የወልዲያው ግጭትና የስፖርት ሁከቶች ሀገራዊ ስጋት

Wednesday, 06 December 2017 13:33

 

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እሁድ እለት በወልዲያና መቀሌ ከተማ የእግር ኳስ ቡድኖች መካከል ሊካሔድ የነበረው ጨዋታ ሳይከናወን ቀርቷል። ሁለቱ ክለቦች ጨዋታቸውን ከማድረጋቸው በፊት ረፋዱ ላይ በደጋፊዎቻቸው መካከል የተነሳው ጸብ ከዚህ በፊት ተከስተው ከነበሩ የተቃራኒ ቡድን ደጋፊዎች ግጭቶች በተለየ ሁኔታ አስከፊ ጉዳቶችን ያስከተለ ነበር።

በቃላት የተጀመረው የሁለቱ ቡድን ደጋፊዎች መዘላለፍ፣ አካላዊ ጸብን አስከትሎ ብዙዎችን ለአካል ጉዳት ዳርጓል። የሁለት ሰዎች ህይወት መጥፋቱም ተገልጿል። በአካባቢው በሚገኙ ሀብትና ንብረቶች ላይም ውድመትን አስከትሏል። በሁለቱ ክለቦች መገኛ ህዝቦችን ግንኙነት የሚያሻክርና እንደ ሀገርም ስጋትን የፈጠረ ነው።

የአማራ ክልል የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በጉዳዩ ላይ ለኢቢሲ በሰጡት ምላሽ እሁድ እለት በማለዳው የተጀመረ ሁከት በሒደት እያደገ በሰዎችና በንብረት ላይ ጉዳቶችን አስከትሏል። “የተፈጠረው ችግር የስፖርት ደጋፊውንም ሆነ የአካባቢውን ማህበረሰብ የማይገልጽ፤ ነገር ግን ጥንቃቄ በጎደለው መልኩ ስሜት ውስጥ የሚከቱ ግጭቶች ነበሩ” ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በደጋፊዎች መካከል የሚከሰቱ ግጭቶችና ጉዳቶች ቢኖሩም ብዙዎቹ መንስኤያቸው በቀጥታ ከስፖርቱ ጋር የተያያዘ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በእግር ኳስ ቡድኖች ደጋፊዎች መካከል የሚከሰቱ ግጭቶች የወልዲያውን ጨምሮ ከስፖርቱ ጋር ብቻ የተያያዘ ብቻ እንዳልሆነ መናገር ይቻላል።

ስፖርቱ እንዲያድግና እንዲስፋፋና ህዝባዊ መሰረትን እንዲይዙ የሚደረገው ጥረት በከፊል ውጤታማ እያስገኘ ቢሆንም አሉታዊ ተጽዕኖዎቹ ግን ባልተጠበቀ ፍጥነት ጎልተው ወጥተዋል። ከቅርብ አመታት ወዲህ በተለያዩ አካባቢዎች የሚመሰረቱ ክለቦች ብሔርንና አካባቢን መሰረት ያደረጉ መሆናቸው በደጋፊዎቻቸው መካከል የሚከሰቱ አለመግባባቶችም የብሔር መልክ ሊይዙ ችለዋል።

እንዲህ ያለው ችግር ደግሞ በጊዜ መፍትሔ አግኝቶ ካልተገታ ሀገርንም ለመበታተን ስጋት መሆኑ አይቀርም። በሌሎች የአለማችን ሀገሮች የተፈጠሩ ተሞክሮዎችም ይህንኑ ስጋት የሚያጠናክሩ ሆነው ነው የምናገኛቸው።

አሁን የስፖርት ሜዳ ግጭቶች የስታዲየም ወንበሮችን በመሰባበርና ከደጋፊ ጋርም ቡጢ በመሰንዘር ብቻ የሚያበቁ አልሆኑም። የሰው ህይወት መጥፋትን፤ የንብረት መውደምንም እያስከተሉ ነው።

