ትርጉመ-አልባ ድርጊት!!! ከዎላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ዎሕዴግ) የተሰጠ መግለጫ

Wednesday, 27 June 2018 13:16

 

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መስተዳደር ሐዋሳ በምትባል ከተማ ባለፈው ሳምንት በተቀሰቀሰ እረብሻ የብዙ ወላይታዎችና የሌሎችም ዜጎች ሕይወት ጠፍቷል። የአካል ጉዳት ደርሷል፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዎላይታዎች ከኑሯቸው እንዲፈናቀሉ ተደርጓል። ሀብት ንብረትም ወድሟል፣ ይህ ሊሆን የቻለው፡-

ሲዳማዎች ፍቼ ጨምበላላ የተባለ በዓል ለማክበር እንቅስቃሴ ሲጀምሩ የዎላይታ ሕዝብ ከሐዋሳ ይውጣ የሚል ሀሳብ በማንሳታቸው እንደሆነ ይገለፃል።

ሐዋሳ ከተማ የተቆረቆረችበት ስፍራ ቀደም ሲል የማን ይዞታ እንደነበረ ወደፊት ታሪክ ሊገልፅ ይችላል።

ከዛሬ 58 ዓመት በፊት ጫካውን መንጥረው ሐዋሳ የምትባል ከተማን ቆርቁረውና ገንብተው አሁን የደረሰችበት ደረጃ ካደረሱ ህዝቦች ከፍተኛውን ድርሻ የያዘ የወላይታ ሕዝብ ከሐዋሳ ከተማ ይውጣ እየተባለ በሲዳማ ህዝብ መጠየቁ እጅግ ያሳዝናል፣ ያስገርማልም። የወላይታ ሕዝብ ወንድም የሆነ የሲዳማ ሕዝብ ከሐዋሳ ከተማ ይውጣ የሚል ጥያቄ አቅርቦ አያውቅም፣ አያስብምም።

የሲዳማ ሕዝብ በአሁኑ ጊዜ እጅግ አንገብጋቢ አድርጎ የሚያቀርበውን በክልል የመደራጀት ጥያቄን ማስተናገድ የሚችለው የወላይታ ሕዝብ አይደለም። ወላይታም ቢቻል ቀደም ሲል የክልል 9 አባል ከነበሩ አጎራባች ህዝቦች ጋር ብሎም የአሁኑ ደቡብ ክልል በምዕራባዊ ደቡብ አቅጣጫ ከሚገኙ እስከ ቱርኪና ድንበር ድረስ ካሉት ሕዝቦች ጋር፣ የነእርሱ ፈቃደኝነት የማይገኝ ከሆነም ለብቻው በክልል ደረጃ የመደራጀት ከፍተኛ ፍላጎት ያለው ሕዝብ ነው። እነዚህ ህዝቦች ኩታገጠም ነዋሪዎች፣ በባህል በታሪክ እና በሥነ ልቦናዊ አመለካከት እንዲሁም በሌሎችም መስፈርቶች የተቀራረቡ ብቻ ሳይሆኑ ፍትሐዊ የልማት ሥርጭትም የተነፈጉ ናቸው።

ይህ ፍላጎቱ ቀደም ሲልም ለሕዝብ ግልፅ ተደርጓል። የወላይታ በክልል ደረጃ መደራጀት ለሕዝቡ የነፍስ አድን ጥያቄ እንጂ የቅንጦት እንዳይደለ የወላይታ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ዎሕዴግ) ሊቀመንበር ግንቦት 27 ቀን 2006 ዓም በታተመ ቁጥር 456 በሆነ ሰንደቅ ጋዜጣ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የወላይታ ሕዝብ የሚተዳደርበት የግብርና ኢኮኖሚ ካለበት የመሬት ጥበትና በፍጥነት እየጨረ ከሚሄድ የህዝብ ብዛት ጋር ተጣጥሞ ሕዝቡን መሸከም አይችልም። መዋቅሩ በቶሎ ወደ ኢንዱስትሪ ኢኮኖሚ መዋቅር መቀየር መቻል አለበት። ይህ ሀሳብ በተለያየ አጋጣሚ በተገኘ መድረክና በመገናኛ ብዙሃን ለተደጋገመ ጊዜ በስፋት ቢገለጽም ትኩረት ሊሰጥ የቻለ አካል አልነበረም። ወላይታ የራሷን እድገት ለማፋጠን የራሷ እቅድ አውጥታ እስትራቴጂንም ነድፋ ከማዕከላዊ መንግስት ጋር በቀጥታ በመገናኘት በጀት እና ሌላም ድጋፍ ማግኘት የምትችለው በክልል ደረጃ ስትደራጅ ብቻ ነው። አለዚያ ሕዝቡ እየተጎዳ ነው። በወላይታ ለአንድ ገበሬ ሊደርስ የሚችል የእርሻ መሬት ከ0.13 ሄክታር በታች መሆኑን ከ6 እና 7 ዓመታት በፊት የተገኘ የስታቲስቲክስ መረጃ ያስረዳል። በትንሹ 3 ልጆች ያሉት አባወራ ገበሬ ቤተሰቡን መቀለብ፣ ማሳከምና ልጆቹንም ማስተማር አልቻለም። ትውልዱ በትምህርት በልፅጎ በኢኮኖሚ ዳብረው ከነገ አገር ተረካቢ ዜጎች ጋር የመቀላቀል እድሉ አስተማማኝ ሊሆን አልቻለም። ለወላይታ በክልል ደረጃ መደራጀት ነፍስ አድን ጥያቄ የሚያደርጉት እነዚህ እና ሌሎችም ገና በስፋት ሊገለፁ የሚችሉ ነጥቦች ናቸው።

