ማህሬዝ የቢቢሲን ሽልማት አሸነፈ

Wednesday, 14 December 2016 14:11

 

በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ከሌስተር ሲቲ ጋር ክስተት ሆኖ የተገኘው አልጄሪያዊው ሪያድ ማህሬዝ የቢቢሲን የ2016 ምርጥ ተጫዋች ሽልማትን አሸንፋል። በአመት ውስጥ ታላላቅ ክብርና ሽልማቶችን በመጎናጸፍ ከምንግዜም የአፍሪካ ኮከቦች ጋር የሚጠራ ስለመሆኑ ብዙዎች እየመሰከሩለት ነው።

የእግር ኳስ አፍቃሪያን በኢንተርኔት በሚሰጡት ድምጽ አማካኝነት የሚካሔደው የቢቢሲ የአፍሪካ ኮከብ ተጫዋች ሽልማት ከሪያድ ማህሬዝ ጋር ጋቦናዊው ፒየር ኤሜሪክ አቡሜያንግ፣ ጋናዊው አንድሬ አየው፣ ሳድዮ ማኔ እና ያያ ቱሬ የመጨረሻ እጩ ነበሩ። በ2016 የውድድር አመት ከሌስተር ሲቲ ጋር የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ በማንሳት ጭምር ስኬታማ አመት ያሳለፈው ማህሬዝ እንደተገመተው ሽልማቱን አሸንፏል።

የ25 አመቱ የክንፍ ተጫዋች ባለፈው የውድድር አመት ከሌስተር ሲቲ ጋር የሊጉን ዋንጫ ከማንሳቱ በተጨማሪ በፕሮፌሽናል ተጫዋቾች ማህበር የሚሰጠውን የኮከብ ተጫዋች ሽልማትንም በግሉ አሸንፏል። የማህበሩ ሽልማትን ያሸነፈ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ተጫዋች በመሆን አዲስ ታሪክ ሰርቷል።

‹‹ይህ ሽልማት ለእኔ ብዙ ትርጉም አለው። ለአፍሪካውያን ተጫዋቾች ትልቅ ነገር ነው። በመሸለሜ በጣም ደስ ብሎኛል። ትልቅ ክብር ነው። አድናቂዎቼን በሙሉ በጣም አመሰግናለሁ።›› ሲል ሽልማቱን ካሸነፈ በኋላ ለቢቢሲ አስተያየቱን የሰጠው ማህሬዝ፤  መታሰቢያነቱም ለመላው አልጄሪያውያን አድናቂዎቹና ቤተሰቦቼ ይሁንልኝ ብሏል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
265 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us