የወልዲያ ከተማ ቅጣትና ህልውና

Wednesday, 18 April 2018 13:29

 

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በዲሲፕሊን ኮሚቴው በኩል በወልዲያ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ላይ ሰሞኑን ያስተላለፈው የቅጣት ውሳኔ የክለቡን ደጋፊዎች ክፉኛ አስቆጥቷል። ቅጣቱ ለተፈጠረው ችግር ፍትህ ከመሆን ይልቅ የበለጠ ጥፋት የሚያስትከትል መሆኑን በመግለጽ ፌዴሬሽኑ ውሳኔውን እንዲቀለብስ የሚጠይቁ ወገኖች ድምጽ ከፍ ብሎ እየተሰማ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንዶች የቅጣቱ ጉዳይ ከእግር ኳስም ባሻገር ፖለቲካዊ መልክና ትርጉም እንዲሰጡትም አስገድዷቸዋል።

ሚያዝያ 3 ቀን 2010 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 19ኛ ሳምንት መርሀ ግብር የወልዲያ ከተማ እና ፋሲል ከነማ ቡድኖችን ያገናኘ ነበር። የሼህ ሁሴን መሐመድ አል አሙዲን ስታዲየምም በርካታ ደጋፊዎች ተሞልቶ ነበር። ወልዲያ ከመውረድ ስጋት ለመውጣት፤ ፋሲል ከነማ ደግሞ ከመሪዎቹ ተርታ ላለመራቅ ጠንካራ ፉክክር የሚያደርጉበት በመሆኑ ጨዋታው ከፍተኛ ግምት ሊያገኝ ችሏል።

ከዚህ በተጨማሪም የወልዲያው አሰልጣኝ ዘማሪያም ወልደጊዮርጊስ የቀድሞ ክለባቸውን በተቃራኒ የገጠሙበት፤ ፋሲሎችም የቀድሞው የወላይታ ዲቻ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪን ይዘው የተገኙበት በመሆኑ ጨዋታው ከፍተኛ ግለት ነበረው። ጨዋታው በአማራ ቲቪ በቀጥታ ስርጭት የተላለፈ ሲሆን፤ የበርካቶች እይታንም ያገኘ ነበር።

ሁለቱ ክለቦች 1 ለ1 በሆነ ውጤት ከ90 ደቂቃ በላይ ቆይተው በጨዋታው ማብቂያ ላይ ልዩነት የምትፈጥር የፍጹም ቅጣት ምት በመሰጠቱ ያልተጠበቀ ሁከት ሊፈጠር ችሏል። በጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ በ92ኛው ደቂቃ የተሰጠችዋ ፍጹም ቅጣት ምት የጨዋታውን አጠቃላይ መንፈስ ቀይራለች። የመሀል ዳኛውን ውሳኔ በመቃወም ለደቂቃዎች ጨዋታው ሊቋረጥ ችሏል። ከብዙ ግርግር በኋላ ጨዋታው እንዲቀጥል ተደርጎ የፍጹም ቅጣት ምቱን ፋሲሎችን መሪ በማድረግ ጨዋታው ሶስት ነጥብ እንዲያገኙ የምታደርጋቸው ሆናለች። ፋሲሎችን የ2ለ1 መሪነት ያጎናጸፈችው ግብ ከተቆጠረች በኋላ ግን ጨዋታውን ሲመለከቱ የነበሩ የተወሰኑ ሰዎች ወደ ሜዳ በመግባት በእለቱ የመሐል ዳኛ እና ረዳት ዳኛ ላይ ድብደባ ፈጽመዋል።

ከፍጹም ቅጣት ምቷ በፊት አሰልጣኝ ዘማሪያም ወደ ሜዳ በመግባት የመሀል ዳኛውን በማነቅና በመገፍተር ያልተገባ ተግባር ፈጽመዋል። የወልዲያው ተጫዋች ብሩክ ቃልቦሬም ዳኛውን ለመማታት ሲጋበዝና ሲገላገል ታይቷል። አሰልጣኝ ዘማሪያምና ተጨዋቹ ብሩክ ከሌሎች የወልዲያ ተጫዋች በተለይ ሁኔታ ያሳዩት ባህሪና ድርጊት ደጋፊዎች በስሜታዊነት ያልተገቡ ድርጊቶችን እንዲፈጽሙ የሚገፋፉ መሆናቸው የሚኮነን ነው። ብዙሀኑን ደጋፊዎች በጨዋነት የመምራት ሀላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው ከወቀሳ የሚድኑ አይደሉም።

