የጆርጅ ዊሃ ከቆሻሻ መንደር እስከ የሀገር መሪነት ጉዞ

Wednesday, 24 January 2018 14:45

 

በዚህ ሰሞን አፍሪካ ለአለም አዲስ ታሪክ አስተዋውቃለች። ላይቤሪያዊው ጆርጅ ዊሃ የእግር ኳስ ተጫዋች ሆኖ የአገር መሪ (ፕሬዝዳንት) የሆነ የአለማችን የመጀመሪያው ሰው ሆኗል። የቀድሞው የፊፋ እና የአፍሪካ ኮከብ ተጫዋች ሰኞ እለት በሞኖሮቪያ በተዘጋጀ ልዩ ስነ ስርአት ሀገሪቷን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት ቃለ መሀላ ፈጽሟል። ከእግር ኳስ ተጫዋቾች እስከ ታላላቅ የአለም መሪዎች በቃለ መሀላ ስነስርአቱ ላይ ተገኝተው ለጥቁሩ ኮከብ ያላቸውን አክብሮት ገልጸዋል።


ሞኖሮቢያ በሚገኘው የሳሙኤል ዶ ስታዲየም በተከናወነው የዊሀ ቃለ መሀላ ላይ ከተገኙ ስመ ጥር ተጫዋቾች መካከልም ዲዲየር ድሮግባ፣ ሳሙኤል ኤቶ ይገኙበታል። በርካቶችም ለቀድሞም የአለም ኮከብ ተጫዋች አድናቆታቸውን ገልጸው መልካም የስራ ዘመን ተመኝተውለታል። ፕሬዝዳንት ጆርጅ ዊሀም በደረሱት መልካም ምኞቶችና ቃለ መሀላ በፈጸመበት ስታዲየም ውስጥ በተደረገለት ደማቅ አቀባበል መደሰቱን ተናግሯል።


‹‹በህይወት ዘመኔ ብዙ ጊዜ በተለያዩ ስታዲየሞች ላይ ተገኝቻለሁ። የዛሬው ግን እጅግ ልዩ ስሜት ነው የፈጠረብኝ።›› ብሏል። በሀገሪቱ የተንሰራፋውን ሙስና ማጽዳትና የመንግስት ሰራተኞች ለመኖር የሚያበቃቸውን ክፍያ እንዲያገኙ ማስቻል ቀዳሚ ተግባሩ እንደሆነም አስታውቋል።

በእግር ኳስ መድረክ እስከ ዓለም ኮከብነት


በላይቤሪያ ሞኖሮቢያ ክላራ በምትባል ቆሻሻ የበዛባት የድሆች ከተማ ተወልዶ ያደገው ጆርጅ በእግር ኳሱ አለም ከማይረሱ ጥቂት ባለ ተሰጥኦ አፍሪካውያን ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው። በአለም ታላላቅ የእግር ኳስ መድረኮች በመጫወት ለብዙ አፍሪካውያን መፍለቅ ትልቅ አርአያ መሆን ችሏል። አፍሪካውያን ከሌሎች የአለማችን ሀገሮች ተጫዋቾች እኩል በአንድ መድረክ መጫወትና ማሸነፍ እንደሚችሉ ቀዳሚው ማሳያ ነበር።


ዊሀ በፊፋ የአለም ዋንጫ መድረኮች አስደናቂ ግቦችን በማስቆጠር ጭምር አድናቆትን አትርፋል። የፊፋን የአመቱ የአለም ምርጥ ተጫዋች ሽልማትንም ለመጀመሪያ ጊዜ ማሸነፍ የቻለ ብቸኛው አፍሪካዊ ነው። ከእሱ በፊትም ሆነ በኋላ ይህንን ክብር ለመጎናጸፍ የቻለ አፍሪካዊ ተጫዋች አልተገኘም።


ጥቁሩ ኮኮብ ዊሃ በእግር ኳሱ መድረክ ከድሀዋ የአፍሪካ ሀገር ከላይቤሪያ ተነስቶ የአለማችን ስመ ጥር ክለቦች ጭምር መሰለፍ ችሏል። በአውሮፓ በፈረንሳይ ለሞናኮ፣ ማርሴይና ፓሪሰን ዠርሜ፤ በጣሊያን ለኤሲ ሚላን፤ በእንግሊዝ ደግሞ ለማንቸስተር ሲቲ እና ቼሊሲ ተሰልፎ ተጫውቷል። በ1994 ከፓሪሰን ዠርሜ ክለብ በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ አጠናቋል። ከኤሲ ሚለን ጋር የሴሪ ኤውን ዋንጫ ለሶስት ጊዜ አንስቷል። በማንቸስተር ሲቲ ደግሞ የኤፍ ኤ ዋንጫን አሸንፏል።


በላይቤሪያ ብሔራዊ ቡድን ውስጥም እ.አ.አ. ከ1987 እስከ 2003 ድረስ በነበረው የተጫዋችነት ዘመኑ በ193 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ ሀገሩን ለአፍሪካና ለአለም ዋንጫ መድረክ ማብቃት ችሏል።
በ1995 ዊሀ በአፍሪካም ሆነ በአለም መድረክ ላይ ጎልቶ የወጣበት ዘመን ነበር። በዚህ አመት ላይቤሪያዊው አጥቂ የፊፋ የአመቱ ኮከብ ተጫዋች መሆን ችሏል። በ1989፣ 1994 እና 1995 ላይም የአፍሪካ የአመቱ ኮከብ ተጫዋች በመሆን ተሸልሟል።

