ገንዘብ ማግኘት የስኬት ምንጭ ነውን?

Wednesday, 03 December 2014 13:14

እውነተኛ ያልሆነ ስኬት ካገኘ ሰው ጨርሶ ያልተሳካለት ሰው ይሻላል። ምክንያቱም አንድ ነገር ሞክሮ ያልተሳካለት ሰው ሁኔታውን ለማስተካከል አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰድ ይችላል። ሌላው ቢቀር ከውድቀቱ ትምህርት የሚያገኝ ከመሆኑም ሌላ በሚቀጥለው ጊዜ ስህተቱን ላለመድገም ያለው ቁርጠኝነት ይጠናከራል።

እውነተኛ ያልሆነ ስኬት ግን ከዚህ ይለያል። አንተ ተሳክቶልኛል ብለህ ታስብ ይሆናል፤ እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው። ለውጥ ማድረግ እንደሚኖርብህ የምትገነዘበው ደግሞ ጊዜው ካለፈ በኋላ ሊሆን ይችላል።

አንድ ሰው ገንዘብብቻ አካብቶ ቢገኝ ስኬታማ ነው ይባላልን?ይህ ሐሳብ መላ ሕይወታቸውን ገንዘብንና ገንዘብ ሊገዛ የሚችላቸውን ነገሮች ለማሳደድ ባዋሉ ሰዎች ላይ ይሠራል፤ እነዚህ ሰዎች የሚያገኙት ስኬት፣ እውነተኛ ላልሆነ ስኬት እንደ ምሳሌ ሊጠቀስ ይችላል። አሜሪካዊው የሥራ መስክ ምርጫ አማካሪ የሆኑት ቶም ዴናም እንዲህ ብለዋል፦ “ነጋ ጠባ ስለ ሥራ እድገት፣ ተጨማሪ ገንዘብ ስለ ማግኘት ወይም ብዙ ንብረት ስለ ማካበት ብቻ ማሰብ እርካታን አያስገኝም። ስኬትን ከገንዘብ አንጻር ብቻ መለካት ብስለት እንደሌለን የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ የኋላ ኋላ የባዶነት ስሜት እንዲሰማን ያደርጋል።”

በአሁኑ ጊዜ ብዙ ሰዎች በዚህ እንደሚስማሙ መረጃዎች ያመለክታሉ። በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመለከተው “ለተሳካ ሕይወት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ” ተብለው ከተዘረዘሩ 22ነገሮች መካከል “ብዙ ገንዘብ ማግኘት” 20ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ጤንነት፣ ከሰዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት መመሥረት እና በሚወዱት የሥራ መስክ ላይ መሰማራት ግን መጀመሪያ አካባቢ ከተቀመጡት ነገሮች መካከል ይገኙበታል።

ከዚህ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው፣ ብዙ ሰዎች በሕይወታቸው ተግባራዊ ባያደርጉትም እንኳ እውነተኛ የሆነን ስኬት እውነተኛ ካልሆነው መለየት አይከብዳቸውም። ይበልጥ ከባድ የሚሆነው ግን ስለ ስኬት ትክክለኛ አመለካከት እንዳለን የሚያሳይ ውሳኔ ማድረግነው።

እውነተኛስኬትማግኘትየሚቻለውእንዴትነው?

ስኬት ጥቂት ዕድለኛ ሰዎች ብቻ የሚያገኙት ነገር እንደሆነ  ማሰብ  አያስፈልግም።ልጆች ከሕፃንነታቸው ጀምሮ የሚነገራቸው ስኬታማ የመሆን ሐሳብ ብዙ ጊዜ በአንዳንዶች ዘንድ እውን ስለማይሆን ውሎ አድሮ ለብስጭት ሊዳረጉ ይችላሉ።

እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ማንኛውም ሰው እውነተኛ ስኬት ሊያገኝ ይችላል፤ ይሁንና ጥረት ማድረግ ግን አለበት። መፅሐፉ “ገንዘብን የሚወድ፣ ገንዘብ አይበቃውም፤ ብልጽግናም የሚወድ፣ በትርፉ አይረካም።” እንዲል፤ -ይህ ምን ማለት ነው?ሀብትና ንብረትን በማካበት ላይ ያተኮረ ሕይወት እርካታ ለማግኘት ዋስትና አይሆንም። እንዲያውም ውጤቱ የተገላቢጦሽ ሊሆን ይችላል።

