የዣሚዬን ማራቶን በኢትዮጵያ የበላይነት ተጠናቋል

Wednesday, 04 January 2017 14:51

 

በቻይና ምድር ከሚካሔዱ የጎዳና ሩጫዎች ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማት በሚያገኘው የዢያሜን ማራቶን በሁለቱም ጾታ ኢትዮጵያውያን የበላይነታቸውን ማሳየት ችለዋል።

በአለምአቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የወርቅ ደረጃ የተሰጠው የዢያሜን ማራቶን ባለፈው እሁድ ከ30ሺ በላይ ተሳተፊዎች ተከናውኗል። በሁለቱም ጾታ ኢትዮጵያውያን ከአንድ እስከ ተከታትለው በመግባት የበላይነታቸውን አሳይተዋል።

በሴቶች መካከል በተካሔደው የማራቶን ፉክክር መስከረም መንግስቱ ስታሸንፍ ርቀቱንም በ2፡25፡58 ነው ያጠናቀቀችው። ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ሯጮች ወርቅነሽ ኢዴሳ እና መልካም ግዛው ሁለተኛና ሶስተኛ ሆነው ገብተዋል። ባለፈው አመት በውድድሩ መድረክ አሸናፊ የነበረችው ወርቅነሽ ርቀቱን 2፡26፡27 ስታጠናቅቅ፤ የሲኡል ማራቶንን በሁለተኛነት አጠናቃ የነበረችው መልካም ደግሞ ከወርቅነሽ በሀያ ሰከንደ ዘግይታ 2፡26፡47 በሆነ ሰአት ውድድሯን ጨርሳለች።

አሸናፊዋ አትሌት መስከረም ከውድድሩ በኋላ በሰጠችው አስተያየት አዲስ የቦታውን አዲስ ክብረወሰን ለመስመዝገብ ባትችልም ማሸነፏ እንዳስደሰታት ተናግራለች።

“በውድድሩ ባሸንፍም ፈጣን ሰአት ማስመዝገብ ባለመቻሌ ቅር ብሎኛል። የዛሬው የአየር ንብረት በጣም ሞቃታማና የመሮጫ መንገዶቹም በጣም ፈታኝ ናቸው።” በማለት ፈጣን ሰአት ያላስመዘገበችበትን ምክንያት ተናግራለች። በቀጣይም በ2017 የለንደን ማራቶን በመወዳደር ለማሸነፍ ማቀዷን አስታውቃለች።

በወንዶች መካከል የተካሔደውን ፉክክር ፈጣን ሰአት የነበረው ለሚ ብርሐኑ በ2፡08 በማጠናቀቅ ሲያሸንፍ፤ ሞስነት ገረመውና ሹራ ቅጣጣ ተከታትለው በመግባት ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን አግኝተዋል። የ2016 የዱባይ ማራቶንን 2፡04፡33 በመግባት አጠናቆ የነበረው ለሚ፤ በአስቸጋሪው የአየር ንብረትና የመሮጫ መንገድ ባሉት የዢያሜን ማራቶንን በማሸነፉ መደሰቱን ከውድድሩ በኋላ በሰጠው አስተያየት ተናግሯል።

“ውድድሩን በማሸነፌ በጣም ደስ ብሎኛል። የመሮጫ ቦታው ብዙ ቁልቁለቶችና ዳገቶች ያሉት ነው። የአየር ንብረቱም በጣም ሞቃታማ ነው” በማለት ከ15 እስከ 19 ዲግሪ ሴልሺየስ በነበረው የአየር ንብረት ሮጦ ማሸነፍ ፈታኝ እንደነበር አስረድቷል።

በውድድሩ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው አትሌት ሞስነት ገረመው ርቀቱን 2፡10፡20 ሲያጠናቅቅ፤ ባለፈው አመት በውድድሩ መድረክ ሁለተኛ የነበረው አትሌት ሹራ ደግሞ ከሞስነት 16 ሰከንድ ዘግይቶ በመግባት ሶስተኛ ደረጃን አግኝቷል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
309 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us