የአህጉሪቱ ኮከቦች ያልተሳተፉበት 31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በጋቦን

Wednesday, 11 January 2017 14:44

 

የ2015 የአፍሪካ ዋንጫን ከኢኳቶሪያል ጊኒ ጋር በጥምር ያስተናገደችው ጋቦን ሊቢያን ተክት የ2017 የአህጉሪቱን የእግር ኳስ ውድድር ለማከናወን ተዘጋጅታለች። 31ኛው የአፍካ ዋንጫ የፊታችን ጥር 6 ቀን ጋቦን ከኢኳቶሪያል ጊኒ በሚያደርጉት የምድብ ማጣሪያ ጨዋታ ይጀመራል። እስከ ጥር 28 ቀን ድረስም ይቆያል። በውድድሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተሳፈተፈችው ጀምሮ ሰባት ጊዜ አሸናፊዋ ግብጽና ያለፈውን ዋንጫ እስካነሳችው አይቮሪኮስት ድረስ 16 ቡድኖች እኩል ለፍጻሜ ለመድረስ ይፎካከራሉ።


የዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ መድረክ የአህጉሪቱ ኮከቦች በብዛት የማይታዩበት በመሆኑ የውድድሩ ውበት መደብዘዙ አይቀርም። ኮከቦቹ አፍሪካውያን አንዳንዶቹ ከሚጫወቱበት የአውሮፓ ታላላቅ ክለቦች ፈቃድ ባለማግኘት አንዳንዶቹ ደግሞ በየሁለት አመቱ ከሚካሔደው የውድድር መድረክ ይልቅ ውድ ክፍያ ለሚከፍላቸው ክለብ መጫወትን በማስቀደም በጋቦን ምድር አይገኙም።


በምድብ አንድ ጋቦን፣ ጊኒ ቢሳው፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ካሜሮን ይገኛሉ። በዚህ ምድብ አስተናጋጇ ጋቦን በደጋፊዎቿ ብቻ ሳይሆን በጀርመን ቡንደስሊጋ ምርጥ ብቃቱን እያሳየ በሚገኘው እና የ2015 የአፍሪካ ኮከብ ተጫዋቿ ፒዬር ሜሪክ አቡሜያግ መሪነት ምድቡን እንደምታልፍ ይጠበቃል።


ምድብ ሁለት አልጄሪያ፣ ዚምባብዌ፣ ቱኒዚያና ሴኔጋል የሚገኙበት ሲሆን የሞት ምድብ ተብሏል። የሰሜን አፍሪካዎቹ ቱኒዚያና አልጄሪያ የሚያደርት ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል። የምዕራብ አፍሪካዊቷ ሴኔጋልም ጠንካራ ቡድን ይዛ እንደምትቀርብ ይታመናል። የአፍሪካ ዋንጫ ጉዞው በብዙ ውጣ ውረዶች የተሞላው የዚምባብዌ ብሔራዊ ቡድን በጊዜ ከምድቡ ተሰናባች እንደሚሆን ከወዲሁ ተገምቷል።


በምድብ ሶስት አይቮሪኮስት፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ሞሮኮና ቶጎ የሚገኙበት ነው። አይቮሪኮስት ያለፈው አፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ ብትሆንም ምድቡን በቀላሉ ማለፍ የምትችል አይመስልም። ከሶስቱም ተፎካካሪዎቿ ፈታኝ ጨዋታ እንደሚገጥማት ይጠበቃል።


በምድብ አራት ጋና፣ ዩጋንዳ፣ ማሊና ግብጽ ይገኛሉ። የአፍሪካ ዋንጫን በብዛት በማንሳት ክብረወሰኑን የያዘችው ግብጽ ባለፉት ሶስት ውድድሮች ባትሳተፍም ጠንካራ ቡድን ይዛ እንደምትቀርብ መገመት ይቻላል። ባለፈው የአፍሪካ ዋጫ ከአይቮሪኮስት ጋር ለፍጻሜ ቀርቦ የነበረው የጋና ቡድን ዘንድሮም እስከ ፍጻሜው የመገስገስ ብቃት እንዳለው ይታመናል። በቀድው የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ሰርቢያዊው ሚቾ የሚመራው የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ከምድቡ በቀላሉ የማለፍ ግምት ባይሰጠውም ለተፎካካሪዎቹ ፈታኝ እንደሚሆን ይጠበቃል።


የ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ቅዳሜ አስተናጋጇ ጋቦን ከጊኒ ቢሳው በሚያደርጉት ጨዋታ ይጀመራል። በዚያው እለት ካሜሮንና ቡርኪናፋሶ ይጫወታሉ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
488 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us