You are here:መነሻ ገፅ»sendekmyideas»news admin - Sendek NewsPaper
news admin

news admin

 


ከጥላሁን እንደሻው (የግል አስተያየት)

የኢህአዴግ አገዛዝ ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ወዲህ ብቻ ሳይሆን የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች እያንዳንዳቸው ከተቋቋሙበት ዕለት ጀምሮ በተደጋጋሚ ሲያስደምጡን የቆዩት እጅግ ተደጋጋሚና አሰልቺ ፕሮፓጋንዳ እስከ መገንጠል፣ እስከ መገንጠል፣ እስከ መገንጠል፣ እስከ መገንጠል የሚል ነበር። በኢህአዴጎች ዘንድ የእስከ መገንጠል
ፕሮፓጋንዳን
ማስተጋባትም ለብዙ ዓመታት ዋነኛው የዴሞክራሲያዊነትና የተራማጅነት መገለጫና መመዘኛ ሆኖ ቆይቶ ነበር። ይሁንና ለሁሉም ጊዜ አለውና አሁን ግን ያ ሚዛናዊ ያልሆነው ፕሮፓጋንዳ የተቀየረ ይመስላል።

ሁሉም ኢህአዴጎች ተለውጠው እንደ ጠቅላይ ሚ/ር አቢይ የመደመርን ዓላማ በማራማድ ላይ ናቸው ማለት ባይቻልም በአሁኑ ወቅት በሕዝባዊ ትግልና በእግዚአብሔር ፈቃድ አማካይነት ከራሱ ከኢህአዴግ በመጡ መሪ ከፋፋዩና ሚዛናዊነት የጎደለው ፕሮፓጋንዳ ተቀይሮ በመደመር ሀሳብና ዓላማ ተተክቶ ለመስማትና ይህንኑ የሚያጠናክሩ ተጨባጭ ተግባራዊ እርምጃዎች ሲወሰዱም በአይናችን ለማየት በቅተናል።

በበኩሌ እንዲህ ያለ ቀና ሀሳብ ከፋፋይ ፕሮፓጋንዳን ከመሠረቱ ስንቃወምና የእኩልነትና የአድነትን ሀሳብና ዓላማ ሲናራምድ ከነበርን ተቃዋሚዎች እንጂ ከኢህአዴግ መሪዎች በኩል ይገኛል፣ የሚል ግምት ያልነበረኝ ቢሆንም አንድ የኢህአዴግ አመራር አባል የሆነ ሰው በኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል ተገዶም ይሁን አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት በእግዚአብሔር ታዝዞ በእርግጥም በአሁኑ ወቅት ይህንን ቀና ሀሳብ በቆራጥነት እያራመደውና በሥራም ላይ እያዋለው ይገኛል።

በአሁኑ ወቅት በዶ/ር አቢይ አሕመድ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚ/ር እየተራመደ ያለው ይህ የመደመር ዓላማ በትዕቢትና በጀብደኝነት ተነሳስቶ የመስፋፋት ዓላማ ሳይሆን የሕዝቦች ማንነትና እኩልነት በተከበረበት ሁኔታ፣ በመከባበርና በፍቅር ላይ የተመሰረተ አንድነት ለመገንባት የታሰበ መሆኑ ደግሞ በሀሳቡ እንድስማማና የራሴንም የድጋፍ አስተያየት እንዲሰጥበት አነሳስቶኛል። ለኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦችና ሀይማኖቶች ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ቀንድ ሕዝቦችና ለመላው የአፍሪካ ሕዝቦች መተጋገዝና መረዳዳት ጭምር የታሰበ ሰፊና ጥልቀት ያለው ሀሳብ መሆኑም
በተጨማሪ ያስደሰተኝ ጉዳይ ነው። ስለዚህ ይህ ቀና ሀሳብ እንዲሳካና ተግባራዊ እንዲሆን የሕዝቦችን በእኩልነትና በመከባበር ላይ የተመሠረተ አንድነት የምንሻ ኢትዮጵያውያን የድሻችንን ለመወጣት መተባበር ይኖርብናል።

ሀሳቡ ዘላቂነት ባለው መልኩ በትክክል ተግባራዊ እንዲሆን ደግሞ ሀሳቡን በንግግር ከመግለጽ ባሻገር የሀገራችን መንግሥት ቋሚ መመሪያ ሆኖ ሥራ ላይ እንዲውል የሚያደርጉ ውይይቶችና ድርድሮች በሚመለከታቸው አካላት ሁሉ
ሊደረጉና በብሔራዊ መግባባት ላይ ሊደረስበት ይገባል። በዚሁም መሠረት የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የህብረተሰብ ክፍሎች በሀገራችን አጨቃጫቂ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጥልቀት በመወያየትና ከስምምነት በመድረስ ቀና ሀሳቡ በሕዝባችን ዴሞክራሲያዊ ውሳኔ የሕገ-መንግሥታችን፣ የሕጎቻችንና የአፈጻጸም መመሪያዎቻችን አካል እንዲሆን በማድረግ በእነዚሁ ሰነዶቻችን ላይ ተገቢውን ማሻሻያዎች ማድረግ ይኖርብናል። በሚሻሻሉ ሰነዶቻችን ላይ ተመሠርተንም ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በማካሄድ ሕዝባችንን በትክክል የሥልጣን ባለቤት ማድረግና የህዝባችን እኩልነትና አንድነት የተረጋገጠበት ትክክለኛውን የፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት እውን ማድረግ ይገባናል።

ይህንን ቀና ሀሳብ በሥራ ላይ እንዲውል ከማድረጋችን ጎን ለጎን ደግሞ በከፋፋይ አስተሳሰቦችና ሥራዎች ምክንያት በተለያዩ የሀገራችን አከባቢዎች በተከሰቱት ግጭቶች ብዙ ጉዳት የደረሰባቸውንና በገዛ ሀገራቸው ከቤት ንብረታቸውም የተፈናቀሉትን ወገኖቻችንን በአስተማማኝና ዘላቂነት ባለው ሁኔታ ወደ ቤታቸውና ኑሮአቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙ ማድረግ ይኖርብናል። ዳግም እንደዚህ አይነት አስከፊ ጉዳቶች በሀገራችን እንዳይከሰቱም አፍራሽና ከፋፋይ አስተሳሰቦችን በማራመድ ሕዝባችን እርሰበርስ እንዲጋጭ የሚያደርግ ተግባራትን የሚፈጽሙ ሰዎች በሕግ ተጠያቂ
እንዲሆኑ በማድረግ፣ የመደመር ቀና ሀሳቡ በሕዝባችን ሕሊና ውስጥ በትክክል እንዲሰርጽና በእኩልነትና በመከባበር ላይ የተመሠረተው የሕዝባችንና የሀገራችን ጠንካራ አንድነት እውን እንዲሆን እያንዳንዳችን የድርሻችንን ሊንወጣ ይገባናል እላለሁ። ሰላምና ፍቅር ለሁላችንም ይሁን።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርካት።¾     


  
  


 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ቃለ መሐላ ከፈፀሙ እነሆ በዛሬው ዕለት (ሐምሌ 4 ቀን 2010 ዓ.ም) 100 ቀናትን ደፈኑ። በእነዚህ ቀናት ካከናወኙዋቸው በርካት ተግባራት መካከል የሚከተሉት የሚጠቀሱ ናቸው።

 

1.    ኢህአዴግ የስራ አስፈጻሚ ኮምቴ በወሰነው መሠረት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የነበረው የድንበር ግጭት እልባት እንዲያገኝ አድርገዋል። ከ20 ዓመታት ቁርሾ በኋላ ባለፈው ሳምንት እሁድ ዕለት ጠ/ሚ አብይ አሕመድ በአስመራ ከተማ ሲገኙ ፕሬዚደንት ኢሳያይስ አፈወርቂ ጨምሮ ከፍተኛ የኤርትራ መንግሥት ባለስልጣናት እና የኤርትራ ሕዝብ ደማቅ አቀባባል አድርገውላቸዋል። ሠላሙን ማስቀጠል የሚያስችል የሁለትዮሽ ስምምነትም ሁለቱ መሪዎች ተፈራርመዋል። ይህን ተከትሎ የቴሌኮምኒኬሽን አግልግሎት ተጀመረ ሰሆን የኢትዮጽያ አየር መንገድ መደበኛ በረራውን ከሚቀጥለው ማክሰኞ ዕለት እንደሚጀምር አስታውቋል።

የኢህአዴግ የስራ አስፈጻሚ ኮምቴ ውሳኔ ምን ነበር?

የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ስብሰባ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ተፈጥሮ የቆየውን አለመግባባት እንዲያበቃና በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር በይፋ ጥሪ አቅርቧል። "ለኢትዮጵያችን እድገትና ለሕዝቦች ተጠቃሚነት ሰላም ከምንም በላይ ትልቅ ዋጋ አለው። ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው። ከግለሰብ የወደፊት የማደግና መለወጥ ህልም ጀምሮ እስከ ሀገር ድረስ ሰላም ከደፈረሰ የቱንም አይነት የልማትና የዲሞክራሲ አላማዎችን ማሳካት አይቻልም።


በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ የተከሰተውን ጦርነት በአፍርካ ከተከሰቱ የድንበር ጦርነቶች ሁሉ ደም አፋሳሹ ሲሆን፣ ከሁለቱም ወገን በርካታ ሺህ የሰው ሕይወት ሊጠፋ ችሏል። ጦርነቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከኤርትራ እና ከኢትዮጵያ የድንበር አካባቢ መኖሪያ ቀዬ አፈናቅሏል።


በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረገው ጦርነት በሁለቱም አገራት ያሉ ቤተሰቦችን አፍርሷል፣ በድንበር አቅራቢያ የሚኖሩ ዜጎች ሁሌም ያለመረጋጋትና የስጋት ስነ-ልቦና ሰለባ አድርጓቸዋል።


በድንበር አካባቢ በንግድ የሚተዳደሩ ሰዎች ላይ ተፅኖ ፈጥሯል። በድምሩ ላለፉት 20 ዓመታት በሁለቱም ሀገራት ህዝቦች ላይ መጠነ ሰፊ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ፈጥሯል። በመሆኑም የሁለቱ ሀገራት የወደፊት ግንኙነት ምን ሊሆን ይችላል? የሚለው ጥያቄ የአብዛኛው ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን እንዲሁም የዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ጥያቄ ሆኖ ቆይቷል።


ከጦርነቱ በኋላ በአፍሪካ አንድነት ድርጅትና በተባበሩት መንግስታት አደራዳሪነት የአልጀርሱ ስምምነት ቢደረግም ላለፉት 20 ዓመታት በሁለቱ ወንድማማች ሀገሮች መካከል ጦርነትም ሆነ ሠላም የሌለበት ሁኔታ ተፈጥሯል። የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት ወደነበረበት ለመመለስ ላለፉት ሃያ አመታት የተደረጉ ሙከራዎች በሙሉ ውጤት አላመጡም። በዚህም ምክንያት በአሁኑ ጊዜ በሁለቱ ሀገራት መካከል የዕውነት ሰላም ለማስፈን ከቀድሞው የተለየ አቋምና አካሄድ ያስፈልጋል። ሁለቱም መንግሥታት ለህዝባቸው ምርጫና ፍላጎት ቦታ የማይሰጡ ሊሆኑ አይችሉም።


እኔ እበልጥ፣ እኔ እበልጥ የሚል ፉክክር ለሁለቱም ህዝቦች የሚፈይደው ነገር አይኖርም። ከዚህም በተጨማሪ ለአፍሪካ ቀንድ ሀገሮችና አካባቢ የፖለቲካ ቀውስ መብረድና መረጋጋት ዘላቂው መፍትሔ የኢትዮጵያና የኤርትራ ጤናማ ግንኙነት መመሥረት ነው። ይህን ባለማድረጋችን በርካታ ለሁለቱ እህትማማች ሀገሮችም ሆነ ለአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ትልቅ ፋይዳ ያላቸዉ እድሎች አምልጠዉናል። የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ህዝቦች ቀድሞም ቢሆን ወዳጅ ነን። በደም፣ በባህል፣ በቋንቋ እና በረጅም ጊዜ የጋራ ታሪክ የተሳሰርን ሕዝቦች ነን።

 

በመሆኑም በጥቅም ብቻ ሳይሆን በደም ለተሳሰሩት የሁለቱ ሀገር ሕዝቦች የጋራ ጥቅም ሲባል የኢትዮጵያ መንግስት የአልጀርሱን ስምምነት እና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ የወሰነና ለተግባራዊነቱ ያለማመንታት በቁርጠኝነት የሚሰራ መሆኑን ለመግለፅ ይፈልጋል።


ይህንኑ በጋራ ተጠቃሚነትና እኩልነት ላይ የተመሰረተውን የሀገራችን ፖሊሲም አጠናክረን እንደምንቀጥል በዚሁ አጋጣሚ በድጋሚ ለማረጋገጥ እንወዳለን። የኤርትራ መንግስትም ተመሳሳይ አቋም በመውሰድ ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ የሰላም ጥሪያችንን ተቀብሎ በሁለቱም ወንድማማች ህዝቦች መካከል ከዚህ በፊት የነበረውን አብሮነትና ሰላም ወደነበረበት ለመመለስና በቀጣይም ዘላቂነቱን ለመጠበቅ ለተግባራዊነቱ ያለማመንታት በቁርጠኝነት እንዲሰራ እንጠይቃለን።" ብሏል።

 

1.    ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አሕመድ ባለፉት 100 ቀናት በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር ተጉዘው ከመሪዎችና ከሕዝብ ጋር ስኬታማ ምክክር አድርገዋል። ከተጓዙባቸው የውጭ አገራት መካከል በሱዳን፣ በጅቡቲ፣ በሳዑዲ ዓረቢያ፣ በግብጽ በተለያዩ ምክንያቶች በእስር ላይ የሚገኙ ወገኖች እንዲፈቱ ከአገራቱ መሪዎች ጋር በደረሱት ስምምነት መሠረት በመቶዎች የሚቆተሩ ወገኖች የነጻነት አየር መተንፈስና ወደአገራቸውም መመለስ ችለዋል። ይህ ድንቅ ስራ እጅግ በርካታ ወገኖችን ድጋፍ አስገኝቶላቸዋል።

2.    ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ባለፉት 100 ቀናት ከወሰዱት ተጨማሪ እርምጃዎች መካከል የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን ማንሳት ይገኝበታል። አዋጁ ባለፉት ጊዜያት ከታየው የሕዝባዊ ተቃውሞ እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ በመደበኛ ሁኔታ የአገሪቱን ላም ማስጠበቅ አልተቻለም በሚል ወጥቶ ስራ ላይ የዋለ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን አዋጁ ከተነሳ በሃላ አንጻራዊ ሠላም ሰፍኗል።

3.    በክልሎች እና የፌዴራል መንግሥታቱ ሥር የተያዙ የፖለቲካ እና የህሊና እስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ማድረጋቸው በተለይም የግንቦት ሰባት ሁለተኛ ሰው የሆኑትን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከመፍታት በተጨማሪም በጽ/ ቤታቸው በክብር ማነጋገራቸው ከላ ወዳድ ወገኖች ታላቅ አድናቆትን አትርፎላቸዋል።

4.    በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት "አሸባሪ" ተብለው የተፈረጁትን ግንቦት 7፣ ኦነግ እና ኦብነግ ፍረጃ እንዲነሳ አድርገዋል።

5.    በውጭ አገር የሚኖሩ ዜጎችና የተቀናቃኝ ፓርቲ መሪዎች ወደአገር ውስጥ ገብተው በሠላም እንዲታገሉ በተደጋጋሚ ባደረጉት ጥሪ መሠረት መግባት ጀምረዋል።

