ምሩጽ ይፍጠር፡ ታሪክ የማይዘነጋው የሩጫ ጀግና

Wednesday, 28 December 2016 14:31

በህይወት ዘመናቸው የሚገባቸውን ክብርና እውቅና ሳያገኙ በሞት ከተለዩን ኢትዮጵያውያን ጀግኖች መካከል ሻምበል ምሩጽ ይፍጠር አንዱ ነው። በሩጫ ዘመኑ በተለይም በጉብዝናው አመታት በአለም የሩጫ አደባባባዮች ካስመዘገባቸው አስናደቂ የሀገር ድሎች አንጻር ዘላለማዊ መጠሪያዎችና መታወሻ የሚሆኑ ቋሚ መታሰቢያዎች ሊኖሩት ይገባ ነበር። በስሙ ስታዲየም፣ የውድድር መድረኮች፣ የሽልማት መጠሪያዎች፣ መንገድ ወይም አደባባይ ቢሰየምለትም የሚበዛበት አልነበረም። የጽናትና የድል ምሳሌነቱን የሚያስረዱ ታሪኮቹ ከትውልድ ትውልድ ይተላለፍ ዘንድ በመጽሐፍ፣ በፊልሞች፣ በሌሎች አማራጮችም… የሚዘጋጁለት ነው።

አዲግራት ተወልዶ ያደገው ምሩጽ ሮም ላይ በአበበ ቢቂላ የተጀመረው የኦሊምፒክ የድል ታሪክ አሁን ድረስ ዘልቆ እንዲቀጥል መሸጋገሪያ ድልድይ የሆኑ ድሎችን አስመዝግቧል። በአፍሪካም ሆነ በአለም የሩጫ መድረኮች ብርቱ እግሮቹና አስተዋይ አእምሮው ድምር ውጤቶች የሆኑ የአሸናፊነት ታሪኮቹን አስመዝግቧል።

ሀገር ግን የዘነጋችው ሆና ተገኝታለች። ይህንንም በህይወት በነበረባቸው ጊዜያት በተደጋጋሚ ሲናገር ተደምጧል። ታሪክ ግን እርሱንና አይዘነጋም። ሁሉም የህይወት ገጾቹ በታሪክ ማህደር ሰፍረው በትውልዶችም እየተገለጹ ይነበባሉ።

 

 

ከኦሊምፒክ ወደ እስር ቤት

1972 የሙኒክ ኦሊምፒክ በወንዶች 10.000 እና 5.000 ሜትር ፍጻሜ ኢትዮጵያዊው ምሩጽ ከአውሮፓ አትሌቶች ብርቱ ተፎካካሪ ስለመሆኑ ማንም አልገመተም። ሀገሩ ግን የሜዳልያ ተስፋዋን በእርሱ ላይ ነበር የጣለችው። በ10.000 ሜትር ያልተሳካለትን የወርቅ ሜዳልያ በ5.000 ሜትር እንደሚያገኝ ተስፋ ተጥሎበት ተጠበቀ።

የፍጻሜው ውድድር እለት ምሩጽ ሰውነቱን ሟሟቅ ጀምሯል። አሰልጣኞቹ ንጉሴ ሮባ እና ወልደመስቀል ኮስትሬ ወደ እርሱ መጥተው እስኪጠሩት እየጠበቅን ሰአቱ ደርሷል ብለው አሰልጣኞቹ መጥተው ወደ መሮጫው ሜዳ ሲመሩት ግን የ5.000 ሜትር ፍጻሜ ውድድር ተጀምሯል።

በሙኒኩ ኦሊምፒኩ በማሞ ወልዴ ማራቶንና በምሩጽ 10.000 ሜትር ሁለት የነሐስ ሜዳልያ ያገኘው የኢትዮጵያ ቡድን ወደ ሀገር ቤት ሲመጣ የጀግና አቀባበል አልተደረገለትም። ምሩፅ ግን በተለየ ሁኔታ ወርቅ ባለማምጣቱ በትችት ብቻ አልታለፈም። በ5.000 ሜትር ያልተወዳደርከው ሆን ብለህ ነው በሚል ተከሰሰ። ወደ እስር ቤትም ተወረወረ።

ከኦሊምፒኩ መልስ እስር ቤት የተወረወረው ምሩጽ የሩጫ ልምምዱን አላቋረጠም። አሳሪዎቹ እውነቱን የተረዱ ጊዜ ይለቁኛል በሚል ተስፋ በየእለቱ ሩጫውን ይሰራ ነበር። ከሶስት ወራት በኋላም ከእስር ተለቆ ወደ መደበኛ የሩጫ ልምምዱን ቀጠለ። ከአመት በኋላም በናይጄሪያ ሌጎስ በተካሔደው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ላይ ሀገሩን ወክሎ በ10.000 ሜትር በመሮጥ የወርቅ ሜዳልያን አሸነፈ። 

