ራስን የማጥፋት ፍላጎት መንስዔ

Wednesday, 17 December 2014 11:52

ራስን የማጥፋት ሁኔታ በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት የሚችል ችግር ሲሆን በአብዛኛው ሰዎች ከቁጥጥራቸው ውጪ የሆነ የተስፋ መቁረጥ ጥግና የኑሮ መጨለም በሚጋጥማቸው ጊዜ የሚከተል ችግር ነው። አንዳንዴም ከሰዎች መገለልንና መበደልን ለማስቆም ብሎም በሌሎች ዘንድ ትኩረት ለማግኘት የሚደረግ ሙከራም ይሆናል። ከልብ ባይደረግም እንደማስፈራሪያ መንገድም ነው ማለት ነው። ራስን ማጥፋት የሚለው ሃሳብ ሶስት አይነት ሁኔታዎችን ያቀፈ ሲሆን፡-

 1.     የራስ ማጥፋት ሃሳብ /ሙከራ /Suicide gesture/ ራስን የማጥፋት ውጥኑና ሙከራው ለጉዳትና ለሞት የማይዳርግ ሆኖ ሲገኝ፣
 2.      ራስን የማጥፋት ሙከራ /Suicide attempt/ ራስን የማጥፋት ፍላጎቱም ሆነ ውጥኑ ጠንካራና ለሞት የሚዳርግ ሆኖ ሳለ በተለያዩ ምክንያቶች ሳይሳካ ሲቀር፣
 3. ራስን ማጥፋት /completed suicide/ ራስን የማጥፋት ሙከራ ሲሳካና ለሞት ሲዳርግ ናቸው።

በመሠረቱ በራስ ማጥፋት ላይ የተሰሩ ጥናቶች በዋነኝነት የተመሰረቱት የሞት የምክስር ወረቀት በማየት እንደመሆኑ መጠን የእውነተኛው ቁጥር ጥናቶች ከሚያመላክቷቸው የበለጠ እንደሆነ ይታወቃል። በአጠቃላይ በአለማችን ውስጥ ያለውን ሁኔታ ስንመለከተው ራስን ማጥፋት ከመጀመሪያዎቹ አስር ሞት የሚያስከትሉ ሁኔታዎች ውስጥ ሲመደብ በወጣቶችና በጎልማሶች ላይ ደግሞ የሁለተኛን ቦታ ይዟል። በተጨማሪም 30 በመቶ የሚሆነው በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውስጥ የሚከሰተው ሞት እና 10 በመቶ የሚሆነው ከ25-34 ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሰዎች ሞት የሚከተለው በዚህ ራስን በማጥፋት ሳቢያ ነው። 70 በመቶ የሚሆኑ ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች ከ40 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች ሲሆኑ በተለይ ከ60 ዓመት በላይ ባሉ ወንዶች ላይ ይህ ቁጥር እጅግ እየጨመረ ይሄዳል። ነገር ግን የራስ ማጥፋት ሙከራ ከ30 ዓመት በታች ባሉ ሰዎች ላይ በዝቶ ይታይ እንጂ የመሳካቱ ሁኔታ አሁንም ቢሆን ከሌላው የእድሜ ክልል ያነሰ ሆኖ ይገኛል።

በተለያዩ የማህበረሰብ ክፍል ውስጥ ያሉ ሁኔታዎችን ስንመለከት

-    የራስ ማጥፋት ሙከራን ሴቶች ከወንዶች ይልቅ በሦስት እጥፍ በበለጠ ሲሞክሩ የመሳካቱ ሁኔታ ግን በወንዶች ላይ በአራት እጥፍ ከሴቶች በልጦ ይገኛል።

