ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)

ለሁለት አስር አመታት ተቋርጦ የነበረውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደገና የጀመሩት ኢትዮጵያና ኤርትራ ብሔራዊ ቡድኖች የወዳጅነት ጨዋታ እንደሚያደርጉ ታውቋል። የፋሲል ከተማ እግር ኳስ ክለብ የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱ ይታወሳል። የትግራይ ክልል ስፖርት ቢሮም ተመሳሳይ የወዳጅነት ጥያቄ ማቅረቡ ተሰምቷል።

በቅርቡ አሰልጣኝ አብርሀም መብራህቱን የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አድርጎ የሾመው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለኤርትራ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ያቀረበው የወዳጅነት ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቷል። የጨዋታው የሚካሄድበት ጊዜ በትክክል ባይገለጽም በነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ እንደሚሆን ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከሴራሊዮን ጋር የሚጫወት ሲሆን፣ ከኤርትራ ጋር የሚያደርገው የወዳጅነት ጨዋታ ብቻ አቋም መፈተሻ አይሆነውም። ከሌላ ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ጋር የወዳጅነት ጨዋታ በማድረግ ለሴራሊዮን ጨዋታ መዘጋጀት ይጠበቅበታል።

በተመሳሳይ ዜና የፋሲል ከተማ እግር ኳስ ክለብ የኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት እንደገና መጀመሩ ጋር በተያያዘ የወዳጅት ጨዋታ ጥያቄ በማቅረብ ቀዳሚ መሆኑ ይታወሳል። ክለቡ ለኤርትራ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን፤ መቼ፣ ከየትኛው ክለብ ጋር እንደሚጫወት ግን እስካሁን አልታወቀም።¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)

- ቼልሲ ብራዚላዊውን የክንፍ መስመር ተጫዋች ዊሊያንን ለመሸጥ ከተለያዩ ክለቦች የቀረቡለትን ጥያቄዎቸ ውድቅ እያደረገ ነው። ሰሞኑንም ከባርሴሎና የቀረበለትን 55 ሚሊዮን ፓውንድ የዝውውር ሒሳብ በቂ አይደለም ብሎ መመለሱ ተዘግቧል። የስፔኑ ሀያል ክለብ ገንዘቡን የሚጨምር ከሆነ ተጫዋቹን ለመሸጥ መዘጋጀቱን ስካይ ስፖርት ዘግቧል።

- በአዲስ አሰልጣኝ በፕሪሚየር ሊጉ የሚፎካከረው አርሴናል ቡድኑን በአዳዲስ ተጫዋቾችን ለማጠናከር በዝውውር ስራ ላይ ተጠምዷል። ክለቡ የተሳካ የግብ ጠባቂ ዝውውር ካከናወነ በኋላ ፈረንሳዊውን አማካይ ተጫዋች ስቴቨን ንዞንዚን ለማስፈረም እየተደራደረ ነው። ከፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ጋር የአለም ዋንጫን ያነሳውን የ29 አመቱ ተጫዋችን ወደ ኢምሬትስ ለማምጣት የተጠየቀውን የ35 ሚሊዮን ፓውንድ ክፍያ በመፈጸም ይኖርበታል።

- የማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ጆሴ ሞውሪንሆ አንቶኒዮ ማርሻል በክለቡ እንዲቆይ አይፈልጉም። አሰልጣኙ የ22 አመቱን ተጫዋች በ50 ሚሊዮን ፓውንድ ለመሸጥ ተዘጋጅተዋል። ተጫዋቹን ለመሸጥም ከእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ውጪ ያሉ ክለቦችን ጥያቄ በማስተናገድ ላይ መሆናቸውን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል።

- ዘንድሮ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግን በድጋሚ የተቀላቀለው ፉልሀም ስናዊው ግብ ጠባቂን ከቱርኩ ቤሽኪታሽ ክለብ ማዛወሩ ተረጋግጧል። ክለቡ የ30 አመቱን ግብ ጠባቂ በ5 ሚሊዮን ፓውንድ ወደ እንግሊዝ ማዛወሩን የስካይ ስፖርት ዘገባ ያመለክታል።