ታዲያ ወላይታ ይህንን እና የመሳሰሉ ጥያቄዎችን ጉዳዩ ለሚመለከተው አካል ሲያቀርብ የሌላ ዜጋ ደም በማፍሰስና በመሳሰሉ ጣኦታዊ እምነቶች እየተደገፈ አይደለም። አሳማኝ በሆነ ትንተና አስደግፎ እንጂ።

ሰኔ 11 ቀን 2010 ዓ.ም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶ/ር አብይ አህመድ በሐዋሳ ከተማ ተገኝተው ከማህበረሰቡ ጋር ሆነው የተከሰተውን ችግር በማስመልከት ውይይት ሲያደርጉ አንድ የሲዳማ ሽማግሌ ያቀረቡት እጅግ በጣም አስገራሚ ሀሳብ የሲዳማ ህዝብ ያንን ድርጊት በወላይታ ህዝብ ላይ የፈፀመው በስህተት ሳይሆን በእውቅ ያደረገ ስለሚያስመስል አሁንም ስጋት እንዲያድር የሚያደርግ ሆኖ ተገኝቷል። ሽማግሌው አስተያየታቸውን በአስተርጓሚያቸው በኩል ሲገልፁ “ይህ ግጭት ምናምን የምትሉት በተራ ሽምግልና የሚያልቅ ጉዳይ ስለሆነ እርሱን ተውትና በክልል ስለመደራጀት ብቻ ተወያዩ” ብለው ተናግረዋል። ያ ሁሉ ሕይወት መጥፋት፣ የህዝብ መፈናቀልና ንብረት ማውደም ለእርሳቸው ምንም አልመሰላቸውም። ይህ አባባል የብቻቸው ካልሆነ አሁንም ጥሩ አዝማሚያ አያመለክትም። የዚህ አይነት አረመኔያዊ አስተሳሰብ ሌላውን በእልህ እና በንዴት ውስጥ እየካተተ ለሚያቋርጥ አመፅ ለመጋበዝ የሚሞክር ሀሳብ ስለሆነ መገታት ብሎም መጥፋት አለበት።

በወላይታ እና በሲዳማ ሕዝበ መካከል ያለ የወንድማማችነት ግንኙነት አሁንም ይበልጥ እየተጠናከረ እንጂ እየላላ መሄድ የለበትም። ይህ አባባልም በአንድ እጅ እንደማጨብጨብ ሊሆንብን አይገባም።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ለጉዳዩ ልዩ ትኩረትና ክብደት ሰጥተው በሐዋሳም በሶዶም ተገኝተው እረብሻው እንዲወገድና ሕዝቡም እንዲረጋጋ የሚያደርግ መመሪያ ስለሰጡልን ምስጋናችን እጅግ የላቀ ነው። ህዝቡም በብርቱ ስሜት ከጎናቸው እንደሚሰለፍ እምነታችን የፀና ነው።

ለረዥም ዘመናት ተፈቃቅረውና ተሳስበው በኖሩ ህዝቦች መካከል ምንም ሚዛን በማይደፋ ምክንያት በደመነፍስ በሚፈፀም እንቅስቃሴ የሰው ልጅ ክቡር ህይወት እንዲጠፋ እና ብሔራዊ ሀብትም እንዲወድም ማድረግ በመላው ሕዝብ መወገዝ ያለበት ተግባር ነው እንላለን።

ስለሆነም፡-

1.  የወገኖቻችን ሕይወት ያጠፉ አካላዊ ጉዳትም እንዲደርስባቸው ያደረጉ ግለሰቦች በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ፣

2.  ከኑሯቸው የተፈናቀሉም ወደ መደበኛ ኑሯቸው ተመልሶ እንዲቋቋም እንዲደረግልን እና

3.  ሀብት ንብረት ለወደመባቸው ተገቢ ካሳ እንዲከፈላቸው እንዲደረግልን እንጠይቃለን።

የወላይታ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ (ዎሕደግ)

ሰኔ 13 ቀን 2010 ዓ.ም

አዲስ አበባ

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
89 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1023 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us