6.    የፕረስ ነጻነት እና የሃሳብ ብዝሃነት እንዲከበር በተደጋጋሚ ባነሱት ሃሳብ መሠረት የመንገሥት መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጽያ ቴሌቭዝንን ጨምሮ የሚደነቅ የይዘት ለውጥ (መሻሻል) ማድረግ ችለዋልረታቸውን በውጭ አገር ያደረጉ ሚዲያዎች እንዲከፈቱ አዎንታዊ አስተዋጽኦ አድርገዋል። በዚህም በመበረታታት የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ በአዲስአበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ለመክፈት በቅቷል።

7.    የፀረ-ሽብርተኝነት፣ የሲቪል ማኅበራት እና የመገናኝ ብዙሃን የመረጃ ነጻነት አዋጆችን ለማሻሻል ኮምቴ ተዋቅሮ ሥራ መጀመሩ በአዎንታ የሚወሰድ ነው።

8.    በቀጣይም የፍትሕ አካላትን (ማለትም ፍርድ ቤቶችን፣ ፖሊስ፣ ደኅንነት እና መከላከያ)፣ በመንግሥት በጀት የሚተዳደሩ ብዙኃን መገናኛዎችን እንዲሁም ምርጫ ቦርድን ለሕዝብ እና ሕገ መንግሥቱ ወገንተኛ እንዲሆኑ በማድረግ መልሶ ማዋቀር ለማከናወን ዕቅዶች መኖራቸው የሚበረታታ ነው።

9.    የጠ/ሚ አብይ አሕመድ አመራር ለመደገፍና አስካሁን ለተሰሩ ሥራዎች ዕውቅና ለመስጠት አዲስአበባን ጨምሮ በተለያዩ የክልል ከተሞች ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቁ ሰልፎች ተካሂደዋል። በተለይ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስአበባ የተካሄደውን ሰልፍ ለማደናቀፍ ታስቦ የተወረወረ ቦምብ ንጹሐን ወገኖቻችን መጎዳታቸው በአስከፊነቱና ነውረኝነቱ በታሪክ ተመዝግቦ የሚቀመጥ ሆኗል።

10.  ሚኒስቴሮች ብክነትን ለማስወገድ ከሰኞ እሰከ አርብ የሚካሄዱ ስብሰባዎቻቸውን ወደ ቅዳሜና እሁድ እንዲያሽጋግሩ እንዲሁም አላስፈላጊ ተደጋጋሚ የውጪ ጉዞዎችን ከማድረግ እንዲቆጠቡና እነዚህን መተላለፍ ቀይ መስመር ነው በማለት ጥብቅ ማሳሰቢያ የሰጡትም ባሳለፍነው 100 ቀናት ውስጥ ነው። በዚሁ መሠረት ጠ/ሚ የሚመሩት የካቢኔ ስብሰባ ወደቅዳሜ የተዛወረ ሲሆን በአንዳንድ መንግሥታዊ ተቋማት ለስብሰባ ሚጠፋ ስራ ጊዜ እንዲቀንስ አዎንታዊ አስተዋጽኦ አድርጓል።

11.  ጠ/ሚኒስትሩ ካቢኔያቸውን እንደአዲስ ከማዋቀራቸው በተጨማሪ በተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት የነበሩ አመራሮች ሹም ሽር አድርገዋል። አንዳንዶችን በጡረታ አሰናብተዋል። በተለይ በሙስናና ብልሹ አሰራር የሚጠረጠሩ ተቋማት መሪዎች "ከቦታቸው መነሳታቸው ብቻ ለምን፣ ለምን አይከሰሱም" የሚል የሕዝብ ጥያቄ ቢኖርም ሹም ሽሩ በሕዝብ ዘንድ በአዎንታ የተወሰደ ነው።¾

“ከህወሓት አንዳንድ አመራሮች በላይ

ለትግራይ ህዝብ ጠላት የለም”

አቶ ታደለ ደርሰህ የቪኢኮድ ዳይሬክተር

በይርጋ አበበ

አቶ ታደለ ደርሰህ የቪዥን ኢትዮጵያ ኮንግረስ ድርጅት (ቪኢኮድ) ዋና ዳይሬክተር ሲሆኑ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ሃሳባቸውን በግልጽ በመስጠት ይታወቃሉ። ለአገር እድገት ሶስት መሰረታዊ ነገሮች መሟላት አለባቸው የሚሉት አቶ ታደለ፤ የሶስቱን ተቋማት ማንነት ሲገልጹም ‹‹ነጻ ሚዲያ፣ የማህበራት ጠንካራነት እና ነጻ የፍትህ ስርዓት›› ናቸው ይላሉ። አቶ ታደለ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለሰንደቅ ጋዜጣ የሰጡትን አጠር ያለ ቃለ ምልልስ ከዚህ በታች አቅርበነዋል።

ሰንደቅ፡- ከ1990 ዓ.ም ወዲህ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ያለው ግንኙነት ፍጹም ሰላም የራቀውና የሻከረ ሆኖ ቆይቷል። በቅርቡ የተጀመረውን የመሪዎችን ግንኙነትና የአገራትን የግንኙነት እንቅስቃሴ እንዴት ያዩታል?

አቶ ታደለ፡- በመጀመሪያም አላስፈላጊና ምክንያት የሌለው ጦርነት ነበር የተካሄደው። የአንድ እናት ልጆች ሁለት ወንድማማችና እህትማማች ህዝቦች መካከል የተካሄደ የመጠፋፋት ጦርነት ነበር። በዚያ ‹‹ምክንያት አልባ ጦርነት›› የህይወት እና አካል መስዋዕት እንዲሁም አላስፈላጊ የንብረት ውድመት ያስከተለ ሲሆን ለዚያ ጦርነት መነሻ ምክንያት የነበሩ ሰዎች በታሪክም በህግም ተጠያቂ መሆናቸው አይቀርም። ከ70ሺህ በላይ ሰዎችን ያጠፋው ጦርነት ምንም እንኳን ለጊዜው የሁለቱን ህዝቦች ግንኙነት ቢያቋርጠውም ሁለቱ አገራትና ህዝቦቻቸው ግን ፈጽሞ የሚለያዩ አይደሉም።

ሁለቱ የማይነጣጠሉ ህዝቦች እንዲነጣጠሉ የተደረገው ከጦርነቱ በፊት ነው። ወደ ስልጣን እንደወጡ ለኤርትራዊያን ከኢትዮጵያ መገንጠል የቀረበላቸው የህዝበ ውሳኔ ምርጫ “ከነጻነትና ከባርነት” የሚል ነበር። በየትኛውም መመዘኛ ስናስበው አእምሮው የሚያገናዝብ ማንኛውም ሰው ከእነዚህ ጥያቄዎች “ባርነትን” ሊመርጥ አይችልም። ይህን ስንመለከት ከመጀመሪያውም ሁለቱ ህዝቦች እንዲለያዩ ሆን ተብሎ የታሰበ እና ኋላ ቀር ቃላትን ነበር የተጠቀሙት። ይህ የተደረገው ደግሞ ከጀርባው መሰሪ ተንኮሎች ስለነበሩ ያንን ለማስፈጸም የተደረገ ሴራ ነው።

ሰንደቅ፡- በሁለቱ አገራት መካከል የተካሄደውን ጦርነት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ያወግዙታል። ነገር ግን ከማውገዝ በዘለለ በህይወት ያሉትን ለጦርነቱ መነሻ ምክንያት የሆኑ ሰዎችን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ አይቻልም? በህይወት የሌሉትስ በታሪክ ተጠያቂ ከመሆን አያመልጡም ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?