- ክርስቲያኖ ሮናልዶን ለጁቬንቱስ አሳልፎ የሰጠው ሪያል ማድሪድ አሜሪካዊውን የቦሩስያ ዶርትሙንድ አማካይ ተጫዋች ክርስቲያን ፑልሲችን ለማስፈረም ድርድር መጀመሩ ተሰምቷል። የ19 አመቱ አማካይ ተጫዋች በበርካታ የአለማችን ስመ ጥር ክለቦች ተፈላጊ አድርጎታል። ክለቡ ተጫዋቹን ለመሸጥ ያስቀመጠውን 60 ሚሊዮን ፓውንድ ተመን ለመድፈር የሚችለውም የስፔኑ ክለብ ማድሪድ ይመስላል።¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)

የቀድሞው የአርሴናል ክለብ እና የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ኮከብ ተጫዋች ቴሪ ዳንኤል ሄንሪ ከአስቶን ቪላ ጋር በድጋሚ ወደ እንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ለመመለስ መስማማቱ ታውቋል። አስቶንቪላን በአሰልጣኝነት የያዙት ስቲቭ ብሩስ ከክለቡ በይፋ ባይሰናበቱም ሄንሪ በቀጣዩ የፕሪሚየር ሊግ ፉክክር ክለቡን በአሰልጣኝነት ይዞ እንደሚቀርብ በስፋት እየተነገረ ነው።

የክለቡ ባለቤትነት ድርሻ ያላቸው ባለሀብቶች ግን በፕሪሚየር ሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ ለመሆን ሄንሪ ትክክለኛ ምርጫ ስለመሆኑ እርግጠኛ መሆን አልቻሉም።

የ40 አመቱ አሰልጣኝ ሄንሪ ከአስቶንቪላ የቀረበለትን ጥያቄ ተቀብሎ ወደ ፕሪሚየር ለመመለስ መስማማቱ ነው የተዘገበው። ከክለቡ ጋርም በደሞዝና በሌሎች የስራ ኃላፊነቶች በቃል ደረጃ መስማማታቸውን ዴይሊ ስታር ጋዜጣ አስነብቧል።

በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ከአርሴናል ጋር ስኬታማ ጊዜን ያሳለፈው ቴሪ ዳንኤል ሄንሪ በ2018 የሩስያው አለም ዋንጫ ከቤልጂየም ብሔራዊ ቡድንን በምክትል አሰልጣኝነት ይዞ መቅረቡ ይታወሳል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)

ድሬደዋ ከተማን በተጫዋችን ያገለገለው ስምኦን አባይ በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የትውልድ ከተማውን ቡድን በምክትልና ዋና አሰልጣኝነትም ማገልገል ችሏል። በቀጣይ አመት ከክለቡ ጋር የሚኖረው ቆይታ ግን አልተረጋገጠም።

ስምኦን ከታናሽ ወንድሙ ጋር የቀድሞው የመብራት ሀይል ክለብን በተጫዋችነት ማገልገሉ የሚታወስ ሲሆን በአሰልጣኝነት ሙያ ከድሬደዋ ከተማ ክለብ ጋር በምክትል አሰልጣኝነት ወደ ፕሪሚየር ሊጉ መምጣቱ ይታወሳል። ክለቡ በመጀመረያው ዙር ደካማ ውጤት ከማስመዝገቡ ጋር በተያያዘ ዋና አሰልጣኙን ዘላለም ሽፈራውን በማሰናበት ምክትሉ የነበረውን ስምኦንን ላይ ከፍተኛ ሀላፊነት ተጥሎበት ነበር።

አሰልጣኝ ስምኦን ድሬደዋ ከተማ ከተጋረጠበት የመውረድ ስጋት ለማትረፍ እስከመጨረሻው የሊጉ ጨዋታ ድረስ ለመታገል ተገዷል። በመጨረሻ ጨዋታውም ወልዋሎ አዲግራትን አሸንፎ ከመውርድ መትረፉ ይታወሳል። ሊጉንም   ደረጃ ይዞ አጠናቋል።

