ወላይታ ድቻ በአፍሪካ መድረክ አዲስ ታሪክ አስመዝግቧል

Wednesday, 21 March 2018 13:23

 

 

 

የዛማሌክ ክለብ ፕሬዝዳንት መንሱር ምሽቱ እስኪያልፍ አልጠበቁም። ክለባቸው ከአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ውጪ ከሆነ ከደቂቃዎች በኋላ ወዲያውኑ ነበር መግለጫ የሰጡት። ቁጣቸውን በሀገሪቱ ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ላይ ገለጹ። 

 

“እድሜ ለሚኒስትሩ እሳቸው በአፍረካ ውድድር ላይ ክለባችን እንዲሸነፍ ነበር የፈለጉት። እንኳን ደስ አላቸው። አል አህሊ ብቻ ስኬታማ እንዲሆን ነው የሚደግፉት። የተሸነፍነው በእሳቸው እንጂ በተጋጣሚያችን አይደለም።” በማለት ተናገሩ።


ዛማሌክ በኮንፈዴሬሽን ዋንጫከወላይታ ዲቻ ጋር በሚያደርገው የመልስ ጨዋታውን በካይሮ ኢንተርናሽናል ስታዲየም 25ሺ ደጋፊዎች በስታዲየም እንዲገቡ ያቀቡት ጥያቄ ተቀባይነት ሳያገኝ መቅረቱ አበሳጭቷቸዋል። በስታዲየሙ የተፈቀደላቸው 3ሺ ብቻ ደጋፊዎች ከወላይታ ዲቻን ለመደገፍ ከተገኙት 15 ደጋፊዎች የበለጠ የድጋፍ ድምጽ ቢኖራቸውም ቡድናቸውን መታደግ አልቻሉም። ብዙዎቹ ስታዲየሙን ለቀው የወጡት እያነቡ ነበር።


የግብጽ የቀድሞ አሰልጣኞችና ተጫዋቾችም በዛማሌክ ሽንፈት ብስጭታቸውን ወዲያውኑ ነበር መግለጽ የጀመሩትታዋቂ። የቀድሞው የአያክስና ቶተንሀም ሆትስፐር አጥቂ ሚዶ ስታቸውን መቆጣጠር ካቃታቸው ግብጻውያን መካከል አንዱ ነበር። ጨዋታውን ለመተንተን በቀረበበት የስፖርት ቴሌቭዥን በቀጥታ ስርጭት ላይ ትችቱን አዘነበበ።


“ዛማሌክ በታሪኩ እንዲህ ያለ አሳፋሪ ሽንፈት ደርሶበት አያውቅም። ይህ ትልቅ ውርደት ነው። ተጋጣሚያችን ወላይታ ዲቻ የአማተር ክብ ነው። ለዛማሌክ ትልቅ ክለብ አይደለም። እንዲህ ያለ ቡድን ግብጽ ውስጥ ቢሆን ደረጃው ሶስተኛ ዲቪዝዮን ነበር። እንዴት እንዲህ ያለ ቡድንን ማሸነፍ አልቻልንም?”


የአፍሪካ እግር ኳስ ላይ ትኩረት ሰጥተው የሚዘግቡ ስመ ጥር ጋዜጦችም ዋነኛ ጉዳያቸው የዛማሌክ ሽንፈት ነበር። የወላይታ ድቻ ማሸነፍ ሳይሆን የዛማሌክ መሸነፍን የሚገልጹ ርዕሶችን የያዙ ዘገባዎች አስነብበዋል።


“ዛማሌክ አስደንጋጭ ሽንፈት ገጠመው”፣ “የካይሮው ሀያል ክለብ በአሳፋሪ ሁኔታ ከውድድር ወጣ”፣ “ዛማሌክ በእንግዳ ክለብ ተዋረደ”፣ “ሀያሉ ክለብ ዛማሌክ በማይታወቅ ቡድን ከካፍ ውድድር ተሰናበተ” የመሳሰሉ ርዕሶች በመስጠተ የዛማሌክና ወላይታ ድቻን የጨዋታ ውጤት አጉልተው ዘግበዋል።


