ከተደጋጋሚ ጥረት በኋላ እውን የሆነው የኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ጥያቄ

Wednesday, 14 December 2016 14:13

 

-    አርቲስት ስዩም ተፈራ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ሆነዋል

የኢትዮጵያ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን በሶስት የተነጣጠሉ የኢንተርናሽናል ቴኳንዶ አሶሴሽኖች ተዋቅሮ በውዝግብና ንትርክ ታጀቦ ዓመታትን አስቆጥሯል። በተለይ አንዳንድ የስፖርቱ ኃላፊዎች ዘንድ ከስፖርቱ ሙያዊ ስነ ምግባር ውጭ በመሄድ በስፖርቱ “ያልተካኑትን” ሰዎች ገንዘብ እየተቀበሉ ጭምር ወደ አሜሪካ እና የአውሮፓ ከተሞች ይዘው በመሄድ ኪሳቸውን ሲያደልቡ ቆይተዋል። በዚህም የተነሳ አጠቃላይ ያርሻል አርት ስፖርቶችን በርካታ ኢትዮጵያዊያን በጥርጣሬ የሚያይዋቸው ስፖርቶች ሆነው ቆይተዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ በኢንተርናሽናል ኢንስትራክተር ማሰተር ኪሮስ ገብረመስቀል የሚመራው ኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ አሶሴሽን (እንግሊዝ ቤዝድ) አገሩን ወክሎ በተወዳደረባቸው ሶስት ዓለም አቀፍ ውድድሮች ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን ይዞ መመለስ ችሏል። በተለይም በ2005 ዓ.ም በህንድ በተካሄደው የኢንተርናሽናል ኦፕን ውድድር ላይ ተካፍሎ 11 ሜዳሊያዎችን በማምጣት በቀድሞው ስፖርት ኮሚሽን ለቡድኑ ልዑካን አባላት የገንዘብና የእውቅና ሽልማት ተበርክቶለት ነበር።

ይህ አሶሴሽንም በፕሬዘዳንቱ ማስተር ኪሮስ ገብረመስቀል አማካኝነት ላለፉት ሁለት ዓመታት ወደ ፌዴሬሽን ለማደግ ባደረገው ያላሰለሰ ጥረት መሰረት በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር እውቅና አግኝቶ “የኢትዮጵያ ኢንተርናሸናል ቴኳንዶ ፌዴሬሽን” ተብሎ ተሰይሟል። በፌዴራል ደረጃ እውቅና ያገኘው ፌዴሬሽኑም በክልሎች ተመሳሳይ አደረጃጀቶችን ለመዘርጋት ጥረት እያደረገ ሲሆን ከአሁኑም የአማራ እና ሶማሊያ ክልሎች እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ የስፖርቱ አሶሴሽኖች ወደ ፌዴሬሽን አድገዋል።

የአዲስ አበባ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ባሳለፍነው ሳምንት የምስረታ እና አንደኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በምክትል ኃላፊ ማዕረግ የስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ በሀይሉ በቀለ በተገኙበት አካሂዷል። ፌዴሬሽኑን የሚመሩ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትንም የመረጠ ሲሆን ታዋቂው አርቲስት ስዩም ተፈራም ፌዴሬሽኑን በፕሬዝዳነትነት እንዲመሩ ተመርጠዋል። ስፖርቱ በአዲስ አበባ አስሩም ክፍለከተሞች የሚዘወተር መሆኑን የገለጹት የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ በሀይሉ በቀለ ገልጸዋል። በከተማዋም 45 ክለቦች እንዳሉ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ማስተር ኪሮሰ ገብረመስቀል በወቅቱ በስፍራው ለተገኙ ጋዜጠኞች የፌዴሬሽኑን ምስረታ ጠቀሜታ ሲገለጹ “በዓለም አቀፍ አቻ ፌዴሬሽኖች ጋር ለምናካሂደው ግንኙነት ወሳኝነት አለው። ምክንያቱም በየትኛውም ዓለም ኢንተርናሽናል ቴኳንዶን በሶስት ከፍላ የያዘቸ አገር ኢትዮጵያ ብቻ በመሆኗ ከእኛ ጋር ግንኙነት ለመፍጠር አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል” ያሉ ሰሆን አያይዘውም “ከክልሎች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ለመፍጠርም ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል” ብለዋል። ኢንተርናሽናል ውድድሮችን ለማካሄድና ለስፖርቱ አስፈላጊ የሆኑ የቁሳቁስ ድጋፎችን ለማካሄድም ወሳኝነት እንዳለው ነው የገለጹት።

ሁሉም ፌዴሬሽኖች የምስረታ ጉባኤያቸወን ቀደም ብለው በማካሄዳቸው ከመንግስት የሚደረግላቸውን የበጀት ድጋፍ ያገኛሉ። ይህ ፌዴሬሽን ግን ዘግይቶ በመመስረቱ የዓመቱን የስራ ማስኬጃ በጀት እንዴት ልታደርጉ ነው? ለሚለው የሰንደቅ ጋዜጣ ጥያቄ ሲመልሱ “በዚህ ዓመት ከሌሎች አሶሴሽኖች ጋር የተመደበልንን እንጠቀማለን። በዋናነት ግን ስፖንሰርና ሌሎች መንገዶችን ተጠቅመን አዲስ አበባ ያሉ ክለቦች ውድድር እንዳያጡ የሚያደርጉበትን መንገድ እንፈጥራለን። በቀጣይ ዓመት ጀምሮ ግን መንግስት በአሰራሩ መሰረት በምክር ቤት የሚጸድቅበት መንገድ ይኖራል” ሲሉ ተናገረዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
280 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us