የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የዕድሜ ልክ ቅጣት

Wednesday, 04 January 2017 14:53

 

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አዲሱ የስራ አመራር ኃላፊነቱን ከተረከበ በኋላ የመጀመሪያ የተባለ ይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰሞኑን ሰጥቷል። አመራሩ ቀዳሚ ተግባር ያደረገው የተከለከለ አበረታች ንጥረ ነገሮች ከመጠቀም ጋር በተያያዘ የሀገሪቷን የጎደፈ ስምን ማጽዳትን ነው። ይህንንም ለማሳካት በዶፒንግ ምርመራ የሚያዙ አትሌቶች ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ መውሰድ የተሻለ አማራጭ አድርጓል።

 የተከለከለ አበረታች መድሀኒት ከመጠቀም ጋር በተያያዘ ጠንካራ ምርመራ ሊደረግባቸው ከሚገባ ሀገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ሆና መጠቀሷ ይታወቃል። በዚህም የተነሳ የሀገሪቷ የአትሌቲክስ ውጤቶች ጥርጣሬ ውስጥ የወደቁበትና የመልካም ታሪክ ባለቤቶች አትሌቶች ድልም የደበዘበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ይህንን የተበላሸ ታሪክ ለማስተካከል ደግሞ በኃይሌ ገብረስላሴ ፕሬዝዳንትነት የሚመራው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ቀዳሚ እርምጃው ከባድ ቅጣት መጣልን ነው።

ይኸውም የተከለከለ ንጥረ ነገር መውሰዳቸው የሚረጋገጥባቸው አትዮጵያውያን አትሌቶች ሀገርን ወክለው የመሮጥ እድላቸው ዜሮ መሆኑን ነው አመራሮቹ ያሳወቁት።

ይህ ውሳኔ ለዓለምአቀፉ ጸረ ዶፒንግ ኤጀንሲ እና የአትሌቲክስ ማህበር የኢትዮጵያን ጠንካራ አቋም ለማሳየት የነበራትን መጥፎ ምስልና ኢ-ተአማኒነት ለማስተካከል ይረዳል። ሀገሪቷ በድጋሚም ስሟ በዚህ ተግባር እንዳይጠራ የምትፈልግ መሆኗን የሚያስረዳ እርምጃ ተደርጐ ይታሰባል።

ከዚህ በተጨማሪም የፌዴሬሽኑ ጥብቅ ማሳሰቢያ ያዘለው ውሳኔ በቀጣይ የኢትዮጵያ አትሌቶች አበረታች መድሀኒት ላይ የበለጠ ጠንቃቃ እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው። ወደ ሰውነታቸው ውስጥ ለሚገባ ማንኛውም ነገር ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉና ሀላፊነቱንም እንዲወስዱ የሚያስገድዳቸው ነው። ስለዚህም የፌዴሬሽኑ የመረረ ውሳኔ የዶፒንግ ችግርን ለማስቀረት  አዎንታዊ ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል ይታመናል።

በሌላ በኩል ግን ውሳኔው ሁለተኛ እድል አለመስጠቱ ፍትሀዊነቱ ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ ሆኗል። በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ስህተት ውስጥ የሚገቡ አትሌቶች በድጋሚ ወደ ውድድር የመመለስና ሀገራቸውን ወክለው የመሮጥ እድል እንዳይኖራቸው የሚያደርግ ነው። በዶፒንግ ለመጀመሪያ ጊዜ ቅጣት የተጣለባቸው አትሌቶች ቅጣታቸውን ጨርሰው መወዳደር የሚችሉበት መብታቸውን የሚያሳጣ ነው።

በአለምአቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ህግ መሰረት ለመጀመሪያ ጊዜ በዶፒንግ ምርመራ የወደቁ አትሌቶች አራት አመት ከማንኛውም የውድድር መድረኮች እንዳይሳፉፍ የሚያደርግ ቅጣት ይተላለፍባቸዋል። በዶፒንግ የተቀጡ አትሌቶች የአራት አመት ቅጣታቸውን ጨርሰው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች መድረክን ጨምሮ በየትኛውም የውድድር መድረክ የመሳተፍ መብት አላቸው። ቅጣታቸውን ጨርሰው ወደ ውድድር ከተመለሱና በድጋሚ ዶፒንግ ምርመራ የተከለከለ አበረታች መድሀኒት መውሰዳቸው ከተረጋገጠ ግን ቅጣታቸው እስከ ህይወት ዘመን እገዳ የሚረዝም ይሆናል።

ከዚህ እውነት በመነሳትም ቀድሞ ሁለት አመት የነበረው ቅጣት ወደ አራት አመት ከፍ ያለው የእገዳ ቅጣት የሚጣልበት አትሌት ለአራት አመታት ከውድድር መታገድ ትልቅ ቅጣት እንደሆነ መናገር ይቻላል። ብዙ የሚያጡት ጥቅሞች አሉ። ከውድደር ተሳትፎ ጋር የሚያገኟቸው የአሸናፊነትና ሌሎች የገንዘብ ጥቅሞችና ሽልማቶች እንዲሁም ክብሮች ሁሉ አብረው ይቀራሉ። ይህንን ቅጣት በመፍራትም አትሌቶች ተገቢውን ጥንቃቄ እንደሚያደርጉ ይታመናል።

ይሁንና ባለማወቅም ይሁን በማወቅ ዶፒንግ ተጠቅመው የተረጋገጠባቸው አትሌቶች የሚጣልባቸውን የአራት አመት ቅጣት ጨርሰው ወደ ውድድር የመመለስ እድል ሊሰጣቸው እንደሚገባም የሚናገሩ ወገኖች አሉ። የኢትዮጵያ አትቲክስ ፌዴሬሽን በዶፒንግ ላይ ያስተላለፈው ጠበቅ ያለ ውሳኔ መልካም ቢሆንም አለምአቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ የሚሰጠውን በድጋሚ ሀገር ወክለው የመወዳደር መብት መንፈጉ አነጋጋሪ ሆኗል።

ከዚህ ጋር በተያያዘም ፌዴሬሽኑ አስቀድሞ ቅጣቶችን በማጥበቅ ጠዶፒንግ ጉዳይን ለማስቀረት ከመሞከር ይልቅ ግንዛቤ በመስጠቱ ላይ ቢያተኩር የተሻለ እንደሆነም የሚናገሩ አስተያየት ሰጪዎች አሉ። በተለይም ደግሞ በቀደመው የፌዴሬሽኑ አመራሮች ተጀምሮ የነበረው የግንዛቤ ማዳበሪያ መድረኮችን አዲሱ አመራር እንደሚያስቀጥል ይጠበቃል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
329 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us