የኢትዮጵያ ቡና ጉዞ … እንዘጭ እንቦጭ ወይስ ተስፋ ሰጭ ?

Wednesday, 27 December 2017 12:54

 

 ሙሉጌታ ደሳለኝ (የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ህዝብ ግንኙነት)

መነሻ የቅርብ ሩቅ ታሪክ

ከሁለት ዓመት በፊት ሁዳዴ ፆም ለስራ አመራር ቦርዱ የርሃብ ሳይሆን የሰው ርብርብ አጣብቂኝ ሆነበት ። በክለቡ ወቅታዊ ውጤት ደስተኛ ያልሆኑ ደጋፊዎች ነባር ጥያቄዎችን በማከል ጩኸታቸውን ማሰማት ጀመሩ ። ችግር ፈጣሪ ነው ብለው ያሰቡት እና መፍትሄው የስራ አስኪያጁ መነሳት እንደሆነ ባገኙት አጋጣሚ መስበክን ተያያዙት … የአስተዳደሩ ሰለባ ነን ያሉ ሌሎች አካላት ጎራውን ተቀላቀሉ ። የተቃውሞው እድገት ግለሰቡን በመልክ እንኳ ወደማያውቁት ደጋፊዎች ተሸጋግሮ ስታዲየሙ በውጣልን ጩኸት መናጥ ጀመረ … አጫጭር ስብሰባዎች በረከቱ። በዚህ ወቅት የስራ አመራር ቦርዱ የአጣብቂኝ ውሳኔ ለመወሰን ተገደደና በማባረር ሳይሆን በስምምነት አስፈላጊው ጥቅማ ጥቅም ተከብሮለት ስራ አስኪያጁ ከክለቡ ለቀቀ። አራት አስርተ አመታት ባስቆጠረው የክለቡ ታሪክ እንዲህ አይነት የውስጥ ተቃውሞ ሲነሳ የመጀመሪያ እንደሆነ ይነገራል፤ ሌሎች አካላትን (እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ መንግስትን፣ ጋዜጠኞች እና ሌሎችንም) ከዚህ በባሰ መልኩ መጠየቅና መቃወሙ እንዳለ ሆኖ ማለት ነው። ለመነሻችን ክስተቱን አነሳን እንጂ ብዙ ክርክር የሚያስነሳውን ምክንያትና ውጤቱን በሌላ ፅሁፍ እመለስበታለሁ።

 

የቡና ጉዞ ከየት ወዴት?

      በ1968 ዓ.ም በፋብሪካ ሰራተኞች ተነሳሽነት ጥንስሱን አድርጎ … በወዳጆቹ ልብ ተቆልቶ … በወቅቱ የፋብሪካው የመንግስት አመራሮች መልካም ይሁንታን አግኝቶ ምስረታው ይፋ ሆነ። ንጋት ኮከብ (በዚህ ስም ተመዝግቦ የተጫወተበት የፅሁፍ ማስረጃ የለም) እና ቡና ገበያ ነባር መጠሪያዎቹ ናቸው። ኋላም ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ ሁሉንም በቡናው ዘርፍ ላይ ያሉ አካላትን ለመወከል በሚያመች መልኩ ስሙ ኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ (ከእግር ኳስ ውጪ በቦክስና መረብ ኳስ ይካፈልም ስለነበር እግር ኳስ ክለብ ብቻ ሳይሆን ስፖርት ክለብ መባሉን ልብ ይሏል) ተብሎ ውድድሩን በመካፈል ላይ ይገኛል። በ42 ዓመት ጉዞው ከድል ታሪኩ በላይ ያሳለፈው ውጣ ውረድ የጎላ ነበር … የመፍረስ አደጋን ተጋፍጧል፤ የፋይናንስ ቀውስ ህልውናውን ተፈታኖታል ፤ የውስጥ ጣጣ አምሶት ያውቃል፤ ግራ የሚያጋቡ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ውሳኔዎችን ፊት ለፊት በመቃወም ዋጋ ሲከፍልም ቆይቷል። ሁሉም ክስተቶች ግን የሁነኛ ደጋፊዎቹን ቁጥር ከአመት አመት ሲጨምሩት እንጂ ሲቀንሱት አይታዩም። አምስት የጥሎ ማለፍ፣ ስድስት የአሸናፊዎች አሸናፊ እና አንድ የፕሪምየር ሊግ ዋንጫዎች በመደርደሪያው ላይ በክብር በከፊል ከተደረደሩት ውስጥ ናቸው። በዚህ አጋጣሚ ቡና በተለያዩ አጋጣሚዎች ያነሳቸውን ዋንጫዎች ሁሉ በቢሮው ማግኘት አስቸጋሪ ነው፤ በቅርቡ ድምፃዊ ታደለ ሮባ ከተናገረው (ታሪካዊው የይደነቃቸው መታሰቢያ ዋንጫ እሱ ጋር እንደሚገኝ) በተጨማሪ በቁመቱ የእህል ሙቀጫ (መውቀጫ) ያክላል የተባለው በአትሌቲክስ የተገኘ ዋንጫ የት እንደደረሰ አይታወቅም።

