የአትሌት ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ 100ኛ ዓመት የልደት በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው

Wednesday, 28 December 2016 14:28

 

በአገር አቀፍና በዓለም አቀፍ የስፖርት መድረኮች በመሳተፍ 51 ወርቅ፣ 44 የብር እና 30 የነሀስ ሜዳሊያዎችን በማግኘት ታላቅ ከበሬታን ያገኙት የሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ 100ኛ ዓመት የልደት በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች መከበር ጀመረ። ኢኢጂ ኤቨንት ኦርጋናይዘር ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ በሸራተን አዲስ ሆቴል በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ የታላቁ አትሌት ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ 100ኛ የልደት በዓልና በሩጫ ውድድር የቆዩበት 64ኛ ዓመት በጥምረት ይከበራል ተብሏል።

የጀግናው አትሌት ገናናነትና ታላቅነት አሁን ላለውና ለመጪው ትውልድ በሚገባ ይተላለፍ ዘንድ ይህን መሰል አጋጣሚ መፍጠሩ አስፈላጊ ነው ያሉት አዘጋጆቹ የበዓሉ አከባበር በፎቶ አውደ-ርዕይ፣ በዘጋቢ ፊልም፣ በባለሙያዎች ምስክርነት፣ በተወለዱበት ሱሉልታ ከተማ የሩጫ ውድድር በማዘጋጀትና የአደባባይ ስያሜ እንዲያገኙ በማድረግ ይከበራል ብለዋል።

በስፖርቱ ዘርፍ ያሳዩት ጀግንነት በማራቶኑ ጀግና አትሌት አበበ በቂላ ጭምር የተመሰከረላቸው ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ፤ በጥር 11 ቀን 1909 ዓ.ም ሱሉልታ አካባቢ በምትገኘው አካኮና መና አቢቹ ቀበሌ ማህበር እንደተወለዱ ተነግሯል። እኚህን የሀገር ባለውለተኛ ለማክበርና አርአያነታቸውንም ለትውልድ ለማስተላለፍ የተሰናዳውን ፕሮግራም ኢኢጂ ኤቨንት ኦጋናይዘር፤ ከአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ፣ ከአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና ከሌሎም አጋር ተቋማት ጋር ማሰናዳቱን ተናግሯል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
329 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us