-    የራስ ማጥፋት ባላገቡ፣ በተፋቱ እንዲሁም ባለቤታቸው በሞት በተለየባቸው ሰዎች ላይ የበለጠ ሆኖ ይገኛል።

-    የከተማ ነዋሪዎች ከገጠር ነዋሪዎች የበለጠ ራሳቸውን የማጥፋት ሁኔታ ይታይባቸዋል። በቤተሰብ ውስጥ ራስን የማጥፋት ሙከራ ወይም ስኬት የኖረ እንደሆነ ይህ ሁኔታ በሌሎች የቤተሰብ አካል ውስጥ የመደገም ዕድሉ ከፍ ያለ ነው።

-    የጥቁር ዘር ያላቸው ሰዎች ራሳቸውን የማጥፋት ቁጥር ከነጮች ያነሰ ይሁን እንጂ የጥቁሮችም የራስ ማጥፋት ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።

-    አብዛኛው በእስር ቤት ውስጥ ያሉ በተለይ ጥፋት ያላጠፉ ሰዎች ራሳቸውን የማጥፋት ዕድላቸው ከፍ ያለ ነው።

-    ከአብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ውስጥ በጦር ሠራዊት ውስጥ ያሉ ሰዎች፣ የህግ ባለሙያዎችና ሐኪሞች/በተለይም ሴቶች ሐኪሞች/ ራሳቸውን የማጥፋት እድላቸው ከፍ ያለ ነው።

ሰዎች ራሳቸውን ለምን ያጠፋሉ?

በአብዛኛው ሰዎች ራሳቸውን ለማጥፋት የሚወስኑበት ምክንያት አንድና ውሱን ሳይሆን የተደራረበ ችግር በሚፈጠርበት ወቅት ነው። ከተለያዩ ምክንያቶች ውስጥም ጥቂቶቹን ስንመለከት፡-

-    የስነ አእምሮ ችግር ያለባቸው ሰዎች በተለይም ከፍተኛ ድብርትና ስኪዞፍሬኒያ ያለባቸው ሰዎች ለዚህ ሁኔታ የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍ ያለ ነው። የተለያዩ የስነ አዕምሮ ችግሮች በተጓዳኝ ወይም በተጨማሪ ድብርትን ያስከትሉ እንደሆነ ለዚህ ችግር የተጋለጡ ይሆናሉ ማለት ነው። ስኪዞፍሬንያ ያለባቸውን ሰዎች ለምሳሌ ስንመለከት ራስን የማጥፋት አላማቸው ጠንካራ እንደመሆኑ መጠን በአብዛኛው ጊዜ ሲሳካላቸው ይታያል።

-    የተለያየ የሱስ ተገዢ የሆኑ ሰዎች ራስን ለማጥፋት የበለጠ የተጋለጡ ናቸው። አብዛኛው ሱስ ሊያስከትሉ የሚችሉ ነገሮች በተለይም አልኮልንና አደንዛዥ ዕፆችን ስንመለከት ድብርት የማስከተልና በሌላም በኩል ደግሞ የመደፋፈር እንዲሁም የጀግንነት ስሜት ስለሚያስከትሉ ራስን ለማጥፋት ሙከራ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አላቸው።

-    የተለያዩ የማህበረሰብ ችግር ያለባቸው ሰዎች ማለትም ሐዘን ያጋጠማቸው፣ የቅርብ ሰው በሞት የተለያቸው፣ ገንዘብ ማጣት፣ ከቅርብ ሰው ጋር መለየት፣ የብቸኝነት ኑሮ እንዲሁም የመሳሰሉት ሁኔታዎች ለዚህ ችግር ሊዳርጉ ይችላሉ።

-    የስነ ባህሪይ ችግር ያለባቸውን ሰዎች ስንመለከት በአብዛኛው ጊዜ በቶሎ የሚናደዱና ትዕግስት የሌላቸው ሰዎች፣ የንዴታቸው መገለጫ የተጋነነ የሆኑ ሰዎች፣ ጭንቀት የመቀበልም ሆነ መፍትሄ የመፈለግ ባህሪያቸው ደካማ የሆኑ ሰዎች፣ እንዲሁም ስሜታቸውን መቆጣጠር የማይችሉ ሰዎች ለዚህ ሁኔታ የተጋለጡ ይሆናሉ። እነዚህ አይነት ሰዎች በተጨማሪ አልኮል የመጠጣት፣ የአደንዛዥ ዕፅ የመጠቀምና ህገወጥ ስራ የመስራት እድላቸው ከፍ ያለ እንደመሆኑ ከዚህ ሁኔታ በተጋነነ መልኩ ይጋለጣሉ ማለት ነው።

