የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ስደት ጨምሯል

Wednesday, 14 December 2016 14:13

 

-    ሶስት የማህበሩ አመራሮች ከሀገር እንደወጡ ቀርተዋል

በተለያዩ አጋጣሚዎች ከሀገር ወጥተው በዚያው የሚቀሩ ኢትዮጵያውያን የስፖርት ጋዜጠኞች ቁጥር ከመቼውም ጊዜ በላይ ጨምሯል። በቅርቡም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ሶስት ከፍተኛ አመራሮች ከሀገር እንደወጡ መቅረታቸው ታውቋል።

በስራም ሆነ በሌሎች አጋጣሚዎች በተለያዩ ጊዜያት ወደ ውጭ ሀገሮች ሔደው የሚቀሩ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች መኖራቸው ይታወቃል። ብዙዎቹም ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ጋር በተያያዘ በሚሰሩት ስራዎች የመንግስት ጫና አላሰራንም ሲሉ ምክንያታቸውን ይገልጻሉ።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን የስፖርት ጋዜጠኞች ስደት እጅጉን በሚያስደነግጥ ሁኔታ ቁጥራቸው አሻቅቧል። ባለፈው አንድ አመት ውስጥ ብቻም ከአስር በላይ የስፖርት ጋዜጠኞች ከሀገር ወጥተው ቀርተዋል። ከነዚህም መካከል የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበርን በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውስጥ በከፍተኛ አመራርነት የሚያገለግሉ ሶስት የስፖርት ጋዜጠኞች ይገኙበታል።

ባለፈው አንድ አመት ውስጥ ብቻ ከሀገር እንደወጡ የቀሩ የስፖርት ጋዜጠኞች በመንግስትና በግል መገናኛ ብዙሀን ሲያገለግሉ የቆዩ ስመጥር ጋዜጠኞች ይገኙበታል። ከእነርሱም መካከል በእለታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ በፋና ብሮድካስቲንግና በመጨረሻም በብስራት ኤፍ ኤም 101.1 ራዲዮ ያገለገለው ታምሩ አለሙ አንዱ ነው። ታምሩ ከስምንት አመት በላይ በቆየበት የስፖርት ጋዜጠኝነት ቆይታው እንደ አፍሪካ ዋንጫና የዳይመንድ ሊግ የአትሌቲክስ ውድድሮችን በአፍሪካና በአውሮፓ ከተሞች ተዘዋውሮ ዘግቧል።

ሌላው በቅርቡ ሀገር ጥለው ከወጡ የስፖርት ጋዜጠኞች መካከል የሚጠቀሰው የኢንተር ስፖርት ጋዜጣ መስራችና ባለቤት ሁሴን አብዱልቀኒ አንደኛው ነው። ከዚህ በተጨማሪም በአዲስ አበባ ብዙሀን መገናኛ ኤጀንሲ ይሰራ የነበረው አምሀ ፍሰሀ፣ ለተለያዩ የሀገር ወስጥና የውጭ መገናኛ ብዙሀን በተለይም ለአለምአቀፉ አትሌቲክስ ማህበር ድረ ገጽ አትሌቲክስ በመዘገብ የሚታወቀው ብዙአየሁ ዋጋው፣ በፋና ብሮድካስቲንግና በብስራት ኤፍ ኤም 101.1 ይሰራ የነበረው ቤተ ማርያም ኃይሉ፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ስፖርት ዘጋቢ ሊባኖስ ዮሐንስ፣ የኢቢሲ ስፖርት ዘጋቢ የነበረው ሳምሶን ከተማ፣ በፋና ብሮድካስቲንግ ስፖርት ዘጋቢ ቶማስ ሰብስቤ ባለፈው አንድ አመት ውስጥ ከኢትዮጵያ ወጥተው ከቀሩት መካከል ይጠቀሳሉ።

ከሀያ አመት በላይ በስፖርት ጋዜጠኝነት ያገለገለው ጋዜጠኛ ሁሴን አብዱልቀኒ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት ሲሆን፤ አምሀ ፍሰሀ በአቃቤ ነዋይነት፤ እንዲሁም ብዙአየሁ ዋጋው በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት ማህበሩን ሲያገለግሉ ቆይተዋል። በኢቢሲው ጋዜጠኛ ዮናስ ተሾመ ፕሬዝዳንትነት የሚመራው ማህበሩ በቅርቡ በሚያካሒደው ጠቅላላ ጉባኤ ከሀገር ወጥተው በቀሩት አባላት ምትክ የሚሰሩ አመራሮች ምርጫን ያካሒዳል ተብሎ ይጠበቃል።  

ሰሞኑን በተለያየ መገናኛ ብዙሀን ላይ በተገለጸው መረጃ መሰረት ከሀገር ወጥተው የቀሩ የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ቁጥር ከሰላሳ በላይ ሆኗል። የስፖርት ጋዜጠኞች ስደት በየጊዜው እያሻቀበ የመምጣቱ ምክንያት በውል ለማወቅ አዳጋች ነው። ስደትን ከሚመርጡት መካከል ደግሞ ለረጅም አመታት በሙያው ያገለገሉና መልካም ስምን የገነቡ መኖራቸው ሲታሰብ ጉዳዩን አሳሳቢ ያደርገዋል።

ኢትዮጵያ ለጋዜጠኞች ምቹ ካልሆኑ የአለማችን ሀገሮች መካከል በቀዳሚነት ትጠቀሳለች። በ2015 ይፋ የሆነ አንድ መረጃ እንዳመለከተው ለጋዜጠኞች ምቹ ካልሆኑ አስር የአለማችን ሀገሮች መካከል ኢትዮጵያ አራተኛዋ ናት። ጎረቤቷ ኤርትራ ቁጥር አንድ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ ሰሜን ኮርያና ሳውዲ አረብያ ሁለተኛና ሶስተኛ ናቸው። ፍሪደም ሀውስ የተባለ አለምአቀፍ ተቋም ይፋ ያደረገው የሀገሮች የ2016 የፕሬስ ነጻነት ደረጃ ላይም ኢትዮጵያ ከ180 የአለማችን ሀገሮች 142ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ኤርትራ የመጨረሻውን 180ኛ ደረጃ ይዛ ትይዛለች።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
621 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us