አቶ ታደለ፡- አንደኛ ምንም ቢሆን ምንም ታሪክን ማዛባት አይቻልም። የሁለቱ አገራት ጦርነት ሲካሄድ በወቅቱ የሚጠቀሙ አካላት ነበሩ፤ እነዚህ አካላት ደግሞ የሚጠቀሙትን ያህል ተጠቅመዋል። በታሪክ ግን ምን ጊዜም ቢሆን ተወቃሾች ናቸው። በታሪክ ተወቃሽ የሚሆኑበት ምክንያት ደግሞ እነዛ ለአገራቸው ሲሉ ህይወታቸውን የከፈሉ የ70 ሺህ ኢትዮጵያዊያን አጽም ይፋረዳቸዋል። አላግባብ የወደመው ኢኮኖሚ ይፋረዳቸዋል፤ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ህዝብ አንድ መሆኑ ስለማይቀር የሁለቱ ህዝቦች በታሪክ ይፋረዷቸዋል። ይህ መሰሪ ተግባራቸው እስከመጨረሻው ድረስ የክፋት አሻራውን ይዞ ይቀጥላል።

ነገር ግን በህይወት ያሉት ለዛ ወንጀላቸው ማሰሪያ የሚሆናቸው ዘመኑ የይቅርታ እና የፍቅር ስለሆነ ማንም ሰው በታሪክ ይሳሳታል። እነዚህ ሰዎች የተሳሳቱት ስህተት፣ ከስህተት ሁሉ የገዘፈ ቢሆንም ለሰሩት ስራ ተጸጽተው የኢትዮጵያንና ኤርትራን ህዝብ በግልጽ ይቅርታ ከጠየቁ የሁለቱም አገራት ህዝቦች የይቅርታ ህዝብ ስለሆኑ ይቅር ይሏቸዋል። ነገር ግን እነዚህ ሰዎች ለመጸጸትና ይቅርታ ለመጠየቅ ወኔ ሊኖራቸው ይገባል። ምንም ሳይደረግና የተፈጸመ ነገር ሳይኖር መስቀል አደባባይ ላይ አስወጥተው በሀሰት ያስጨፈሩን ሰዎች ናቸው። እነዚህ የህወሓት መሪዎች በህግም በታሪክም ተጠያቂ መሆን ያለባቸው ለዚህ ሁሉ ጥፋታቸው ነው። እዚህ ላይ ግን በጥንቃቄ ሊታይ የሚገባው የትግራይን ህዝብ ከህወሓት መሪዎች ለይቶ ማየት እንደሚኖርብን ነው።

ሰንደቅ፡- ህወሓትን እና የትግራይን ህዝብ ለይተን ማየት አለብን ብለዋል። ቀደም ሲል ዶክተር አብይ አህመድም ይህንኑ ብለውታል። ህወሓቶች ደግሞ የትግራይ ህዝብ እና ህወሓት አይነጣጠሉም ሲሉ ተናግረዋል። እርስዎ ሁለቱ ይለያያሉ ያሉበትን ምክንያት ያብራሩልን?

አቶ ታደለ፡- የትግራይ ህዝብ ትልቁ ጠላት ማንም ሳይሆን ህወሓት ነው። ከህወሓት መሪዎች በላይ ለትግራይ ህዝብ ጠላት የለም። ለዚህ ነው የትግራይ ህዝብን እና ህወሓትን ለይተን ማየት አለብን የምለው። ምክንያም ጥቂት የህወሓት አፈጮሌዎች እና ካድሬዎች ወይም ደካሞች ሰሩት ብለን የትግራይን ህዝብ አንጠላም። እንደመር ስንል የትግራይን ህዝብ ጨምረን ነው፤ እንደመር ስንል ትናንት ህዝቡን ያናከሱት የህወሓት መሪዎች ተጸጽተው ህዝብን ይቅርታ መጠየቅ አለባቸው እያልን ነው። እነዚህ የህወሓት መሪዎች ለዚህ ጥፋታቸው በመጀመሪያ ደረጃ የትግራይን ህዝብ ይቅርታ መጠየቅ ይኖርባቸዋል።

ሰንደቅ፡- ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ደም አፋሳሽ ጦርነት በኋላ አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ ለመጀመር በመሪዎች ደረጃ ጥረት እየተካሄደ ነው። ዛሬም (ቃለ ምልልሱ በተካሄደበት እለት) ዶክተር አብይ ወደ አስመራ ተጉዘዋል። ነገር ግን ይህን የዶክተር አብይ እንቅስቃሴ የሚተቹ ፖለቲከኞች ‹‹ግንኙነቱ ትግራይን ያላካተተ ስለሆነ ትርጉም አልባ ነው›› ይሉታል። ትግራዮች ያልተሳተፉበት ግንኙነት ሲባል ምን ማለት ነው?

አቶ ታደለ፡- ቀደም ብዬ እንደነገርኩህ እኮ ነው። ‹‹ዛሬም ቢሆን ህወሓት የበላይ ነው። ስለዚህ የህወሓት መሰሪ ተግባር መቀጠል አለበት›› እያሉን ነው ያሉት። የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ የህወሓት መሰሪ ተግባር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መቆም አለበት ነው እያለ ያለው። እነዚህ የህወሓት መሪዎች መሰሪነት የጀመረው እኮ አሁን አይደለም። በመጀመሪያ ደረጃ ገና በ1968 ዓ.ም ወደ ደደቢት በርሃ ሲወርዱ ባወጡት ማንፌስቶ ገጽ አራት ላይ ‹አማራ ጠላታችን ነው› ብለው አማራንና ትግራይን ያናከሱ ናቸው። ስለዚህ ያ መሰሪ ተግባራቸው ዛሬም እንዲቀጥል ነው የሚፈልጉት። ነገር ግን ያ መሰሪ ተግባራቸው የተቃጠለ ካርታ ነው፤ የትም ቦታ ሄዶ ሊሰራላቸው አይችልም። የትግራይ ህዝብ ዛሬ የሚፈልገው ከሌሎቹ የኢትዮጵያ ወንድምና እህቶቹ ጋር በጋራ ሆኖ በዚህች አገር ላይ ሁሉም እኩል ተጠቃሚ ሆኖ መኖርን እንጂ፤ በጥይት መደባደብን እና በሌላው ጉዳይ መወነጃጀልን እንዲሁም አድማ እና የህወሓትን መሰሪ ተግባር መፈጸም እና ሰለባ መሆንን አይደለም።

የትግራይ ህዝብ እንደሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ መብቱን ያጣና በህወሓት መሰሪዎች ጭቆና የተረገጠ ህዝብ ነው። ንጹህ ውሃ ለማግኘት የተቸገረ እና የትምህርትም ሆነ የጤና አቅርቦት ያጣ ህዝብ ነው። እነዚህ የህወሓት መሰሪዎች ‹‹የትግራይን ህዝብ እንወክላለን›› የሚሉት ህዝቡን እንደዚህ እየበደሉ ነገር ግን የትግራይን ህዝብ ከሌሎቹ ወንድምና እህቶቹ ጋር እንዲለያይ እያደረጉት ነው። ስለዚህ የትግራይ ህዝብ እነዚህን ሰዎች በጽኑ ታግሎ ከትከሻው ላይ ሊያወርዳቸውና ላደረሱበት በደልም በህግ ሊፋረዳቸው ይገባል።

እነዚህ በትግራይ ህዝብ ትከሻ ላይ ተቀምጠው 27 ዓመት ሙሉ በደልና ግፍ ሲፈጽሙብን የከረሙት የህወሓት አንዳንድ መሪዎች ለፈጸሙት ግፍ ተጽጽተው ይቅርታ ሊጠይቁ ብቻ ሳይሆን እነሱ ለጨቆኑት ህዝብ ነጻ እንዲወጣ የተመረጠው ዶክተር አብይም በፈርኦን ቤት ያደገ ሙሴ መሆኑን ሊያውቁት ይገባል።

ሰንደቅ፡- ዶክተር አብይ አህመድ በፈርኦን ቤት ያደጉ ሙሴ ናቸው ለማለት ያስደፈረዎት ምንድን ነው?