ድሬደዋ ከተማን ከመውረድ ስጋት ያተረፈው አሰልጣኝ ስምኦን ከክለቡ ጋር በዋና አሰልጣኝነት እንደማይቀጥል ታውቋል። አሰልጣኙ ከክለቡ ጋር በቀድሞ ሀላፊነቱ በምክትል አሰልጣኝነት የመቀጠሉ ነገር አጠራጣሪ ሆኗል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)

ከሐዋሳ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ጋር ያለፉትን ሁለት አመታት ያሳለፈው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ወደ ፋሲል ከተማ አቅንቷል። በ2003 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ቡና ጋር የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ያነሳው አሰልጣኝ ውበቱ፤ ከጎንደሩ ክለብ ከፋሲል ከተማ የዘንድሮውን የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 7ኛ ደረጃን በመያዝ ነበር ያጠናቀቀው።

ፋሲል ከተማ እግር ኳስ ክለብ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ኢትዮጵያ ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተገለጸው ከሆነ ክለቡ የጀመረውን የለውጥ ጉዞ ለማራመድ አሰልጣኝ ውበቱ አባተን መቅጠር አስፈላጊ ሆኗል። ቡድኑ በፕሪሚየር ሊጉ ጠንካራ የዋንጫ ተፎካከሪ ለማድረግ እንሚሰራም ነው ያስታወቀው።

‹‹ፋሲል ከተማ ስፖርት ክለብ›› በሚል መጠሪያ እንደሚጠራ የክለቡ አመራሮች ተናግረዋል። የክለቡን አደረጃጀት ዘመናዊ ለማድረግም በቀጣይ ጊዜያት የተለያዩ ባለሞያዎችን እንደሚቀጠሩም አስታውቋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን በሩዋንዳ አስተናጋጅነት እየተካሔደ በሚገኘው የሴካፋ የሴቶች ዋንጫ ላይ እየተፎካከሩ ነው።

በአሰልጣኝ ሰላም ዘርአይ የሚመራው የሉሲዎቹ ስብስብ ከኡጋንዳ ጋር ባደረገው በመጀመሪያ ጨዋታው የ2ለ1 ሽንፈት ገጥሞት ነበር። በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ በአምበሏ ብርትኳን ገብረክርስቶስ ግብ 1ለ0 እየመሩ የነበረ ቢሆንም ከእረፍት መልስ ባስተናገዱት ሁለት ግቦች ሽንፈትን አስተናግደዋል።

ሉሲዎቹ በመጀመሪያ ጨዋታ የገጠማቸውን ሽንፈት በመርሳት ሰኞ እለት ከአስተናጋጇ ሀገር ጋር ባደረጉት በሁለተኛ ጨዋታቸው የ3ለ0 ድል አስመዝግበዋል። ለቡድኑ የተመዘገቡት ግቦችን ሶስት የተለያዩ ተጫዋቾች ናቸው። ከእረፍት በፊት በ31ኛው ደቂቃ መሰሉ አበራ ለቡድኗ የመጀመሪያውን ግብ ስታስቆጥር፤ በሁለተኛው አጋማሽ በ62ኛው ደቂቃ አለምነሽ ገረመው ስታስቆጥር፤ ሶስተኛውን ግብ ደግሞ ሰናፍ ዋኩማ በ76ኛው ደቂቃ አስመዝግባለች።

በሜዳቸውና በደጋፊያቸው ፊት የተጫወቱትን የሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን መርታታቸው ለቀጣይ ጨዋታቸው በጥሩ ስነ ልቦና ለመዘጋጀት የሚረዳቸው ይሆናል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)

 

የመካከለኛና ረጅም ርቀት ሯጩ ቀነኒሳ በቀለ በዘንድሮው የአምስተርዳም ማራቶን ላይ እንደሚወዳደር አዘጋጆቹ አስታውቀዋል። አትሌቱ የቦታውን ክብረወሰን እንደሚያሻሻልም ይጠበቃል።

በአለምአቀፉ የአትሌቲክስ ማህበር የወርቅ ደረጃ የተሰጠው የአምስተርዳም ማራቶን ከሁለት ወር በኋላ ይካሔዳል። በውድድሩ ላይ ከሚሳተፉ የአለማችን ስመ ጥር አትሌቶች መካከልም ኢትዮጵያዊው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ አንዱ ነው።

