የአሰልጣኝ አብርሀም ስኬት በየመን እግር ኳስ

Wednesday, 04 April 2018 14:29

 

ላለፉት አራት ዓመታት በእርስ በርስ ጦርነት እየፈራረሰች የምትገኘው የመን፣ የህዝቦቿ አንድነት የተናጋባት የመን፣ የውጭ ሀገር ስደተኞች መተላለፊያና የባርነት ንግድ የሚካሔድባት የመን፣ ሰሞኑን አለም ሁሉ በአድናቆት የተመለከተው መልካምዜና ተሰምቶባታል። በኢትዮጵያዊው አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ የሚመራው ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድኗ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ለእስያ ዋንጫ ማለፍ ችሏል።


በአሁኑ ወቅት በዚህች ምስቅልቅሏ በወጣ የበረሀ ሀገር እግር ኳስን መጫወት ቅንጦት ሊመስል ይችላል። ነገር ግን የእግር ኳስ ስፖርት የተረጋጋችና አንድ የሆነች የመንን ለመፍጠር ከፖለቲከኞች የበለጠ ሚና ያለው መሰረታዊ ሀይል ነው። ሰሞኑን ብሔራዊ ቡድኗ ለእስያ ዋንጫ የውድድር መድረክ ያለፈበትን ውጤት ሲያስመዘግብ የመናዊያን ደስታቸውን ሲገልጹ ታይተዋል። ውጤቱ ተስፈኛ ወጣቶችን ለማየትም የተቻለበት ነበር።


የመን በተለያዩ ሀይሎች ተከፋፍላ በምትገኝበት በዚህ ወቅት በእግር ኳስ ያስመዘገበችው ውጤት በእርግጥም ለሀገሪቱ ሰላምና አንድነት ለማምጣት ሚና እንዳለው ብዙዎች እየመሰከሩ ነው።
በፖለቲካ ቀውስ ምክንያት የሀገር ውስጥ የእግር ኳስ ውድድሮች መካሔድ ከቆመ አራት አመት ሆኗል። ሀገሪቱ የዓለም አቀፍ ግጥሚያዎችን በሜዳዋ አታደርግም። ከሀገሯ ውጪ ርቆ በሚገኘው ኳታር ነው የምትጫወተው።


በዚህ ሁሉ ፈተናዎች እየተጨነቀ የሚጓዘው ብሔራዊ ቡድኗ ለ2019 የእስያ ዋንጫ ማለፉ መነጋገሪያ ሆኗል። ከዚህ ትልቅ ስኬት ጀርባ ደግሞ ኢትዮጵያዊው አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ይጠቀሳል። እ.ኤ.አ. በ2016 ዋናውን ብሔራዊ ቡድን የማሰልጠን ኃላፊነት የወሰደው ኢትዮጵያዊው አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ የመንን ታላቅ ለሚባል የእግር ኳስ የውድድር መድረክ በማብቃት የመጀመሪያው የውጭ ሀገር አሰልጣኝ ሆኗል።


በየመን እግር ኳስ ውስጥ ለረጅም አመታት የቆየው አሰልጣኝ አብረሀም ቀደም ሲል ከ21 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን አሰልጥኗል። በወቅቱም ለ2013 መድረክ ማብቃት ችሎ ነበር።


አብርሃም ከሁለት አመት በፈት የተረከበውን ዋናውን የየመን ብሔራዊ ቡድንን ለ2019 የእስያ ዋንጫ ለማብቃት በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ማለፍ ነበረበት። ከአራት አመት በላይ የሀገር ውስጥ የሊግ ውድድሮች በተቋረጡበት ሁኔታና ያለ ደጋፊዎች ብሔራዊ ቡድንን ለውድድር ማዘጋጀት ከባድ እንደነበር ተናግሯል። ይሁንና የማጣሪያ ጨዋታዎቹን ባልተጠበቀ ሁኔታ ነው ያስመዘገበው። ቡድኑ በምድብ ማጣሪያ ሁለት ጨዋታዎችን በማሸነፍና አራቱን አቻ በመለያየት ያለምንም ሽንፈት የነው ያጠናቀቀው።


ቡድኑ ወደ እስያ ዋንጫ ማለፉን ያረጋገጠው በመጨረሻው የምድብ የማጣሪያ ጨዋታ ኔፓልን 2ለ1 በማሸነፉ እና በተመሳሳይ ምድብ የምትገኘው ፊሊፒንስ ታጅክስታንን በተመሳሳይ ውጤት በመርታቷ ነበር።


በየመን ኦሊምፒክ ኮሚቴ ውስጥ በአመራርነትም የማገልገል ኃላፊነት የነበረው አሰልጣኝ አብርሀም፣ የመንን ለ2019 የእስያ ዋንጫ ያሳለፈበት ውጤት በእግር ኳስ ህይወቱ ትልቅ ስኬት ሆኖ ይጠቀሳል። እርሱም በዚህ ውጤት የተሰማውን ደስታ ለቢቢሲ በሰጠው አስተያየት እንዲህ ሲል ገልጾታል።


‹‹ለእስያ ዋንጫ ለመድረስ ያደረግነው ጉዞ ሁሉ እጅጉን አስቸጋሪ ሁኔታዎች የተሞላ ነበር። የማይሳካ የሚመስለውን ነገር በማሳካቴ በጣም ደስ ብሎኛል። የመን በእርስ በእርስ ጦርነቶች ባለመረጋጋቷ በሀገር ውስጥ የእግር ኳስ ውድድሮች አይካሔዱም። ኢንተርናሽናል ጨዋታዎችንም በሜዳችን ማድረግ አንችልም። በዚህ ሁኔታ ብሔራዊ ቡድን መገንባትና ለኢንተርናሽናል መድረክ ለማዘጋጀት በጣም ፈታኝ ነው። ይህንን ሁሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች አልፈን ለእስያ ዋንጫ በመብቃታችን በጣም ደስ ብሎኛል።›› ብሏል።


አሰልጣኝ አብርሃም የየመንን ብሔራዊ ቡድን ለትልቅ የውድድር መድረክ በማብቃት የመጀመሪያው የውጭ ሀገር አሰልጣኝ ሆኖ በታሪክ መመዝገቡ የፈጠረበትን ስሜት በተመለከተም ‹‹ይህንን ስኬት ማስመዝገብ የቻለ ኢትዮጵያዊ አሰልጣኝ በመሆኔ ደግሞ ይበልጥ ኮርቻለሁ›› ብሏል።¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
96 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 721 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us