አቶ ታደለ፡- ዶክተር አብይ ገና ከ15 ዓመታቸው ጀምረው ያደጉት በጨቋኝና መሰሪ ከሆኑት ከህወሓት መሪዎች ጋር ቢሆንም፤ እሳቸው ግን ለህዝባቸው ነጻነት፣ ፍቅርና ሰላም መስበክ የቻሉ ሰው ስለሆኑ ነው። ገና ከ15 ዓመታቸው ጀምረው እነዚህን ሰዎች በሚገባ አይተዋቸው መሰሪነታቸውንም ተረድተው እና ይህ አካሄዳቸውም ለኢትዮጵያ እንደማያዋጣ ተረድተው ጊዜውን ጠብቀው የተነሱ ሰው ናቸው። እሳቸውን ለዚህ ህዝብ የላካቸውም እግዚአብሔር ነው።

በነገራችን ላይ ዶክተር አብይ የሚያስፈልጉት ለኢትዮጵያ ብቻ አይደለም፤ ለምስራቅ አፍሪካ እና ለአፍሪካም የሚያስፈልጉ ሰው ናቸው። እኛም ብንሆን እኒህን ጠቅላይ ሚኒስትር በማንኛውም በምንችለው መንገድ ሁሉ ልናግዛቸውና ልንተባበራቸው ይገባል ብዬ አስባለሁ። እነዚህ ሰዎች ግን (የህወሓት መሪዎችን) ይህን እውነታ መቀበል ካልቻሉ ሰውነታቸውም ያጠራጥረኛል። ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ይህን መሰሪነታቸውን ካላቆሙ እንኳን ለኢትዮጵያ እና ለትግራይ ህዝብ ቀርቶ ለራሱ ለህወሓት እና ለራሳቸውም አይበጁም። ጊዜው መሽቶባቸዋል።

ሰንደቅ፡- ዶክተር አብይ አህመድና አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ የጀመሩት ግንኙነት ለቀጠናውና ለሁለቱ አገራት የሚኖረው ትርጉም ምንድን ነው?

አቶ ታደለ፡- በመጀመሪያ ደረጃ በዚህ ጉዳይ ይኖራል ብዬ የማስበው ጥቅም የሰው አእምሮ ሰላም ይሆናል። እናት ከልጇ፤ ባል ከሚስቱ፤ ወንድም ከወንድሙና እህት ከእህቷ ጋር ተለያይቶ ነው ላለፉት 27 ዓመታት የቆዩት። ስለዚህ እነዚህ መለያየት ያልነበረባቸው ህዝቦች አለመለያየታቸውን ያመጣል።

በሌላ ጎን ደግሞ ‹‹የውሃ እናት›› እየተባለች የምትጠራውን አገር (ኢትዮጵያን ለማለት ነው) ወደብ አልባ ማድረግ በታሪክ ማንም ይቅር ሊለው የማይችል ወንጀል ነው። ስለዚህ አሁን የሁለቱ መሪዎች ግንኙነት ይህንን ወንጀል እንዲቀር ያደርገዋል። አሰብ የእኛ ንብረት ሆኖ ሳለ በንብረታችን መጠቀም እየቻልን በሌላ ቦታ እንድንጠቀም የተደረገው በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚ አሻጥር በመፈፀሙ ነው። ይህንንም ስለሚቃልል የመሪዎቹ መገናኘት ጠቀሜታ አለው።

ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ቦታው ስትራቴጂክ ነው። በዚህ ስትራቴጂክ ቦታ ላይየድርሻውን ለማግኘት የማይጠቀም አካል የለም። ብዙዎቹም አሰፍስፈው እየተጠባበቁ ነው። ስለዚህ ይህን የመሰለ ስትራቴጂክ ቦታ ሰላም እንዲሆን ማድረግ ለቀጠናው ሰላም ይሆናል። ምስራቅ አፍሪካ ሰላም ከሆነ ደግሞ መላ አህጉሩ ሰላም ይሆናል። ቀይ ባህር ሰላም ከሰፈነበት ዓለምም እንዲረጋጋ የራሱን ሚና ይጫወታል።

ከጦርነት ያተረፍነው ነገር ቢኖር ኪሳራችንን ማብዛት ብቻ ነው። እኛ ስንጣላ እነሱ (ምዕራባዊያንን) ለእኛ መሳሪያ ያቀብላሉ። እኛ በእነሱ ዘመን ያለፈበት መሳሪያ ስንተላለቅ ‹‹የሰላም ኮንፈረንስ›› ብለው ይጠሩንና በሌላ አቅጣጫ አዳዲስ የጦር መሳሪያዎችን እያመረቱ እንደገና እንድንጫረስ ያደርጉናል። ስለዚህ ይህ እኩይ ተግባር በምስራቅ አፍሪካ እንዲቆም የሚያደርግ የግንኙነት ጅማሮ ነው ብዬ አስባለሁ።

ሰንደቅ፡- የወደብ ጉዳይ ካነሱ አይቀር ኢትዮጵያ ወደብ እንዲኖራት ከኢህአዴግ ውጭ ያሉ ፖለቲከኞች ደጋግመው ይናገራሉ። በኢህአዴግ በኩል ግን ከአቶ መለስ ዜናዊ ጀምሮ የፓርቲው ከፍተኛ መሪዎች የወደብ ጥያቄን የሚያነሱትን ሰዎች ‹‹ጦርነት ናፋቂዎች›› ሲሉ ይወቅሷቸዋል። ቀደም ሲል የኢህአዴግ መሪዎች ወደብን ይገልጹበት ከነበረው እይታ ወጣ ባለ መልኩ ዶክተር አብይ የወደብን አስፈላጊነት ማቀንቀናቸው የኢህአዴግ እምነት ተቀይሯል ብለው ያስባሉ?

አቶ ታደለ፡- ይህ የኢህአዴግ እምነት ነው ብዬ አላስብም፤ አላንምም። የወደብ ጉዳይ የኢህአዴግ እምነት ቢሆንማ ኖሮ ታሪክ ወደፊት ዝርዝር ሁኔታውን ቢያወጣውም ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም መስቀል አደባባይ ላይ በተጠራ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ እንደዛ አይነት የህዝብን ስሜት የሚነካ ተግባር አይፈጸምም ነበር (ዶክተር አብይን ኢላማ ያደረገ የቦንብ ጥቃት መፈጸሙን)። የወደብ ጥያቄም የኢህአዴግ ፍላጎት አይደለም። የወደብ ጥያቄ ከኢህአዴግ ውጭ ያሉ ከመቶ ሚሊዮን በላይ ዜጎች የሚጠይቁት ጥያቄ ነው። ይህን የህዝብ ጥያቄ ደግሞ ኢህአዴግ መቀበል አለበት። ኢትዮጵያ ላይ ወደብ እንዳይኖራት የተፈረደባትም በኢህአዴግ በተለይም በህወሓት መሪዎች አማካኝነት ነው።

 

በይርጋ አበበ

 

የደራሲ ያሬድ ነጋሽ አዲስ መፅሐፍ “የካድሬው ንሰሃ” የፊታችን አርብ ከአመሻሹ ፀሐይ ከመጥለቋ በፊት ይመረቃል።

በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ከአብራጃው 11፡00 የሚመረቀው የካድሬው ንሰሃ ላይ ዶ/ር ዮናስ ባህረ ጥበብ፣ አርክቴክት ሚካኤል ሽፈራው፣ ገጣሚያኑ ማርቆስ አውራሪስ፣ ልዑል ሀይሌ፣ ስጦታው አስማረ፣ ብሩክ ሚፍታህ እና መላኩ ስብሃትን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይገኙና መፅሐፉን “ከአይን ያውጣህ” ሳይሆን ለአይን ያብቃህ ብለው ይመርቁታል።

 

በይርጋ አበበ

አንጋፋው የታሪክ ተመራማሪ ንጉሴ አየለ ተካ ለ18 ዓመታት ያካሄዱት የምርምር ስራ የሆነው “ታላቁ ጥቁር ኢትዮ-አሜሪካ ዘዳግማዊ ምኒልክ” ለገበያ የቀረበው በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ነው።