ከኢትዮጵያ ተነባቢዋ የእግር ኳስ የገጽ ድር ሶከር ኢትዮጵያ ‹የጦና ንቦች ካይሮ ላይ ተናደፉ› የሚል ርዕስ ይዛ ወጥታለች።


ታዋቂው የግብጽ እለታዊ ጋዜጣ አል አህራም የዛማሌክን ሽንፈት ዛማሌክ አስደንጋጭ ሽንፈት ከኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ወጣ› በሚል ርዕስ ዘግቧል።


የናይል ቲቪ ደግሞ ከጨዋታው በኋላ ከግማሽ ሰአት በላይ በዛማሌክ ሽንፈት ላይ ባለሞያዎችን ከያሉበት እየጋበዘ አወያይቷል። የስፖርት መረጃ አዘጋጅዋ ጋዜጠኛ ከስቱዲዮ በቁጭት ስሜት ትጠይቃለች።


“እንዴት ወላይታ ዲቻ በሚባል ምንም ኮከብ ተጫዋች የሌለው ክለብ ዛማሌክን የሚያህል ሀያል ክለብከውድድር አስወጣ? በሩሲያው የአለም ዋንጫ ግብጽን የሚወክሉ ተጫዋቾች ያሉበት ቡድን እንዴት ደጋፊውን አሳፈረ?” የሚሉ ጥያቄዎችን እያነሳች ባለሞያዎችን አወያየች። በርካታ ተንታኞችም ምላሽ እየሰጡ ዛማሌክን ወቀሱ።


ከአል አህሊ ደጋፊዎች በስተቀር በግብጽ የዛማሌክ ሽንፈት ያላሳዘነው ያላበሳጨው ደጋፊ አልነበረም ማለት ይቻላል። ትዊተር ላይ የአል አህሊ ደጋፊዎች በተቀናቃኛቸው ዛማሌክ ሽንፈት ሲሳለቁና ደስታቸውንም ሲገልጹ ነበር ያመሹት።


በኢትዮጵያውያን ዘንድም በምሽቱ ዋነኛ መነጋገሪያ የነበረውና በብዛት የተጠቀሰው ወላይታ ድቻና የካይሮ ድሉ ነበር። የእግር ኳስ አፍቃሪ የሆኑም ያልሆኑም፤ የወላይታ ዲቻ ደጋፊ የሆኑም ያልሆኑም ካይሮ ላይ የተመዘገበው ድል እንደ ብሔራዊ ቡድናችን ድል አስፈንድቋቸውን ስሜታቸውን ሲገልጹ ነበር። ብዙ ያስፈነደቃቸው ኢትዮጵያውያን በፌስ ቡክና በትዊተር ገጾቻቸው ላይ ደስታና አድናቆታቸውን ሲገልጹ ነበር። ለዲቻዎችን እንኳን ደስ አላችሁ ከሚለው የደስታ መግለጫ ጀምሮ የድቻን ድል ከወቅቱ የፖለቲካ ስሜቶች ጋርም ተያይዘው የሚጠቀሱ አስገራሚና አስቂኝ አስተያየቶችም ነበሩ። ሙያዊ አስተያየቶችም ከእግር ኳስ ቤተሰቦች ተሰንዝረዋል።


ለእግር ኳሱ እጅግ ቅርብ ከሆኑና ስልጠነ ላይ ትንታኔ በመስጠት ከሚታወቁ ባለሞያዎች አንዱ የሆነው ሳሙኤል ብዙነህ ለውጤቱ አሰልጣኙ የመረጠው መንገድ አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጾ ዘነበ ፍሰሀን አድንቋል።


“የኢትዮጵያ እግር ኳስ የሚፈልገው እውቀት ነው። ኢትዮጵያዊ እውቀት! አሰልጣኝ ዘነበ የአውሮጳ ወይም የአሜሪካ ምሩቅ አይደለም። ዘነበ ጮማና ስብ ካለን ዋጋ የለንም የሚል የዐካ ብቃት አሰልጣኝ አጠገቡ የለም። ዘነበ ያው መረዳት ብቻ ነው። የኢትዮጵያውያን ተጨዋቾች አቅም መረዳት! ከአውሮጳና አሜሪካ በመጣ ላይሰንስ ግብጽ ላይ አንገታችን ደፍተናል። በግዚና በእርዳታ በመጡ ፈረንጅ አሰልጣኞች ተዋርደናል! የኢትዮጵያን እግር ኳስ በተረዳው በሲ ላይሰንስ ባለቤቱ ዘነበ ፍሰሀ ግን በግብጽ አደባባይ በክብር ቀና ብለናል!”


