ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች በባህር ማዶ ሊጎች

Wednesday, 03 January 2018 17:19

በተለያዩ ሀገሮች የሚጫወቱ ኢትዮጵያዊያን የ2017 የውድድር ዓመትን ያሳለፉት ብዙዎቹ በስኬት አይደለም። በዚህ ጽሑፍ የተዳሰሱት ተጫዋቾችም የፈረንጆቹን አሮጌ አመት ከተሰጣቸው ግምት በታች ሆነው ነው የተገኙት። ይሁንና ተጫዋቾቹ ከኢትዮጵያ የተሻለ ጠንካራ የሚባል ሊግ ውስጥ መጫወታቸው ጥሩ ብቃት ሊያዳብሩና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ሊጠቅሙ እንደሚችሉ ተስፋ የሚጣልባቸው ናቸው።

 

ኡመድ ኡኩሪ እና ሽመልስ በቀለ በግብጽ ሊግ


ኢትዮጵያውያኑ ተጫዋቾች ኡመድ ኡክሪና ሽመልስ በቀለ በግብጽ ሊግ የ2017 የውድድር አመትን ያልተሳካ በሚባል ሁኔታ አሳልፈዋል። ሁለቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አባላት በክለቦቻቸው የላቀ ብቃት በማሳየት የሚጠበቅባቸውን ያህል ግቦችን ማስቆጠር አልቻሉም። በ2017 በሊጉ በተሰለፉባቸው አንድ አንድ ግብ ብቻ ነው ያስቆጠሩት።


የቀድሞው የመከላከያና ቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቂ ኡመድ ኡክሪ ስሙሃ ለተባለ ክለብ ዘንድሮ መፈረሙ የሚታወስ ሲሆን፤ በፕሪሚየር ሊጉ በ15 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ አንድ ግብ ነው ያስቆጠረው። በግብጽ የክለቦች ዋንጫ ደግሞ አንድ ግብ አስቆጥሯል። ኡመድ በቡድኑ በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ የተካተተ ቢሆንም እንደ አጥቂ ተጫዋች በርካታ ግቦችን ለማስቆጠር አልቻለም። ከ2017 እስከአሁን ሁለት ግቦችን ብቻ ማስቆጠሩ ቀጣይ ቆይታውን ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው።


የሐዋሳ ከነማና ቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋች የነበረው ሽመልስ በቀለ ከ2014 ጀምሮ በክለቡ ፔትሮ ጄት በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ የሚገኝ ተጫዋች ነው። በአማካይ መስመር ቦታ ተጫዋችነት የላቀ የእግር ኳስ ተሰጥኦ ቢኖረውም በ2017 የውድድር አመት ክለቡን ውጤታማ ማድረግ የቻለ እንቅስቃሴ ማሳየት አልቻለም። ይሁንና በቦታው እሱን የሚልቅ ተጫዋች ባለመኖሩ በክለቡ የመቆየቱ ነገር ስጋት የሚገጥመው አይመስልም።


የግብጽ ሊግን ኤል ኢስማኢሊያ በ16 ጨዋታዎች 37 ነጥብ ይዞ በመምራት ላይ ይገኛል። የኡመድ ክለብ ስሙሃ 16 ጨዋታ 23 ነጥቦች 6ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ፤ የሽመልስ በቀለ ክለብ ፔትሮጄት ደግሞ በተመሳሳይ 16 ጨዋታ 17 ነጥብ ይዞ 13ኛ ነው። ሁለቱ ኢትጵያውያን ተጫዋቾች ጠንካራ ፉክክር በሚታይበት የግብጽ ሊግ የላቀ ብቃታቸውን በማሳየት ክለቦቻቸውን ውጤታማ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ቢኒያም በላይ አልባኒያ ሊግ


የቀድሞው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጫዋች ቢንያም በላይ በጀርመን ያሳለፈው የሙከራ ጊዜ የተሳካ ባይሆንም ወደ ሌላ የአውሮፓ ሀገር ለመጓዝ በር ከፍቶለታል። ተጫዋቹ በባህር ማዶ ሊግ ለመቆየት ባደረገው ጥረት በስተመጨረሻ ማረፊያው የአልባኒያ ሊግ ሆኗል። በሀገሪቱ ስኬንደሬቡ ለተባለ ክለብ ለመጫወት ፈርሟል።


