ሞ ፋራህ በእንግሊዝ ከፍተኛውን የክብር ማዕረግ አገኘ

Wednesday, 04 January 2017 14:48

 

የብሪታንያ መንግስት በተሰማሩበት ሙያ የላቀ ውጤት ላስመዘገቡና ሀገርን ላስጠሩ ዜጎች የሚሰጠው “ሰር” የተሰኘው የክብር ማዕረግ ዘንድሮ የመካከለኛ ርቀት ሯጩን ሞ ፋራህን ያካተተ ሆኗል። ሶማሌ እንግሊዛዊው አትሌት በ2016 የውድድር አመት ብቻ ሳይሆን በቀደሙት አመታትም በትራክ ላይ ሩጫዎች የበላይነቱን እንደያዘ አጠናቋል።

የ33 አመቱ ፋራህ በ2016 የሪዮ ኦሊምፒክና በ2012 ለንደን ኦሊምፒክ በ5 እና 10 ሺ ሜትር ርቀቶች በማሸነፍ አራት የኦሊምፒከ ወርቆች ባለቤት ነው። ባለፉት አምስት አመታት በመካከለኛ ርቀት ሩጫዎች ለእንግሊዝ ባንዲራን በተደጋጋሚ በአለም አደባባዮች በድል ማውለብለብ ችሏል። እንግሊዝም ለአትሌቱ ያላትን ክብር ከፍተኛውን የማእረግ መጠሪያ በመስጠት አክብራዋለች። በዚህም እጅጉን ኩራት እንደተሰማው ተናግሯል።

“ይህንን የክብር ሽልማት ገና ከ8 አመቴ ጀምሮ መኖሪያዬ ከሆነችኝ ሀገር በመሸለሜ ትልቅ ክብር ተሰምቶኛል። ወደ ኋላ መለስ ብዬ ያኔ ከሶማሊያ ወደ እዚህ የመጣውና ምንም እንግሊዘኛ የማይናገረው ልጅ ሳስብ አሁን የደረስኩበትን ፈጽሞ አስቤ አላውቅም ነበር። እውን መሆን የቻለ ህልም አይነት ነገር ነው የሆነብኝ። ለሀገሬ የመሮጥ እድል በማግኘቴና ድጋፋቸው ላልተለየኝ የብሪታንያ ህዝቦች የወርቅ ሜዳልያዎችን በማሸነፌ ኩራት ይሰማኛል።

ከሞ ፋራህ በተጨማሪ በሪዮ ኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊና የሁለት ጊዜ የዌምብልደን የሜዳ ቴኒስ አሸናፊ አንዲ መሪ “ሰር” የተሰኘውን የክብር ማዕረግ ችሏል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
294 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us