አስመራጭ ኮሚቴው በውዝግብ እንደታመሰ ቀጥሏል

Wednesday, 17 January 2018 13:55

 

ሴኔጋላዊቷ የፊፋ ዋና ጸሐፊ ፋቱማ ሳሙራ ወደ ኃላፊነት ከመጡ በተደጋጋሚ ፊርማቸውን በማኖር ደብዳቤ የሰደዱት ወደ ኢትዮጵያ መሆን መናገር ይቻላል። የሴትየዋ ደብዳቤ ይዘት አድናቆትና ምስጋናን ያዘለ ሳይሆን በጠንካራ ማስጠንቀቂያዎችና ማሳሰቢያዎች የታጀቡ ምክሮችን የያዙ ናቸው።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን መስራች ከሆኑ ሀገሮች አንዷ የሆነችው፤ ለ16 አመታት ካፍን በፕሬዝዳንትነት የመሩ ግለሰብን (አቶ ይድነቃቸው ተሰማ) ያፈራችዋ ኢትዮጵያ አሁን ላይ እግር ኳሷን የሚመራ ሁነኛ አመራር አጥታ ውጥንቅጧ ሲወጣ ማየት ያሳዝናል። ሀገሪቱ ከምርጫ ጋር ተያይዞ ግለሰቦች የፈጠሩት ውዝግቦች በፊፋም ሆነ በካፍ ዘንድ ክብሯን የሚያሳንስ ሆኗል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምርጫ ጋር ተያይዞ ግለሰቦች ለፊፋ የሚልኳቸው ደብዳቤዎች አሁንም ቀጥለዋል። የደብዳቤዎቹ ውጤቶችም የሀገሪቷን እግር ኳስ ይበልጥ ወደኋላ የሚጎትተው ሆኗል። ከምርጫው አትራፊ መሆን የሚፈልግ ወገን ሁሉ ባልተገባ መንገድም ጭምር ደብዳቤ እየጻፈ ወደ ዙሪኩ ቢሮ መስደዱን ተያይዞታል።

አሁን ደግሞ ሀገሪቱ የእግር ኳስ ደረጃዋ ከምንግዜውም በበለጠ የወረደበት ወቅት ላይ ከምትገኘው ከኢትዮጵያ ወደ ፊፋ የሚላከው ደብዳቤ ብዛትና ይዘትም እፍረት የሚያከናንብ ነው።

ግለሰቦች በጎንዮሽ የሚልኳቸው ደብዳቤዎች አሁንም እንደቀጠሉ ናቸው። ቀደም ሲል በእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በተናጥል ለፊፋ ይላኩ የነበሩትን አይነት አወዛጋቢ ደብዳቤዎች አሁን ደግሞ በአስመራጭ ኮሚቴ አባላት እየተጻፉ ነው።

ከምርጫው አትራፊ ለመሆን የሚፈልጉ አካላት በሚከተሉት ያልተገባ መንገድ የሀገሪቱ ስፖርት አደጋ ላይ ወድቋል። ኢትዮጵያ እንደገና በፊፋ ለቅጣት የምትዳረግበት ተግባሮች በይፋ እየተስተዋሉ ነው። የፊፋም ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያዎች ከእግር ኳስ ፌዴሬሽኑና ከምርጫው ሒደት ጋር ተያይዞ የተበላሹ አሰራሮች እየተንሰራፉ መሆኑን ያስረዳሉ።

በቅርቡም የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የአስመራጭ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዘሪሁን መኮንን ዲሴምበር 20 ቀን 2017 የጻፉት ደብዳቤን መሰረት በማድረግ ፊፋ ከማስጠንቀቂያዎች ጋር ምርጫው የካቲት 24 ቀን 2010 ዓ.ም እንዲካሄድ እና ለሶስተኛ ጊዜ እንዲራዘም አድርጓል። ሶስተኛው የአራዝሙት ደብዳቤ ለየት የሚያደርገው የካፍና የፊፋ ተወካዮች ለምርመራ እንደሚመጡ ማሳወቁ ነው።