በዳግማዊ አፄ ምኒልክና በቀደምት ኢትዮጵያ ላይ የሚያተኩረው ይኸው ወርደ ሰፊና ሀሳበ ብዙ መፅሐፍ 473 ገፆች አሉት። ቀጣይ ክፍል እንዳለው የተገለፀው ይህ መፅሐፍ 25 ምዕራፎች ሲኖሩት ኢክሊፕስ ማተሚያ ቤት ደግሞ የህትመት ስራውን ያከናውነው ድርጅት ነው።

ሁለት መቶ ብር በማይሞላ ገንዘብ ለገበያ የቀረበው “ታላቁ- ጥቁር” ጸሐፊውን ሰፊ የምርምርና የጥናት ጊዜ እንደወሰደባቸው ተገልጿል። ታላቁ ጥቁር ኢትዮ- አሜሪካ ዘዳግማዊ ምኒልክ በ195 ብር ብቻ በሁሉም መፅሐፍት መደብሮችና የመፅሀፍት አዟሪዎ እጅ ላይ አፄ ምኒልክን በዙፋናቸው ላይ በክብር አስቀምጦ በክብርና በኩራት የሚገኝ መጽሐፍ ነው።

 

 

(ይህ ጽሑፍ በ1992 ከታተመው "Ethnic Federalism in a Dominant Party State: The Ethiopian Experience 1991-2000" ከሚለው የሎቪስ አለን ጥናት ውስጥ ካለ ንዑስ ርዕስ ተቀንጭቦ የተተረጎመ ነው።)

በሽግግር መንግሥቱ ግዜ የታተሙት ዐዋጆች ሁሉ ክልሎች እና ንዑስ ክፍሎቻቸው የማዕከላዊ መንግሥቱ ምንዝሮች እንደሆኑ ተመልክቷል። የሽግግር ምክርቤቱ ለብሔሮች ‹የራስን ዕድል በራስ መወሰን› የሚል ቃል በስተቀር የክልሎች ሥልጣን የተገደበ ነበር። የኢትዮጵያ መንግሥት ያልተማከለ፣ አሀዳዊ፣ ወይም ፌዴራላዊ ስለመሆኑ ምንም አይታወቅም ነበር። የ1987ቱ ሕገ መንግሥት ግን ይህንን ግራ መጋባት ቀርፎታል። አሀዳዊውን ስርዓት በመተው ፌዴራላዊውን እንደሚከተል በግልጽ ያስቀምጣል (አንቀፅ1)። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ የፌዴራል አወቃቀር ላይ በርካታ እንግዳ እና አሻሚ ነገሮች አሉ። ይህም ከነባር ፌዴሬሽኖች የፌዴራል ኅልዮት እና አተገባበር አንፃር ይገጥማሉ ወይም ይጋጫሉ የሚለውን የመደምደሙን ነገር ከባድ ያደርገዋል። የመገንጠል መብት፣ ለፌዴሬሽኑ አባል አገረ-መንግሥታት ፈንታ ሉዓላዊነት "ለብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች" መሰጠቱ፣ ገለልተኛ የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት አለመኖር፣ እና ጠንካራው የሥራ አስፈጻሚ አካል ለዚህ ውስብስብ ባሕሪው ተጨማሪ ምክንያቶች ናቸው።

የክልሎች ሥልጣን ተቃርኖ

በኢትዮጵያ ፌዴራል አወቃቀር ግልጽ የሆነ አያዎ እንዳለ ብዙ ጸሐፊዎች አስፍረዋል። በአንድ በኩል ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የተወሰኑ ሁኔታዎችን አሟልተው የመገንጠል መብት ተሰጥቷቸዋል። ይህ ከሌሎች የፌዴራል ስርዓታት በተለየ የፌዴራሉ አካላትን ነጻነት የተለጠጠ ያደርገዋል። በሌላ በኩል፣ የአባል አገረ-መንግሥታቱ ሥልጣን በአንፃሩ በጣም ውሱን ነው። የክልል መንግሥታቱ ሥራቸውን ለመሥራት በፌዴራል መንግሥቱ ላይ ጥገኛ ናቸው። በብሬዝኬ እንደተገለጸው፣ ሕገ መንግሥቱ “ጥቂት የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብቶችን መድኅን” ያቀርብና፣ እስከ መገንጠል በሚለው መካከል ምን እንዳለ ስላልተገለጸ፣ ጠባብ የራስን ዕድል የመወሰን ቅርፅ እና የተገደበ የባሕል ነጻነት ያጎናፅፋል።"

ዱካቼክን ጨምሮ የተወሰኑ የፌዴራሊዝም አጥኚዎች የመገንጠል መብት አንድን አገረ መንግሥት ፌዴራላዊ ለመባል እንዳይበቃ ያደርገዋል በማለት እስከመከራከር ይደርሳሉ። የመገንጠል መብት ዜጎች ለማዕከላዊ መንግሥቱ ያላቸው ታማኝነት ቀስ በቀስ እንዲቀንስ ያደርገዋል። በተጨማሪም፣ ክልሎች ኅብረቱን የመልቀቅ ነጻነቱ ሲኖራቸው፣ በማዕከሉ እና አገረ መንግሥታቱ መካከል ያለው የፖለቲካ መዋቅር ከፌዴሬሽን ይልቅ የላላ ንዑስ ብሔራዊ ቁጥጥር ያለው ኮንፌዴሬሽን ዓይነት ይሆናል። ሉዓላዊነት ለብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች መሰጠቱም ቢሆን ብሔረሰቦች ከፌዴሬሽኑ ብቻ ሳይሆን ከክልሉ አገረ መንግሥታት ሳይቀር እንዲገነጠሉ ሊያደርግ ይችላል። ይህ ያልተለመደ ሕገ መንግሥታዊ ስርዓት ከመሆኑም ባሻገር የሚመስለው አንድም የፌዴራል ስርዓት ዛሬ ላይ የለም። የመገንጠል መብት መኖር ኢትዮጵያን ፌዴራላዊ ለመባል አያበቃትም የሚለው እንደ አስተያየት ሰጪው ይወሰናል። ሌሎች የፌዴራል ስርዓቶችን ብንመለከት፣ አንዳንድ የዘውግ ቡድኖችን ወይም ክልሎችን የመገንጠል መብት የሰጡ ስርዓቶች አሉ። ነገር ግን እነዚህኞች ከሕገ መንግሥት ድንጋጌዎች ውጪ የተሰጡ ናቸው።

እንደስፔንና ካናዳ ያሉ ኅብረብሔራዊ ፌዴሬሽኖች መሰል ፈቃዶችን በዘውግ ለተለዩ ክልሎች ሰጥተዋል። ሆኖም እነዚህ ፈቃዶች ከሕገ መንግሥት ውጪ ነው የተደነገጉት። ይህም መዋቅሩን የበለጠ ተለዋዋጭ አድርጎታል። ይህንንም ማድረግ የተቻለው ቀስ በቀስ የወቅታዊ የፖለቲካ ፍላጎቶችን ለማሟላት ነው። ኩዩቤክ ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች ከካናዳ ፌዴሬሽን ለመገንጠል እንቅስቃሴ ሲጀምሩ፣ በካናዳ የፖለቲካ ሒደት ውስጥ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል ሳያስፈልግ ትልቅ ለውጥ ተደርጓል። የኪዩቤክ ገዢ ፓርቲ በሪፈረንደም ከተሳካለት ሉዓላዊ አገር የመፍጠር መብቱን አረጋግጧል። እኤአ የ1995ቱ የሉዓላዊነት ዐዋጅ የዚያን ዓመት የተካሔደውን ሪፈረንደም ማሸነፍ ቢችሉ ኖሮ ለኪዩቤኮች የመገንጠል ሕጋዊ ዕድል ሰጥቷቸው ነበር።

