፁ ይደመጣሉ። ዛሬ ዛሬ ዳኛ ለመሆን የሚያበቁ መስፈርቶች ጠበቅ ያሉና ብቃትን፣ የስራልምድን፣ ሥነ-ምግባርንና ህዝባዊ አመለካከትን መነሻ ያደረጉ መሆን አለባቸው የሚለው ሃሳብ ሚዛን እየደፋ የመጣውም ዳኞች ከተሸከሙት ወገብ የሚያጎብጥ ኃላፊነትና ከባድ ሸክም ጋር ለማጣጣም እንደሆነ ግልፅ እየሆነ መጥቷል። ስለዚህ በተለይ ከባድና ውስብስብ የፍትሀብሔርና የወንጀል ጉዳዮች ለሚመለከቱ የከፍተኛ ፍ/ቤት ዳኞች የካበተ የዳኝነት ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎች መሾም ህጋዊም ተገቢም መሆኑን ለመረዳት ምርምር የሚያስፈልገው ጉዳይም አይደለም።

ቅሬታ አቅራቢዎቹ ብለውታል እንደተባለው ጉባዔው በምን መልኩ ከሕግ አግባብ ውጭ እንደተጓዘና አድልዎ እንደፈፀመ ፍንጭ የሚሰጥ አንዳችም በሕግና በማስረጃ የተደገፈ የቀረበ ነገር የለም። ሂደቱም የምልመላው ግልፅነትና አሳታፊነት ያጎላው እንደሆነ እንጂ ለትችት የሚዳረገው ነገር አለ ብለን አናምንም።

አቤቱታ አቅራቢዎች አንባቢውን ለማደናገር እና ጉባኤው እያካሄደ ያለውን የዕጩ ዳኞች የምልመላ ሂደት ለማደናቀፍ ቆርጠው መነሳታቸውን የሚያመላክተው ሌላው ጉዳይ ቅሬታ አቅርበው የጉባዔው ጽ/ቤትና የጉባኤው ሰብሳቢ ለቅሬታቸው ምላሽ እንደሰጧቸው እንኳ ለመግለፅ ድፍረት አላገኙም። አንባቢንና የመንግሥት አካላትን ለማደናገር እነሱ ከሕግ ውጪ ተጠቃሚ ባለመሆናቸው ብቻ በህግ ማዕቀፍ እየተመራ ያለውን የምልመላ ሂደት ማጠልሸት ተገቢ አይሆንም። እኔ ካልተመለመልኩ ሁሉም ነገር ገደል ይግባ የሚል መፈክር ያነገቡ እነዚህ ወገኖች እነሱ የማይካተቱ ከሆነ እየተካሄደ ያለው የዳኞች የምልመላ ሂደቱ እንዲሰረዝ ድፍረት የታከለበት ጥያቄ ማቅረባቸውም ተሰምቷል። እንዴት ነው ነገሩ? በሕግና በሥርዓት በሚመራ አገር እንዲህ አይነት አጉራ ዘለል ጥያቄ ማቅረብ ያውም የህግ እውቀት ካለው ሰው ተገቢነት አለውን? ዓላማው ግልፅ ነው። ሂደቱን ሆን ብሎ ለመረበሽና ለማደናቀፍ የታሰበ ከመሆኑም በተጨማሪ በሂደት ላይ ያለን የምልመላ ስርዓት ተዓሚኒነት እንዲያጣ፣ ተወዳዳሪዎች ተስፋ እንዲቆርጡ በውጤቱ የምልመላ ስርዓቱ ዋጋ ለማሳጣት የሚደረግ ሴራ መሆኑ ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል።

“እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” መፈክር ያነገቡ እነዚህ ቅሬታ አቅራቢዎች መስፈርቱን ባለማሟላታቸው ምክንያት ከማጣሪያው እንደቀሩ እያወቁና ጉባዔው በዘረጋው የቅሬታ አቀራረብ ሥርዓት መሰረት ቅሬታቸውን አቅርበው በቂ ምላሽ ተሰጥቷቸው እያለ ጉባዔው የጀመረውን ግልጽነት የተላበሰ አሳታፊና ብቃት ላይ የተመሰረተ የምልመላ ሂደት እንዲሰረዝ በድፍረት ጠይቀዋል። ቅሬታ ማቅረብ መብት ቢሆንም ማንኛውም የሚቀርብ ጥያቄ ሕግንና አሰራርን የተከተለና እውነት ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት ይቅርና የህግን ሀሁ የሰነቁ ሰዎች ሌላው ዜጋም ይዘነጋዋል ተብሎ አይጠበቅም። እውነታው ይህ ከሆነ ህግን ያልተከተለ አሰራር ያማረው ታዲያ ማን ነው? ጉባኤው ወይስ ቅሬታ አቅራቢዎቹ?

የሚገርመው ነገር ሰንደቅ ጋዜጣ የአንድ ወገን ያውም በሂደት ላይ ያለ ያላላቀ ጉዳይን ለህዝብ ያሰራጨው በአቤቱታ አቅራቢዎቹ ክስ የቀረበበት የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤን በጉዳዩ ላይ ሳያናግርና ሳይጠይቅ መሆኑ ነው። ያልተረጋገጠና ለአንድ ወገን የወገን ወሬ ይዞ መውጣት የፕሬስ ህግና የጋዜጠኝነት ስነምግባር እንደማይፈቅድ ይቅርና በፕሬስ ስራ የተሰማራ ባለሙያ ተራ ዜጋም ያውቀዋል። ዓላማው ህዝብ እውነታውን እንዲያውቅ ታስቦ ከሆነ ዘገባውን ይዞ የወጣው ሰንደቅ ጋዜጣ በጉዳዩ ላይ የጉባኤውን ጽ/ቤት ማነጋገርና ምላሹን ለማድመጥ ያልተፈለገው ለምን ይሆን? እየተካሄደ ያለን የዕጩ ዳኞች የምልመላ ሂደትን ለማደናቀፍ የተሰጠን የአንድ ወገን አስተያየት ይዞ መውጣት ከሁሉም በፊት የጋዜጠኝነት ሙያ የሚጠይቀውን የሚዛናዊነት መርህ እንደሚጥስ ለጋዜጣው አዘጋጅ ይጠፋዋል የሚል እምነት የለንም። እንዲህ አይነት የተቀነባበረ ወሬ የሚያስከትለውን ውጤት ተገንዝቦ ጉዳዩን ሚዛን ለመጠበቅ አዘጋጁ ጥረትና ትጋት ማድረግ እንደነበረበት ማስታወስም አያስፈልገውም። ሰንደቅ ጋዜጣ በዚህ ረገድ የፈፀመው የህግና የሙያ ጥሰት አንባቢዎቹን ይቅርታ እንዲጠይቅ በዚሁ አጋጣሚ ለመጠቆም እንወዳለን። ስለሆነም ግልጽነት በተላበሰ፣ አሳታፊና ብቃትን ማዕከል ባደረገ መልኩ እየተከናወነ ያለውን የፌዴራል ፍ/ቤቶች የዕጩ ዳኞች ምልመላ ለማደናቀፍ፣ ሂደቱን ከእውነታው በራቀና በተወናበደ መንገድ ተአማኒነት ለማሳጣትና ተወዳዳሪዎችን ተስፋ ለማስቆረጥ የተጀመረው ዘመቻ መቆም እንዳለበት ለማሳሰብ እንወዳለን።

 

                 ሰለሞን በላይ

            የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ጽ/ቤት ኃላፊ

                  (ፊርማና ማህተም አለው)

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
120 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 484 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us