ዶክተር ጂን ትዌንጂ የተባለች አንዲት ጸሐፊጀነሬሽን ሚበተባለ መጽሐፏ ላይ እንዲህ ብላለች፦ “በሕይወታቸው ውስጥ ለገንዘብ ዋነኛ ቦታ የሚሰጡ ሰዎች ከሌሎች ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረትን ከፍ አድርገው ከሚመለከቱ ሰዎች ጋር ሲነጻጸሩ የበለጠ ጭንቀትና ውጥረት ይሰማቸዋል። ... በርካታ ጥናቶች ገንዘብ ደስታ ሊያስገኝ እንደማይችል አረጋግጠዋል፤ መሠረታዊ ነገሮችን ለማግኘት የሚበቃ ገቢ እስካላችሁ ድረስ የገቢያችሁ መጠን በሚኖራችሁ እርካታ ላይ ያን ያህል ለውጥ አይኖረውም።”

ሀብትና ንብረት ከማካበት የተሻለ እርካታ የሚያስገኝ ግብ ማውጣት ያስፈልጋል፡፡ ከፍ ያለ ቦታ ለማግኘት መቋመጥ እውነተኛ ስኬት ለማግኘት አይረዳም። እንዲያውምጉድ ቱ ግሬትየተባለው መጽሐፍ ለረጅም ጊዜ ስኬታማ ስለሆኑ የድርጅት ኃላፊዎች ሲናገር “ትሑት፣ ልታይ ልታይ የማይሉ እንዲሁም የተለየ ትኩረት እንዲሰጣቸው የማይፈልጉ ናቸው” ብሏል።

“በአንጻሩ ደግሞ ጥሩ የድርጅት ኃላፊ ሆነው ካልተገኙት ሰዎች መካከል ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት ራሳቸውን ከልክ በላይ ከፍ አድርገው ስለሚመለከቱ ለድርጅታቸው ውድቀት ወይም እድገት አለማግኘት ምክንያት ሆነዋል” ብሏል። ከዚህ የምንረዳው ራስን ከፍ አድርጎ መመልከት ከስኬት ይልቅ ውድቀትን ያስከትላል።

ለራስ ክብርና ማዕረግ ከመፈለግ ይልቅ ትሕትናን ማዳበር ያስፈልጋል። “አንድ ሰው ራሱን ከፍ አድርጎ የሚመለከትበት ምንም ነገር ሳይኖረው ራሱን ከፍ አድርጎ የሚመለከት ከሆነ ራሱን እያታለለ ነው።” ይህ ደግሞ ስኬት ሊባል አይችልም።

አንድ ሰው ጥሩ የሥራ ባሕል ካዳበረ ሥራውን ይበልጥ ይወደዋል። ዶክተር ማደሊን ለቫይንቲች ዩር ችልድረን ዌልበተባለ መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “በአንድ ነገር ስኬት እንዳገኘን የሚሰማን ያንን ነገር ጥሩ አድርገን ማከናወን ስንችል ነው፤ አንድን ነገር ጥሩ አድርጎ የመሥራት ችሎታ የሚገኘው ደግሞ በጥረትና ተስፋ ባለመቁረጥ ነው።” ይህ ደግሞ አልፎ አልፎ ባይሳካልህም እንኳ ሁኔታውን ተቋቁሞ ማለፍን ይጠይቃል።

በሥራህ የተዋጣልህ እንድትሆን በርትተህ ሥራ፤ እንዲሁም እንቅፋት ሲያጋጥምህ ተስፋ አትቁረጥ። ልጆች ካሉህ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በራሳቸው እንዲወጡ (ዕድሜያቸውንና አቅማቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት) አጋጣሚ ስጣቸው። የሚያጋጥማቸውን ችግር በሙሉ ጣልቃ ገብተህ ለመፍታት አትቸኩል። ልጆች በሕይወታቸው እውነተኛ እርካታ የሚኖራቸው እንዲሁም አዋቂ ሲሆኑ የሚጠቅማቸውን ሥልጠና የሚያገኙት ችግሮችን ተቋቁሞ የማለፍ ችሎታ ካዳበሩነው።

ራስህን ለማስተዳደር የምትሠራው ሥራ የሕይወትህ አንድ ክፍል እንጂ መላው ሕይወትህ መሆን የለበትም። እውነቱን ለመናገር፣ ጤንነትህን ወይም የቤተሰብህን አክብሮት አጥተህ በሥራህ ትልቅ ደረጃ ላይ ብትደርስ ስኬታማ እንደሆንክ ሊሰማህ ይችላል? ለሥራቸው፣ ለጤንነታቸውና ለቤተሰብ ሕይወታቸው ተገቢውን ቦታ የሚሰጡ ሰዎች እውነተኛ ስኬት ያገኛሉ።