ይህ የፊፋ ምላሽ የምርጫው መራዘምን ለሚፈልጉ ወገኖች አስደሳች ነው። የአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ዘሪሁን መኮንን በይፋ ሚዲያ ላይ ወጥተው በጣም አስደስቶኛል ብለዋል።

“ያደረኩት ነገር ትክክል ነው”

ከተመረጠ አንድ ጊዜ ብቻ በቡድን የይስሙላ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጠው የአስመራጭ ኮሚቴው ሰሞኑን ደግሞ አባላቱ በተናጥል በመገናኛ ብዙሀን ላይ እየወጡ የግል አስተያየታቸውን መስጠት ጀምረዋል። የአስመራጭ ኮሚቴው እርስ በእርሱ የማይስማሙ የተለያየ አቋም የያዙ ሰዎች ስብስብ መሆኑ በይፋ ታይቷል።

በተቃራኒነት የተሰለፉት መካከልም ሰብሳቢው አቶ ዘሪሁን መኮንን እና ምክትላቸው አቶ መኮንን ደስታ ሰሞኑን በአንድ ላይ በቴሌቭዥን መስኮት ላይ ቀርበው መዘላለፍም ጭምር  የታየበት ክርክር አድርገዋል። በሀገር ደረጃ የተረከቡትን ኃላፊነት ለመወጣት ከሚያደርት ጥረት ይልቅ የግል ፍላጎት ለማሳካት የሚሞክሩ ነው የሚመስሉት።

አቶ ዘሪሁን ሌሎቹ የአስመራጭ ኮሚቴ አባላት ሳያውቁ ለፊፋ ደብዳቤ መጻፋቸው ቢያስተቻቸውም እሳቸው ግን እንዳላጠፉ ነው የተናገሩት።

‹‹ለፊፋ ደብዳቤ የጻፍኩት በጠቅላላ ጉባኤ የተሰጠኝን ኃላፊነትና እውቅና ተጠቅሜ ነው። ይህም ባይሆን እኔ ያደረኩትን ማንም ሰው ሊያደርገው የሚችለውን ነው›› ብዋለዋል። ተጠያቂ ላለመሆንም በማለትም ተጨማሪ ምክንያታቸውን ገልጸዋል።

‹‹ራሴን ነጻ ለማውጣት ነው ደብዳቤውን የጻፍኩት። ምክንያቱም እከሌ ገንዘብ ተቀብሎ እነ እከሌን ለማስመረጥ ነው የሚሰራው እየተባለ ይወራል። ስለዚህ በኋላ ተወቃሽ ላለመሆን ነው ለፊፋ ምርጫው ከመደረጉ በፊት ከጥቅምት አምስት ቀን በፊት ማለት ነው ኑ እና ግምገማ አድርጉ ብዬ የጻፍኩት።›› ብለዋል።

በምክትላቸው አቶ መኮንን ደስታ በኩል ድርጊታቸው ቢኮነንንም እሳቸው ግን ያደረኩት ትክክል ነው። ፊፋም የሰጠው ምላሽ አስደስቶኛል›› ሲሉ በኩራት ነው የተናገሩት። አቶ መኮንን ድሬዳዋን ወክለው የቀረቡትን አቶ ጁነዲን ባሻ እየተቹ ዶክተር አሸብርን መደገፋቸው ያልተገባ እንደሆነ በመግለጽም ግለሰቡን በቃላት ሸንቁጠዋቸዋል።

“በትርምስ ውስጥ የሚመጣ አሸናፊም ተሸናፊም የለም”

በአቶ ዘሪሁን ተደጋጋሚ ትችት የተሰነዘረባቸው የአስመራጭ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ መኮንን ደስታ ደግሞ ለፊፋ የተጻፈው ደብዳቤ ኃላፊነት ከሚሰማው አካል የሚጠበቅ እንዳልሆነ ነው የሚናገሩት። ፊፋ ጋር ከመድረሱ በፊት እዚሁ ሒደቶችን መከተል አስፈላጊ እንደነበርም ይገልጻሉ።

አቶ ዘሪሁን ከኮሚቴው እውቅና ውጪ አሁን ስራ ላይ ያለው አመራር በሰጣቸው ትዕዛዝ መሰረት ምርጫው እንዲራዘም ለፊፋ ደብዳቤ መዳፋቸው ተገቢ እንዳልሆነም ይናገራሉ።