ቀን ነጉዶ ዛሬ ዛሬ በአስደንጋጭ መልኩ የቡና መለያ ማራኪ ጨዋታ እና የድጋፍ ድባብ ብቻ ሳይሆን በየአመቱ አሰልጣኝ መቀያየር እየሆነ ከመጣ ሰነበተ። ከአስር አመት በላይ ለሆነ ጊዜ ከአሰልጣኝ ውበቱ አባተ (ሁለት አመት 2003/2004 ዓ.ም ቡናን ያሰለጠነ አሰልጣኝ) ውጪ ክለቡን የሚይዙ አሰልጣኞች ሁሉ ሁለት አመት የሚዋዋሉ ነገር ግን አንዱን አመት በማስጠንቀቂያ የሚጨርሱ ሆነዋል። ይህ ያለመረጋጋት ውሳኔው የከፋ ሆኖ ከ2009 ዓ.ም በኋላ አመት ከሰባት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሰባት ዋና አሰልጣኝ የሚታይበት ከባድ ጊዜ መጣ። አመት ከሰባት ወር ከሰባት አሰልጣኝ በላይ ያዩ ተመሳሳይ ተጫዋቾች ደግሞ በከባድ ጫና ውስጥ እንደሚጫወቱና እንደተቸገሩ በድፍረት መናገር ጀምረዋል። ለውጡን ከባድ ካደረገው ዋናው ከሰባቱ ውስጥ አራቱ አሰልጣኞች የሀገሪቷን የእግር ኳስ ባህልና ደረጃ የማያውቁ የውጪ አሰልጣኞች መሆናቸው እንዲሁም በቴክኒክ ዳይሬክተር እየሰለጠነ በአካል ብቃት አሰልጣኝ ሜዳ ውስጥ የሚገባ ቡድን መታየት መጀመሩ ጭምር ነው ። በግለሰቦች መቀያየር ያልተፈታው የውጤት ርሃብ እንዲሁም በድጋፍ ውስጥ እያደገ የመጣው የጠያቂነት መንፈስ የሰዉን እይታ ቀይሮታል ። ለቡድን ውጤት ማጣት ብቸኛ ተጠያቂና ሀጥያት ማወራረጃ አሰልጣኙ ብቻ ወይስ ሌሎችም ? ከሜዳ ውጪ ያለው የክለቡ አስተዳደራዊ ስራ በምን ይገመገማል ? የደጋፊው ሚና የት ድረስ ነው ? ቀጣይ የክለቡ እጣ ፋንታ እና ጉዞ ወዴት እያመራ ነው ? … እነዚህን ጥያቄዎች ብቻ መዘን የተወሰኑ ሃሳቦች እናንሳ ።

 በፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ተፅፎ በቅርቡ ለንባብ በበቃው 'እንዘጭ እንቦጭ' መፅሐፋቸው የኢትዮጵያን ሁኔታ ካስቀመጡበት አመክንዮ ዋናው … ችግራችን በስርዓት ለውጥ ላይ ሳይሆን በግለሰቦች ለውጥ ላይ ማነጣጠራችን ነው፤ እያንዳንንዱ በገዢዎቹ ላይ ቂም በመያዝ ሳይደራጅና ሳይወያይ በማድፈጥ በመቆየት ኋላ ላይ ቀን ሲደርስ አንባ ይፈርስ እንደተባለው ዘላቂ መፍትሄ ሳይሆን የገዢዎች ለውጥ ብቻ እንደመጣ በማስረጃ ይሞግታሉ (ሀሳቡ ቃል በቃል ያልተወሰደ)። ከዚሁ አውድ ተነስተን የቡናን ድባብ ስንቃኘው ሁነኛ የችግሩ ሰለባ ሆኖ እናገኘዋለን። ችግሮች ሲፈጠሩ ስርዓትና መመሪያዎችን ከማስተካከልና ከማሻሻል በላይ መንስኤውን ወደ ውጪ አካል በመወርወር እንዲሁም ከፊት ተጋፋጭ የሆኑ ግለሰቦችን በማባረር ላይ የተመሰረተ መፍትሄ የመውሰድ የታሪክ አዙሪት ውስጥ ተገብቷል። አሰልጣኞች፣ ተጫዋቾች፣ አስተዳደራዊ ሰራተኞች፣ የደጋፊ ማህበር አመራሮች እና ሌሎችም በክብር ሳይሆን በነቀፌታ ተሰናብተዋል፤ ችግሩ ግን እስካሁንም አልተፈታም።

በኢትዮጵያ ቡና ዙሪያ የሚሰጡ ሀሳቦችን ስናይ ብዙዎች ሜዳ ላይ የሚገባውን የወንዶች ዋና ቡድን ብቻ በማየት ውዳሴና ወቀሳ ያቀርባሉ፤ ጥቂቶች በአመዛኙ ከመጋረጃ ጀርባ ያለውን ምስል ጭምር በመግለጥ ለማሳየት ይጥራሉ። የሁለቱም የሃሳብ ልዩነት እንዳለ ሆኖ ሁሉንም አንድ የሚያደርጋቸው ዋና ጉዳይ ክለቡ የቁልቁለት ጉዞ ላይ መሆኑን ማመናቸው ነው።

 

 

ፋይናንስና ቡና ፡-

እግር ኳሱ አሁን ላይ ከሚፈልገው ከፍተኛ ኢንቨትመንት አንፃር በቡና ቤት ውስጥ በፋይናንስ ረገድ መንገራገጭ እንዳለ የውስጥ የመረጃ ምንጮች ያሳያሉ፤ ትንሹ ማሳያ የተጫዋቾች ማበረታቻ ክፍያ (Insentive) በወቅቱ ያለመከፈል ሊጠቀስ ይችላል። የቡና የገቢ ምንጮችን በየደረጃው ስናይ ከቡናው ሴክተር ላይ ካሉት ባለድርሻ አካላት በቶን የሚቆረጥ 30 ብር፣ ከስፖንሰሮች (የማሊያ ላይ ስፖንሰር እና ሌሎች ስፖንሰሮች)፣ የክለቡ አርማ ያረፈባቸው ቁሳቁስ ሽያጭ እና የስታድየም የሜዳ ገቢ ናቸው። አማራጭ የገቢ ምንጮች ካለማምጣት በተጨማሪ ያሉትን በእቅድ ማጠናከር ላይ ክፍተቱ እየጎላ መምጣቱ ጉዞውን ባለህበት እርገጥ አድርጎታል። በተለይም በቅርብ ጊዜያት የክልል ተሳታፊ ክለቦች በመጨመራቸው ተዘዋውሮ የመጫወት ወጪን ማናሩ፣ የተጫዋቾችና አሰልጣኝ ክፍያ ማደግ፣ ገቢ ሳይጨምር አስተዳደራዊ ወጪዎች መጨመር፣ ከቡናው ሴክተር የሚገኝ ገቢ መቀነሱ፣ ቡናው ሴክተር ላይ ሆነው የገንዘብ አስተዋፅዖ የማያበረክቱ መኖራቸው፣ ተጨማሪ ስፖንሰር ያለመቀላቀል እንዲሁም ከቁሳቁስ ሽያጭና ሌሎች የማርኬቲንግ ዘዴዎች የሚገኙ ገቢዎች አለመኖር ታክሎበት ወደ ሌላ ሂሳባዊ ትንታኔ ሳንገባ በሃሳብ እንዲሁ ግራ እንድንጋባ ያደርገናል።