በእለቱ በተፈጠረው ግርግር በጨዋታው ዳኞች ላይ የተፈጸመው አካላዊ ጥቃት ፈጽሞ የማይገባና በዝምታ የማይታለፍም ነው። ሊለወጡ የማይችሉ የዳኞች ውሳኔዎች (ትክክል ባይሆኑም እንኳን) ውሳኔዎቹን በጸጋ ተቀብሎ ቅሬታዎችን በህጋዊ ሁኔታ ማሰማት ሊለመድ ያልቻለ መንገድ ሆኗል። ደጋፊዎች በስሜታዊነት የሚፈጽሟቸው ጥፋቶች ክለቦችን ለከፍተኛ ጉዳት እየዳረገ ነው።

ፋሲሎችን ከወልደያ መግቢያቸው አካባቢ ድረስ ሔዶ በፍቅርና በክብር ተቀብለው ያስተናገዱት ወልዲያዎች በሜዳ ውስጥ ተቀናቃኝ ከ90 ደቂቃ በላይ ቡድናቸውን ሲደግፉ ቆይተዋል። በመሆኑም ደጋፊውን በሙሉ በጠብ ጫሪነት መፈረጅ አይቻልም። ይሁንና ጥቂቶች የፈጠሩት ጥፋት መላው ደጋፊውን የሚያሳዝን፤ ቡድኑንም የሚጎዳ ሆኖ ተገኝቷል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም በእለቱ ለተፈጠረው የስታዲየም ውስጥ ሁከትና ጥፋት ወልዲያ ላይ የተላለፈውን የቅጣት ውሳኔ አሳውቋል። በፌዴሬሽኑ የስነምግባር ኮሚቴ በኩል ተላለፈ የተባለው የቅጣት ውሳኔ ምናልባትም ከመቼውም ጊዜ የበለጠና የከፋ ነው። በገንዘብም ሆነ በሌሎች ቅጣቶች በአይነቱ ወደር የለሽ ሆኖ ነው የምናገኘው።

የወልዲያ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ለተፈጠረው ሁከት ተጠያቂ በማድረግ የ250 ሺህ ብር ቅጣት እንዲከፍል ተወስኖበታል።

ከዚህ በተጨማሪም ወልዲያ ከተማ የሚጠቀምበት የሼህ ሁሴን መሐመድ አል አሙዲን ስታዲየም ለአንድ አመት ምንም አይነት ጨዋታ እንዳይካሔድበት ታግዷል። ወልዲያ በሜዳው የሚያደርገውን ጨዋታ 500 ኪ.ሜ ርቀት በሚገኝ በፌዴሬሽኑ በተመዘገበ ስታዲየም እንዲያደርግ ነው የተወሰነበት።

የወልዲያ ከተማ አካላዊ ጥቃት ለተሰነዘረባቸው ዳኞችን የህክምና ወጪዎች እንዲሸፍንም ቅጣት ተላልፎበታል።

በእለቱ ለተፈጠረው ሁከት ከፍተኛ ሚና ነበራቸው የተባሉት የክለቡ አሰልጣኝ ዘማሪያም ወልደጊዮርጊስ እና ተጨዋች ብሩክ ቃልቦሬ ላይም ቅጣት ተጥሎባቸዋል። አሰልጣኙ ዳኛውን በማነቅና በመገፍተር እንዲሁም በመሳደብ ለፈጸሙት ጥፋት ለአንድ አመት ከማንኛውም የአሰልጣኝነት ሙያ እንዳይቀርቡ የታገዱ ሲሆን፤ የ20 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣትም ተላልፎባቸዋል። ተጨዋቹ ብሩክ ቃልቦሬም ተመሳሳይ አንድ አመት ከጨዋታ የታገደ ሲሆን፤ የ10 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣትም ተጥሎበታል።

በወልዲያ ላይ የተላለፈው ቅጣት ተገቢነት መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል። መሰል ውሳኔዎች ሲተላለፉ ከፍትህ ባሻገር ለእግር ኳሱ ጥፋቶች መፍትሔ መሆን ይኖርባቸዋል። ከዚህ አንጻር በወልዲያ ላይ የተላለፈው ቅጣት በብዙ ችግሮች ውስጥ ለሚገኘው ወልዲያ እግር ኳስ ክለብ ከነጭራሹ የሚያፈርስ እንደሆነ መረዳት ይቻላል። ክለቡ ቅጣት መጣሉ ተገቢ ቢሆንም፤ ክለቡ ብቻ ሀላፊነት ሊወስድ በሚችለው ጥፋቶች ላይ መሆን ይኖርበታል። ለረብሻው መንስኤ የሆኑ አካላት በእርግጥ የወልዲያ ከተማ ደጋፊዎች መሆናቸውን ማረጋገጥ ባልተቻለበት ሁኔታ ፌዴሬሽኑ ክለቡ ሀላፊነቱን ሙሉ ለሙሉ እንዲወስድ አድርጓል።