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ከስፔኑ የ1978 (እኤአ) ሕገ መንግሥት ጋር ሊነፃፀር ይችላል። ልክ እንደ ኢትዮጵያ ስፔን ደም አፋሳሽ የመንገንጠል ንቅናቄ እና ዴሞክራሲያዊ ያልሆነ ታሪክ ችግር ነበረባት። እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ፣ የስፔን መንግሥት የሆነ ዓይነት ነጻነት ማስተዋወቅ ፈልጓል። ነገር ግን ክልሎቹን እና የጥያቄ አቅራቢዎቹን ድንበሮች በሕገ መንግሥታዊ አንቀፆች ለመለየት አልሞከረም። በምትኩ፣ "ራስ ገዝ ማኅበረሰቦች” በሚል ቀስ በቀስ የሚያድግ ራስን የማስተዳደር ሥልጣን ተሰጣቸው። ይህም የሆነው በሌሎች የፌዴራል መንግሥታት ከተለመደው በተለየ ሁኔታ በክልል እና ማዕከላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር ነበር። ሆኖም፣ ዋናዎቹ የመከላከያ እና የኢኮኖሚ አውታሮች በማዕከላዊው መንግሥት ቁጥጥር ሥር ናቸው። ራስ ገዝ ማኅበረሰቦቹ ሁሉም እንደየ ድርድራቸው የተለየ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ነው የተሰጣቸው። ይህ አለመመጣጠን ከአዲሱ የራሽያ ፌዴሬሽን ጋር አንዳንድ መመሳል አለው። በ1992ቱ (እኤአ) የራሽያ ፌዴሬሽን ስምምነት የተለያዩ የዘውግ ሪፐብሊኮች የመገንጠል መብት ተሰጥቷቸው ነበር። ይህ የሶቪየት ኅብረት ግዜም የነበረ ነው። ሆኖም ስምምነቱ (እኤአ) በ1993 ሲከለስ ተሰርዟል። በፈንታው፣ ማዕከላዊው መንግሥት ከዘውግ ሪፐብሊኮቹ ጋር ሥልጣን የመጋራት የሁለትዮሽ ስምምነቶችን መደራደር የጀመረበት "ድኅረ ሕገ መንግሥታዊ ሒደት" ውስጥ ገብቷል።

የካናዳ፣ ስፔን እና ራሽያ ሕገ መንግሥቶች የመገንጠል መብትን አላካተቱም። ነገር ግን በተግባር የተለጠጠ “የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መድኅኖችን” ለአባላቱ የተለያየ የራስ ገዝ አስተዳደር ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ ፌዴሬሽን ግን በተቃራኒው መሔድን መርጧል። የመጨረሻውን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ማለትም የመገንጠል መብትን ሰጥቶ የክልሎቹን የለት ጉዳዮች ለመፈፀም የሚያስፈልገውን ሥልጣን ግን ባንፃሩ ይገድበዋል። መሬት እና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች ለምሳሌ የሚተዳደሩት በፌዴራል ሕግጋት ነው። የክልል መንግሥታቱ የዕለት ተለት ሥራቸውን ለመከወን የአገርዐቀፉን መደብ መከተል አለባቸው። ይህም ማለት በፌዴራሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚፀድቀው የአምስት ዓመት የኢሕአዴግ ዕቅድ በሁሉም የክልል መንግሥታት፣ በያንዳንዱ የአስተዳደር እርከን ተፈፃሚ መሆን አለበት። የክልል የገቢ ምንጮች ከፌዴራሉ አንፃር ጥቂት እና እዚህ ግባ የማይባሉ ናቸው። ይህም ማለት የክልል መንግሥታት ሥራዎቻቸውን ለመከወን የፌዴራል መንግሥቱ ድጎማ እና ሥጦታ ላይ ጥገኛ መሆን አለባቸው።

ቁጥጥር አልባው ገዢ ፓርቲ

በርካታ የፌዴራሊዝም አጥኚዎች እንደሚሉት አንድ ፌዴሬሽን መንግሥት ከሕግ በታች ካልሆነ ሐቀኛ ሊሆን አይችልም፡፡ የፖለቲካ ኃይሎቹ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡትን ድንጋጌዎች ካላከበሩ የተሰጡት ዋስትናዎች ዋጋ የላቸውም፡፡ መንግሥት ለሕግ ታዛዥ መሆኑን ለማረጋገጥ የፌዴራል ስርዓቱን አተገባበር እና የፖለቲካ አመራሮችን ሥራዎች መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን የሕግ ማዕቀፉ በራሱ የፌዴራል ስርዓቱ የፌዴራል እና ክልሎች ግንኙነትን በመወሰን ረገድ መዋቅራዊ የቁጥጥር ድንጋጌዎችን መጣል አለበት፡፡ እዚህ ጋር መነሳት ያለበት ጥያቄ ‹የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የፖለቲካ አመራሩ የፌዴራል መርሖችን እንዳይጥስ በቂ የቁጥጥር መንገዶችን አስቀምጧል ወይ?› የሚለው ነው፡፡

እንደ አሜሪካው ዓይነት የፌዴራል ስርዓት ውስጥ፣ የሕግ አውጪው ሁለተኛ ምክር ቤት የሌሎች የፌዴራል ተቋማትን ሥልጣን በመቆጣጠር የሥልጣን ክፍፍልን በተመለከተ መሠረታዊ ሚና ይጫወታል፡፡ እንደ አውስትራሊያ እና ካናዳ ባሉ የፓርላሜንታዊ ፌዴራል ስርዓቶች ውስጥ ደግሞ ሁለተኛው ምክር ቤት የአገርዐቀፉ መንግሥት ሕጋዊ ተግባራት ውስጥ ክልሎቹ መማከራቸውን ያረጋግጣል፡፡ በኢትዮጵያ ሁለተኛው ምክር ቤት፣ ማለትም የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ አንዳቸውንም መሰል ዓይነቶቹን ክፍተቶች አይሞላም፡፡ የኢትዮጵያ ስርዓት በተፈጥሮው ፓርላሜንታዊ ነው፤ ነገር ግን የፕሬዘዳንታዊ ስርዓት ፀባይ አለው፡፡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እና በአፅፈፃሚው አካል መካከል ያለው ግንኙነት የሚዳኘው በምክር ቤቱ መርሕ መሆኑ በአሜሪካ ሕገ መንግሥት እንደሚታየው ዓይነት የሥልጣን ክፍፍልን እና የቁጥጥር መንገዶችን ይቀንሳል፡፡ ነገር ግን ከሌሎች የፓርላሜንታዊ ስርዓቶች በተለየ ሠራዊቱ እና የምኒስትሮች ምክር ቤት ተጠሪነታቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትልቅ ሥልጣን አለው፡፡ በተጨማሪም፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን በሕግ ማውጣት ሒደት ውስጥ የሚቆጣጠርበት መንገድ የለውም፡፡ ይህም ከሌሎች ባለሁለት ምክር ቤት ስርዓቶች አሠራር ጋር ይቃረናል፡፡ ከላይ እንደተገለጸው፣ ሕገ መንግሥቱ አደጋ ላይ በሆነ ግዜ ብቻ ነው የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ጣልቃ ገብቶ ውሳኔ የሚያሳልፈው፡፡ በዚህም ክልሎች በፌዴሬሽን ምክር ቤቱ በኩል ጠቅላላ የፌዴራል ድንጋጌዎችን የመምከር ወይም በፌዴራል ደረጃ ሕግጋትን የመጠቆም ምንም ዕድል የላቸውም፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴሬሽን ተቋማዊ መዋቅር ለተጠናከረ ማዕከላዊ የሥራ አስፈፃሚ አካል ቦታ የሚሰጥ ሲሆን የፌዴሬሽኑም ይሁን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ ማዕከላዊ የሥራ አስፈፃሚውን ለመቆጣጠር የሚያስችለው ተቋማዊ ሁኔታ አናሳ ነው፡፡