 

አስተዳደራዊ ቁመና፡-

ክለቡ ከሜዳ ላይ ውጤቱ በፊት አስተዳደራዊ ቁመናው ነጥብ መጣል ከጀመረ ሰነባብቷል። በ2004 የተጠናው የአደረጃጀት ጥናት ምሉዕ ባይሆንም ለሌላው ክለብ ተሞክሮ ሊሆን በሚችል መልኩ ከላይ እስከ ታች ያለውን መዋቅር በግልፅ አስቀምጧል። ጠቅላላ ጉባኤ፣ ስራ አመራር ቦርድ እና ፅ/ቤት ከላይ ወደ ታች እንዲሁም ከደጋፊ ማህበርና ሌሎች ጋር ስላለው የጎንዮሽ ግንኙነቶች ይዳስሳል። ይህ ጅምር በሂደት ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ የአብዮት (Revolution) ሳይሆን ጥገናዊ (Reform) ለውጥ ያስፈልገው እንደነበር ግን አምናለሁ። በተቃራኒው ከላይ በተጠቀሱት የስልጣን እርከኖች ላይ በሂደት እየሆኑ ያሉ አጠያያቂ ጉዳዮችን እናንሳ ፡-

1ኛ. በተከታታይ ለስድስት አመት ህዳር ወር ላይ ይካሄድ የነበረው አርባ አባላት ያሉት ጠቅላላ ጉባኤ ዘንድሮ አልተካሄደም ። ስለዚህም በየትኛው ጉባኤና ምክር ቤት የፀደቀ በጀትና አመራር ይዘን ስራ እየሰራን ነው ? የስራ አመራር ቦርዱ ተጠሪነት ለጠቅላላ ጉባኤው መሆኑ በመተዳደሪያ ደንቡ መቀመጡን ልብ ይሏል ።

2ኛ. ምንም እንኳ አገልግሎቱ አማተርነት ቢሆንም በቁጥር አስራ አንድ አባላት ያሉት የስራ አመራር ቦርድ  በተግባር ደግሞ በሁለትና ሶስት ሰዎች ውሳኔ ሰጪነት ስራዎችን እየሰራ የመሄዱን ጉዳይ የዴሞከራሲያዊ አካሄድ ወይስ የፈላጭ ቆራጭነት መገለጫ? በዚህ አጋጣሚ በተለያዩ የውስጥና የውጪ ጫናና ምክንያቶች ውክልናቸውን በአግባቡ የማይጠቀሙ እንዳሉ የማይታበል ሀቅ ነው።

 3ኛ. ከ2008 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ በተቀራራቢ ምክንያት አስር የማይሞሉ ሰራተኞች ባሉበት ፅ/ቤቱ ውስጥ አምስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አምስት በኃላፊነት ይሰሩ የነበሩ ሰራተኞች ለቀዋል፤ ይህ ተግባር የተቋም መፍረስ ወይስ መታደስ?  ከነዚህ ባለሙያዎች ውስጥ የማርኬቲንግና ፕሮሞሽን ክፍል ሃላፊ፣ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ፣ የሰው ሃይልና ጠቅላላ አገልግሎት ክፍል ሃላፊ፣ የፋይናንስ ክፍል ሃላፊ እንዲሁም የፕሮሞሽንና ዶክመንቴሽን ክፍል ተጠቃሽ ናቸው። የሁሉም መውጣት ላይ አከራካሪ ጉዳዮች እንዳሉ ሆነው ይህን ተከትሎ ሁሉም መደቦች በትክክለኛ ቁመና ላይ ባሉ ባለሙያዎች ተተክተው ስራዎች እየተሰሩ ነበር ወይ የሚለው ያጠያይቃል፤ … የመረጃ ማፋለስ፣ ከቡና ብር ይዞ መጥፋት፣ የሌላውን ፕሮፖዛል አሽመድምዶ እውቅና ሳይሰጡ መስራት፣ ከትርፍ ይልቅ ክለቡን ለኪሳራ የሚዳርጉ ተግባሮች ላይ መሳተፍ እንዲሁም ሌሎች አስተዳደራዊ ውድቀቶች እንደነበሩ በመረጃ አስደግፎ መጥቀሱ ችግሩ ላይ እንንቦራጨቅ ካልሆነ የሚያመጣው መፍትሄ አይኖርም።

