ሳሙኤል ኤቶ ለ10 ዓመት እስር ሊዳረግ ይችላል

Thursday, 01 December 2016 15:27

 

ካሜሮናዊው የእግር ኳስ ኮከብ ሳሙኤል ኤቶ እስከ አስር ዓመት የሚደርስ እስር የሚዳርግ ክስ ቀርቦበታል። ተጫዋቹ ግን ለእስርም ሆነ ለገንዘብ ቅጣት የሚዳርግ ምንም አይነት ጥፋት እንዳልፈጸመ ነው የተናገረው።

አራት ጊዜ የአፍሪካ የአመቱ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ የተሸለመው ሳሙኤል ኤቶ በስፔን ባስልጣናት ዘንድ የቀረበበት ክስ ለአስር ዓመት እስር ሊዳርገው እንደሚችል የሀገሪቱ ጋዜጦች በመዘገብ ላይ ናቸው። ተጫዋቹ በስፔን ለባርሴሎና በሚጫወትበት ጊዜ መክፈል የሚጠበቅበትን  አራት ሚሊዮን ዩሮ ታክስ እንዳልከፈለ ነው የተገለጸው።

የ35 አመቱ ኤቶ እ.አ.አ. ከ2004 ጀምሮ ለአምስት አመታት በባርሴሎና ስኬታማ ጊዜያትን አሳልፏል። በቆይታውም ለክለቡ ከ100 በላይ ግቦችን ያስቆጠረ ሲሆን፤ የላሊጋውንና የቻምፒየንስ ሊጉን ዋንጫ አንስቷል። ተጫዋቹ ከ2006 እስከ 2009 በነበረው ቆይታ መክፈል የሚጠበቅበትን ከ4 ሚሊዮን ዶላር በላይ የገቢ ታክስ አለመክፈሉን በመጥቀስ የስፔን የግብር ባለስልጣናት ክስ ማቅረባቸው ነው የተሰማው። በዚህም የተነሳ ተጫዋቹ ለ10 ዓመት ከስድስት ወር እስር እና የ15 ሚሊዮን ዶላር ቅጣት እንዲጣልበት ጠይቀዋል።

አሁን ለቱርኩ አንታሊይአስፖር ክለብ በመጫወት ላይ የሚገኘው የ35 አመቱ ሳሙኤል ኤቶ ግን በስፔን የግብር ባለስልጣናት የቀረበበት ክስ ምንም መሰረት የሌለውና ሀሰተኛ እንደሆነ ተናግሯል። በስፔን በነበረው ቆይታም የሚጠበቅበትን የገቢ ግብር መክፈሉን ለመገናኛ ብዙሀን አስታውቋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
247 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us