ከዚህ በተጨማሪም የሼህ መሐመድ ሁሴን አል አሙዲን ስታዲየም ላይ የተላለፈው የአንድ አመት እገዳም መነጋገሪያ ነው። ስታዲየሙ ወልዲያ ከተማ ክለብ በሜዳው የሚያደርገውን ጨዋታ ቢጠቀምበትም በባለቤትነት ያሰራውና የሚያስተዳድረው አይደለም። የአካባቢው ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን የአማራ ክልል እና የኢትዮጵያ አንደኛው ስታዲየምም ነው። ስታዲየሙን ለአንድ አመት ከማንኛውም ውድድር እንዳያስተናግድ ማገድ ክለቡን ብቻ ሳይሆን ሀገርንም የሚጎዳ ውሳኔ እንደሆነ መረዳት ይቻላል። ለመሰል የስታዲየም ውስጥ ጥፋቶች የሚጣለው ቅጣት ክለቦች በሜዳቸው የሚያደርጉትን ጨዋታ ያለደጋፊ በዝግ እንዲያከናውኑ አሊያም ከፍ ሲል የተወሰኑ ጨዋታዎችን ከሜዳቸው ውጪ እንዲያደርጉ ነው።

ከእግር ኳስም በላይ

በወልዲያ እግር ኳስ ቡድን ላይ የተላለፈው ቅጣት የስፖርት ጥፋትና ቅጣት ብቻ ነው ብለው ለማመን የሚከብዳቸው ወገኖች ጉዳዩን በፖለቲካ መነጽርም ይቃኙታል። ክለቡ የእግር ኳስ ብቻ ሳይሆን የማንነታችን መገለጫና መጠሪያችን ነው ብለው የሚያምኑ ደጋፊዎች ፍትህ ለማግኘት እንደሚታገሉ እየተናገሩ ነው። ቡድኑ መፍረስ የእኛን ለማጥፋት የተጠነሰሰ ሴራ አለ ብለው ይሞግታሉ።

እነዚህ ወገኖች በሌሎች መሰል መድረኮች የተፈጠሩ ግጭቶች ላይ ፌዴሬሽኑ ውሳኔ አለመስጠቱን የሚገልጹ ሲሆን፤ በቅርቡ በአዲግራትና መቀሌ ከተማ መካከል የተፈጠረውን ግጭት ለአብነት ይጠቅሳሉ። ጨዋታው እንዲቋረጥ ለማድረግ ያስገደደ ሁከት በተፈጠረበት ጨዋታ ላይ በፌዴሬሽኑ የቅጣት ውሳኔ አለመተላለፉ ለምንድነው ሲሉም ይጠይቃሉ። ከሌሎች ተመሳሳይ ጥፋቶች በተለየ ሁኔታ ወልዲያ ላይ ቅጣት መተላለፉ እግር ኳሳዊ ምክንያት ነው ብለው ለመቀበልም ያዳግታቸዋል።

ከቅርብ አመታት ወዲህ የፖለቲካ መንፈስም የሚታይበት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ሁኔታዎችን ሁሉ በስፖርታዊ ትርጉም መመልከት የማይቻል ሆኗል። የወልዲያ ከተማ ላይ የተላለፈው ቅጣትም ከጀርባው ፖለቲካዊ መልዕክት እንዳዘለ የሚናገሩ ወገኖች በብዛት እየተሰሙ ነው።

የወልዲያ ጉዳይ ከእግር ኳስም ባሻገር ነው የሚሉት እነዚህ ወገኖች ውሳኔው ‹ወልዲያን የማፍረስ ሴራ ነው› ሲሉ ይደመጣሉ። የወልዲያን ቡድን መፍረስ የአንድ ክለብ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ እግር ኳስ በተለይም ለክልሉ እግር ኳስ እድገት ጉዳትም እንደሆነ በመግለጽም በፕሪሚየር ሊጉ ያላቸውን ውክልና ለማቆየት እየተሟገቱ ነው።

በአጠቃላይም በወልዲያ ከተማ የእግር ኳስ ክለብ ላይ የተላለፈው ቅጣት ያልተገባ መሆኑን በመግለጽ የሚቃወሙ የወልዲያ ደጋፊዎች ከፌዴሬሽኑ ፍትህን ይፈልጋሉ። በማህበራዊ የገጽ ትስስር መረቦች ላይም ‹ወልዲያን እናድን› እና ‹ፍትህ ለወልዲያ› በሚል መሪ ቃሎች ዘመቻ ብዙዎች ጀምረዋል።

