በማራቶን ጉዞ - ቀነኒሳ እና ሌሊሳ ሙከራ እየተደረገባቸው ነው

Wednesday, 21 December 2016 14:55

 

ከአበበ ቢቂላ ጀምሮ በላይነህ ዴንሳሞና ኃይሌ ገብረስላሴ ስም ደምቆ የተጻፈበት የማራቶን ርቀት የኢትዮጵያና ኬንያ አትሌቶች የበላይነታቸው እንደታየበት አሁንም ድረስ አለ። ሁለት ጊዜ በኃይሌ የተሻሻለው የርቀቱ የአለም ክብረወሰን ከሁለት አመት በፊት በኬንያዊው ዴኒስ ኪሜቶ ተሻሽሎ 2፡02፡57 ላይ ቆሟል። ከሶስት ወራት በፊት ይህንን ክብረወሰን ለመስበር ስድስት ሰከንዶች ብቻ ቀርተውት የነበረው ቀነኒሳ በቀለ አሊያም ሌሎች የኢትዮጵያና ኬንያ ሯጮች እንደሚያሻሽሉት ይጠበቃል።

መቼ እንደሆነ በውል ባይታወቅም የማራቶን የአለም ክብረወሰን በሰከንዶች መሻሻል ብቻ ሳይሆን ከሁለት ሰአት በታችም የሚሆንበት ዘመን መምጣቱ አይቀርም። የክብረወሰኑ እድገት እስካሁን በተጓዘበት መንገድ ከሆነ ርቀቱን ከሁለት ሰአት በታች ለማጠናቀቅ ከ20 እስከ 50 አመት ሊፈጅ እንደሚችል ጥናቶች ጠቁመዋል።

ይሁንና ሳይንሳዊ የሆነ መንገዶችን በመተግበር የርቀቱን ጊዜ ከሁለት ሰአት በታች ማድረግ እንደሚቻል የሚያስረዱ ሀሳቦች ከፍ ብለው መሰማት ጀምረዋል። ሀሳባቸውን በተግባር ለማሳየትም ፕሮጀክት አዘጋጅተው ሙከራቸውን የጀመሩም አሉ። ከእነርሱም መካከል በዚህ ጽሑፍ በስፋት የሚዳሰሱት ሁለት ፕሮጀክቶች በዋናነት ይጠቀሳሉ። አንደኛው ሰብቱሀውር (sub2hour) የተሰኘ ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ ብሬኪንግ2 (Breaking2) የሚል መጠሪያ አለው። ሁለቱም ፕሮጀክቶች ዋነኛ አላማቸው በተመሳሳይ ማራቶንን ከሁለት ሰአት በታች ማጠናቀቅ እንደሚቻል ማሳየት ቢሆንም በተለያዩ አካላት ለየብቻ የሚከናወኑ ናቸው።

የሰብ ቱ ሀወር ፕሮጀክት ባለቤት የኃይሌና ቦልትን ጨምሮ የስመ ጥር አትሌቶች ማናጀር የሆኑት ጆስ ኸርመንስ ናቸው። ግሪካዊው የስፖርት ስነ ልቦና ባለሞያና መምህር የሆኑት ግሪካዊው ፕሮፌሰር ያኒስ ፒሲላደስ ጥናቶችን በማድረግ በበላይነት ይመሩታል።

ከሁለት ዓመት በፊት የተጀመረውና ከ30 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚጠይቀው ይህ ፕሮጀክት የማራቶን ርቀትን ከሁለት ሰአት በታች የማጠናቀቅ ዘመቻውን እስከ 2019 ከግብ የማድረስ አላማ አለው። ፕሮጀክቱም በኢትዮጵያ በቆጂና በኬንያ ኤልድሮት ከተሞች ላይ የተዘረጋ ሲሆን፡ ቀነኒሳ በቀለን ዋና ተዋናይ ያደረገ ነው። ፕሮፌሰር ያኒስ ካለፉት አራት አመታት ወዲህ በቀነኒሳና ሌሎች የኢትዮጵያ ሯጮች ላይ ጥናት በማድረግ ላይ ናቸው።

