በኢትዮጵያና በኤርትራ ሕዝቦች የታየው የፍቅርና አንድነት ትርኢት ያስተላለፈው መልዕክት ሊከበርና ተግባራዊ ሊሆን ይገባል

Wednesday, 18 July 2018 15:45

 

ከጥላሁን እንዳሻው (አዲስ አበባ)

 

ውድ ወገኖቼና ደንበኞቼ፣ ሰሞኑን የኤርትራና የኢትዮጵያ ሕዝቦች በአስመራ፣ በአዲስ አበባና በሐዋሳ ከተሞች ሐምሌ 1 እና 7 ቀን 2010 ስላሳዩትና እጅግ አስተማሪ ስለሆኑት ሕዝባዊ ትርኢቶች አጭር ጽሑፍ ማሰራጨቴ ይታወሳል። በዛሬው ዕለት ደግሞ ሐምሌ 8 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የሚሊኒየም አዳራሽ ስለታየው እጅግ ደማቅና ስሜት ቀስቃሽ ሕዝባዊ ትርኢትና በበኩሌ ይህንኑ ሕዝባዊ ትርኢት ስመለከት የተሰማኝን ላካፍላችሁ እፈልጋለሁ።


ይህንን ሕዝባዊ ትርኢት ለመከታተል የቻልኩት በስፍራው በአካል ተገኝቼ ስለነበረ ተመልካች ብቻ ሳልሆን በትንሹም ቢሆን ተሳታፊም በመሆንም ነበር። ማለቴ እንደ ሌሎቹ ትልቅ ሥራ ሠርቼ ሳይሆን ትርኢቱን ስመለከት ከውስጤ የተሰማኝን እጅግ ከፍተኛ የደስታ ስሜት ሞቅ ባለ ጭብጨባ በመግለጽ ማለቴ ነው። ወደ ቦታው የሄድኩት ለተሳታፊዎች ከምሽቱ በ11፡00 እንዲትገኙ ተብሎ በተላለፈው ጥሪ መሠረት ለእኔም ጥሪው ደርሶኝ ሲሆን ሀገሪቱዋ ካላት ባለሥልጣኖች ሳይሆን ካሏት ፖለቲከኞች ውስጥ እንደ አንዱ ስለተቆጠርኩ መሰለኝ የVIP የጥሪ ወረቀት ደርሶኝ ስለነበረ ብዙሃኑ ተሳታፊ ከሚገባበት በር በተለየ በር ማለትም ወደ ሰገነት በሚያወጣ በኩል ነበር።


ከእኔ ጋር ተመሳሳይ ጥሪ የተደረገለትና አብረን የሄድነው የትግል ጓዴ (አቶ ሉምባ ደምሴ) ከእኔ የተሻለ ቀልጣፋ ሰው ስለሆነ ከእኔ ፈጠን ብሎ በመግባት ፊት ለፊት ሆነን ትርኢቱን ለመመልከት የምንችልበትን ሥፍራ መርጦ ስለጠበቀኝ ሁሉንም ነገር ለማየት ምቹ የሆነ ቦታ ነበር ያጋጠመኝ።


የሚሊኒየም አዳራሽ ወደ አንድ ትልቅ ሐይቅ የሚፈስ ትልቅ ወንዝ የሚመስል ሕዝብ ሲፈስበት የማይሞላ አይነት ስለሆነ መጀመሪያ በመደነቅ የተመለከትኩት ትርኢት ወደ አዳራሹ የሚገባው የሕዝብ ብዛትና የአዳራሹ አለመሙላት ነበር። እንደዚሁም የአስተናጋጆቹ ትህትናና ቀናነትም ለወደፊቱም ይልመድባችሁ የሚያስብል ነበር። በአዳራሹ ውስጥ የገባውና ብዛቱን በእኔ አቅም ለመገመት ያዳገተኝ እጅግ ብዙ ሕዝብ በአንድ ቋንቋ እንዲናገር ማን እንደሚመራው በፍጹም ለማወቅ ባልቻልኩበትና ምናልባትም ተመሳሳይ ድምጽ እንዲያሰሙና አንድ አይነት ሀሳብ እንዲያራምዱ አድርጎ የሚመራቸው የፍቅር አምላክ ሳይሆን አይቀርም፣ ብዬ በገመትኩበት ሁኔታ በአሁኑ ወቅት በሁለት ሀገሮችና መንግሥታት እንዲሆኑ የተደረጉትን የኤርትራንና የኢትዮጵያን ሕዝቦች አንድነትና ወንድማማችነት የሚያበስሩ መልዕክቶችን እጅግ በደመቀና በተዋበ ሁኔታና ዜማ ሲያስተጋቡ የቆዩበት ሂደትም የእግዚአብሔር እንጂ የሰው ልጅ ሥራ አልመስል ብሎኝ ሲደነቅበት ቆይቻለሁ።


