መሐመድ ሳላህ- ግብጻዊው ሜሲ!

Wednesday, 07 February 2018 13:34

 

ናግሪግ ከግብጽ መዲና ካይሮ 150 ኪ.ሜ ርቀት በምትገኘው የጋርቢያ ግዛት የሆነችው ባስዮን ከተማ ውስጥ ያለች አነስተኛ መንደር ናት። በመንደሯ ውስጥ ባለው ሰፊና አባጣ ጎርባጣ እንዲሁም አቧራማ ሜዳ ላይ በርካታ ህጻናት እግር ኳስን ሲጫወቱ ይታያሉ። በአስቸጋሪው ሜዳ ላይ ከሚጫወቱት ህጻናት መካከል ነገ የአለማችን ምርጥ ክለቦችን የመቀላቀል ተስፋ ያለው ልጅ ይወጣል ብሎ ማንም አይገምትም። ህጻናቱ ግን ነገ ታላቅ ተጫዋች መሆን እንደሚችሉ በማመን ዘወትር ይጫወታሉ። ምክንያቱም ከዚህች መንደራቸው ሜዳ የወቅቱ የአፍሪካ ኮከብ ተጫዋች መሐመድ ሳላህ እንደተገኘ ያውቃሉና!  


ከመሀመድ ሳላህ በፊት ከናግሪግ መንደር የተገኘ ስመ ጥር ግብጻዊ ተጨዋች የለም። ራሱ በልጅነቱ እንደ ዚነዲን ዚዳን፣ ሮናልዶ ሉዊስናዛሪዮ ዴሊማ እና ፍራሲስኮ ቶቲ ለመሆን በመመኘት ነበር የኳስ ጥበቦችን እያሳየ ይጫወት የነበረው። አሁን ግን የናግሪግ ህጻናት የአውሮፓ ተጫዋቾችን ሳይሆን የሰፈራቸው ልጅ የሆነውን የመሐመድ ሳላህን አይነት እንቅስቃሴ ለማሳየት እየጣሩ እግር ኳስን ይጫወታሉ።


በአነስተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ብዙ ነዋሪዎች የሚገኙባት ናግሪግ አሁን በሳምንት ከ100ሺ ፓውንድ በላይ የሚከፈለው፣ አመታዊ ገቢው እስከ ሶስት ሚሊዮን ፓውንድ የደረሰ ተጫዋች የመሐመድ ሳላህ ባለቤት ሆናለች። ስሟን በአለም የእግር ኳስ መድረኮች ማስጠራት የቻለ ልጅ በማፍራቷ ነዋሪዎቿ ደስተኞች ናቸው። የጋርቢያ ከተማ በስሙ ትምህርት ቤትና ማዕከል በመሰየም ለተጫዋቹ ያላትን ክብር ገልጻለች።


የእንግሊዙን ሊቨርፑልን በ40 ሚሊዮን ዶላር ባሳለፍነው ነሐሴ ወር የተቀላቀለው መሐመድ ሳላህም የተገኘበት የናግሪግ አካባቢና ማህረሰብ ለሰጠው ፍቅርና ክብር መልሶ መክፈል ጀምሯል። ወደ ትውልድ መንደሩ በተደጋጋሚ በመሔድ ህጻናትና ታዳጊዎች ህልማቸውን እንዲያሳኩ ድጋፍ ይሰጣል።


“መሐመድ ሳላህ የነበረበትን የማይረሳ ተጫዋች ነው። እርሱ ለአካባቢው ወጣቶች መልካም ነገር ከማድረግ ሁሌም የማይቦዝን ደግ ልብ ያለው ነው።” ሲሉ የቅርብ ወዳጆቹ ይገልጹታል።

 