በብዙዎቹ የፌዴራል ስርዓቶች ውስጥ፣ ነጻ የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት ስላለ ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም እና ተለዋዋጭ ኩነቶች ጋር የማስማማት ሥራዎችን ያከናውናል፡፡ ገለልተኝነቱ የግድ አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም የፖለቲካ ኃይሎች እና ሁሉም የአገሪቱ ወገኖች ለማንም እንደማያደላ አውቀው ውሳኔውን እንዲቀበሉ ያደርጋል፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራል ስርዓት የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት ስለሌለው ከሌሎቹ ስርዓቶች ይለያል፡፡ በምትኩ፣ ሕገ መንግሥታዊው ጉዳይ ለፖለቲካው አካል፣ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ተትቷል (አንቀፅ 62)፡፡ በፍርድ ቤት የሚነሳ ማንኛውም አለመግባባት የሚታየው በፌዴሬሽን ምክር ቤት ሥር በ1988 በተቋቋመው የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ነው፡፡ ጉባዔው የተቋቋመው ከፖለቲካ እና የሕግ አካላት ተውጣጥቶ ነው፡- እነዚህም የፍርድ ቤቱ ፕሬዚደንት እና ምክትላቸው፣ ሦስት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተመረጡ ስድስት የሕግ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ጉባዔውም በመጨረሻ ለፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ጥቆማውን በመላክ ውሳኔ ያስገኝለታል (አንቀጥ 83)፡፡

ይህ የሚያመለክተው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ፈጣሪዎች በክልሎች መሐል የሚነሱ አለመግባባቶች በሕግ አግባብ ይፈታሉ ብለው የማያምኑ መሆኑን፣ ነገር ግን የሆነ ዓይነት ፖለቲካዊ መፍትሔ መኖር አለበት ብለው መገመታቸውን ነው፡፡ ይሁን እንጂ በተግባር፣ ምንም እንኳን ፍርድ ቤቶች በጥቅሉ ነጻ ቢሆኑም፣ የሕገ መንግሥት ትርጉም ሥራ ሥልጣን በተቆጣጠረው የፖለቲካ ፓርቲ እጅ ነው፡፡ የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ አባላትን ጨምሮ ዳኞች የሚሾሙት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው (አንቀፅ 81)፡፡ ነጻ የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት አለመኖሩ፣ የኢትዮጵያ ስርዓት መንግሥታዊ የሥልጣን ገደቦች ስለሚያጥሩት ለሕገ መንግሥታዊነት መርሖች ቁርጠኝነት እንዳይኖር ማድረጉን እንዲናገሩ ታዛቢዎችን አስገድዷቸዋል፡፡ ነገር ግን፣ ለምሳሌ፣ የኢትዮጵያን ስርዓተ ናሙና ከራሽያ ፌዴሬሽን ጋር ካወዳደርነው የኢትዮጵያ ስርዓት ቁጥጥር ማጣት በአንፃሩ የተሻለ ነው፡፡ የራሽያ ሕገ መንግሥት ለፕሬዚዳንቱ የሕግ ክለሳ እና በክልሎች እና በፌዴራል መንግሥቱ መካከል ያሉ አለመግባባቶችን የመገላገል ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ይህም ከፌዴራላዊ መርሖች ያፈነገጠ ነው፤ የማዕከሉ ባለሥልጣናት ለብቻቸው የፌዴራሉ አባላትን ሥልጣን መወሰን የለባቸውም፡፡

በፍቃዱ በሀይሉ

 

በየዓመቱ ከሰኔ ወር ጀምሮ በርካታ በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከተለያዩ ትምህርት ተቋማት ይመረቃሉ። ዘንድሮም በርካታ ተማሪዎች እየተመረቁ ናቸው፤ ገናም ይመረቃሉ። የተመራቂዎችን ቁጥር ማብዛቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ጥራት ያለው ተመራቂን ማፍራቱ ደግሞ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ የሚጠበቅ ቀዳሚው ተግባር ነው። ተቋማቱ በዚህ ጉዳይ በየጊዜው የሚወቀሱ ከመሆኑ አንጻር ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርገው ብዙ የተማረ የሰው ሃይልን አስተምረው ማስመረቃቸውን እርግጠኛ መሆን አለባቸው። በተለይ የመንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በየዓመቱ በሚቀርብ የኦዲት ሪፖርት የሀገር እና የህዝብ ሀብትን ያለአግባብ በማባከን ስማቸው ከሚነሳ ተቋማት ቀዳሚዎቹ ናቸው። ይሄንን ችግር መቅረፍ የሚቻለው ብቁ እና ለህዝብ ተቆርቋሪ የሆነ የተማረ ዜጋን በማፍራት መሆኑን አውቀው የበለጠ ሊተጉ ይገባል። ዛሬ ላይ አግበስብሶ ቢያስመርቁት ነገ ሌላ ችግር ፈጣሪ ሆኖ መገኘቱ ስለማይቀር ይሄን ያህል ቁጥር ያለው ተማሪ አስመረቅን ለማለት ከመሮጥ ይልቅ ጥራቱ ላይ ማተኮሩ የተሻለ ይሆናል።

                             

በስልክ የተሰጠ አስተያየት

ቁጥሮች

Wednesday, 11 July 2018 12:55

(በ2010 ዓ.ም)

170,578                       ከመንግሥት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመደበኛ እና መደበኛ ባልሆኑ መርሀግብሮች የሚመረቁ ተማሪዎች ብዛት፤

 

116,128                      በመደበኛ የሚመረቁ፤

 

54,450                        መደበኛ ባልሆኑ መርሀግብሮች የሚመረቁ፤

 

              ምንጭ፡- አዲስ ዘመን ጋዜጣ

 

ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ ባለፈው እሁድ ወደአሥመራ በማቅናት ሁለቱ አገራት ላለፉት 20 ዓመታት "ጦርነት አልባ፣ ሠላም አልባ" ግንኙነት መንጭቆ የሚያወጣ ታሪካዊ እርምጃ ወስደዋል። በኤርትራ በኩል ፕሬዚደንት ኢሳያይስ ጨምሮ ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ ለኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን ያደረገላቸው አቀባበል መቼም የሚረሳ አይደለም። የሁለቱ አገራት መሪዎች በወቅቱ የሚከተሉትን አምስት ነጥቦችን ያካተተ ስምምነት አድርገዋል።

1ኛ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል የነበረው ጦርነት ስለማብቃቱ፣

2ኛ ሁለቱ ሐገራት ጥብቅ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊ እና የደህንነት ትብብር እና ትስስር እንደሚመሰረት፣

3ኛ የንግድ፣ የኢኮኖሚ እና የዲፕሎማሲ ግንኙነቶች በሁለቱ ሐገራት መካከል እንደሚጀመር፣

4ኛ የድንበር ውሳኔው ተግባራዊ እንደሚሆን፣

5ኛ ሁለቱ ሐገራት በአካባቢው የፀጥታ ጉዳዮች ላይ በጋራ እንደሚሰሩ መስማማታቸውን ይፋ ሆኗል።

ይህ ስምምነት በተለይ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ሕዝቦች ለዓመታት በናፍቆት ሲጠብቁት የነበረ በመሆኑ አስደሳችና አርኪ ውሳኔ ነው። ለዚህ ስምምነት ተግባራዊነት የሁለቱ አገራት መሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ዜጎች የተናጠልና የጋራ ኃላፊነት አለባቸው። የእስከዛሬው ደም አፋሳሽ ጦርነት፣ ትንኮሳ፣ እልህ ላይመለስ ወደመቃብር እንዲወርድ ሁሉም ወገኖች በንቃት ሊንቀሳቀሱ ይገባል።

ሠላሙን ለማስቀጠል በጋራ መቆም የሚጠበቅብን ሠላም የማይፈልጉ ኃይሎች አፍራሽ እንቅስቃሴ ለመመከት ጭምር ነው። እነዚህ ኃይሎች “በቃችሁ” ማለት የሚቻለው የመሪዎቹ በጎ ተነሳሽነት በሕዝብ በበቂ ሁኔታ መደገፍና ለተግባራዊነቱ አብሮ መቆም ሲቻል ብቻ ነው።¾

የጠ/ሚ ዐብይ አሕመድ 100 ስኬታማ ቀናት በፎቶ

Page 1 of 226

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us