አዲሱ የቢኒያም ክለብ 10 ክለቦች በሚሳተፉበት አልባኒያ ሱፐር ሊግ በ16 ጨዋታዎች 37 ነጥብ ሰብስቦ አንደኛ ሲሆን፤ ፍላሙታሪ የተባለው ክለብ 28 ነጥብ ይዞ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። የቢንያም ክለብ ከተከታዩ ክለብ ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት ሰፊ በመሆኑ የሊጉን ዋንጫ የማንሳት እድሉ ሰፊ እንደሆነ መናገር ይቻላል። ኢትዮጵያዊው ተጫዋችም ከአልባኒያው ክለብ ጋር በቀጣዩ አመት በዩሮፓ ሊግ የመጫወት አጋጣሚ ሊያገኝ ይችላል።


ከኦገስት 10 ጀምሮ ቡድኑን የተቀላቀለው ኢትዮጵያዊው ተጫዋች እስከአሁን በአራት ጨዋታዎች ላይ ነው የተሰለፈው። በዩሮፓ ሊግ ከዳይናሞ ኬቭ ጋር በነበራቸው ጨዋታ ተቀይሮ በመግባት የተጫወተ ሲሆን፤ በሀገሪቱ ዋና ሊግ ደግሞ በሁለት ጨዋታዎች ላይ ተቀይሮ ገብቷል። በአልባኒያ ሱፐር ካፕ እንዲሁ በአንድ ጨዋታ መሰለፍ ችሏል።


ቢንያም በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ አስደናቂ ክህሎት ማሳየት ከቻሉ ወጣት ተጫዋቾች አንዱ ነው። በአልባኒያ ሊግ በተደጋጋሚ የመሰለፍ እድል ሲያገኝ የተሻለ አቅሙን በማሳየት የተሳካ ጊዜ እንደሚያሳልፍ እምነት የሚጣልበት ነው።

 

ጋቶች ፓኖም ከሩስያ ሊግ ተመልሷል


በኢትዮጵያ ቡና እግ ኳስ ክለብ ተወዳጅ ከሆኑ ተጫዋቾች አንዱ የነበረው ጋቶች ፓኖም በቅርቡ በሩስያ ሊግ ለመጫወት የሚያስችለውን ስምምነት እንደፈጸመ ይታወሳል። ይሁንና ተጫዋቹ ከክለቡ ጋር የፈጸመው ስምምነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ፈርሶ ወደ ኢትዮጵያ መመለሱ ታውቋል።


ጋምቤላ ካፈራቻቸው ተጫዋቾች መካከል ከኡመድ ኡክሪ ቀጥሎ ጎልቶ መውጣት የቻለው ጋቶች ፓኖም ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በአወዛጋቢ ሁኔታ ተለያይቶ ወደ ሩስያው አንዚ ማቻካላ ክለብ ማምራት ችሎ ነበር። በሩስያው ክለብ ጥሩ ጊዜ እንደሚያሳልፍ የተሰጠው ግምት ሳይሰምር ቀርቷል። ተጫዋቹ ከሶስት ወራት በኋላም ከክለቡ መለያየቱ ተሰምቷል።


በቅርቡ ኢዮጵያ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ያለግብ የተለያዩበትን የሸገር ደርቢን በአዲስ አበባ ስታዲየም ተገኝቶ የተከታተለው ጋቶች፤ ቀጣይ ማረፊያው አልታወቀም። የተጫዋቹ ወኪል ዴቪድ በሻህ ሌላ የአውሮፓ ክለብ እየፈለገለት እንደሆነ ተሰምቷል። የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብም ተጫዋቹን የማስፈረም ፍላጎት እንዳለው ተወርቷል። የቀድሞ ክለቡ ኢትዮጵያ ቡናም የተጫዋቹ ፈላጊ ሆኖ ቀርቧል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
93 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 241 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us