ጠቅላላ ጉባኤው አስመራጭ ኮሚቴ ለመምረጥ ይሰበሰባል

Wednesday, 22 November 2017 12:52

 

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የአመራሮች ምርጫ የአንድ ወር ያህል ጊዜ ቀርቶታል። ከሳምንት በፊት በአዲስ አበባ ተሰብስቦ የምርጫ ጊዜውን ያራዘመው ጠቅላላ ጉባኤ የአስመራጭ ኮሚቴ ላይ ውሳኔ ሳያስተላልፍ መበተኑ ይታወሳል። ፌዴሬሽኑ በነገው እለት በአዲስ አበባ በጠራው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ላይም አስመራጭ ኮሚቴ ይቋቋማል ተብሏል።

በፊፋ የምርጫ ደንብ መሰረት የብሔራዊ ፌዴሬሽኖች የአመራር ምርጫ በዲሞክራሲያዊ ሒደት ለማካሔድ ገለልተኛ የሆነ አስመራጭ ኮሚቴ መቋቋም አለበት። ኮሚቴውም የሚያካትታቸው አባላት ከተለያዩ የሙያ ዘርፎች የተውጣጡ በእግር ኳስ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳትፎ የሌላቸው፣ በእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ውስጥ የማይሰሩና የሚሰራ ዘመድም የሌላቸው፣ ከተወዳዳሪዎች ጋርም ምንም አይነት ዝምድና የሌላቸው መሆን ይኖርባቸዋል።

የአስመራጭ ኮሚቴው ዋና እና ምክትል ፕሬዝዳንት እንዲሁም ዋና ጸሐፊ ይኖረዋል። ሌሎች ደግሞ በአባልነት የሚያዙ ይሆናል።

የአስራጭ ኮሚቴ አባላቱም ግለታሪክም በጠቅላላ ጉባኤ ላይ የሚቀርብ ቀርቦ በዝርዝር የሚተዋወቅ ሲሆን፤ ለተወዳዳሪዎች ወገንተኛ እንዳልሆነ ሲታመንበት ብቻ በአስመራጭ ኮሚቴ ውስጥ እንዲካተት ውሳኔ ይሰጥበታል። አወዛጋቢ ሁነቶች በሚኖሩ ጊዜም ሲሆን በድምጽ ብልጫ ውሳኔ ይተላለፍበታል።

በአስመራጭ ኮሚቴው ዋና ጸሐፊ ሆኖ የሚመረጠው ሰው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑን በዋና ጸሐፊነት የሚያገለግል ሰው ነው። በአሁኑ ወቅት ዋና ጸሐፊው አቶ ወንድምኩን አላዩ ከሀላፊነታቸው ለመነሳት መልቀቂያ በማስገባታቸው እሳቸውን የሚተካው ሰው ማን እንደሚሆን አልታወቀም። ግለሰቡ ወደ ስራቸው እንዲመለሱ የሚደረገው ድርደር ከተሳካ በአስመራጭ ኮሚቴው ውስጥ የሚያገለግሉ ሲሆን፤ እሳቸው ካልሆኑ ምናልባት ምክትላቸው መስከረም ታደሰ ልትሆን እንደምትችል ይገመታል።

የአስመራጭ ኮሚቴው ዋንኛ አላማና ተግባር የአመራር ምርጫው ህጋዊና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን ማድረግ ነው። ይህንንም ለማከናወን ኮሚቴው ውሳኔዎችን የማስተላለፍ ስላጣንና ሀላፊነት አለው።

ከምርጫው በፊትም የአስራጭ ኮሚቴው በእጩነት የሚቀርቡ ተወካዮች ግለ ታሪክ በዝርዝር ቀርበውለት ይመለከታል። ውክልናቸው ትክክል መሆኑን በማጣራትም ውሳኔ ያስተላልፋል። ተገቢ ያልሆነ ውክልና ወይም እጩ መኖሩን ካረጋገጠ እስከ ማስወጣት ድረስ የመወሰን መብት አለው።

እጩዎች ያልተገባ ተግባር ሲፈጽሙ ካገኘ የእርምት እርምጃ ከመውሰድ ጀምሮ ከምርጫው እስከማገድ ድረስ ስልጣን አለው።

የምርጫው እለትም የድምጽ አሰጣጡ ሚስጥራዊ መሆኑን ማረጋገጥና በአጠቃላይም የምርጫ ሒደቱ ህጋዊ መስመር ይዞ እንዲከናወን የማድረግ ሀላፊነት አለበት።

በመጨረሻም የምርጫው ውጤት በተገቢው መንገድ ይፋ እንዲሆን ያደርጋል። ለካፍ እና ለፊፋ ተወካዮችም አጠቃላይ የምርጫ ሒደቱንና ውጤቱን በተመለከተ ዝርዝር ሪፖርት ያቀርባል።

ይህና ሌሎችም ኃላፊነቶች ያሉት የአስመራጭ ኮሚቴ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ ከተቋቋመ በኋላ ከቀጣዮቹ ቀናት ጀምሮ በፍጥነት ስራውን እንደሚጀምር ይጠበቃል።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
102 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 997 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us