ቀነኒሳ በ2016 የበበርሊን ማራቶንን ሲያሸንፍ ያስመዘገበው 2፡03፡03 በማራቶን ሁለተኛው ፈጣን ሰአት ባለቤት አድርጎታል። የርቀቱን የአለም ክብረወሰን በኬንያዊው ዴኒስ ኪሜቶ 2፡02፡57 መመዝገቡ ይታወሳል። በዘንድሮው የአምስተርዳም ማራቶን ክብረወሰኑ እንደሚሻሻል ባይጠበቅም የቦታው ክብረወሰን ሊሰበር እንደሚችል ተገምቷል። የቦታው ክብረወሰን 2፡05፡09 በኬንያዊው ላውረንስ ቼሬኖ የተመዘገበ ሲሆን፤ ዘንድሮ ሰአቱ በቀነኒሳ በቀለ ሊሻሻል እንደሚችል ተገምቷል።

ቀነኒሳ ለመጀመሪያ ጊዜ በኔዘርላንድ ምድር የሚያደርገውን የማራቶን ፉክክር እንደሚያሸንፍና ፈጣን ሰአት እንደሚያስመዘግብ ይጠበቃል። ኢትዮጵያዊው አትሌት በውድድሩ በመሳተፉ ብቻ ደስተኛ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

‹‹ቀነኒሳ ከአለማችን ምርጥ ሯጮች አንዱ ነው። ይህ የአለማችን ድንቅ ሯጭ በአምስተርዳም ማራቶን ለመሳተፍ ፈቃደኛ ስለሆነ እጅጉን ኮርተናል በማለት የውድድሩ ዳይሬክተር ሲስ ፕሮንክ መናገራቸውን የአለም አቀፉ አትሌቲክስ ማህበር ድረገጽ ዘግቧል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)

 

ጅማ አባጅፋር የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን በተቀላቀለበት የመጀመሪያ አመት ዋንጫውን በማንሳት አስገራሚ ታሪክ ሲያስመዘግብ፤ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ደጋፊዎች ደግሞ ውጤቱን በመቃወም ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከ1995 ዓ.ም በኋላ እስከመጨረሻው ሳምንት መርሀ ግብር ድረስ አሸናፊው ያልተለየበት ነበር። በተለይም ደግሞ በተመሳሳይ ነጥብና ደረጃ ላይ የሚገኙት የሊጉን ዋንጫ በማንሳት ክብረወሰኑን የያዘው ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ዘንድሮ ሊጉን የተቀላቀለው ጅማ አባጅፋር ፉክክር ትኩረት የሚስብ ክስተት ነበር። ሁለቱ ክለቦች አሸናፊነታቸው የሚረጋገጠው በግብ ልዩነት በመሆኑ በመጨረሻው ሳምንት የሊጉ መርሀ ግብር የሚያስመዘግቡት ውጤት በጉጉት ሲጠበቅ ቆይቷል።

ሰኞ እለትም ሁለቱ ክለቦች በተመሳሳይ ሰአት ያደረጉትን ጨዋታ አሸንፈው እኩል ነጥብ አስመዝግበዋል። ጅማ አባጅፋር በሜዳው አዳማ ከነማን 5ለ0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት ሲረታ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ በአዲስ አበባ ስታዲየም ሐዋሳ ከተማን 2ለ0 አሸንፏል። ውጤቱ ሁለቱን የዋንጫ ተፎካካሪ ክለቦች እኩል 55 ነጥብ እንዲይዙ ቢያደርጋቸውም፤ ጅማ አባጅፋር በ3 የግብ ልዩነት ብልጫ በመያዙ የሊጉን ዋንጫ ለማሸነፍ ችሏል።

