ዶክተር አሸብር ወደ ስፖርት መሪነት ተመልሰዋል

Wednesday, 14 December 2016 14:15

በኢትየጵያ እግር ኳስ ታሪክ ስማቸው ተጠቃሽ ከሆኑ አመራሮች መካከል ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ አንዱ ናቸው። ከኢትዮጵያ እግር ኳስ በበጎም ሆነ መጥፎ ትዝታዎች ስማቸውና ተግባራቸው ተያይዞ ይነሳል። በተለይም ደግሞ ኢትዮጵያን ለሁለት አመታት ከአለምአቀፍ የውድድር መድረኮች እንድትርቅ ባደረገው ውዝግብ ጋር ጎልተው ይጠቀሳሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ በእሳቸው የፕሬዝዳንትነት ዘመን ባገኘችው ሁለት የሴካፋ ዋንጫዎች ስማቸው ተያይዞ ይጠራል።

ዶክተር አሸብር ከእግር ኳስ ኃላፊነታቸው በኋላ በ2002 ዓ.ም. አገር አቀፍ ምርጫ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልነት አካባቢያቸው ቦንጋን ወክለው በመወዳደር ማሸነፋቸው ይታወቃል። በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ብቸኛው የግል ተወካይ በመሆን በተለያዩ ቋሚ ኮሜቴዎች ውስጥ በማገልገል ቆይተዋል። የዛሬ ሶስት አመት ለፓን አፍሪካ ፓርላማ ምክትል ፕሬዝዳንትነት ምርጫ ተወዳድረው የርዋንዳ ተወካይ የሆኑትን ወይዘሮ ጁሊያና ካንቴንግዋን አሸንፈው መመረጣቸው ይታወሳል።

ወደ ፖለቲካው አለም ገብተው ጠፍተዋል ሲባል የዶክተሩ ወደ ስፖርቱ የመመለስ ዜና ድንገት መሰማቱ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል። ወደ ስፖርት አመራርነት ዳግም የተመለሱት ቀድሞ በሚታወቁበት የእግር ኳስ ስፖርት ሳይሆን ቅርጫት ኳስ መሆኑ ሰፊ የመገናኛ ብዙሀን ሽፋን ሊያገኝ ችሏል።

የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ባለፈው ሐሙስ ጠቅላላ ጉባኤውን ያካሔደ ሲሆን፤ በቅርቡ በስራ ምክንያት ከኃላፊነታቸው የለቀቁት ፕሬዝዳንቱን አቶ ብርሀነ ኪዳነማርያምን ለመተካት በእጩነት በቀረቡ ሶስት ተፎካካሪዎች ላይ ድምጽ ሰጥቷል። ከኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን በተጨማሪ የኦሊምፒክ ኮሚቴንም በፕሬዝዳንትነት ይመሩ የነበሩትን የአቶ ብርሀነን ቦታ ለመተካትም ዶክተር አሸብር የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልልን፣ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ኦሮሚያን እና በዛሚ ራዲዮ ጋዜጠኛ የሆኑት ወይዘሮ ሚሚ ስብሀቱ የትግራይ ክልልን በመወከል ቀርበው ነበር።

የጉባኤተኛው ድምጽ ሲቆጠርም ዶክተር አሸብር ተፎካካሪዎቻቸውን በከፍተኛ ልዩነት ማሸነፋቸው ነው የታወቀወ። ይኸውም 22 ድምጽ በማግኘት የፕሬዝዳንትነት ምርጫውን ማሸነፋቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ሶስት ድምጽ፤ ወይዘሮ ሚሚ ስብሀቱ ደግሞ ሁለት ድምጽ ብቻ በማግኘታቸው ሳያሸንፉ ቀርተዋል። የጥርስ ህክምና ባለሞያና የጥርስ ህክምና ክሊኒኮች ባለቤት የሆኑት ዶክተር አሸብር የቅርጫት ኳስ አመራር ሆነው በመመረጣቸው ዙሪያም ከተለያዩ ወገኖች በኩል አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ነው።

የስፖርት ተቋምን ለመምራት የአመራር ልዩ ብቃትን የሚጠይቅ መሆኑን የሚገልጹ ወገኖች የዶክተሩ በቅርጫት ኳስ ስፖርት አመራርነት መመረጥ ስህተት እንዳልሆነ ያስረዳሉ። ከስፖርቱ ጋር በደንብ መተዋወቅ የሚያስችል ተሞክሮና የሙያ ብቃትን እንደሚያስፈልግ የሚያምኑት ደግሞ ዶክተር አሸብር ከቅርጫት ኳስ ይልቅ እግር ኳሱ ላይ ተመልሰው ቢሰሩ የተሻለ እንደሆነ ይገልጻሉ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
289 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us