በአብዛኛው ጊዜ ሰዎች ራሳቸውን ለማጥፋት የሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች እንደ ፀባይ፣ ባህል፣ ለአጋጣሚው የሚዳርጉ መንገዶች መኖር ወይ አለመኖር፣ የመሳሰሉት ሁኔታዎች ይለያያሉ። በጥቅሉ ግን ስንመለከት ወንዶች በብዛት የሚጠቀሙበት መንገድ ኃይለኛና ቁርጠኝነት የተሞላበትን እርምጃዎች የመውሰድ ባህል ሲኖራቸው፣ ሴቶች ደግሞ መለስ ያለ መንገዶችን ይጠቀማሉ። ይህንን ስንል ለምሳሌ ወንዶች ራሳቸውን በሽጉጥ በመተኮስ፣ በገመድ አንገታቸውን በማነቅ እንዲሁም ከፍተኛ ከሆነ ፎቅ ላይ ራስን በመወርወር የመሳሰሉትን መንገዶች ሲጠቀሙ፣ ሴቶች ደግሞ መድሃኒት መውሰድና ራሳቸውን በጋዝ በማፈን የመሳሰሉ መንገዶችን ይጠቀማሉ። በአጠቃላይ ሰዎች ራሳቸውን ለማጥፋት የእውነት ሲፈልጉና ሰዎችን ብቻ የማስፈራራትና ሰውን ትኩረት ወደ እነሱ ለማድረግ በመሞከር ራስን የማጥፋት ሙከራ ሲያደርጉ የሚጠቀሙባቸው መንገዶች የተለያዩ ናቸው። በአንዳንድ ሁኔታም ከአንድ በላይ መንገዶችን በመጠቀም የነገሩን መፈፀም የበለጠ እርግጠኛ የሚያደርጋቸውን መንገዶች ይጠቀማሉ። ለምሳሌ ደብዳቤ ጽፎና ምክንያቱን አስረድቶ ድርጊቱን ለመፈፀም ሙከራ ማድረግ።

እንደመፍትሄ፣

አንድ ሰው ማንኛውም አይነት ከላይ የተጠቀሱት ራስን የማጥፋት ሙከራ ለማድረግ የሚገፋፋ ስሜትና ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ሲገኝ ለነገሩ መፍትሄ ለመሻት ከመሞከርም በላይ የስነ አዕምሮ ሐኪም ጋር በመውሰድ /በመሄድ/ አስፈላጊውን የምክር አገልግሎት መውሰድ ተገቢ ነው።

ራስን የማጥፋት ሙከራም ያደረገን ሰው በመጀመሪያ ደረጃ እንደየአስፈላጊነቱ ወደ ህክምና ማዕከል በመውሰድ የድንገተኛም ሆነ ሌላ የህክምና አገልግሎት ካገኘ በኋላ ወደ የስነ አዕምሮ ሐኪም መውሰድ ግድ ይላል። ማንኛውም ሰው ራስን የማጥፋት ሙከራ አንድ ጊዜ ካደረገና ካልተሳካለት የመደገም ዕድሉ ከፍተኛ እንደመሆኑ መጠን ችላ ሳይሉ አስፈላጊውን ክትትልና እርምጃ መውሰድ ተገቢ ነው።

                     ከመረጃ መረብ ተወስዶ የተስተካከለ

ይምረጡ
(16 ሰዎች መርጠዋል)
4172 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

 • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

 • Aaddvrrt5.jpg
 • adverts4.jpg
 • Advertt1.jpg
 • Advertt2.jpg
 • Advrrtt.jpg
 • Advverttt.jpg
 • Advvrt1.jpg
 • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1018 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us