በቀድሞው የመከላከያ አሰልጣኝ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቂ ገብረመድህን ሀይሌ የሚመራው ጅማ አባጅፋር ፕሪሚየር ሊጉን በተቀላቀለበት በዘንድሮው አመት ዋንጫ ማንሳቱ ክስተት አስብሎታል። ክለቡ የሊጉ አሸናፊ በመሆኑ በቀጣዩ አመት በአህጉራዊው በካፍ ሻምፒየንስ ሊግ የሚካፈል ይሆናል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የቅዱስ ጊዮርስ ክለብ ደጋፊዎች በጅማ አባጅፋር አሸናፊነት ላይ ቅሬታ አሰምተዋል። ደጋፊዎቹ ጅማ አባጅፋር በመጨረሻው ጨዋታ አዳማ ከተማን 5ለ0 አሸንፎ ዋንጫ የወሰደበት መንገድ ፍትሀዊ ነው ብለው አያምኑም። ይልቁንም ክለቡ ዋንጫ እንዲያነሳ ከፌዴሬሽን አመራሮች ከፍተኛ ድጋፍ እንደተደረገለት ነው የሚናገሩት። በተለይም ደግሞ በቅርቡ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት አቶ ኢሳያስ ጅራ ከጅማ መሆናቸውን በመጥቀስ የከተማቸው ክለብ ዋንጫ እንዲያነሳ ከፍተኛ ጫና መፍጠራቸውን ይጠቅሳሉ።

ሰኞ እለት በአዲስ አበባ ስታዲየም ታድመው በነበሩት ፕሬዝዳንቱ ላይም ደጋፊው ከፍተኛ ተቃውሞ እና ስድብ ሲያወርድባቸው ነበር። የተወሰኑ ደጋፊዎችም ጥቃት ለመሰንዘር ሞክረዋል። ይሁንና የፌዴራል ፖሊሶች ባደረጉት ጥበቃ ፕሬዝዳንቱ አካለዊ ጥቃት ሳይደርስባቸው ከስታዲየሙ መውጣታቸው ታውቋል።

ጅማ አባጅፋር አዳማ ከተማን 5 ለ 0 ባሸነፈበት ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለት ግቦችን ነበር ያስቆጠረው። ናይጄሪያዊው አጥቂ ኦኪኪ ኦፎላቢ በ9ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ግብ ጅማ አባጅፋርን መሪ ስታደርግ፤ ተመስገን ገብረኪዳን በ35ኛው ደቂቃ ሁለተኛዋን ግብ አስቆጥሯል።

ከእረፍት መልስም የጅማ አባጅፋር የፊት መስመር ተጫዋች ኦኪኪ ኦፎላቢ በ59ኛው እና በ66ኛው ደቂቃ ያስቆጠራቸው ሁለት ግቦች ቡድኑ የ4ለ0 መሪነት እንዲይዝ አስችለዋል። ናይጄሪያዊው አጥቂ በ82ኛው ደቂቃ ላይ ለራሱ አራተኛ ግብ አስቆጥሮ ጅማን 5 ለ 0 እንዲያሸንፍ አድርጋለች።

ጅማ አባጅፋር በዚህ ዓመት ሊጉን ሲቀላቀል በከፍተኛ ሊጉ ይጠራበት የነበረውን “ጅማ ከተማ” የሚለውን ስሙንና ወደፕሪሚየር ሊጉ ያሳደጉት አሰልጣኙን በአዲስ ተክቶ ነበር ውድድሩን የጀመረው። በመጀመሪያዎቹ ሳምንታትም በገጠመው የውጤት ቀውስ አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ትችት በርክቶባቸው የነበረ ሲሆን፤ በተለይ አሰልጣኝ ገብረመድህን ከዓመት በፊት ሌላኛውን የጅማ ክለብ “ጅማ አባ ቡና” ይዘው ወደ ሱፐር ሊጉ በመውረዳቸው ጅማ አባ ጅፋርን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያሳደጉትን አሰልጣኝ ተክተው ሥራውን በመረከባቸው ደጋፊው ቁጣ አሰምቶ ነበር። ሆኖም አሰልጣኙ “እመኑኝ የሊጉን ዋንጫ አነሳለሁ” ባሉት መሠረት የፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን እና ኮከብ አሰልጣኝ ሆነው ጨርሰዋል።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን ኢትዮጵያ ቡና በ50 ነጥብ ሶስተኛ ሆኖ አጠናቋል። በሁለተኛው ዙር ለሳምንታት ሊጉን ይመራ የነበረው መቀሌ ከተማ ደግሞ በ49 ነጥብ አራተኛ ሆኗል። በመጀመሪያው ዙር በሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪና ቀዳሚ የነበረው ደደቢት በ41 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን በማግኘት ሊጉን አጠናቋል። የፋሲል ከተማ ክለብም ከደደቢት ተመሳሳይ 41 ነጥብ በመያዝ በግብ ክፍያ ተበልጦ ስድስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)