ብሬኪንግ 2 የተሰኘው ፕሮጀክት ደግሞ በታዋቂው የስፖርት ትጥቆች አምራች ኩባንያ በናይክ አማካኝነት የሚካሔድ ነው። በአንድ አመት ውስጥ 2017 ይጠናቀቃል ተብሏል። የፕሮጀክቱ ገንዘብ በይፋ ባይገለጽም ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሚፈጅ ተገምቷል። የአለማችን ስመ ጥር የህክምና፣ የስነ ልቦና፣ የስነ ምግብ፣ ባለሞያዎችን ጨምሮ ከሀያ በላይ ባለሞያዎች የሚሳተፉበት ነው።

ናይክ ኩባንያ ማራቶንን ከሁለት ሰዓት በታች ለማውረድ የሚያስችል ሙከራውን ለማሳካት ሙከራ ከሚያደርግባቸው ሶስት አትሌቶች መካከልም የሁለት ጊዜ የቦስተን ማራቶን አሸናፊው ኢትዮጵያዊው ሌሊሳ ዴሲሳ አንዱ ነው። ከሌሊሳ ጋርም በሪዮ ኦሊምፒክ የማራቶን አሸናፊ ኬንያዊው ኢውድ ኪፕቾጌና የግማሽ ማራቶን የአለም ክብረወሰን ባለቤት ኤርትራዊው ዘረሰናይ ታደሰም ይገኛሉ።

የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶችን ይዘው ማራቶንን ከሁለት ሰአት በታች የማጠናቀቅ አላማ ያላቸው እነዚህ ሁለት ፕሮጀክቶች የአትሌቲክሱ አለም የወቅቱ መነጋገሪያ ሆነዋል። የስፖርቱ አፍቃሪም ፕሮጀክቶቹ ያነገቡት አላማ ፍጻሜ ምን ሊሆን እንደሚችል ለማወቅም በጉጉት ይጠብቃቸዋል።  

 

ለቀነኒሳ መልካም አጋጣሚ

በትራክ ላይ ሩጫዎች ታላቅነቱን ያስመሰከረው ቀነኒሳ በቀለ በማራቶንም መሰል ሰብዕና ለመጎናጸፍ ጉዞውን ጀምሯል። ማራቶን ከሁለት ሰአት በታች የማጠናቀቅ አላማ ያነገበው ሰብ ቱ ሀወር ፕሮጀክት ዋነኛ አካል መሆኑ መልካም አጋጣሚ ሆኖለታል። በሰብ ቱ ሀወር ፕሮጀክት መስራት ከጀመረ በኋላ መልካም ለውጥ ማሳየት ችላል።

ፕሮፌሰር ያኒስ በቀነኒሳ ላይ መሞከር የጀመሩት ማራቶንን ከሁለት ሰአት በታች የማጠናቀቅ ፕሮጀክታቸው እንደሚሳካ ያምናሉ። ለዚህም ደግሞ አትሌቱ በቅርቡ በበርሊን ማራቶን ያስመዘገበው ውጤት “ተስፋ ሰጪ ነው” ይላሉ። ቀነኒሳ በውድድሩ ከቀድሞ የማራቶን ሰአቱን ከሁለት ደቀቂ በላይ ያሻሻለበት ሰአት ነበር ያስመዘገበው። በቀጣይም ቀነኒሳ በሰብ ቱ ሀወር ፕሮጀክት ውስጥ የተሸለ ውጤት እንደሚያመጣ ይጠበቃል።

