በዛብህ መለዮ ዑመድ ኡኩሪ ለተጫወተለት አል ሃርቢ ያመራል

Wednesday, 11 April 2018 14:55

 

በወላይታ ዲቻ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ አይረሴ ታሪክ በማስመዝገብ ከሚጠቀሱ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው የፊት መስመር ተጫዋቹ በዛብህ መለዮ ወደ ግብጽ ሊግ የመዛወር እድል አግኝቷል። ዛማሌክን ከኮንፌዴሬሽን ውጭ ያደረገበት እንቅስቃሴው ተጫዋቹ ተፈላጊ አድርጎታል።

 

በሐዋሳ ስታዲየም ተመልካቾች በሞሉበት ጨዋታ ያልተጠበቀ ክስተት ተፈጠረ። በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ በ16ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ዳዊት ያሻገረለትን ኳስ በዛብህ መለዮ ወደ ግቡ መረብ በቀጥታ ይመታታል። ኳሷም አይደፈሬ በሚመስለው የዛማሌኩ ግብ ጠባቂ ኤል ሻውሪ መረብ ላይም አረፈች። በወቅቱም የሐዋሳ ስታዲየምን ዳር እስከ ዳር የሞላው ተመልካችም ከተቀመጠበት በመነሳት ደስታውን በጩኸት ገለጸ።


የሐዋሳ ስታዲየምን በደስታ ማዕበል ያናወጠችው የበዛብህ ግብ በወላይታ ዲቻ ክለብ ታሪክ በኢንተርናሽናል ጨዋታ መድረክ በኢትዮጵያዊ ተጫዋች የተቆጠረች የመጀመሪያ ግብ ሆና ተመዝግባለች። በዛብህ መለዮም ከግቧ ጋርና ከእለቱ የ2ለ1 አሸናፊነት ታሪክ ጋር ሁሌም ተያይዞ የሚጠቀስ ሆኗል።


በመልሱ ጨዋታ በዛማሌክ ሜዳ በመረጠው የመከላከል ጨዋታ አማካኝነት በዛብህ በማጥቃት እንቅስቃሴ ያለውን ክህሎት ማሳየት አልቻለም ነበር። ይሁንና ተጨዋቹ በመጀመሪያው የሐዋሳ ሜዳ ላይ ያሳየው እንቅስቃሴና ግብ ያስቆጠረበት ልዩ ክህሎት ዋጋ አግኝቷል። የበዛብህን ግብና የጨዋታ ክህሎት የተመለከቱ የሀገር ውስጥና የግብጽ ክለቦች አይኖቻቸውን አሳርፈውበታል። በተለይም ደግሞ ሀያሉ ክለብ ላይ በከፍተኛ የራስ መተማመን መንፈስ ተረጋግቶ ግብ ያስቆጠረው ተጫዋች በግብጽ ክለቦች ዘንድ ትኩረት አግኝቷል።


በኢትዮጵያ እግር ኳስ የሚያተኩረው የገጽ ድር ሶከር ኢትዮጵያ ሰሞኑን ታማኝ ምንጩን በመጥቀስ እንደዘገበው ከሆነ የግብጽ ክለቦች የወላይ ዲቻ ሁለት ተጫዋችን ለመውሰድ ፍላጎት አሳይተዋል። አንደኛው ተጫዋች የቶጎው አጥቂ ጃኮ አረፋት ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ በዛብህ መለዮ ነው። የበዛብህ ፈላጊ ክለብ የቀድሞው የኡመድ ኡክሪ ክለብ ኤል አህሪ መሆኑን ሶከሮች ዘግዋበል።


በግብጽ ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ የሆነው ኤል ኤንታግ ኤል ሀርቢ በዛብህን ለማስፈረም ከተጫዋቹ ወኪል ጋርም ድርድር ያደረገ ሲሆን፤ ኢትዮጵያዊውን አጥቂ በሙከራ ጊዜ ለመመልከት ጥሪ አድርጎለታል። በቅርቡም ወደ ግብጽ እንደሚያመራ ተጫዋቹ ራሱ በሰጠው አስተያየት አስታውቋል።


በዛብህ ወላይታ ዲቻን የተቀላቀለው ከአራት አመት በፊት በክለቡ ለረጅም ጊዜ አሰልጣኝ በነበረው መሳይ ተፈሪ አማካኝነት ነበር። አሰልጣኝ መሳይ ከአራት አመት በፊት ከሃድያ ሆሳዕና ወደ ወላይታ ዲቻ በማዛወር ለዛሬ ብቃቱ አስተዋጸኦ ማድረጉን ይናገራል። በክለቡ የመሰለፍ እድል ስለሰጠውም ሁሌም ያመሰግነዋል። ከቤተሰቡ መካከልም መልካም አርአያ ከሆነው በወላይታ ዲቻ ከታላቅ ወንድሙ ጋር የመሰለፍ እድል በማግኘቱም ደስተኛ እደሆነ ነው የገለጸው።


በቀጣይ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መለያ ለብሶ ለሐገሩ የመጫወት ከፍተኛ ፍላጎትና ምኞት እንዳለው የተናገረው በዛብህ፤ በክለብ ደረጃ ከሀገር ውጪ ባሉ ክለቦች በመጫወት የእግር ኳስ ህይወቱን ወደ ላቀ ደረጃ ማሻገር ይፈልጋል። ከወላይታ ዲቻ ጋር በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ መድረክ ያሳየው ብቃት ያመጣለት እድል እንደ ትልቅ አጋጣሚ የሚቆጠር ነው።


በቅርቡ ከግብጹ ክለብ የቀረበለትን የሙከራ ጊዜ ተቀብሎ ወደ ካይሮ የሚያመራ ሲሆን፤ ክለቡ የሰጠውን የሙከራ ጊዜ በጥሩ ሁኔታ እንደሚያሳልፍ ተናግሯል። የግብጽ ሊግ የመጫወት እድሉ ባይሳካ እንኳን ለሌሎች የባህር ማዶ ክለቦች የመጫወት እድል የማግኘት ተስፋ እንዳለውና ሙከራውን እንደማያቋርጥ ነው የተናገረው።
የበዛብህ ፈላጊ ክለብ የሆነው አል ኤንታግ አል ሀርቢ በግብጽ ፕሪሚየር ሊግ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
77 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 475 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us