 

የዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በተለያዩ ቦታዎች ላይ የሚሰለፉ በርካታ የውጭ ሀገር ተጫዋቾች የታዩበት ነበር። በተለይም ደግሞ በግብ ጠባቂነት ሊጉን የተቆጣጠሩት ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ተጨዋቾች ናቸው። ከ80 በመቶ በላይ የፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊ ክለቦች የተለያዩ የአፍሪካ ሀገሮች ዜግነት ያላቸው ናቸው። ከግብ ጠባቂዎች በተጨማሪም በሊጉ በፊት መስመር በኩል የሚጫወቱ ተጫዋቾች በብዛት የሚገኙበት ሆኗል። በኮከብ ግብ አግቢነትም ዘንድሮ ከአንድ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ የያዙት የውጭ ሀገር ተጫዋቾች ናቸው።

ለጅማ አባጅፋር የሚጫወተው ናይጄሪያዊው አጥቂ ኦኪኪ ኦፎላቢ አንደኛው ሲሆን፤ 23 ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ በኮከብ ግብ አግቢነት ሊጉን ማጠናቀቅ ችሏል። ጅማ አባጅፋር የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ለማንሳት ካስቻሉ ቁልፍ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው። ለክለቡ ውጤት ወሳኝ ሚና የነበራቸው ግቦችን በማስቆጠር የላቀ ሚና እንደነበረው መናገር ይቻላል። ክለቡ ካስቆጠራቸው ጎሎች 59 በመቶ የተቆጠሩት በናይጀሪያዊው ነው።

አፎላቢ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ታሪክ ኮከብ ጎል አግቢ ሆኖ በማጠናቀቅ ሁለተኛው የውጭ ዜጋ ሲሆን፤ በሊጉ ታሪክም 23 ጎል በማግባት የመጀመሪያው ነው። ከዚህ በፊት 22 ጎሎችን በማግባት የመጀመሪያው ነው። ከዚህ በፊት 22 ጎሎችን በማግባት ኮኮብ ጎል አግቢ መሆን የቻለው የውጭ ዜግነት ያለው አጥቂ ሳሙኤል ሳኑሚ ነበር።

በመከተል በሁለተኛ ኮከብ ግብ አግቢነት ሊጉን ያጠናቀቀውም የውጭ ሀገር ዜግነት ያለው ተጨዋች ነው። እርሱም የኢትዮጵያ ቡናው አጥቂ ናይጄሪያዊ ተጫዋች ሳሙኤል ሳኑሚ ሲሆን፤ ተጫዋቹ 13 ግቦችን ከመረብ አሳርፏል።

ተመሳሳይ 13 ግቦችን በማስቆጠር የሚጠቀሰው ሶስተኛው የውጭ ሀገር ዜግነት ያለው ተጫዋች ጋናዊው የኢትዮ ኤሌትሪክ አጥቂ አልሀሰን ካሉሻ ነው። ተጫዋቹ ከሳሙኤል ሳኑሚ በተመሳሳይ የግብ መጠን በማስቆጠሩ እኩል ሁለተኛ የኮከብ ግብ አግቢነት ደረጃን ይጋራል።

በኮከብ ግብ አግቢነት ፉክክሩ እኩል 12 ግቦችን በማስቆጠር ሁለት ተጫዋቾች ይጠቀሳሉ። እነርሱም የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ እና የደደቢቱ ጌታነህ ከበደ ናቸው።

በዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ የዋንጫ ተፎካካሪ በሆነውና የአምናው ሻምፒዮን በነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ውስጥ በርካታ ግቦችን በማስቆጠር በኮከብ ግብ አግቢነት ፉክክር ውስጥ የገቡ ተጫዋቾች አለመኖሩ አስገራሚ ሆኗል። በክለቡ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የተከላካይ መስመር ተጫዋች የሆነው ሳላዲን ባርጌቾ ነው። ሳላዲን በውድድር አመቱ 5 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። ይህም የክለቡ የፊት መስመር ተጫዋቾች ብቃት ጉዳይ ከፍተኛ ጥያቄን የሚያጭር ነው።¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)

