ደቡብ አፍሪካዊው አትሌት የሀገሪቱን ከፍተኛ የስፖርት ሽልማት አሸንፏል

Thursday, 01 December 2016 15:28

 

·        ካስተር ሴማንያ የደቡብ አፍሪካ ምርጥ የሴት ስፖርተኛ ተብላለች

ደቡብ አፍሪካ በ2016 በተለያዩ የስፖርት ዘርፎች ስኬታማ ጊዜን ያሳለፉ ባለሞያዎቿን ያከበረችበት የሽልማት ስነ ስርአት አከናውናለች። ካስተር ሴማንያና ዋይዴ ቫን ኔክሬክ ከፍተኛ ቦታ ለሚሰጠው ለአመቱ ምርጥ የስፖርት ሰው ሽልማት በእጩነት የቀረቡ ሲሆን፣ የ400 ሜትር ሻምፒዮኑ ዋይዴ ቫን ኔክሬክ ሽልማቱን አሸንፏል። ሴማንያ ምርጥ የሴት ስፖርተኛ ስትባል፣ ኔክሬክ በወንዶች ዘርፍ አሸንፏል። በአጠቃላይም ኔክሬክ በእጩነት በቀረበበት በሶስት ዘርፎች ሽልማቶችን በመውሰድ የደቡብ አፍሪካ ምርጥ ስፖርተኛነቱን አረጋግጧል።

በሪዮ ኦሊምፒክ የ400 ሜትር የአለም ክብረወሰንን በማሻሻል ከፍተኛ አድናቆትን ያተረፈው ኔክሬክ የደቡብ አፍሪካ ምርጥ የወንድ ስፖርተኛ ሲባል፤ በህዝብ ምርጫ የሚሰጠውን ምርጥ ስፖርተኛ ሽልማትንም አሸንፏል። ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠውን ሽልማት ማለትም የአመቱ ምርጥ የስፖርት ሰው ሽልማትንም ከሴማንያ ጋር ተፎካክሮ ማሸነፍ  ችሏል።

በአሜሪካዊው ማይክል ጆንሰን ተይዞ የነበረውን የ400 ሜትር የአለም ክብረወሰን በሪዮ ኦሊምፒክ በማሻሻል የብዙዎችን አድናቆት ማግኘቱ ይታወሳል። አትሌቱ ለአመቱ ምርጥ የአለም አትሌት ሽልማትም ከእንግሊዛዊው ሞ ፋራህና ጃማይካዊው ዩሴን ቦልት ጋር በእጩነት የቀረ ሲሆን፣ ሽልማቱን ሊያሸንፍ እንደሚችልም ተገምቷል።

በሴቶች በሪዮ ኦሊምፒክ በ800 ሜትር የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊዋ ካስተር ሴማንያ የደቡብ አፍሪካ ምርጥ የሴት ስፖርተኛ ሽልማት ማሸነፍ ችላለች። ለአመቱ ምርጥ የደቡብ አፍሪካ ስፖርተኛ ሽልማት ከዋይዴ ቫን ኔክሬክ ጋር በእጩነት መቅረቧ እንዳስደሰታት ተናግራለች። አሸናፊው ኔክሬክንም እንኳን ደስ ያለህ መልዕክቷን አቅርባለታለች።

በእግር ኳስ ደግሞ የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ አሸናፊ የሆነው የማሜሎዲ ሰንዳውንስ ክለብ የአመቱ የደቡብ አፍሪካ ምርጥ የእግር ኳስ ክለብ ሽልማት ማሸነፉ ታውቋል።

ከዚህ በተጨማሪም ደቡብ አፍሪካ የአመቱ ምርጥ የስፖርት ጋዜጠኛ፣ ምርጥ ፎቶግራፍ አንሺ፣ ምርጥ የትምህርት ቤት ስፖርት ቡድን፣ ምርጥ የአካል ጉዳተኛ ስፖርቶችን በሁለቱም ጾታዎች ሸልማለች።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
261 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us