ከአሰልጣኞች መካከልም የሐዋሳ ከተማ አሰልጣኙ ውበቱ አባተ ብቻ በይፋ ደስታቸውን ተካፋይ መሆኑን ገልጻል።እንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክቱን ያስተላለፈ ኢትዮጵያዊ አሰልጣኝ ነው።


“ለመላው የወላይታ ድቻ የቡድን አባላተና ደጋፊዎች በሙሉ፤ እንኳን ደስ ያላችሁ! ውጤቱ በትልቅ ትግል፣ ልበሙሉነትና ጥረት ያሳካችሁት በመሆኑ ይገባችኋል።” በማለት ነበር በግሉ የፌስቡክ ገጹ ላይ መልዕክቱን ያስተላለፈው።


እሁድ ምሽት መጋቢት 9 ቀን 2010 ዓ.ም. ለወላይታ ዲቻ እግር ኳስ ክለብ የማትረሳ ታሪካዊ ቀን ሆና ተጽፋለች። የቡድኑ አባላትና ደጋፊዎች በደስታ የሰከሩባት፤ ብዙ የኢትዮጵያእግር ኳስ አፍቃሪዎችም የተደነቁባት እለት ናት። በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥም የግብጽ ቡድኖችን የበላይነት የተገታበት ተብሎ የሚታወስ ይሆናል።


አሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀም ከወላይታ ዲቻ ጋር ያመዘገበውን ታሪክ በህይወቱ ከማይረሳቸው ድንቅ ክስተቶች መካከል አንዱ አድርጎ ጽፎታል። በተጫዋችነት ዘመኑ ያላሳካውን ድል በአሰልጣኝነት ጊዜው ማግኘቱ እጅግ እንዳስደሰተው ነው የተናገረው።


ወላይታ ዲቻ ከዛማሌክ ጋር በነበረው የካፍ ኮንፌዴሬሽን የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ በሐዋሳ ስታዲየም በጥሩ እቅስቃሴ 2ለ1 ማሸነፉ አይዘነጋም። በመልሱ ጨዋታ ግን ካይሮ ላይ ያሰቡትን ያህል የጨዋታ እንቅስቃሴ አለማሳየታቸውን የገለጸው ዘነበ፤ ለቀጣይ ጨዋታዎች ጥሩ ልምድ የተገኘበት መድረክ መሆኑን ይናገራል።


በዘንድሮው የካፍ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ወላይታ ድቻ በመጀመሪያ አህጉራዊ ተሳትፎው ያስመዘገበው ውጤት የብዙዎች መነጋገሪያ መሆኑ በእርግጥም ተገቢ ነው። በተለይም ደግሞ ዛማሌክን በደርሶ መልስ ጨዋታ ገጥሞ ያስመዘገበው ውጤት ለእግር ኳሳችን ትርጉም የሚሰጥ ነው። ከሌሎች ሀገሮች ቡድኖች ጋር በብዙ ነገሮች ልዩነት ቢኖረንም፣ በሊግ ጥራት፣ በአሰልጣኞች ታላቅነት፣ በተጨዋቾች ደሞዝ፣ በስታዲየሞች፣ አካላዊ ልዩነትም ቢኖረንም ተጋጣሚን ማሸነፍ የሚቻልበት ጉዳይ ላይ መስራት እንደሚገባ የሚያረዳ ነው።


በእግር ኳስ ጨዋታ ተጋጣሚን በልጦ ለማሸነፍ በዋናነት አቅምንና ክህሎትን መጠቀም መቻል አስፈላጊ እንደሆነ ወላይታ ዲቻ ምሳሌ ነው። የቡድን እንቅስቃሴ ደግሞ ሀያል ቡድን ለመቋቋምና ለማሸነፍ ጠቃሚ ታክቲክ ሆኖት ወላይታ ዲቻን ለአብነት የሚጠቀስ አድርጎታል። አሰልጣኝ ዘነበም ዛማሌክን ሐዋሳ ላይ 2ለ1 ካሸነፈ በኋላ በሰጠው አስተያየት ላይ ለቡድን እንቅስቃሴ ትኩረት መስጠታቸውን ገልጾ ነበር።