 

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ለብዙ ክለቦች በመልካም አርአያነት የሚጠቀስ ታሪክ በመስራት የሚታወቀው የኢትዮ ኤሌትሪክ (ቀድሞ መብራት ሀይል) ዘንድሮ ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ወርዷል። ወልዲያ ከተማ እና አርባ ምንጭ ከተማ ከሊጉ የወረዱ ሌሎች ክለቦች ናቸው።

ኢትዮ ኤሌትሪክ መብራት ሀይል እየተባለ በሚጠራበት አመታት በተለይም በ1990ዎቹ ላይ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አስፈሪ ቡድን ነበር። የሊጉን ዋንጫም በ1990 እና በ1993 ዓ.ም. አንስቷል። ክለቡ ለብሔራዊ ቡድን የሚጫወቱ ስመ ጥር ተጫዋቾችንም በማፍራት የሚታወቅ ነበር። ወንድማማቾቹ ዮርዳኖስ እና ስምኦን አባይ፣ ኤልያስ ጁሀር፣ ታፈሰ ተስፋዬ እና አንዋር ሲራጅ የመሳሰሉ ተጫዋቾች ከክለቡ ታሪክ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ስመ ጥር ተጫዋቾች ናቸው።

ከቅርብ አመታት ወዲህ ግን ክለቡ በሊጉ ላለመውረድ የሚጫወት ለመሆን ተገዷል። ባለፉት ሶስትና አራት አመታት ሊጉን ላለመውረድ ሲታገል ቆይቷል። ዘንድሮ ግን ከመውረድ መትረፍ አልቻለም።

ኢትዮ ኤሌትሪክ በሊጉ ሁለተኛ ዙር የቀድሞውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን ቢቀጥርም ውጤታማ መሆን አልቻለም። አሰልጣኝ አሸናፊ ተደጋጋሚ ሽንፈቶችን በማስተናገድ አሳዛኝ ታሪክ ጽፈዋል።

እሁድ እለት የተከናወነው የድሬደዋ እና ወልዋሎ ክለቦች የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታ በኢትዮ ኤሌትሪክ እጣ ፈንታ ላይ ወሳኝ ነበረ። ከመውረድ ስጋት ፈጽሞ ነጻ ያልነበረው ድሬ ደዋ ከተማ ወልዋሎን 2ለ0 በመርታት በሊጉ መቆየት የቻለበትን ውጤት ማስመዝገብ ችሏል። በአሰልጣኝ ስምኦን አባይ የሚመራው የድሬደዋ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ጨዋታውን በማሸነፉ ነጥቡን 35 አድርሶ በግብ ልዩነት ተጠቃሚ በመሆን ከመውረድ ድኗል።

በአስደናቂ ሁኔታ ዘንድሮ በፕሪሚየር ሊጉ እኩል 35 ነጥብ ይዘው ያጠናቀቁት ክለቦች ብዛት አምስት ናቸው። እነርሱም ድሬ ደዋ ከተማ፣ ወላይታ ድቻ፣ መከላከያ፣ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ እና ኢትዮ ኤሌትሪክ ናቸው። ከእነዚህም መካከል የመውረድ ሰለባ የሆነው ኢትዮ ኤሌትሪክ ነው። ክለቡ በ30 ጨዋታዎች 35 ነጥብ ሲያስመዘግብ 15 የግብ እዳ ተመዝግቦበታል።

በተመሳሳይ ሁኔታ ከሊጉ የመውረድ እጣ የገጠማቸው አርባ ምንጭ ከተማ እና የወልዲያ ከተማ ክለቦች ናቸው። አርባ ምንጭ በሊጉ 30 ጨዋታዎችን አድርጎ 33 ነጥብ በማስዝገብና በ7 የግብ እዳ ነው ከሊጉ የወረደው። ወልዲያ ከተማ ደግሞ 21 ነጥብ እና 29 የግብ እዳዎች በማስመዝገብ የመጨረሻውን ደረጃ ይዞ ነው ከሊጉ የወረደው።¾

Page 1 of 58

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 172 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us