4ተኛ. ደጋፊውን እንደሚወክል ተገልፆ በጠቅላላ ጉባኤው ሁለት መቀመጫ በስራ አመራር ቦርዱ አንድ መቀመጫ ያለው የክለቡ ደጋፊ ማህበር በተግባር በስራ አመራር ቦርዱ ያለው ተደማጭነት እና ተፈላጊነት የት ድረስ ነው?... በተደጋጋሚ ትልልቅ ውሳኔ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ በመገለል እንዲሳተፍ ያለመደረጉ፣ በጥርጣሬ መታየቱና ተማምኖ ስራዎችን ያለመስራት በአንድ ተቋም ውስጥ ሁለት መዋቅር ያለ ያስመስለዋል።

 

የመፍትሄ ጉዞው፡-

ወደ መፍትሄው ለመንደርደር መንስዔውን መፈተሽ ይፈልጋል። ይህ ፅሑፍ ለመነሻነት ቢያገለግል እንጂ እንደ ጥናታዊ ፅሁፍ ሁሉንም ጥግ ሊዳስስ አይችልም። አሁን ላይ በኢትዮጵያ ቡና ውስጥ በብዙ አድካሚ ሂደቶች መሃል ያለው ተስፋ ሰጪ ተግባር በጋለ ቁጭት 'ለምን?' ብሎ እስከመጨረሻው የሚጠይቀው አካል መበርከቱ (በውስጡ አላስፈላጊ ስድቦችና የውክልና ገደብ መጣሱ ሊታረም የሚገባ መሆኑ ሳይዘነጋ)፤ የጋራ መግባባቱ ባይኖርም በተለያዩ መደበኛ ቡድኖች (Formal Groups) እና መደበኛ ያልሆኑ ቡድኖች (Informal Groups) መሃል የተለያዩ ውይይቶችና የመፍትሄ ሃሳቦች ከሁሉም አቅጣጫ እየተሰነዘረ መምጣቱ(በዚህ መሃል ያሉ አላስፈላጊ ቡድንተኝነቶች ሳይዘነጉ) ይጠቀሳል ። 

በውጤት ርሃብ የሚንገላታው ደጋፊ ጥያቄውን በአሰልጣኝና ተጫዋቾች ላይ ብቻ ማንጠልጠሉን ትቶ ሁሉንም የመንስኤና መፍትሄ አቅጣጫ መፈተሽ ይዟል። ቡና አሁን ላይ የግለሰቦችን ለውጥ ብቻ ሳይሆን የስርዓት ለውጥ የሚፈልግበት ደረጃ ላይ እንደደረሰ ብዙ ማሳያዎች በርክተዋል። በቡና ላኪዎች፣ ቡና ቸርቻሪዎች፣ የሀገር ውስጥ ጅምላ ቡና ነጋዴዎች፣ ቡና አብቃዮች እና ቡና ቆይዎች (ይህ ማህበር አመታዊ ገቢው ላይ ምንም እንደማያበረክት የፋይናንስ ሰነዱ ያሳያል) ላይ ብቻ ጥገኛ የሆነው ክለብ ስሙን ብቻ አስቀርቶ አማራጭ ካልፈለገ ነገ ስለሚፈጠረው አደጋ እርግጠኛ መሆን አይቻልም። ስፖርት ክለቡ ሃምሳ በመቶ ገቢውን ከዚህ ሴክተር ቢያገኝም ያልተመለሱ ጥያቄዎች ግን በውስጡ አሉ። የቡና ሰዎች አጠቃላይ የብቃት ማዕቀፍ ዲሞግራፊ በተቀየረበት ወቅት ፕሬዝዳንት የሚሆነው ግለሰብ ከቡና ላኪዎች ማህበር ብቻ እንዲሆን መገደቡ፣ አብዛኛው የመዋቅራዊ ሂደቱ መቀመጫ ለቡናው ሴክተር ለተወከሉ የሚያደላ መሆኑ፣ በቡና ስም እየመጡ ያሉ የክልል ክለቦች መበራከትና የገቢ መሳሳት፣ በቡና ንግድ ላይ ያሉ ግለሰቦች ስለክለቡ ያላቸው መረጃ አነስተኛ መሆንና ሌሎች የሚጠቀሱ ፈታኝ የውስጥ አካሄዶች አሉ።

