የማነ ጸጋዬ በጃፓን የፉኩካ ማራቶንን አሸነፈ

Wednesday, 07 December 2016 15:50

ባለፉት አመታት በኬንያውያን ተይዞ የነበረውን የበላይነት ኢትዮጵያዊው አትሌት የማነ ጸጋዬ መስበር ችሏል። በአስቸጋሪ የአየር ንብረት በመሮጥ ያስመዘገበው ሰአት ከእቅዱ ውጭ መሆኑን ተናግሯል።

በአለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የወርቅ ደረጃ የተሰጠው የፉኩካ ማራቶን ባለፈው እሁድ በድምቀት ተካሒዷል። በወንዶች መካከል የተካሔደውን ፉክክር አትዮጵያዊው የማነ ጸጋይ በማሸነፍ ኬንያውያን በውድድሩ መድረክ የነበራቸውን የበላይነት ታሪክ መቀየር ችሏል። በተለይም ባለፉት ሁለት አመታት አሸናፊ የነበረውንና ዘንድሮም ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት የነበረውን ፓትሪክ ማካውን አስከትሎ በመግባት ድል ማድረጉ አድናቆት አስጥቶታል።

በቻይና ቤጂንግ ከተማ በተካሔደው በ2015 የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በማራቶን የብር ሜዳል ያያገኘው የማነ ጸጋዬ የፉኩካ ማራቶንን 2፡08፡48 በመግባት ያሸነፈ ሲሆን፤ ፓትሪክ ማካው ደግሞ 2፡08፡57 ነበር ያጠናቀቀው።

በጃፓን በየአመቱ በጉጉት ከሚጠበቁ የሩጫ መድረኮች መካከል ቀዳሚ የሆነው የፉኩካ ማራቶን ዘንድሮ ዝናባማና ወበቃማ የአየር ንብረት መካሔዱ ለተወዳዳሪዎች እጅጉን ፈታኝ ነበር። በዚህም ምክንያት ብዙ ተወዳዳሪዎች ከእቅዳቸው በዘገየ ሰአት ነው ያጠናቀቁት። አሸናፊው አትሌት የማነ ጸጋዬም ርቀቱን 2፡ከ06 በታች ለመግባት የነበረው እቅድ ሳይሳካ መቅረቱን ከውድድሩ በኋላ በሰጠው አስተያየት ተናግሯል።

“ውድድሩን በማሸነፌ በጣም ደስ ብሎኛል። ነገር ግን ርቀቱን ያጠናቀቅኩበት ሰአት ካሰብኩት ስለዘገየ ቅር ብሎኛል። ርቀቱን 2፡ከ05 ወይም 2፡ከ06 ለማጠናቀቅ ነበር ስዘጋጅ የቆየሁት። ይሁንና በዝናቡ ምክንያት እንዳሰብኩት በጥሩ ሰአት ማጠናቀቅ አልቻልኩም።”

በውድደሩ የማነን በመከተል ኬንያዊው ማካው ሁለተኛ ሆኖ ሲገባ፣ ጃፓናዊው ዩኪ ካዋቺ ሶስተኛ ሆኖ ማጠናቀቅ ችሏል።¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
262 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us