በጎ አግራጊው ኮከብ
መሐመድ ሳላህ ባለፈው የፈረንጆቹ የ2017 አመት ስኬታማ ጊዜን በማሳለፍ የላቀ አፍሪካዊ ተጫዋች ነው። ለክለቡ ሊቨርፑልም ሆነ ለግብጽ ብሔራዊ ቡድን ውጤታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። በአመቱ ውስጥ ላስመዘገበው ድንቅ ብቃትም የ2017 የአፍሪካ ኮከብ ተጫዋችነት ሽልማትን አግኝቷል። ቢበሲም የአመቱ ምርጥ አፍሪካዊ ተጫዋች ሲል ሸልሞታል። በፕሪሚየር ሊጉ ብዙ ጊዜ የጨዋታ እና የወሩ ኮከብ ተጫዋች ተብሎም ተመርጧል።


የ25 አመቱ ግብጻዊ በሜዳ ውስጥ ብቃቱ ብቻ ሳይሆን በበጎ አድራጎት ተግባሮቹም በኮከብነት የሚጠቀስ ተጫዋች ነው። መልካም ዝናውን ተጠቅሞ የነበረበትን ማህበረሰብ በመርዳት ይታወቃል።


የሰርግ ወጫቸውን መሸፈን ያቃታቸው ጥንዶችን የሰርግ ወጪ ከመሸፈን ጀምሮ ትምህርት ቤት እስከ መገንባት፤ ለህክምና ተቋማትና ለስፖርት ማሰልጠኛዎች ድጋፍ እስከ ማድረግ አስገራሚ በጎ ተግባሮችን ፈጽሟል።


ከአስገራሚ በጎ ተግባሮቹ መካከል የቤተሰቡ መኖሪያ ቤት ላይ ዝርፊያ የፈጸመ ሌባን የረዳበት ታሪክ ይጠቀሳል። ከአንድ አመት በፊት በወላጆቹ መኖሪያ ቤት ዝርፊያ ሲፈጽም ተይዞ የተከሰሰው ወጣት ክሱ እንዲቋረጥ እና ወጣቱ ዘራፊ ስራ እየሰራ ራሱን እንዲረዳ ገንዘብ በመስጠትም ድጋፍ አድርጎለታል።


በሊቨርፑል እስከ 100ሺ ፓውንድ የሚደርስ ሳምንታዊ ደሞዝ፤ 3ሚሊዮን ፓውንድ አመታዊ ገቢ ያለው መሐመድ ሳላህ፤ ያልተንደላቀቀ ቀለል ያለ ህይወትን ነው የሚኖረው። የሚያገኘውን ገንዘብና ስጦታ ለተገኘበት ማህረሰብ መልሶ በመስጠት ተግባሩ ይታወቃል።


በቅርቡ በግብጽ ባለጸጋ ነጋዴ የሆኑት መሀመድ አባስ በስጦታ ያበረከቱለትን ውድና ዘመናዊ የመኖሪያ ቪላ አመስግኖ ቢቀበልም ቪላው ከእኔ ይልቅ በድህነት ለሚኖሩ ለናግሪግ መንደር ነዋሪዎች ይጠቅማል በማለት ለድሆች እንዲሰጥ አድርጓል።


የድሆችን ህይወት ለመለወጥ መለያ ልብሱን በጨረታ በመሸጥ ጭምር ገንዘቡን ወደ ግብጽ ይልካል። በየአመቱ በረመዳን የጾም ወቅት ድሆችን የመመገብና አልባሳትንም በመሰብሰብ የማደል ተግባርን ይፈጽማል።
ለህጻናት እግር ኳስ መጫወቻ ትጥቆችን ከሟሟላት ጀምሮ ለአንጋፋ ተጫዋቾች መጦሪያ ገንዘብ ድጋፍ በመስጠት ደግነቱን በተግባር የገለጠ ነው። ባለፈው አመት በቂ ገቢ ለሌላቸውና ለግብጽ የቀድሞ ተጫዋቾችን ላሰባሰበው ማህበር 27 ሺ ፓውንድ ሰጥቷል።


በናግሪግ የሚገኝ ሆስፒታል አስፈላጊ የሆኑ የመሳሪያ ቁሶችን ያሟላ ሲሆን፤ የአካባቢው የማህበረሰብ ጂም ማዕከልንም ሙሉ መሳሪያዎች እንዲኖሩት አድርጓል። “መሀመድ አያድ አል ታንታዊ ሀይ ስኩል” ለተባለ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የእግር ኳስ ሜዳ በማንኛውም የአየር ንብረት መጫወት የሚያስችል ሳር አስነጥፏል። በናግሪግ መንደር ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ቤት ለማስገንባት ቅድመ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ላይ ነው።


