የናይጄሪያ ሴት ተጫዋቾች አድማቸውን በድል አጠናቀዋል

Wednesday, 21 December 2016 14:56

 

በአፍሪካ እግር ኳስ ከሽልማት ጋር በተያያዘ ውዝግብ የማያጣው ሆኗል። በቅርቡም የናይጄሪያ የሴት ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን አባላት በአህጉራዊው መድረክ ላስመዘገቡት የሻምፒዮናነት ክብር የሚገባቸውን ሽልማት ባለማግኘታቸው ከፍተኛ ቅሬታ ሲያሰሙ ቆይተዋል። ካሜሮን ባስተናገደችው የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ የሆኑት ሱፐር ፋልኮኖች ወደ ሀገሪቱ ፓርላማ መግቢያ መውጪያ በር ድረስ ተጉዘውም ቅሬታቸውን በሰላማዊ ሰልፍ አቅርበዋል። ያረፉበትን ሆቴል ላለመልቀቅ በመወሰንም አድማቸውን እስከ ሰኞ እለት ቀጥለው ነበር።

ባለፈው ሰኞ እለት የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ የናይጄሪያ ሴት እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን አባላት ለሳምንታት የቆዩበትን አድማ በድል አጠናቀዋል። እያንዳንዳቸው ተጫዋቾች የጠየቁት ገንዘብ ስለተሰጣቸው አቡጃ ላይ ያረፉበትን ሆቴል ለቀው መውጣታቸው ተሰምቷል።

‹‹ሁሉም ተጫዋቾች የጠየቁት ገንዘብ ስለተሰጣቸው የነበሩበትን ሆቴል ለቀው ወጥተዋል›› ሲሉ ለቢቢሲ አስተያየታቸውን የሰጡት የቡድኑ ሚዲያ ኦፊሰር ሬሚ ሱሎላ ናቸው።

የናይጄሪያ ሴት ብሔራዊ እግር ኳስ ተጫዋቾች ካሜሮን ላይ ሻምፒዮን መሆናቸውን ካረጋገጡ በኋላ ሀገራቸው እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለእያንዳንዳቸው 23 ሺህ 650 ዶላር እንዲሰጣቸው ጠይቀው እንደነበር ይታወሳል።

ተጫዋቾቹ የናይጄሪያ ህዝብን ያስደሰተ ውጤት በማስመዝገባቸው ሊመሰገኑና ገንዘባቸውም ሊሰጣቸው እንደሚገባ ፕሬዝዳንቱ ቡሀሪ አሳስበው እንደነበር ይታወሳል። ተጫዋቾቹም መንግስታቸውና መገናኛ ብዙሀን ላደረጉት ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በአፍሪካ የሴቶች እግር ኳስ ዋንጫን በተደጋጋሚ በማንሳት ናይጄሪያዎችን የሚደርስባቸው አልተገኘም። “ሱፐር ፋልኮን” በመባል የሚጠራው ቡድናቸው የአህጉሪቱን ዋንጫ ላይ አስር ጊዜ ተሳትፈው ስምንት ጊዜ ዋንጫ ማንሳት ችለዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
258 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us