በማስከተልም አርትስቶቻችን በተለያዩ ቋንቋዎች ሲያሰሙ የነበሩት ጣዕመ ዜማዎች ከጉዳዩ ጋር ያላቸው ትሥሥርና ሲያስተላልፉ የነበሩት ትላልቅ ቁም ነገሮችን ያዘሉ መልዕክቶች እጅግ ስሜት ቀስቃሽና ማራኪ ስለነበሩ እኔም እጅግ ተመስጬ ሲከታተል ቆይቻለሁ። ሁሉም ሙዚቀኞቻችን ከታዳጊዎቹ ጀምሮ እስከ ትልልቆቹ ማለትም  እስከ እነ መሐሙድ አሕመድ ድረስ ያሉት ያቀረቧቸውና የኤርትራና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ብቻ ሳይሆኑ የዓለም ሕዝቦች በሙሉ ሊጠቀሙባቸው የሚገባቸው የፍቅር፣ የመተባበርና የወንድማማችነትና የእህትማማችነት ስሜት አንጸባራቂ ስለነበሩ እነዚህን ዜማዎች በተመስጦ ስሜት ከተጋበዝኩት የብርቱካን ጭማቂ ጋር  እያጣጣምኩና እያወራረድኩ ሲከታተል ቆየሁኝ።


በበኩሌ እነዚህ ሕዝባዊ ትርኢቶች በፖለቲካው ዓለም በቆየሁባቸው ረጅም ጊዜያት ውስጥ ገና ታዳጊ ወጣት ዕድሜ ላይ እያለሁ በየካቲት 25 ቀን 1967 ዓ.ም ከታወጀው የመሬት ለአራሹ አዋጅ ቀጥሎ እጅግ በጣም ያስደሰቱኝ ክስተቶች ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። ምክንያቱም የመሬት ለአራሹ አዋጅ በሥር ነቀል ለውጥ  በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩትን የኢትዮጵያን አርሶ አደሮች ከአስከፊው ፊውዳላዊ ብዝበዛ ሥርዓት ነፃ ያወጣ ክስተት የነበረ ሲሆን፣ እነዚህ በኤርትራና በኢትዮጵያ ምድር እየታዩ ያሉት ሕዝባዊ ትርኢቶች ደግሞ በፍጹም መለያየት የማይፈልጉ ሕዝቦች የተለያዩ አሰተዳደራዊ ጥፋቶችና ፖለቲካዊ አስተሳሰቦች ባስከተሉዋቸው ሁኔታዎች ምክንያቶች ተለያይተው መቆየታቸው እጅግ ያሳዘናቸውና ለወደ ፊቱም እንደዚህ አይነት መለያየት በፍጹም እንደማይፈልጉ በነፃነት፣ ከልባቸው አውጥተው በመግለጽ አንድ ሕዝብ ሆነው ለዘለዓለም ለመኖር ያላቸውን ቁርጠኛ ፍላጎት ያረጋገጡበት ታላቅ ታሪካዊ ክስተት በመሆኑ ነው። በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር ዕድሜ ሰጥቶኝ ይህንን ለማየትና ለመስማት በመብቃቴ ፈጣሪዬን ከልብ አመስግኛለሁ።


ደማቁ ስነ ሥርዓት በዚህ መልክ እየተካሄደ ሳለ የዕለቱ የክብር እንግዶች ማለትም  ክቡር ዶ/ር አቢይ አሕመድ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና ክቡር አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ የኤርትራ ፕሬዘዳንት ወደ አዳራሹ ገቡ። ከዚያን በኋላ ነበረ በእኔ እይታ በተለይም ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ባለሥልጣናትና ፖለቲከኞች በሙሉ ወደር የማይገኝለት መልዕክት የተላለፈበት፣ የክቡር ዶ/ር አሊቢራ ዜማ የተዜመው።  ዶ/ር አሊቢራ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ሀብትና ንብረት አንዱ በሆነው በኦሮምኛ ቋንቋ ያሰማው ዜማ  (አንተ ያልኩት አርቲስት ስለሆነና አርቲስት አንቱ ስለማይባል ነው) ስንኞች እንደሌሎቹ ሙዚቀኞች ዜማዎች ቁም ነገር ያዘሉ ብቻ ሳይሆኑ እያንዳንዱ የኢትዮጵያና የኤርትራ ባለሥልጣናትና ፖለቲከኞች እራሳቸውን እንዲጠይቁና ከሌላ ሰው ሳይሆን ከራሳቸው ሕሊና  ለጥያቄው ምላሽ እንዲሰጡና  ፍርድ እንዲቀበሉ ከፍተኛና ጥብቅ የሆነ መልዕክት ያዘለ ጥያቄ የተላለፈባቸው ነበሩ።