ከሜዳ ውጪ ያለው መደላድል አሁንም ክፍት እንደሆነ እንዳይቀር አደረጃጀቱ በደንብ መፈተሽ ይኖርበታል። ደጋፊውም ሆነ ሌላው አካል አስተዳደሩን በምንጠብቀው ደረጃ አልሰራችሁም ሲል የባለውለታዎችን ሚና በዜሮ ማጣፋት ሳይሆን የሚጠብቀውን በትግስቱ ያለማግኘቱ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። ክለቡን እዚህ ደረጃ ጠብቆ ለማቆየት መስዋትነት የከፈሉና እየከፈሉ ያሉ ባለውለታዎች የሚመሰገኑበት መድረክና አሰራር ሊመቻች ይገባል፤ ነገር ግን ታሪካዊውን የለውጥ አጋጣሚውን በመጠቀም ግለሰቦች ብቻ ሳይሆን አሰራሩ ተገምግሞ እንዲሻሻል ውትወታው ሊጠነክር እንጂ ሊዳከም ደግሞ አይገባም። ቀጣዩ ጊዜ ሁሉም የቡና ቤተሰብ ከእልህና 'እኔ ብቻ ልክ ነኝ' ከሚል ኢጎ (Ego) ወጥቶ ክለቡን የሚታደግበት እንዲሆን መሞገት ያለብን ሃሳቦችን እንጂ የሃሳብ አመንጪዎች ማንነት በመመዘን አይደለም። ለዚህም አመራሩን የሚያነቃና በመረጃ የተደገፈ ደጋፊና ደጋፊ ማህበር፣ ለሁለገብ ለውጥ የተዘጋጀ አመራር፣ የክለቡን የማሊያ ክብር የተረዳ ተጫዋችና የአሰልጣኝ ስብስብ፣ በእውቀት ላይ የተመሰረተና ኃላፊነት የሚወስድ የሰራተኞች መዋቅር ለማየት ነባር ባለውለታዎችም ሆኑ ታሪክ ተረካቢዎቹ አሻራቸውን ሊያሳርፉ ይገባል። ከዚህ ጋር በተያያዘ በቅርቡ ለታህሳስ 21 ቡና ላይ ለመምከር የውይይት መድረክ ተመቻችቷል፤ መድረኩን 'እኔ እንዲህ አልኳቸው' በሚል የስሜት ጩኸት የንግግር ነጥብ ማስቆጠሪያ ለማድረግ ሳይሆን ለዘላቂና ተከታታይ ውይይት መደላድል የምንፈጥርበት እንዲሆን እናስብ። የሪፎርም ለውጥ ለማምጣት የረፈደበት - መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የተፈረደበት ቤት አለን፤ ስለዚህ ለሀገሪቷ ስፖርት እድገት ባለውለታ የሆነው ኢትዮጵያ ቡናን ለመታደግ ለደከማችሁና ለምትደክሙ ሁሉ ክብር እየሰጠን በአህጉር አቀፍ ደረጃ ተፎካካሪ የሆነ ኢትዮጵያ ቡና ይፈጠር ዘንድ ደግሞ የጋራ ርብርብ እናድርግ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
157 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 240 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us