“እሱ እንደ ብዙዎቹ የግብፅ ዝነኛ ተጫዋቾች አይደለም። የስኬት ጣሪያ ላይ ሲደርስ የነበረበትን ማንነቱን የሚረሳ አይደለም። መሀመድ ሳላህን የተለየ የሚያደርገው ዝናውን ለመልካም ተግባር የሚጠቀም በመሆኑም ጭምር ነው።” ሲሉ የቀድሞ አሰልጣኙ መስክረውለታል።


በትርፍ ጊዜው እንደብዙዎቹ ዝነኛ ተጫዋቾች ምሽት ክለቦች እየዞረ መጨፈር ሳይሆን ከባለቤቱና ሴት ልጁ ጋር ማሳለፍ ብቻ ነው የሚስደስተው።

አስቸጋሪው የኮከብነት ጉዞ
መሀመድ ሳላህ ባለፉት አምስት አመታት በሶስት የአውሮፓ ሀገሮችና በአምስት ክለቦች ተዘዋውሯል። በስዊዘርላንድ ለባዜል፣ በጣሊያን ለፊዮረንቲና እና ለሮማ፣ በእንግሊዝ ለቼልሲና ለአሁኑ ክለቡ ለሊቨርፑል ተጫውቷል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ስኬት ያስመዘገበው በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በሊቨርፑል አመት ያልሞላ ቆይታው ነው።


በሊቨርፑል 11 ቁጥር መለያ ለባሹ ሳላህ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አውሮፓ የተጓዘው በ2012 ከግብጹ ኤል ሞካውሎን ክለብ ለስዊዘርላንዱ ባዜል በመፈረም ነው። ያን ጊዜ እድሜው 20 አመቱ ነበር። በ2014 ከባዜል ወደ ቼልሲ የተዛወረ ቢሆንም በፍጥነት መላመድ አልቻለም። ክለቡ በውሰት ለጣሊያኑ ፊዮረንቲና ሰጠው። በጣሊያን ከፊዮረንቲና በተጨማሪ ለሮማ ተጫውቷል። በሮማ በ2016/2017 የውድድር አመት ያሳየው ድንቅ ብቃት ሊቨርፑሎች እንዲያስፈርሙት አድርጓቸዋል።


የዛሬ አመት በድጋሚ ወደ እንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የተመለሰው መሐመድ ሳላህ፤ በ2017 የውድድር አመት በአንፊልድ ከየርገን ክሎፕ ቡድን ጋር ስኬታማ ጊዜን አሳልፏል። በተደጋጋሚ የወሩና የእለቱ ምርጥ የጨዋታ ኮከብ ሆኖ ተመርጧል። ዘንድሮም በሊጉ ከቶተንሀም ሆትሰፐርሱ አጥቂው ከሀሪ ኬን አንድ ግብ ዝቅ ብሎ በ21 ግቦች የኮከብ ግብ አግቢ ደረጃ ውስጥ ይገኛል። በአሁኑ ወቅቀ በታላላቅ ክለቦች ጭምር የሚፈለግ የፊት መስመር ተጫዋች ነው።


ይሁንና ተጨዋቹ አሁን የደረሰበትን ስኬት ያገኘው በአጋጣሚ ወይም በአቋራጭ መንገድ አይደለም። ለአመታት በትጋት የመስራቱ ውጤት ነው። ከልጅነቱ ጀምሮ የአለማችን ታላቅ ተጫዋች ለመሆን ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው። ፍላጎቱንም በከፍተኛ ጥረት አግዞ ሰርቷል። አሁን ደግሞ የልፋቱን ፍሬ እየለቀመ የሚገኝበትን ዘመን ጀምሯል።

 