 

ዊሀ በፖለቲካው መድረክ እስከ ፕሬዝዳንትነት
ዊሀ ወደ ፖለቲካው መድረክ የገባው ከእግር ኳስ ህይወቱ ጡረታ በወጣ ማግስት በ2003 ላይ ነበር። ‹ኮንግረስ ፎር ዲሞክራቲክ ቼንጅ› የተባለ ፓርቲ በማቋቋም ለ2005 የላይቤሪያ ፕሬዝዳንታዊ ፉክክር ራሱን በእጩነት አቀረበ። በፉክክሩም በሁለተኛው ዙር በኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ ሽንፈት የገጠመው ሲሆን፤ እንደገና በ2011 ምርጫ ላይም ለምክትል ፕሬዝዳንትነት ያደረገው ፉክክር ሳይሳካለት ቀርቷል።


በ2017 አጋማሽ ላይ ለፕሬዝዳንታዊ ፉክክር የቀረበው ዊሃ እንደገና የአለም መነጋገሪያ የሆነበትን የአሸናፊነት ታሪክን ተጎናጽፏል። በላይቤሪያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከቀድሞው ምክትል ፕሬዝዳንቱ ከጆሴፍ ቦአኪ ጋር ያደረገውን ፉክክር በማሸነፍ የሀገሪቱ መሪ ሆኗል። በመጪዎቹ ስድስት አመታት ፕሬዝዳንትነት ሀገሪቱንና ህዝቦቿን እንደገና ለማኩራት ተዘጋጅቷል።


በሞኖሮቢያ ቆሻሻ መንደር ተወልዶ ያደገው ጆርጅ ዊሃ ለዚህ ታላቅ ሀላፊነት ይበቃል ብሎ ያሰበ ግን አልነበረም። የዛሬ 12 አመት ለፕሬዝዳንትነት ከኤለን ሰርሊፍ ጆንሰን ጋር ሲፎካከር ‹ያልተማረና ኳስ ብቻ ሲገፋ የኖረ› በሚል ትችት ደርሶበት ነበር። ፕሬዝዳንታዊ ምርጫውንም በኤለን ጆንሰን ከተሸነፈ በኋላ ወደ ፖለቲካው ተመልሶ እንደሚመጣ የገመተ አልነበረም። በሜዳ ውስጥ ያሳየው የነበረው አልሸነፍ ባይነት ወድቆ አለመቅረት ሰብዕናውን እንደገና በፖለቲካ ህይወቱም መግለጥ ችሏል።


ዊሃ በድጋሚ ለፕሬዝዳንትነት ለመፎካካር ሲመጣ ታዲያ የዩኒቨርስቲ ዲግሪውን ይዞ ነበር። በአሜሪካ በቢዝነስ የመጀመሪያ ዲግሪውን በማጠናቀቅ አልተማረም የሚሉትን ተቺዎች አፍ አስይዟል። ዲግሪው ብቻውን ግን ምንም ትርጉም እንደሌለው ቀድሞም ቢሆን ይናገር ነበር።


‹‹ተቺዎቼ የትምህርት ደረጃው ዝቅተኛ ነው ይላሉ። የእነርሱን ዲግሪና ዶክትሬት ምን ሰሩበት? ዛሬም በሀገሩ ሙስና፣ በሽታና ድህነት ተንሰራፍቷል። የእነሱ ትምህርት የላይቤሪያ ወጣቶችን ስራ ፍለጋ ከመሰደድ አልታደገም። እነርሱ ከእኔ የበለጠ የትምህርት ደረጃ ኖሯቸው የተሻለች ላይቤሪያን መፍጠር አልቻሉም›› በማለት ተናግሮ ነበር።


ዊሃ በድጋሚ ወደ ፖለቲካው መድረክ ሲመጣ በትምህርት ዝግጅት ብቻ ሳይሆን በፖለቲካ አስተሳሰቡም የተሻለ ብስለት በማሳየት ነበር። በየመድረኩ በሚያደርጋቸው ንግግሮች ላይቤሪያውያንን ተስፋ የሚሰጡና የሚያነቃቁ፤ በሀገራቸውም እምነት እንዲኖራቸው የሚያደርግ ነበር።


ቀጣዩ የቤት ስራውም ሀገሩ ላይቤሪያ ከተዘፈቀችበት የሙስና ዝቅጠት ውስጥ ማውጣትና ለብዙ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር እንደሆነ ተናግሯል። ወጣቶች ከሀገር ሳይሰደዱ ሀገራቸውን ማበልጸግ የሚችሉበት አማራጮች መፍጠር ከተቻለ ላይቤሪያ በኢኮኖሚም የበለጸገች ሀገር ማድረግ እንችላለንም ብሏል። ይህን ለማሳካትም እያንዳንዱ የሀገሪቱ ዜጋ የበኩሉን አስተዋጽዖ እንዲያደርግ ጠይቋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
81 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 241 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us