የበርሊን ማራቶን ክስተት፤ ኢትዮጵያዊው ጉዬ አዶላ

Thursday, 28 September 2017 14:52

በከፍተኛ ጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የበርሊን ማራቶን እሁድ እለት ተካሒዷል። ለወራት ብዙ የተባለለት የ2017 የበርሊን ማራቶን ፉክክር ያልጠበቁ ክስተቶችን በማስተናገድ ተጠናቋል። ለአሸናፊነት ብቻ ሳይሆን ለክብረወሰን ጭምር የተጠበቁት ሯጮች ሳይሳካላቸው ቀርተዋል። ፍጹም ያልተጠበቀ አትሌትም በመድረኩ ታይቷል። ለመጀመሪያ ጊዜ ማራቶንን የሮጠው ኢትዮጵያዊው አትሌት ጉዬ አዶላ የበርሊን ማራቶን ክስተት ሆኖ በመድረኩ ደምቆ ወጥቷል። በመጀመሪያ የማራቶን ሩጫ ፈጣን ሰአት ያስመዘገበ አትሌት ሆኗል።

የአሸናፊነትና ለአለም ክብረወሰንም ግምት ተሰጥቷቸው ከነበሩት መካከል ኢትዮጵያዊው ቀነኒሳ በቀለ እና ኬንያው ዊልሰን ኪፕሳንግ ውድድሩን አቋርጠው ወጥተዋል። ለማራቶን የተፈጠረ ሯጭ የሚባለው ኬንያዊው ኦሊምፒክ አሸናፊ ኢሉድ ኪፕቾጌ የአለም ክብረወሰን የማሻሻል እቅዱ ባይሳካለትም ድል አድርጓል። ኪፕቾጌ ርቀቱን 2፡03፡32 በሆነ ሰአት ነበር ያጠናቀቀው።

በውድድሩ አነጋጋሪ የሆነው ጉዳይ ታዲያ የኪፕቾጌ ማሸነፍ አሊያም የቀነኒሳና ኪፕሳንግ ማቋረጥ አልነበረም። ይልቁንም ትኩረት የሳበው የበርሊን ማራቶንን ሁለተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ኢትዮጵያዊው ጉዬ አዶላ ነበር። ለመድረኩ ብቻ ሳይሆን ለማራቶን ውድድርም እንግዳ የሆነው ጉዬ ርቀቱን በሁለተኛነት ማጠናቀቁ በተጨማሪ ያስመዘገበው ፈጣን ሰአት በአድናቆት እንዲጠራ አድርጎታል።

የ27 አመቱ ጉዬ አዶላ በበርሊን ማራቶን ሁለተኛ ሆኖ ሲገባ ርቀቱን ያጠናቀቀው በ2፡03፡46 ነበር። ይህም ሰአት በመጀመሪያ ሩጫ ፈጣን ሰአት ባለቤት እንዲሆን አስችሎታል። በመድረኩ ምንም ግምት ሳይሰጠው ያስመዘገበው ውጤት ብዙዎችን አስገርሟል።

ከውድድሩ በፊት የአሸናፊነት ግምት ከተሰጣቸው ሶስት አትሌቶችን ጋራ 24 አትሌቶች ስማቸው ተገልጾ ነበር። ይሁንና ብዙ የስፖርት አፍቃሪዎች ከመጀመሪያዎቹ ሶስት የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች ስም ቀጥለው የተገለጹትን ሌሎች ሯጮች የመመልከት ፍላጎት አልነበራቸውም። ቀነኒሳ፣ ኪፕቾጌ እና ኪፕሳንግ ፉክክር ነበር የተጠበቀው። ማንም የጉዬ አዶላን ስም ተመልክቶ ምንም አይት ግምት አልሰጠም።

በውድድሩ ወቅትም ሶስቱ አትሌቶች ግማሽ ርቀቱን በቅርብ ርቀት ሲፎካከሩ ቆይተዋል። ከ30 ኪሎ ሜትር በኋላ ግን የቀድሞው የአለም ክብረወሰን ባለቤት ዊልሰን ኪፕሳንግ አቋርጦ ወጣ። ብዘም ሳይቆይ ቀነኒሳ በቀለ የኪፕሳግ መንገድ ተከተለ። ኪፕቾጌ ብቻውን መርቶ እንደሚያሸንፍ ብዙዎች እርግጠኛ ሆኑ።

ድንገት ግን ውድድሩ ሊጠናቀቅ 10ኪ.ሜ ሲቀሩት ከሁለተኛው መሪ ቡድን ጋር የነበረው ኢትዮጵያዊው ጉዬ አዶላ ከኪፕቾጌ አጠገብ ደርሶ ታየ። አንዴ ከኋላ፣ ደግሞም ከፊቱ እየሮጠ ጠንካራ መንፈስ በማሳየት ለኬንያዊው ሯጭ ስጋት ሆኖ ተገኘ። ከዚህ ክስተት በኋላም የአትሌቱ ስም በመገናኛ ብዙሀን እና ማህበራዊ ገጾች በተደጋጋሚ ይጠራ ጀመር። የአትሌቱ ማንነትም ትኩረት መሳብ ቻለ። በተለይም በትዊተር ገጽ በእለቱ በተደጋጋሚ የተጠቀሰ ስም የጉዬ አዶላ ነበር።