የዘጠኝ ሰአት የአውቶብስ ጉዞ
የወቅቱ የአፍሪካ ኮከብ ተጫዋች መሐመድ ሳላህ እግር ኳስ ተጫዋች የመሆን ህልሙን ለማሳካት ገና በለጋነቱ ከፍተኛ የኑሮና የተጫዋችነት ጫናዎችን ተጋፍጧል። አነስተኛ ገቢ ያላቸው ወላጆቹ ግን ሁሌም ጥረቱን ይደግፉ ነበር። በተለይም ወላጅ አባቱ ከፍተኛ እገዛ ስላደረጉለት ፈተናዎቹን መወጣት ችሏል።


ከመኖሪያ ቤቱ ናግሪግ ካይሮ ወደሚገኘው የታዳጊነት ክለቡ ኤል ሞካውሎን ልምምድ ለመስራት ያደርግ የነበረው ጉዞ ግን እጅግ አድካሚና ለ14 አመት ታዳጊ በጣም ፈታኝ ነበር። ከትውልድ መንደሩ ናግሪግ ክለቡ የሚገኘበት ካይሮ ከተማ ልምምድ ለመስራት ደርሶ መልስ ለዘጠኝ ሰአት በህዝብ አውቶብስ መመላለስ እንደነበረበት ያስታውሳል።


“በየቀኑ ጠዋት ሶስት ሰአት ላይ ጉዞ እጀምራለሁ። ልምምድ ቦታ ከሰአት 8 ወይም 8፡30 እደርሳለሁ። ልምምዳችን 9፡30 ወይም 10፡00 ይጀምርና 12 ሰአት ይጠናቀቃል። ከዚያም ወደ ቤት ጉዞ እጀምራለሁ። ምሽት 4፡00 ወይም 4፡30 ሲሆን ቤት እደርሳለሁ። ወዲያውኑ ምግብ በልቼ እተኛለሁ”


“ልምምድ ቦታ ለመድረስ ታዲያ በየቀኑ አንድ አውቶብስ ብቻ ሳይሆን ሶስትና አራት አንዳንዴም አራትና አምስት አውቶብሶችን እጠቀም ነበር። በዚህ አይነት ሁኔታ በሳምንት አራት ቀናት ለሶስትና አራት አመት ሰርቻለሁ” ብሏል።


“ወደ ልምምድ ቦታ ለመሔድ ከትምህርት ቤት ቀድሜ ነበር የምወጣው። ታዲያ አሁን ላይ እግር ኳስ ተጫዋች ባልሆን ኖሮ ነገሮች በጣም አስቸጋሪ ይሆኑ ነበር ብሏል።”


በልጅነቱ እግር ኳስ ተጫዋች ለመሆን በየቀኑ በአስቸጋሪ የአውቶብስ ላይ ጉዞዎች ይደክም የነበረው መሀመድ ሳላህ፤ አሁን የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ተከላካዮችን የሚያደክም አጥቂ ሆኗል።


ተሰጥኦውን በተመለከተ በርካች አድናቆታቸውን እየገለጹለት የሚገኝ የወቅቱ የአውሮፓ ምርጥ አጥቂ ነው። ሀገሩ ብሔራዊ ቡድን ለ2018 የሩስያ አለም ዋንጫ እንድታልፍ ወሳኝ የሆነችዋን ግብ ካስቆጠረ በኋላ በርካታ ቅጽል ስሞች ጎርፈውለታል። ከሁሉም በላይ ግን ተጨዋቹ “ግብጻዊው ሜሲ” በሚለው ቅጽል ስሙ ይታወቃል።


ባለፈው ሳምንት በፕሪሚየር ሊጉ ሊቨርፑል ከቶተንሀም ሆትስፐርስ 2ለ2 በተለያየበት ጨዋታ ተከላካዮችን አልፎ ያስቆጠራት ድንቅ ግብ ደግሞ በእርግጥም ሜሲን የሚያስታውስ ነበር። አፍሪካዊው ኮከብ ብቃቱን እያሳደገ ከሄደ በቀጣይ አመታት ከአለማችን ኮከብ ተጫዋቾች አንዱ ሊሆን እንደሚችል ብዙዎች እየመሰከሩለት ነው።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
128 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 611 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us