እንዲህ አይነት ጥፋቶች በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ገና ከመጀመሩ ነበር ጎልተው የወጡት። አዲግራት ላይ የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ ቡድን ከፋሲል ከነማ ባደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ ላይ በደጋፊዎች መካከል የተነሳ ጸብ የአካል ጉዳቶች ያስከተለ ነበር።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም በዚህ ችግር ላይ ምርመራ አድርጎ ተገቢውን ውሳኔ ሳያስተላልፍ መቅረቱ ለችግሩ መባባስ መንስኤ ተደርጎ ሊነሳ ይችላል። በዚህም የተነሳ ክለቦችና ደጋፊዎቻቸውም በፌዴሬሽኑ እምነት አጥተው የራሳቸውን የመፍትሔ መንገዶች ለመውሰድ እንደተገደዱ መረዳት ይቻላል። ይህ ደግሞ ያልተገባ መንገድ በመሆኑ ከፍተኛ ጥፋትን እያስከተለ ይገኛል።  

እሁድ እለት በወልዲያ ከተማ በደጋፊዎች መካከል የተለኮሰው ጸብ ወደ አስከፊ የጥፋት መንገድ ለማምራቱ ፌዴሬሽኑ በቀጥታ ተጠያቂ የሚሆንበት ድርሻ እንዳበረከተ መናገር ይቻላል። ከዚህ ቀደም የተከሰቱ የደጋፊዎች ግጭቶች መነሻቸውን መመርመርና ፍትህ ካለመስጠቱ ባሻገር ከፍተኛ ረብሻ ሊነሳባቸው የሚችሉ ጨዋታዎችን ቀድሞ በመገመት ተገቢውን ቅድመ ጥንቃቄ አለማድረጉ በሰውና በንብረት ላይ ጥፋቶች እንዲከሰቱ አድርጓል።

በ2009 የውድድር አመት ላይ መቀሌ ላይ መቀሌ ከተማ እና ባህር ዳር ከተማ ጨዋታ ላይ በደጋፊዎች መካከል የተከሰተው ግጭት ችግሩ አሳሳቢ እንደሚሆን ፍንጭ ሰጥቶ ነበር። በዚሁ በ2010 አመት መጀመሪያ ላይም በወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ እና ፋሲል ከተማ ቡድኖች ጨዋታ የተፈጠረው ግጭትም ከፍተኛ የማስጠንቀቂያ ደወል ሆኖ ፌዴሬሽኑን ሊነቃው ይገባ ነበር።

በደጋፊዎች የሚነሱ ሁከቶች ምክንያታቸው ምንም ሊሆን ቢችል ስፖርታዊ እንዲኖር ፌዴሬሽኑ ከአካባቢው የጸጥታ ሀይሎችና አስተዳደር እንዲሁም ከማህበረሰቡ ጋር ተቀናጅቶ መስራት ይጠበቅበታል። ግጭቶች እንዳይከሰቱና ሊደርሱ የሚችሉ ጥፋቶችን ለመቆጣጠር አሊያም ለመቀነስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ፌዴሬሽኑ ከባለድርሸ አካላት ጋር በመሆን ግንዛቤ ከማስጨበጥ ጀምሮ በርካታ ስራዎችን የማከናወን ሀላፊነት አለበት።

ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ባለፈው ቅዳሜ የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህር ከኢቢሲ ጋር በመሆን ባዘጋጀው ሀገር አቀፍ ሲምፖዚየም ላይ በርካታ ተሳታፊዎች እንደገለጹትም የስፖርት ስርአት አልበኝነት ለሀገር መበታተንም ትልቅ ስጋት ነው። ችግሩ በቀጣይ ጊዜያትም በተለያዩ የስፖርት መድረኮች ላይ ተባብሶ ሊቀጥል ስለሚችል ባለድርሻ አካለት ፈጣንና ፍትሀዊ እርምጃዎችን መውሰድ ይጠበቅባቸዋል።¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
147 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1015 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us