አልማዝ አያና ከወልበራ እስከ ዓለም ኮከብ አትሌትነት

Wednesday, 07 December 2016 15:54

 

አርብ ምሽት በአልማዝ አያና አዕምሮ ውስጥ የሚመላለሰውን ሀሳብ መገመት ከባድ አይደለም። ሁሉም ነገር ህልም ይመስላል። ከሶስት አመታት በፊት ጥቂቶች ብቻ የሚያውቋት አልማዝ የተሰኘችው የኢትሌቷ የውትውንስም በአለም ታላቅ መድረክ መጠራት ችሏል። ያኔ ለብዙዎች አዲስ የነበረው የኢትዮጵያዊቷ ገጽታ አሁን በሚሊዮኖች ዘንድ የተለመደ ሆኗል። ባለፈው አርብ ምሽት በፈረንሳይዋ ሞናኮ ከተማ አልማዝ አያና የ2016 የአመቱ የአለም ምርጥ የሴት አትሌት መሆኗ ይፋ ሆኗል።

ይህ የአለም ኮከብ አትሌትነት ክብር ብዙዎች የሚመኙት ግን ጥቂቶች የሚያሳኩት ነው። ኢትዮጵያዊቷ አልማዝ ደግሞ እንደ ሀገሯ ልጆች ኃይሌ ገብረስላሴ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ መሰረት ደፋርና ገንዘቤ ዲባባ ከጥቂቶቹ አንዷ ሆናለች። የዚህ ክብርና ሽልማት ምክንያት የአመታት ልፋትና ህልም ብቻ ሳይሆን የ2016 የውድድር አመት ውጤት ብቻ ነው። የሪዮ ኦሊምፒክ አስደናቂ ድል ደግሞ ዋነኛው ነው።

በሪዮ ኦሊምፒክ አልማዝ ለሁለተኛ የወርቅ ሜዳልያ የታጨችበት በ5000 ሜትር ፍጻሜ ውድድር ከመካሔዱ በፊት ሰውነቷን በማሟሟቅ ላይ የነበረችው ኬንያዊቷ ቪቪያን ቺርዮት የአጭር ርቀት ንጉሱ ቦልትን አግኝታ ስትጨብጠው ታይታ ነበር። በውድድሩም ፍጻሜ ባልተጠበቀ ሁኔታ አሸንፋ የወርቅ ሜዳልያ ወሰደች። ከውድድር በፊት ቦልትን መጨበጥ አሸናፊ ያደርጋል ተብሎም ተጻፈ።

አልማዝ አያና ግን በተቃራኒው ታላቅ ሽልማትን አሸንፎ ቦልትን መጨበጥ እንደሚቻል አሳየች። አርብ ምሽት በፈረንሳይዋ ሞናኮ በተካሔደ የአለም አቀፉ የአትሌቲክስ ማህበር የአመቱ የአለማችን ምርጥ አትሌት ሽልማት ስነስርአት በሴቶች አሸንፋ ቦልትን ስትጨብጠው ታየች።

አልማዝ በወቅቱ ታላቁን የአትሌቲክስ ሽልማት ይዛ ከቦልት ጋር ብቻ ሳይሆን ከሌሎችም ታላላቅ የአለማች ሰዎች ጋር በክብር መቆም ችላለች። ከበስተግራዋ የሞናኮ ከተማ ገዢ ልኡል አልበርት ሁለተኛ፣ ከበስተቀኟ ደግሞ አትሌቲክስን ተወዳጅ ያደረገው ጃማይካዊው ዩሴን ቦልት፣ የአለም አቀፉ አትሌቲክስ ማህበርን የሚመራው እንግሊዛዊው ሴባስቲያን ኮ ቆመው ነበር።

ከሽልማት ስነስርአቱ ቀን ዋዜማ ደግሞ አልማዝ የሀገሯ ልጆች ከኃይሌ ገብረስላሴና ገንዘቤ ዲባባ በተገኙበት የወግ መድረክ ተቀምጣ ስትጫወት ነበር። ከትንየትውልድ ስፍራ ዋወልበራ ተነስታ ለታላቅ የሩጫ መድረክ የደረሰችበትን መንገድና የወደፊት ምኞቷንም ጭምር በቀላልና አጭር አማርኛ ስትናገር ሀይሌ ገብረስላሴ ደግሞ ሀሳቧን በእንግሊዝኛ እየተረጎመ ለአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን አቅርቧል።