አርቲስቱ በዜማው ስንኞች ውስጥ ቀደም ሲል በዜማው ውስጥ ከነበሩት ሌላ ቃላት በማስገባት አቢይሞ ኢሳያስ፣ ካንሴራ ጃሊሴ?*2 ሀቲት ቴና ቶኮ፣ ኤኑቱ ኑ ጋርጋር ባሴ?*2 ትርጉም (የእራሴ ነው) አቢይ ነው ወይስ ኢሳያስ ነው፣ ሕጉን ያዛባው?*2 እናታችን አንድ ሆና፣ እኛን የለያየው?*2 የሚል ጥያቄ ያቀረበበት ነበር። እኔም የኦሮምኛ ቋንቋን ከሚጋሩና ከሚጠቀሙ ዜጎች አንዱ ስለሆንኩኝ መልዕክቱን ለመረዳት አስተርጓሚ አላስፈለገኝም። የአርቲስቱን ጥያቄ የተረዳሁት ግን ለሁለቱ ስማቸው ለተጠቀሱ ሰዎች ብቻ የቀረበ ጥያቄ አድርጌ አይደለም። እንዲያውም በሁለቱም ሀገሮች ላሉት ባለሥልጣናትና ፖለቲከኞች በሙሉ የቀረበ ጥያቄ አድርጌ ነው የወሰድኩት። 


በወቅቱ ስማቸው ከተጠቀሱት መሪዎች ከበስተሰሜን በኩል ካሉት መቀመጫዎች በአንዱ ላይ ቁጭ ብዬ ስለነበርኩኝ የተቀመጥኩት ቅርብ ቦታ ቢሆንም በመካከላችን በነበረው ትንሽ ከለላ ምክንያት ለጥያቄው ምን ምላሽ እንደሚሰጡ በቀጥታ አይናቸውን በማየት ለማወቅ ስላልተመቸኝ በፊት ለፊታችን ባለው ትልቅ ስክሪን ወደ እነርሱ ተመለከትኩኝ። ሁለቱም መሪዎች አርቲስቱ ዜማውን አንድ ጊዜ ብሎ በመድገም ላይ እያለ ገና ሳይጨርስ እጅ ለእጅ በመያያዝ የተያያዙ እጆቻቸውን ከፍ አድርገው ከአሁን በኋላ አንድ መሆናቸውን ለመግለጽ ይመስለኛል ወዲያውኑ በምልክት ምላሽ ሲሰጡ አየሁኝ።


ዶ/ር አቢይና አቶ ኢሳያስ በበኩላቸው ይህንን የመሰለ ምላሽ ለታሪካዊው የአርቲስቱ ጥያቄ መልስ የሰጡ ቢሆንም በእኔ እምነት ጥያቄው የቀረበው ለእነርሱ ብቻ ስለማይመስለኝ የእነርሱ ምላሽ ብቻ ለጥያቄው በቂ መልስ ሊሆን ይችላል ብዬ አላምንም። ምክንያቱም የኤርትራንና የኢትዮጵያን ሕዝቦች በመለያየትም ሆነ የተቀረውን የኢትዮጵያ ሕዝቦች ትናንት ብቻ ሳይሆን ዛሬም እየለያዩና እርሰበርስ እያጋጩ ለብዙ ችግርና ሥቃይ እየዳረጉ ያሉት በየደረጃው ያሉት ባለሥልጣናትና ፖለቲከኞች እጅግ በጣም ብዙ ስለሆኑ ሁሉም በየበኩላቸው የይምሰልና የለበጣ ሳይሆን የምርና ከልብ የመነጨ እንዲሁም በተጨባጭ በተግባር የሚገለጽ ምላሽ ለአርቲስቱ ጥያቄ ሊሰጡ ይገባል እላለሁ።


በዚሁም መሠረት የኢትዮጵያና የኤርትራ ባለሥልጣናትና ፖለቲከኞች አርቲስቱ ለሁለቱ መሪዎች እንዳቀረቡት አይነት ጥያቄ ለራሳቸው በማቅረብ የአንድ እናት ልጆች የሆኑትን የኤርትራንና የኢትዮጵያን ሕዝቦች በመለያየት ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የኢትዮጵያ አከባቢዎችም የአንድ እናት ልጆች የሆኑትን ብሔር ብሔረሰቦችን በመለያየት ሕዝባችን አምርሮ የሚጠላውን የመለያየት ተግባራት እንደማይፈጽሙ ሊያረጋግጡ ይገባል።