‹‹ለፊፋ ደብዳቤ መጻፍ አያስፈልግም ነበር። ለይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ማቅረብና የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴውን ውሳኔ መቀበል እንደሚገባ የፊፋ መመሪያም ላይ ተቀምጧል።

አቶ ዘሪሁን ሃሳባቸው በድምጽ ብልጫ ውድቅ ሲሆን ነው ወደ ፊፋ ደብዳቤ የላኩት። ነገር ግን ለፊፋ ደብዳቤ ከመጻፍ ይልቅ ብዙሀኑ ለተስማማበት ውሳኔ መገዛት አሊያም ራሳቸውን ከኃላፊነታቸው ማንሳት የነበረባቸው።

በቀጣይ መደረግ ያለበት የመፍትሔ ሐሳብም እንደገና አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ጠርቶ በአስመራጭ ኮሚቴው ላይ ውሳኔ እንዲሰጥ ማድረግና ወደ ፊት መቀጠል ነው” ብለዋል።

‹‹በዚህ ትርምስ ውስጥ የሚመጣ አሸናፊም ተሸናፊም የለም። ሀገር ናት የምትጎዳው›› በማለትም ሀሳባቸውን ያጠቃልላሉ።

የአስመራጭ ኮሚቴውና የምርጫው ዕጣ ፈንታ

ከዘጠኝ ክልሎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች የተወከሉ ግለሰቦችን ያሰባሰበው አስመራጭ ኮሚቴ ወትሮም ገለልተኛነቱ ያልታመነበት ነበር። የጠቅላላ ጉባኤው ታሪካዊ ስህተትም ግለሰቦቹን እውቅና መስጠቱ ነው። የምርጫውን ሒደት ፍትሐዊ ሊያደርግ ቀርቶ ራሱ ፍትሐዊ መሆን አልቻለም። ኮሚቴው ለሁለትና ለሶስት ወገን ተከፍሎ በውሳኔዎች መግባባት አልቻለም።

በስተመጨረሻም የአስመራጭ ኮሚቴ እጣ ፈንታው መጨረሻው ውዝግቡን የሚያጋግል ደብፋቤ ለፊፋ በመጻፍ መበታተን ሆኗል። ሰብሳቢው አቶ ዘሪሁን ለፊፋ ደብዳቤ ከጻፉ በኋላ ተሰባስበው አያውቅም። በአሁኑ ወቅትም ስራም መስራት አቁሟል።

የአስመራጭ ኮሚቴው በቀጣይ ይካሔዳል የተባለውን የአመራሮች ምርጫን በእርግጥም ሊያስፈጽም መቻሉ አጠራጣሪ ሆኗል። ከካፍና ከፊፋ የሚመጡ ተወካዮች በሚያደርጉት ምርመራ ዕጣ ፈንታው የሚወሰን ይሆናል። የኮሚቴው ገለልተኛነት እምነት ከታጣበት ሙሉ በሙሉ ፈርሶ ሌላ ሊቋቋም ይችላል። አሊያም ከኮሚቴው ውስጥ የገለልተኝነት ችግር አለባቸው የሚባሉ አባላት ሊቀነሱና በምትካቸውም ሌሎች ሊመረጡ ይችላሉ።

ለሦስተኛ ጊዜ የተራዘመው የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንታዊ እና ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ የካቲት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. እንዲከናወን ፊፋ ለመጨረሻ ጊዜ በላከው ደብዳቤ ላይ ገልጻል። በተጠቀሰው ቀን ምርጫው ስለመከናወኑ ግን እርግጠኛ መሆን አይቻልም።

ለፕሬዝዳንትነት አምስት እጩዎችና ለስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት 16 እጩዎችን ማሳወቁ ይታወሳል። ከአምስት ዕጩዎች መካከልም ፉክክሩ ከአማራ ክልል በተወከሉት በአቶ ተካ አስፋውና ከደቡብ ክልል ተወካዩ ዶክተር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ መካከል እንደሚሆን ይጠበቃል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
60 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 237 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us