ምንም እንኳን ከበርሊኑ መድረክ በፊት ብዙዎች ባያውቁትም ጉዬ አዶላ በአለም አቀፍ መድረክ ተሳትፎ ሜዳልያ ማግኘት የቻለ አትሌት ነው። ከሶስት አመት በፊት በዴንማርክ ኮፐንሀገን በተካሔደ የአለም የግማሽ ማራቶን ውድድር ሶስተኛ ደረጃ በማጠናቀቅ የነሐስ ሜዳልያ ተሸላሚ ነበር። ቀጥሎም በኢትዮጵያ ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና አራተኛ፤ በስዊዘርላንድ ግማሽ ማራቶን ሶስተኛ፤ እንዲሁም አንጎላ ላይ በሉዋንዳ ግማሽ ማራቶን ተመሳሳይ ሶስተኛ ደረጃን አግኝቷል።

የዛሬ ሶስት አመት በ2014 በህንድ የዴልሂ ግማሽ ማራቶንን ሲያሸንፍ ያስመዘገበው የግል ፈጣን ሰአት 59፡06 ነበር። ይህም እሁድ እለት በበርሊን ማራቶን የአሸናፊነት ግምት ከተሰጣቸው ሶስት አትሌቶች ካስመዘገቡት ሰአት የተሻለ ነው። ይህም ቢሆን ምርጥ የማራቶን ሯጭ ሊያደርገው እንደማይችል ነበር የተገመተው።

በእሁዱ የበርሊን ማራቶን ግን ጉዬ አዶላ ቀነኒሳና ኪፕሳንግ አቋርጠው ከወጡ በኋላ የብዙዎችን ግምት ያፈራረሰ አቋም ማሳየት ችሏል። የማራቶን ስፔሻሊስት ለሚባለው ኪፕቾጌም ስጋት ሆኖ ተገኝቷል። ውድድሩ 10 ኪሎ ሜትር ሲቀሩት በመታጠፊያ ቦታዎች ላይ እያሰፋ መሮጡ የማራቶን ጀማሪነቱን ያሳበቀ ነበር። ፍጥነቱን በማዘግየትም ዋጋ አስከፍሎታል።

የሪዮ ኦሊምክ የማራቶን አሸናፊው ኢሉድ ኪፕቾጌም የረጅም ጊዜ ልምዱን ተጠቅሞ በመጨረሻዎቹ ኪሎ ሜትሮች ላይ ኢትዮጵያዊውን አትሌት ቀድሞት መግባት ችሏል። ከውድድሩ በኋላ በሰጠው አስተያየትም የበርሊን የአየር ንብረት ቀዝቃዛና ዝናባማ መሆኑ የአለም ክብወሰንን ለማስመዝገብ የነበረውን እቅድ እንቅፋት እንደሆነበት አስታውቆ፤ ውድድሩን በማሸነፉ ግን መደሰቱን ተናግሯል። እርሱን ተከትሎ ለገባው ኢትዮጵያዊ አትሌትም አድናቆቱን ገልጿል።

“ኢትዮጵያዊው አትሌት በውድድሩ ያሳየው አቋም እጅግ አስደንቆኛል። ጠንካራ ተፎካካሪ እንደሚሆኑ የገመትኩት ቀነኒሳ እና ኪፕሳንግን ነበር። ይሄ ወጣት አትሌት ግን ሳይጠበቅ እስከመጨረሻው ያሳየው ሩጫ አድናቆት ይገባዋል” ብሏል።

በመጀመሪያ የማራቶን ሩጫው ያልተጠበቀ ብቃት ያሳየው ጉዬ አዶላ በቀጣይ የርቀቱ ምርጥ ሯጭ እንደሚሆን ከወዲሁ ግምት ተሰጥቶታል። በተለይም በበርሊን ማራቶን ያሳየው አሯሯጥ፣ የታላላቅ ሯጮች የስነ ልቦና ጫና ሳይበግረው መፎካከሩና የውጤት ደረጃ ውስጥ መግባቱ ተስፋ እንዲጣልበት አድርጓል።

በጣሊያኑ ማናጀር ጂያኒ ዴማዶና ጋር የሚሰራው ጉዬ አዶላ ከውድድሩ በኋላ በሰጠው አስተያየት በቀጣይ መድረኮች የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚሮጥ ነው ያስታወቀው። በተደጋጋሚ የውድድር መድረኮች ላይ በመሳተፍ ልምድ ማግኘት ሲችል የበለጠ ውጤታማ እንደሚሆንም ተናግሯል። ለመጀመሪያ ጊዜ ማራቶንን በሮጠበት በርሊን ማራቶን ያስመዘገበው የሁለተኛነት ውጤትና ፈጣን ሰአትም እጅጉን ደስተኛ መሆኑን ነው የገለጸው።

ከጉዬ አዶላ በተጨማሪ በውድድሩ ያልተጠበቀ ውጤት ያስመዘገበው ኢትዮጵዊ ሞስነት ገረመው ነው። አትሌቱ ርቀቱን በ2፡06፡09 በማጠናቀቅ ሶስተኛ ደረጃን ማግኘት ችሏል። አትሌቱ በጎዳና ላይ ሩጫዎች የመሳተፍ ልምድና ውጤት ቢኖረውም በርሊን ላይ ያስመዘገበው ውጤት በትልቅ የውድድር መድረክ ትልቅ የሚባል የመጀመሪያ ውጤቱ ነው።

በተያያዘ ዜና በበርሊን ማራቶን በሴቶች መካካል የተካሔደውን ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ ሩታ አጋ ርቀቱን 2፡20፡23 በማጠናቀቅ ሁለተኛ ደረጃን አግኝታለች። ኬንያዊቷ ግላዲ ቼሬኖ በ2፡20፡23 ቀዳሚ ሆና የገባች ሲሆን፤ ሌላዋ የሀገሯ ልጅ ቫለሪ አያቤ በሶስተኛነት አጠናቃለች።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
131 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1020 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us