“እኛ እንደ ቡድን መንቀሳቀሳችን ነው የጠቀመን። ይህንን የቡድን መንፈስ ጠብቀን ከቆየንና ካይሮ ላይ መድገም ከቻልን እንደምናሸንፍ እርግጠኛ ነኝ” ሲል ከመልሱ ጨዋታ በፊት ተናግሮ ነበር።
ተጫዋቾቹም አላሳፈሩትም የግል ክህሎታቸውን ብቻ ከማሳየት ይልቅ ለቡድናቸው ውጤት መስዋዕትት የከፈሉበትን የቡድን እንቅስቃሴ አሳይተዋል። በእርግጥ ቡድኑ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ መከላከል ላይ ያመዘነ ጫና ውስጥ ገብቶ ተመልክተነዋል። በዚህም በተደጋጋሚ ዛማሌኮች የግብ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። ተክሉ ተስፉ በእጁ ኳስ ነካ ብለው (በወገቡ ነበር የነካው) ኬንያዊው ዳኛ ያልተገባ የፍጹም ምት ሰጡ። ወላይታ ዲቻዎች ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ነበር ኳስን መቀባበል ወደፊት ለመሔድ የሞከሩት።


ባለሜዳው ዛማሌክ 1ለ0 ማሸነፍ ብቻ ወደ ቀጣዩ ዙር ሊያሳልፈው ቢችልም ከእረፍት መልስ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ተጫውቷል። ወዲያውኑም የመጀመሪያዋን ግብ ባስቆጠረው በአህመድ ማደቡሊ አማካኝነት ሁለተኛ ግብ ማስመዝገብ ቻለ። ከዚህ በኋላ መከላከል እንደማያዋጣ የተረዱት ወላይታ ዲቻዎች ወደ ተጋጣሚያቸው ሜዳ መድረስ የቻሉበትን እቅስቃሴ ማድረግ የጀመሩት። በዚህም በዛማሌኮች ሜዳ በማዕዘን ምት መምቻ አካባቢ ቅጣት ምት ማግኘት ቻሉ። የተሰጠውን ቅጣት ምት ሀይማኖት ወርቁ ወደ ግብ አካባቢ ያሻገራትን ኳስ አብዱልሰመድ ሳኒ በግምባሩ ገጭቶ ከመረብ አሳርፏታል።


የአብዱልሰመድ ሳኒ ግብ የጨዋታውን ታሪክ የቀየረች ሲሆን፤ ሁለቱምን ቡድኖች በደርሶ መልስ ውጤት እኩል 3ለ3 እንዲሆኑ ያደረገች ነበረች። በሁለት ግቦች ልዩነት ሲመራ የነበረው ዛማሌክ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር፤ ዲቻዎችም እየተከላከሉ በመልሶ ማጥቃት ግብ ለማስቆጠር ሲሞክሩ ቆዩ። መደበኛው የጨዋታ ጊዜ አልቆ ወደ መለያ ምት ለማምራት የፈለጉበትን እንቅስቃሴ ማሳየታቸው አዋጥቷቸዋል።


የወላይታ ዲቻው ግብ ጠባቂ ወንደሰን ገረመው እና የዛማሌኪ መሀመድ ኤል ሸዋሪ ከተጫዋቾችን ሙከራዎች የማምከን ሀላፊነት ይዘው ተገኙ። የመጀመሪያ መቺው የዛማሌኩ ተጨዋች ግብ አስቆጠረ። የዲቻ የመጀመሪያ መቺ ጃኮ አረፋትም ኳስን ከመረብ አሳረፈ። ተመስገን ዱባና ተክሉ ታፈሰ ሀላፊነታቸውን ተወጡ። ሶስት እኩል ሆኑ። አራተኛውን መለያ ምት የሞከረው የዛማሌኩ አይማ ሄፍኒ የግብ ብረት መለሰበት። የዲቻው አብዱልሰመድ ሳኒ አራተኛውን ግብ አስቆጠረ። ዛማሌኮች አምስተኛ ሙከራቸውን በመሀመድ አብድላዚዝ ለማድረግ ተዘጋጁ።


