ዮርዳኖስ አባይ ሚዲያዎች ለሀገር ውስጥ ስፖርት ትኩረት እንዲሰጡ ጠየቀ

Wednesday, 31 January 2018 12:31

 

በቅርቡ ከእግር ኳስ ተጫዋችነት በይፋ የሚሰናበተው የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አጥቂ ዮርዳኖስ አባይ መገናኛ ብዙሀን ለሀገር ውስጥ ስፖርታዊ ጉዳዮች ሰፊ ሽፋን ሊሰጡ እንደሚገባ አስገንዝቧል።


ከትውልድ ከተማው ከድሬደዋ እስከ የመን ለተለያዩ ክለቦች የተጫወተው ዮርዳኖስ አባይ በአዲስ አበባ በሚከናወኑ የስንብት ዝግጅቶች የተጫዋችነት ዘመኑን በይፋ ማብቃቱን ያውጃል። ይህንን አስመልክቶም በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ለተገኙ የመገናኛ ብዙሀን አስቀድሞ ያሳሰበው ነገር ቢኖር የሀገር ውስጥ የስፖርት ተገቢውን ሽፋን እንዲያገኝ ነው።


‹‹ለመገናኛ ብዙሀን ትልቅ ክብር አለኝ። ማንኛውንም ሚዲያ በጣም አከብራለሁ። ምክንያቱም ሚዲያዎች ለስፖርተኞችም ሆነ ለስርፖርቱ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረግ ይችላሉ ብዬ ነው። ብዙ ነገሮችን ገላልጠው ማሳየት ይችላሉ።›› ያለው ዮርዳኖስ፤ የየመን ሀገር መገናኛ ብዙሀንን ልምድ ምን እንደሚመስል ተናግሯል።


“እኔ በነበርኩበት የመን ሀገር የሀገሪቱ ሚዲያዎች ለሀገራቸው እግር ኳስ ነው ሰፊ ሽፋን ሰጥተው የሚዘግቡት እና የሚተነትኑት። ይሔ በጣም ይገርመኛል። የውጭ ሀገር ጉዳዮች የቱንም ያህል ቢሆን ጥቂት ነገር ነው የሚያወሩት። ማድሪድ ወይ ባርሴሎናን በተመለከተ አሸነፉ ተሸነፉ ከሚል ውስን መረጃ ባለፈ ሰፊ ዘገባ አያቀርቡም። ስለ ሀገራቸው እግር ኳስ ነው ቅድሚያ ሰጥተው የሚጨነቁት።” ብሏል።


“በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ለሀገር ውስጥ ስፖርት ትኩረት ሰጥተው የሚሰሩ መገናኛ ብዙሀን ቢኖሩም የበለጠ መሰራት እንዳለበት ዮርዳኖስ ተናግሯል። መገናኛ ብዙሀን ለሀገር ውስጥ የስፖርት ጉዳዮች የበለጠ ሽፋን ቢሰጡ በስፖርቱ የተሻለ ለውጥ ሊፈጠር እንደሚችል በማመን መልዕክቱን አስተላልፏል። “መገናኛ ብዙሀን ለሀገር ውስጥ ስፖርት ሰፊ ሽፋን ቢሰጡ ባለሞያዎችንም ሆነ ስፖርቱንም ለማሳደግ፤ እንዲሁም ከስፖርቱ የሚገኘውን ጥቅም ለመፍጠርም ይቻላል” ብሏል።


ዮርዳኖስ አባይ በተጫዋችነት ከድሬደዋ ጨርቃጨርቅ ጀምሮ ለኢትዮጵያ መድን፣ መብራት ሀይልና ኢትዮጵያ ቡና ተሰልፏል። በመብራት ሀይል ያሳለፋቸው ስኬታማ አመታት የተጫዋችነት ዘመኑ አይረሴ ጊዜያት ናቸው። በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በኮከብ ግብ አግቢነትና ተጫዋችነት ስሙን አጽፏል። በ26 ጨዋታዎች 24 ግቦችን በማስቆጠር የኮከብ ግብ አግቢነት ክብረወሰንን ይዞ ቆይቷል። ይህንን ክብረወሰን በ2009 ዓ.ም. በ26 ጨዋታዎች 25 ግቦችን ያቆጠረው የደደቢቱ ጌታነህ ከበደ መውሰዱ ይታወሳል።


ከመብራት ሀይል በተጨማሪ በኢትዮጵያ ቡና ክለብም በተወዳጅነት ከሚጠበቁ ተጫዋቾች አንደዱ ያደረገውን ቆይታ ነበረው። ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውስጥም አርጀንቲና ላይ በአለም ዋንጫ በተካፈለው ወጣት ቡድን ውስጥ ቁልፍ ሚና ነበረው።


ዮርዳኖስ በየመን ሊግም እንደ አል ሳክር ላሉ ክልቦች በመጫወት አሳልፏል። በሊጉ ከ12 አመት ቆይታው በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ ለቀድሞ ክለቡ ለኤሌትሪክ በመጫወት ግቦችንም ማስቆጠር ችሏል። ለድሬዳዋ ከተማ ክለብም ተጫውቷል። አሁን ግን የተጫዋችነት ህይወቱን ምዕራፍ በይፋ ለመዝጋት ተዘጋጅቷል። በቀጣይም ከሚወደው ስፖርት ጋር የሚያቆየውን ሌላ ምዕራፍ ለመግለጥ ማሰቡን አስታውቋል።


የዮርዳኖስ አባይ የስንብት ዝግጅቶች መካከል የእግር ኳስ ግጥሚያዎችና ህዝባዊ ሩጫም ይገኙበታል። የእግር ኳስ ህይወቱን የሚዳስስ መጽሐፍ በአንጋፋው ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ የተዘጋጀ ሲሆን፤ የሽያጩን ሙሉ ገቢም ለኩላሊት ህመምተኞች ማህበር ለመስጠት ተስማምቷል። በርካታ ባለሞያዎች የተሳተፉበት ዘጋቢ ፊልምም ተዘጋጅቷል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
79 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 244 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us