የ2018 የቻን ዋንጫን ሞሮኮ አስቀርታዋለች: ኢትዮጵያ ቀጣይ አዘጋጅ ሆናለች

Wednesday, 07 February 2018 13:30

 

በአገር ውስጥ ሊጎች ብቻ የሚጫወቱ ተጫዋቾችን ያካተቱ ብሔራዊ ቡድኖች የሚፎካከሩበት የአፍሪካ ሀገሮች እግር ኳስ ዋንጫ (ቻን) በአዘጋጇ ሞሮኮ አሸናፊነት ተጠናቋል። ቀጣዩን የውድድር መድረክ የማዘጋጀት ሀላፊነቱን ኢትዮጵያ ተቀብላለች።


ባለፈው እሁድ በተካሔደው የቻን ፍጻሜ ሞሮኮን ከናይጄሪያ ያገናኘ ነበር። ውድድሩን የማዘጋጀት ኃላፊነትን ከኬንያ ተነጥቆ የተሰጣት ሞሮኮ በዝግጅትም ሆነ በብሔራዊ ቡድኗም ስኬታማ ሆናለች። ናይጄሪያን በፍጻሜ ጨዋታ 4ለ0 በማሸነፍ ዋንጫውን ወስዳለች።


በውድድሩ ለደረጃ በተካሔደው ጨዋታ ሱዳንና ሊቢያ ተገናኝተው ሱዳን አሸንፋለች። ሁለቱ ቡድኖች በመደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 1ለ1 በመለያየታቸው ወደ መለያ ምት ለማምራት ተገደው ነበር። በመለያ ምትም ሱዳን አራት የፍጹም ቅጣት ምቶችን ያስቆጠረች ሲሆን፤ ሊቢያ ደግሞ ሁለት ፍጹም ቅጣት ምቶችን በማምከን ሽንፈት ገጥሟታል። ሱዳንም የሶስተኛነት ደረጃን በማግኘት ውድድሩን አጠናቃለች።


በየሁለት አመቱ የሚካሔደው የቻን ውድድር በቀጣይ 2020 ላይ ኢትዮጵያ ለማስተናገድ ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱ ይታወሳል። የአዘጋጅነት አርማውንም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ ተቀብለዋል።
በውድድሩ መሳተፍ ያልቻለችው ኢትዮጵያ ቀጣዩን የ2020 የቻን ዋንጫ ለማዘጋጀት ተመርጣለች። ውድድሩ ከመካሄዱ በፊት የኢትዮጵያን ዝግጅት በተመለከተ ካፍ ግምገማዎችን ያደርጋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
31 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us