 

 

ምሩጽ ሞስኮ ኦሊምፒክ

ኢትዮጵያ በሞንትሪያሉ የ1976 ኦሊምፒክ ራሷን በማግለሏ ምሩጽ በሙኒክ ላይ የጀመረውን የ5 እና 10 ሺ ሜትር የንግስና ጉዞ ሊቋረጥ ችሏል። ጽኑው ሯጭ ግን ተስፋ አልቆረጠም። በቀጣዩ የ1980 የሞስኮ ኦሊምፒክ ለመገኘት አቅዶ በትጋት መስራቱን ቀጠለ። ጊዜው ደርሶም በሁለቱም ርቀቶች አሸንፎ ህልሙን እውን አደረገ።

“በሞስኮ ኦሊምፒክ ያስመዘገብኩትን ውጤት ለማግኘት የምችለውን ሁሉ ነው ያደረኩት። ያለኝን ነገር ሁሉ ነው የሰጠሁት” ሲል ተናግሮ ነበር።

በመካከለኛና ረጅም ርቀቶች የበላይነት የነበራቸውን የአውሮፓ አትሌቶች ሞስኮ ኦሊምፒክ ላይ የሰበረው ምሩጽ የአለም መነጋገሪያ ያደረገው የሁለት ወርቅ ሜዳልያ ድሎቹ ብቻ አልነበረም። የእድሜው ጉዳይም ነበር። አወዛጋቢ መረጃዎችም ይወጡ ነበር። እድሜው ከ35 እስከ 40 እንደሆነ በመገመት የተናገሩ መገናኛ ብዙሃን በአንጋፋ እድሜው ማሸነነፉ ተጨማሪ አድናቆት ሊሰጠው ይገባል አሉ። የእርሱ ስምም ከሞስኮ ኦሊምፒክ ጋርም ነጥለው የማይጠሩት ሆነ።

የምሩጽ የሞስኮ ኦሊምፒክ ድል እንደ ኃይሌ ገብረስላሴ አይነት ብርቱ ሯጮች መፈጠር ምክንያት ነበር። የአውሮፓ የበላይነት መስበር እንደሚቻልም የተረጋገጠበት ነበር። የአፍሪካውያን ራጮች ድሎችም በተከታታይ ይመዘገቡ ጀመር። የእርሱ ሕይወት ግን በፈታኝ ውጣ ውረዶች የተሞላ ሆኖ ቀጠለ።

የማርሽ ቀያሪው የመጨረሻዎቹ የክፉ የህይወት ዘመኖች ወደ ተሻለ መንገድ መቀየር አልተቻለም። በ2008 የቤጂንግ ኦሊምፒክ ከኢትዮጵያ ቡድን ጋር በክብር አባልነት ተጉዞ ቢመለስም በሙያው ለማገልገል ቦታ አላገኘም። በፈታኝ ኑሮው ላይ ህመም ተጨምሮ ህይወቱ ይበልጥ አስቸጋሪ ሆነ። ከህመሙ ለማገገም በአደባባይ መዋጮ መጠየቅ አስፈልጎ ነበር።

ኢትዮጵያዊው ጀግና ሩጫውን ሲያበቃ በደስታ በተቀበለችው ካናዳ ላለፉት ሶስት ወራት በላይ ህክምና ሲደረግለት ቆይቶ ነበር። በመተንፈሻ አካሉ ላይ የገጠመው ህመም ለማዳን ግን አልተቻለም። ባለፈው ሐሙስ ማለዳ 11 ሰአት ላይ ህይወቱ ማለፉ ተሰማ።

ምሩጽ በህይወት እያለ የሚገባውን ክብር አላገኘም ሲሉ የሚናገሩት ቤተሰቦቹ አስክሬኑ ወደ ሀገር ቤት ሲመጣ ግን ህዝቡ የጀግና አቀባበል እንዲደረግለት ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል። ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና ሰምሩጽ ይፍጠር ቤተሰቦች የተዋቀረ ኮሚቴ በአስክሬኑ አቀባበልና የቀብር ስነስርዓትን ለማስፈፀም እየሰራ ነው። የጀግናው አትሌት አስክሬን የፊታችን እሁድ አዲስ አበባ እንደሚመጣ የሚጠበቅ ሲሆን ሰኞ እለትም የቀብር ስነስርዓቱ ይከናወናል ተብሏል።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
613 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us