ስለዚህም ባለፉት 27 ዓመታትና በአሁኑ ወቅትም ጭምር ሶማሌንና ኦሮሞን፣ ጌዴኦንና ጉጂን፣ ቡርጂንና ጉጂን፣ ኮሬንና ጉጂን፣ ሲዳማንና ወላይታን፣ አማራንና ኦሮሞን፣ አማራንና ትግራዋይን፣ አማራንና በቤንሻጉል ጉሙዝ ክልል የሚኖሩ ብሔር ብሔረሰቦችን፣ ሶማሌንና አፋርን፣ ኦሮሞንና አፋርን፣ ሱርማንና ዲዚን ወዘተ በአጠቃላይ ባልጠቀስኳቸው በብዙ የሀገራችን አከባቢዎች  ጭምር ጎን ለጎን ያሉትን ጎረቤታም ብሔር ብሔረሰቦችን በክልሎች ድንበሮችና በተለያዩ ሰበባ አሰበቦች እያመካኙ ሲያጋጩ የኖሩትና በግለሰብ ደረጃም በተለያዩ ክልሎች ሲኖሩ የነበሩ ዜጎችን በብሔር ብሔረሰብ ማንነታቸው ምክንያት ብቻ ከገዛ ሀገራቸው ሲያሳድዱ የኖሩት ባለሥልጣናትና ፖለቲከኞች ለዶ/ር አሊቢራ ጥያቄ ቢያንስ ለራሳቸው ሕሊና ከአሁን በኋላ የአንድ እናት ልጆችን እንደማይለያዩና እንደማያጋጩ በማረጋገጥ አስቸኳይ ምላሽ ሊሰጡ ይገባቸዋል ብዬ አምናለሁ።


ምክንያቱም እውነተኛና ዘላቂነት ያለው ሰላም በኢትዮጵያና በኤርትራ ምድር  በሁሉም አካባቢዎች በትክክል ሊረጋገጥ የሚችለው ሁሉም ይህንን ሊያደርግ ሲነሳና በተግባር ሲያረጋግጥ ነው ብዬ ስለማምን ነው። ስለዚህ ሁላችንም የድርሻችንን ልንወጣ የምንችለው የአርቲስቱን ጥያቄ በትክክል በመመለስና የሕዝባችን እውነተኛ ፍላጎት በተግባርና በግልጽ በታየባቸው በእነዚህ ሕዝባዊ ትርኢቶች ለተላለፉት መልዕክቶች ተገቢውን ግምት በመስጠትና ትምህርትም በመቅሰም መሆን ስለሚገባ እኔም የአርትስቶቻችንን መልዕክቶች በመደገፍ የአንዲት እናት ልጆችን ከሚለያዩና ከሚያጋጩ ተግባራት እንቆጠብ የሚል የበኩሌን መልዕክት በዚህ አጋጣሚ ማስተላለፍ እፈልጋለሁ።


ዶ/ር አቢይና አቶ ኢሳያስ በሥነ ሥርዓቱ ባደረጓቸው ንግግሮችም ከአሁን በኋላ አንድነታችንን የሚያጠናክሩ ተግባራትን እንደሚሠሩና ከፋፋይና ፀረ- ልማት ለሆኑ አስተሳሰቦችና ኃይሎች ቦታና እድል እንደማይሰጡ ቃል ገብተዋል። በተለይ ዶ/ር አቢይ አጋጣሚውን ተጠቅመው “መደመር” የሚለው ሀሳባቸው ይዘት ምን ማለት እንደሆነ ቀላልና ለሁሉም ግልጽ ሊሆን በሚችል አነጋገር የሰጡት ማብራሪያ በአዳራሹ ለነበሩት ብቻ ሳይሆን ሁሉም ቦታ ሆነው ሥነ ሥርዓቱን ለተከታተሉ ሁሉ ጥሩ ግንዛቤ ሊያስጨብጥ የሚችል ነበርና ሁለቱም በዚህ ታሪካዊ ሕዝባዊ ትርኢት ላይ ተገኝተው የገቡትን ቃል ተግባራዊ በማድረግ ለመላው የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች ተግባራዊ ምላሽ መስጠት ይጠበቅባቸዋል እላለሁ።


ሰላም ለሁላችን ይሁን። ሁላችንም የአንዲት እናት ልጆችን ከሚለያዩ ተግባራት እንቆጠብ። የኤርትራና የኢትዮጵያ ሕዝቦች አንድነት ለዘልዓለም ትኑር።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
13 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 89 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us