ከፋፋይ ፕሮፓጋንዳዎችን “በመደመር” ቀና ሀሳብ የቀየሩ መሪ ሀሳባቸው በትክክል ተግባራዊ እንዲሆን ሁላችንም የድርሻችንን እንወጣ

Wednesday, 11 July 2018 13:31

 


ከጥላሁን እንደሻው (የግል አስተያየት)

የኢህአዴግ አገዛዝ ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ወዲህ ብቻ ሳይሆን የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች እያንዳንዳቸው ከተቋቋሙበት ዕለት ጀምሮ በተደጋጋሚ ሲያስደምጡን የቆዩት እጅግ ተደጋጋሚና አሰልቺ ፕሮፓጋንዳ እስከ መገንጠል፣ እስከ መገንጠል፣ እስከ መገንጠል፣ እስከ መገንጠል የሚል ነበር። በኢህአዴጎች ዘንድ የእስከ መገንጠል
ፕሮፓጋንዳን
ማስተጋባትም ለብዙ ዓመታት ዋነኛው የዴሞክራሲያዊነትና የተራማጅነት መገለጫና መመዘኛ ሆኖ ቆይቶ ነበር። ይሁንና ለሁሉም ጊዜ አለውና አሁን ግን ያ ሚዛናዊ ያልሆነው ፕሮፓጋንዳ የተቀየረ ይመስላል።

ሁሉም ኢህአዴጎች ተለውጠው እንደ ጠቅላይ ሚ/ር አቢይ የመደመርን ዓላማ በማራማድ ላይ ናቸው ማለት ባይቻልም በአሁኑ ወቅት በሕዝባዊ ትግልና በእግዚአብሔር ፈቃድ አማካይነት ከራሱ ከኢህአዴግ በመጡ መሪ ከፋፋዩና ሚዛናዊነት የጎደለው ፕሮፓጋንዳ ተቀይሮ በመደመር ሀሳብና ዓላማ ተተክቶ ለመስማትና ይህንኑ የሚያጠናክሩ ተጨባጭ ተግባራዊ እርምጃዎች ሲወሰዱም በአይናችን ለማየት በቅተናል።

በበኩሌ እንዲህ ያለ ቀና ሀሳብ ከፋፋይ ፕሮፓጋንዳን ከመሠረቱ ስንቃወምና የእኩልነትና የአድነትን ሀሳብና ዓላማ ሲናራምድ ከነበርን ተቃዋሚዎች እንጂ ከኢህአዴግ መሪዎች በኩል ይገኛል፣ የሚል ግምት ያልነበረኝ ቢሆንም አንድ የኢህአዴግ አመራር አባል የሆነ ሰው በኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል ተገዶም ይሁን አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት በእግዚአብሔር ታዝዞ በእርግጥም በአሁኑ ወቅት ይህንን ቀና ሀሳብ በቆራጥነት እያራመደውና በሥራም ላይ እያዋለው ይገኛል።

በአሁኑ ወቅት በዶ/ር አቢይ አሕመድ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚ/ር እየተራመደ ያለው ይህ የመደመር ዓላማ በትዕቢትና በጀብደኝነት ተነሳስቶ የመስፋፋት ዓላማ ሳይሆን የሕዝቦች ማንነትና እኩልነት በተከበረበት ሁኔታ፣ በመከባበርና በፍቅር ላይ የተመሰረተ አንድነት ለመገንባት የታሰበ መሆኑ ደግሞ በሀሳቡ እንድስማማና የራሴንም የድጋፍ አስተያየት እንዲሰጥበት አነሳስቶኛል። ለኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦችና ሀይማኖቶች ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ቀንድ ሕዝቦችና ለመላው የአፍሪካ ሕዝቦች መተጋገዝና መረዳዳት ጭምር የታሰበ ሰፊና ጥልቀት ያለው ሀሳብ መሆኑም
በተጨማሪ ያስደሰተኝ ጉዳይ ነው። ስለዚህ ይህ ቀና ሀሳብ እንዲሳካና ተግባራዊ እንዲሆን የሕዝቦችን በእኩልነትና በመከባበር ላይ የተመሠረተ አንድነት የምንሻ ኢትዮጵያውያን የድሻችንን ለመወጣት መተባበር ይኖርብናል።

ሀሳቡ ዘላቂነት ባለው መልኩ በትክክል ተግባራዊ እንዲሆን ደግሞ ሀሳቡን በንግግር ከመግለጽ ባሻገር የሀገራችን መንግሥት ቋሚ መመሪያ ሆኖ ሥራ ላይ እንዲውል የሚያደርጉ ውይይቶችና ድርድሮች በሚመለከታቸው አካላት ሁሉ
ሊደረጉና በብሔራዊ መግባባት ላይ ሊደረስበት ይገባል። በዚሁም መሠረት የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የህብረተሰብ ክፍሎች በሀገራችን አጨቃጫቂ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጥልቀት በመወያየትና ከስምምነት በመድረስ ቀና ሀሳቡ በሕዝባችን ዴሞክራሲያዊ ውሳኔ የሕገ-መንግሥታችን፣ የሕጎቻችንና የአፈጻጸም መመሪያዎቻችን አካል እንዲሆን በማድረግ በእነዚሁ ሰነዶቻችን ላይ ተገቢውን ማሻሻያዎች ማድረግ ይኖርብናል። በሚሻሻሉ ሰነዶቻችን ላይ ተመሠርተንም ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በማካሄድ ሕዝባችንን በትክክል የሥልጣን ባለቤት ማድረግና የህዝባችን እኩልነትና አንድነት የተረጋገጠበት ትክክለኛውን የፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት እውን ማድረግ ይገባናል።

ይህንን ቀና ሀሳብ በሥራ ላይ እንዲውል ከማድረጋችን ጎን ለጎን ደግሞ በከፋፋይ አስተሳሰቦችና ሥራዎች ምክንያት በተለያዩ የሀገራችን አከባቢዎች በተከሰቱት ግጭቶች ብዙ ጉዳት የደረሰባቸውንና በገዛ ሀገራቸው ከቤት ንብረታቸውም የተፈናቀሉትን ወገኖቻችንን በአስተማማኝና ዘላቂነት ባለው ሁኔታ ወደ ቤታቸውና ኑሮአቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙ ማድረግ ይኖርብናል። ዳግም እንደዚህ አይነት አስከፊ ጉዳቶች በሀገራችን እንዳይከሰቱም አፍራሽና ከፋፋይ አስተሳሰቦችን በማራመድ ሕዝባችን እርሰበርስ እንዲጋጭ የሚያደርግ ተግባራትን የሚፈጽሙ ሰዎች በሕግ ተጠያቂ
እንዲሆኑ በማድረግ፣ የመደመር ቀና ሀሳቡ በሕዝባችን ሕሊና ውስጥ በትክክል እንዲሰርጽና በእኩልነትና በመከባበር ላይ የተመሠረተው የሕዝባችንና የሀገራችን ጠንካራ አንድነት እውን እንዲሆን እያንዳንዳችን የድርሻችንን ሊንወጣ ይገባናል እላለሁ። ሰላምና ፍቅር ለሁላችንም ይሁን።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርካት።¾     


  
  


ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
93 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 938 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us