የዛማሌኩ ተጨዋች አምስተኛዋ መለያ ምት ቢያስቆጥር አምስተኛዋን የወላይታ ዲቻን አምስተኛ ሙከራ ለመምታት ተዘጋጅቶ የነበረው ግብ ጠባቂው ወንደሰን ገረመው ኳሷን በእጆቹ መለሰ። ወዲያውኑም በግቡ መረብ ጥግ በኩል እየሮጠ ቀኝ እጁን ወደላይ ከፍ አድር ሩጫውን ቀጠለ- በስታዲየሙ ወደ ሚገኙ ኢትዮጵያውያን የወላይታ ዲቻ ደጋፊዎች። የቡድኑ አባላትም ተከትለውት ደጋፊዎቻቸው ጋር ደስታቸውን በጭፈራ መግለጽ ጀመሩ።


ጨዋታውን ከስፍራው ሆኖ በራዲዮ በቀጥታ ሲያተላልፍ የነበረው የስፖርት ዞኑ ጋዜጠኛ ሰኢድ ኪያር ከጨዋታው በኋላ ሲናገር ስታዲየም እንዲገቡ የተፈቀደላቸው 3.000 የዛማሌክ ደጋፊዎች በከፍተኛ ሀዘንና ብስጭት ስሜት ውስጥ እንደተመለከታቸው ተናግሯል።


ጨዋታውን በቀጥታ ሲያስተላልፍ የነበረው ኦኤን ስፖርት የተባለው የስፖርት ቴሌቭዥን ጣቢያም ወዲያውኑ ነበር በአረብኛ ቋንቋ የባለሞያዎች ውይይት ማድረግ የጀመረው። ናይል ስፖርት ቲቪም የዛማሌክ ሽንፈት ላይ ያተኮረ ዘገባውን ቀጥሏል። በእንግሊዘኛ የሚሰራው ናይል ቲቪ ጣቢያም ሰፊ ትንታኔ መስጠት ጀመረ።


ቅዳሜ እለት እንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋትፎርድ ላይ አራት ግቦችን ያዘነበው መሀመድ ሳላህን ብቃት ጉዳይ ዋነኛ አጀንዳቸው አድርገው ሲዘግቡ ለነበሩት የግብጽ መገናኛ ብዙሀን የዛማሌክ ሽንፈት ሌላ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖላቸዋል። የሳላህን ስኬት በማጣጣም ላይ ለነበሩ ግብጻውያን እግር ኳስ አፍቃሪዎችም የዛማሌክ ሽንፈት ደስታቸውን አብርዶታል።


ወላይታ ዲቻ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ በመጀመሪያ ተሳትፎው በቅድመ ማጣሪያ የዛንዚባሩን ዚማማቶ ክለብን ከውድድር ካስወጣ በኋላ ከግብጹ ዛማሌክ ጋር ሲደርሰው እንደሚሸነፍ ተገምቶ ነበር። ይሁንና ግምቶቸን ያፈራረሰ አቋም በማሳየት ወደ ቀጣዩ የምድብ ድልድል መግባት ችሏለል። በዚህም ቡድኑ አድናቆትና ድጋፍ ሊሰጠው ቢገባ ተገቢ ነው።


በቀጣይ ወላይታ ዲቻ ከካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ወደ ኮንፌዴሬሽኑ የወረዱ ክለቦች አንደኛቸው ጋር ሊደለደል ይችላ። ወደ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ከወረዱ ክለቦች መካከልም አንዱ የኢትዮጵያ ክለብ የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊገጥመው ይችላል።


ቅዱስ ጊዮርጊስ በቻምፒየንስ ሊጉ ከኡጋንዳው ኬሲሲኤ ጋር በነበረው ጨዋታ በደርሶ መልስ 1ለ0 ተሸንፎ ከውድድሩ መውጣቱ ይታወሳል። በቀጣይም በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳታፊ ከሆኑ ክለቦች መካከልም አንዱ በመሆን ይወዳራል።

 

 

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
112 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 786 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us