ቀነኒሳ የሰብ ቱ ሀወር ፕሮጀክትን ማሳካት ይችል ዘንድም የልምምድ፣ የአካልም የስነ ልቦናም ህክምና፣ የአመጋገብና የውድድር ሁኔታዎቹ በልዩ ሁኔታ ትኩረት ይሰጣቸዋል። በእያንዳንዱ የሩጫ እንቅስቃሴው ላይ ፕሮፌሰር ያኒስ ክትትል ያደርጋሉ። ውሳኔም ይሰጣሉ።

የባዶ እግር አይነት ጫማ፤ “አፍሪካውያን ሯጮች በጫማና በባዶ እግራቸው ሲሮጡ ሀይላቸው እኩል እንዳልሆነ የሚናገሩት ፕሮፌሰሩ፡ በጫማ ሲሮጡ አንድ ከመቶ ያህል ኃይላቸው ይቀንሳል” ይላሉ። እናም በጫማ ሲሮጡ የሚያጡትን አንድ ከመቶ የሚሆነውን ሀይላቸውን እንዳያጡት የሚያደርግ መላ ዘይደዋል። ይኸውም አትሌቶቹ በባዶ እግር ሲሮጡ የሚኖራቸውን ፍጥነትና አቅም መስጠት የሚችል ልዩ ጫማ ማዘጋጀት ነው። ይህንንም ለቀነኒሳ አዘጋጅተው በበርሊን ማራቶን ለብሶ እንዲሮጥ አድርገዋል። “ጥሩ ውጤት ስላገኘንበት በቀጣይ በፕሮጀክታችን በተለየ ሁኔታ የሚዘጋጅ ጫማ ይኖረናል” ብለዋል።

የስፖርት መጠጥ፤ ሰብ ቱ ሀወር ፕሮጀክትን በዋናነት ይረዳሉ ከተባሉት መንገዶች መካከል አንዱ በሩጫ ጊዜ የሚጠጣ የሚፈቀድ ፈሳሽ የስፖርተኞች መጠጥ ነው። ይህ መጠጥ ሞርቴን በተባለ የስዊድን ኩባንያ የሚመረት ሲሆን፤ በውስጡ የያዛቸው ንጥረ ነገሮች በረጅም ርቀት ሩጫ ወቅት አትሌቶች አቅማቸውን ማደስ የሚችሉ ንጥረ ነገሮችን በውስጡ የያዘ ነው።

ይህንን መጠጥ ቀነኒሳ በበርሊን ማራቶን ሩጫው ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲጠጣ ታይቷል። በወቅቱ ቀነኒሳ ርቀቱን ሊያጠናቅቅ ሲቃረብ ሲል ባልተለመደ ሁኔታ የስፖርተኞች ፈሳሽ መጠጣቱና ፍጥነቱም መጨመሩ ከፍተኛ ጥርጣሬ ፈጥሮ መነጋገሪያ ነበር።

 

 

የናይክ አቋራጭ ጉዞ

ሌሊሳ ዴሲሳን ጨምሮ ሶስት የምስራቅ አፍሪካ ሯጮች ላይ የሚሞከረው የናይክ ብሬኪንግ2 የተሰኘው ፕሮጀክት ከእነ ፕሮፌሰር ያኒስ ከያዙት የጊዜ ገደብ ቀድሞ የሚጠናቀቅ ነው።

ሶስቱም አትሌቶች ኦሪገን በሚገኘው የናይክ የስልጠና ማዕከል ገብተው የመጀመሪያውን ሙከራ በአካል ብቃታቸው ላይ እየተደረገባቸው ነው። በቀጣይም አትሌቶቹ በመረጡት አሰልጣኝና የስልጠና አካባቢና ልምምዳቸውን እንዲሰሩ ይደረጋል። በአመጋገባቸው ሁኔታ ላይ ክትትል ይደረጋል። ጉዳት ሲደርስባቸው ብቻ ሳይሆን ጉዳትን የመከላከል ስራ ይሰራባቸዋል።