‹‹በትውልድ አካባቢዬ ሩጫን ስጀምር በመሰናክል አልነበረም። ወደ አዲስ አበባ ስመጣ ግን የመሰናክል ሩጫን ለመሞከር ተገደድኩ። ነገር ግን የመሰናክል ሩጫን አልወደውም ነበር። በብዙ ውድድሮች ላይ ውጤታማ አልነበርኩም። በኋላ ላይም መሰናክልን ትቼ በጣም የምፈልገውን አይነት እንደ በ3000 እና 5000 ሜትር ሩጫዎች አመራሁ። የምፈልገውን ሩጫን መሮጥ ጀመርኩ።

በ3,000 ሜትርና በ5,000 ሜትር ውጤታማ መሆኗን በተግባር ብታረጋግጥም እጅጉን የምትወደው ርቀት ግን ሪዮ ኦሊምፒክ ላይ አለምን በአድናቆት ያስደመመችበት የ10,000 ሜትር ርቀት መሆኑን ነው የተናገረችው።

የወቅቱ የአለማችን ኮከብ አትሌት አልማዝ በሪዮ አሊምፒክ ሀገሯ ኢትዮጵያ ያገኘችውን ብቸኛ የወርቅ ሜዳልያ በ10,000 ሜትር ያስመዘገበችው ነበር። የ5,000 ሜትር ፉክክርን ደግሞ በሶስተኛ ደረጃ አጠናቃ የነሐስ ሜዳልያ ማግኘቷ ይታወሳል።

ከዚህ በተጨማሪም በውድድር አመቱ በዳይመንድ ሊግ መድረኮች ያደረገቻቸውን ውድድሮች በሙሉ ማሸነፏ ለሽልማቱ ክብር አብቅቷታል። በአመቱ ውስጥ በሪዮ ኦሊምፒክ ከአንዱ በስተቀር ያደረገቻቸውን ውድድሮችን በሙሉ አሸንፋለች። በውድድር አመቱ በ5,000 ሜትር በጥሩነሽ ዲባባ የተያዘውን የአለም ክብረወሰን ለመስበር የተቃረበችበትን ውጤት አስመዝግባለች። በአሁኑ ወቅትም የርቀቱን ክብረወሰን ከእርሷ ሌላ ልታሻሽል የምትችል አትሌት አለች ተብሎ አይገመትም። እርሷ ግን ትኩረቷ ክብረወሰን መስበር ሳይሆን በሀሉም ርቀቶች ብቃቷን ማሻሻል እንደሆነ ነው ያስታወቀችው።

“በዚህ አመት የ10,000 ሜትር የአለም ክብወሰን ሰብሬያለሁ። በቀጣዩ የውድድር አመት ደግሞ በምወዳደርባቸው ርቀቶች ሁሉ የግል ብቃቴን ማሻሻል እፈልጋለሁ። እንደገናም ደግሞ ሀገሬን ወክዬ እንደምሮጥ ተስፋ አደርጋለሁ” ብላለች። በተለይም ደግሞ በእንግሊዟ ለንደን ከተማ ደግሞ የኢትዮጵያን መለያ ለብሳ እንደምትገኝ ትጠበቃለች።

የ2017 የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በለንደን ከተማ የሚካሔድ ሲሆን፤ አልማዝ ለሶስተኛ ጊዜ በምትሳተፍበት የውድድር መድረክ የላቀ ውጤት እንደምታስመዘግብ ይጠበቃል። ለመጀመሪያ ጊዜ በአለምሻምፒዮና የተሳተፈችውና መሰረት ደፋር ባሸነፈችበት በ2013 የሞስኮ የአለምሻምፒዮና ሲሆን በውድድሩ ሶስተኛ ሆና የነሀስ ሜዳልያ መውሰዷ ይታወሳል። ሻምፒዮናው ለአልማዝ የመጀመሪያዋ ትልቁ የውድድር መድረክ ስለነበር ያገኘችው ውጤት የሚያስከፋ አልነበረም። ከሁለት አመት በኋላ ግን በቤጂንግ የ2015 የአለም ሻምፒዮና በ5,000 ሜትር የውድድሩን ክብረወሰን በማሻሻል ጭምር ማሸነፍ ችላለች። በተፎካካሪቿ ላይ ፍጹም የበላይነት ባሳየችበት የሩጫ ብቃቷም ተደንቃ የአዲዳስን የወርቅ ጫማ መሸለሟ አይዘነጋም። በለንደን ሻምፒዮናም ለሶስተኛ ጊዜ በድንቅ ብቃት ሜዳልያ እንደምትወስድ ትጠበቃለች። በሻምፒዮናውም በ5,000 እና 10,000 ሜትር ትወዳደራለች ተብሎ ይጠበቃል።¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
303 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us