ራስህን ተንከባከብ። በቂ እረፍት አድርግ። ጤንነትን፣ ቤተሰብንና ወዳጆችን ሠውቶ ሙሉ በሙሉ በሥራ በመጠመድ የሚገኘው ጥቅም ከንቱ ነው፤ ምክንያቱም ይህ እውነተኛ ያልሆነ ስኬትነው።

******               ******               *******

አለመግባባትንማስወገድ

ሁለት ሰዎች በመካከላቸው አለመግባባት ሲፈጠር ብዙውን ጊዜ በንዴት ይጦፋሉ፤ እንዲሁም አንዱ ሌላውን ሊወነጅል ይችላል። ይህን ሁኔታ ለማስተካከል እርምጃ ካልወሰዱ ጓደኝነታቸው ሊያከትም ይችላል።

አንተም ተመሳሳይ ሁኔታ አጋጥሞህ የሚያውቅ ከሆነ ሁኔታው እንዳላስደሰተህ ግልጽ ነው! በእርግጥ፣ አብዛኞቻችን ከወዳጆቻችንና ከጎረቤቶቻችን ጋር በሠላምና በስምምነት መኖር እንፈልጋለን። ይሁንና አልፎ አልፎ አለመግባባት ቢፈጠርስ? በውስጣችን ያሉትን መጥፎ ባሕርያት ማሸነፍና ስሜታችንን የጎዳንን ሰው ይቅር ማለት እንችላለን? የተፈጠረውን አለመግባባት ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፍታትስ እንችላለን?

ነገሮችን ምክንያታዊ በሆነ መንገድ መመልከትና የተፈጠረውን አለመግባባት በሠላም መፍታት፤ አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜ ወዳጅነት እንዳይፈርስ ብቻ ሳይሆን ከተፈጠረው ችግር በኋላም ወዳጅነቱ ይበልጥ እንዲጠናከር የሚረዱ ጠቃሚ መመሪያዎችን መከተላቸውያስፈልጋል።

የጠብ መንስኤዎች ውስብስብና የተለያዩ ናቸው፤ በተጨማሪም ሰላም ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት በጎ ምላሽ የሚሰጠው ሁሉም ሰው አይደለም። በመሆኑም ሐይማኖታዊው አስተምህሮት ”ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖርበእናንተ በኩልየተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ” የሚል እውነታውን ያገናዘበ ምክር ይሰጣል።

ከአንዳንዶች ተሞክሮ የምንረዳው አስተዳደግ ከፍተኛ ተፅእኖ ማሳደሩን ነው አሜሪካዊው ሮበርት፤-”ያደግሁት ደስታ በራቀው ቤተሰብ ውስጥ ነው። አባቴ ግልፍተኛ ስለነበር ብዙውን ጊዜ ይደበድበኝ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ደም በደም ሆኜ ራሴን እስክስት ድረስ ይደበድበኛል። በመሆኑም እኔም እያደር ይበልጥ ግልፍተኛና ዓመፀኛ ሆንኩ።

በአሥራዎቹ ዕድሜ ሳለሁ በፀባይ ማረሚያ ውስጥ ሁለት ዓመታት አሳልፌያለሁ። በኋላም ከባድ ወንጀል በመፈጸሜ ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግበት እስር ቤት ገባሁ። ከእስር ቤት ስለቀቅ ሕይወትን እንደ አዲስ ለመጀመር በማሰብ ወደ አውስትራሊያ ሄድኩ።

ፀባዬን ለመለወጥ የረዳኝ ወደዚያ መሄዴ ሳይሆን የራሴ ውሳኔ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የግልፍተኝነት ባሕሪዬን መቆጣጠር በጣም ከባድ ሆኖብኝ ነበር፤ በዚህም ምክንያት ብዙውን ጊዜ የተስፋ መቁረጥና የዋጋ ቢስነት ስሜት ይሰማኝ ነበር። ቀስ በቀስ ከአንድ ሰው ስሜት፣ ንግግር ወይም ድርጊት በስተ ጀርባ ያለው ምን እንደሆነ ማሰብ ጀመርኩ። በዚህም የተነሳ ይበልጥ የሰው ችግር የሚገባኝ፣ ታጋሽና ይቅር ባይ እየሆንኩ መጣሁ”። ሲል ይናገራል፡፡

    ከዚህ ሁሉ እሳቤ ጀርባ ሰዎች በድንገት ሀሳባቸውን ለውጠው ተቆጪየሚሆኑበት ወቅት ይከሰታል፡፡ ይህ ሁኔታ ሲያጋጥም አእምሮን ማረጋጋት እንደሚያስልግ የስነልቦና ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡

ይምረጡ
(39 ሰዎች መርጠዋል)
4682 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 179 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us