አትሌቶቹ በናይክ ፕሮጀክት እስካሉ ድረስ በ2017 የውድድር አመት የፈለጉት ቦታ እየሔዱ አይፎካከሩም። ለንደን በምታስተናግደው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይም ሀገራቸውን ወክለው እንደማይወዳደሩም ታውቋል። መቼ እና የት እንደሆነ በይፋ ባይነገርም ማራቶንን ከሁለት ሰአት በታች ለመሮጥ የሚያስችል የሩጫ መድረክ ናይክ ራሱ ሊያዘጋጅላቸው ይችላልም ተብሏል።

አትሌቶቹ ከአለም ሻምፒዮናም ሆነ ሌሎች የገንዘብ ውድድሮች ላለመሳተፍ እንዲስማማሙ ያደረጋቸው የናይክ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ሲገቡ የሚያገኙት ጥቅም ምን እንደሆነ በይፋ አልተገለጸም። ቢሆንም ግን ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ እንደሚሰጣቸው ይታመናል።

አንዳንዶች አትሌቶቹ ላይ ሙሉ ቁጥጥር ማድረጉን ቢተቹም ሶስቱም አትሌቶች የፕሮጀክቱ አካል መሆናቸው እንዳስደስታቸው ነው የተናገሩት።

 

እውቅና የሌለው ድል

ሁለቱም የማራቶን ፕሮጀክቶች ግባቸው ማራቶንን ከሁለት ሰአት በታች ማጠናቅቅ እንደሚቻል ማረጋገጥ ነው። የፕሮጀክቶቹ ግብ ስኬታማ ቢሆን ለባለቤቶቹ ትልቅ ድል ይሆንላቸዋል። አሳዛኙ ነገር ታዲያ ፕሮጀክቶቹ ግባቸው ቢሳካና አዲስ የአለም ክብረወሰን ቢመዘገብ ስፖርቱን በሚመራው ዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ተቋም እውቅና የማይሰጠው መሆኑ ነው።

የሰብ ቱ ሀወር ፕሮጀክት መሪው ጆስ ኻርመንስ ‹‹እኔን የሚያሳስበኝ ማራቶንን ከሁለት ሰአት በታች ማጠናቀቅ እንደሚቻል ማረጋገጥ መቻል እንጂ እውቅናው አይደለም›› በማለት ለእውቅናው ግድ እንደሌላቸው ገልጸዋል። ፕሮፌሰር ያኒስ ደግሞ፤ ፕሮጀክቱ የተከለከለ አበረታች ቅመሞችን ሳይጠቀሙ ማሸነፍና ክብረወሰን መስበር እንደሚቻል ስለሚያሳይ ወደፊት እውቅና እንደሚሰጠው ተስፋ ያደርጋሉ። አለምአቀፉ የጸረ አበረታች መድሀኒቶች ኤጀንሲ (ዋዳ) ፕሮጀክቱን ለመደገፍ የአንድ ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት መቃረቡ መልካም ምልክት መሆኑ ተነግሯል።

የናይክ ሰዎችም ‹‹ዋናው አላማችን ማራቶን ከሁለት ሰአት በታች ማጠናቀቅ የሰው ልጆች አቅም የሚቻል መሆኑን ማሳየት ነው። ከእኛ በኋላ ሌሎች እንዲሞክሩት መንገዱን ማሳየት መቻላችን በራሱ ትልቅ ድል ነው›› ብለዋል።

የማራቶንን ከሁለት ሰአት በታች ለማጠናቀቅ ዘመቻዎችን በተመለከተ የተለያዩ አስተያቶች እየተሰጡ ነው። እውቅና ለማይኖረው ድል መልፋትን የቂልነት ስራ እንደሆነ የጻፉት ደቡብ አፍሪካዊው የስፖርት ተመራማሪው ሮክ ተከር፤ የእነ ናይክ ዘመቻ ‹‹ለተመልካቾች ግን አዝናኝ ትዕይንት ይሆናል›› ብለዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
289 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us