የሊጉ ቆይታ

በእርግጥም በወልዲያ ላይ የተላለፈው የቅጣት ውሳኔ በክለቡ ህልውና ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስበት ነው። በዘንድሮው የፕሪሚየር ሊግ ቆይታውን አደጋ ውስጥ የሚጥል ነው። ክለቡ በሊጉ 12ኛ ደረጃ ላይ ነው። በቀጣይ ደግሞ የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች ከሜዳው ውጪ ስለሆነ ደጋፊዎቹን በቀላሉ ማግኘት አይችልም። ይህም በውጤቱ ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩ አይቀርም። የክለቡን የገንዘብ አቅም ስለሚፈታተን እና በተጫዋቾች ላይም ድካም ስለሚፈጥር ውጤቱ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ከፍተኛ መሆኑ አያጠያይቅም።

የወልዲያ ከተማ የተላለፈበትን ውሳኔ በመቃወም ይግባኝ እንደሚጠይቅ ይጠበቃል። ውሳኔው በመጀመሪያው የሚጸድቅ ከሆነ በወልዲያ ክለብ በፕሪሚየር ሊጉ የመቆየቱ ነገር አዳጋች ይሆናል። በፕሪሚየር ሊጉ የመቆየቱ ነገር ካበቃ ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ ተነቃቅቶ የነበረው የአካባቢው እግር ኳስ የሚቀዛቀዝና ወደኋላ ሊጓዝም እንደሚችል ይገመታል።¾

ፌዴሬሽኑ በእድሜ ማጭበርበር

5,000 ዶላር ተቀጣ

በብሩንዲ እየተካሔደ ባለው ከ17 አመት በታች የሴካፋ ዋንጫ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በእድሜ ማጭበርበር የ5,000 ዶላር ቅጣት ተላልፎበታል። የታዳጊ ቡድኑ በመጀመሪያ ጨዋታ ያስመዘገበው ሶስት ነጥብም ተወስዶበታል።

በውድድሩ መድረክ የኢትዮጵያ ቡድን በምድቡ ከሶማሊያ፣ ኬንያ ጋር የተደለደለ ሲሆን፤ እሁድ እለት በአደረገው የመጀመሪያ ጨዋታው ሶማሊያን 3ለ1 ማሸነፍ ችሎ ነበር። ይሁንና ከጨዋታው በኋላ የሶማሌ ቡድን ቅሬታውን በማቅረቡ በተደረገው ማጣራት የኢትዮጵያ ቡድን ከእድሜያቸው በላይ የሆኑ ሶስት ተጨዋቾችን ማሰለፉ ተረጋግጧል። በዚህም የተነሳ ሴካፋ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ላይ የ5,000 ዶላር ቅጣት አስተላልፏል። ለሶማሊያ ቡድንም የሶስት ነጥብና የ3ለ0 አሸናፊነትን አጎናጽፏል።

በዘንድሮው ከ17 አመት በታች የሴካፋ ዋንጫ ስምንት ሀገሮች ተሳታፊ ናቸው። በምድብ አንድ ብሩንዲ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያና ሶማሊያ በምድብ ሁለት የአምና ሻምፒዮኑ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ሱዳንና ዛንዚባር ተመድበዋል። ከሁለቱ ምድቦች አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ይዘው የሚያጠናቅቁት ወደ ግማሽ ፍጻሜ ውድድር ያልፏሉ። የዋንጫው ጨዋታ አፕሪል 28 በንሆዚ ስታዲየም እንደሚካሔድ የወጣው መርሀግብር ያመለክታል።¾

የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር

ያዘጋጀው ስልጠና ተካሔደ

የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እና ከአለምአቀፉ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የሁለት ቀናት ስልጠና በስኬት ተጠናቋል። በስልጠናው ላይ የተካፈሉ የማህበሩ አባላት መሰል የስልጠና መድረኮች በማዘጋጀት የጋዜጠኛውን አቅም ማጎልበት እንደሚኖርበት ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ አዜማን ሆቴም ባለፈው ቅዳሜና እሁድ የተካሔደው የስልጠና መድረክ በጋዜጠኝነት ስነ ምግባር እና በወቅቱ የስፖርት ጋዜጠኝነት ፈተናዎች ዙሪያ ላይ ያተኮረ ነበር። ስልጠናውን በዋናነት የሰጡትም በጣሊያኑ ዴሎ ስፖርት ጋዜጣና ስካይ ኢታሊያ ቴሌቭዥን ጨምሮ በአለም አቀፍ ሚዲያዎች በመስራት ከ25 አመት በላይ የካበተ ልምድ ያላቸው ጣሊያናዊው ሪካርዶ ሮማኒ ናቸው። በስልጠናው ላይም ከ50 በላይ የማህበሩ አባላት ተካፋይ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር የአባላቱን አቅም ለማጎልበት የስልጠና እና የልምድ ልውውጥ የሚደረግባቸው መድኮችን በየጊዜው እያዘጋጀ ነው። በዚህ አመትም ሶስተኛ በሆነው መድረክ ላይ ከፍተኛ የሆነ እውቀት እንዳገኙበት ተሳታፊ የሆኑ አባላት ገልጸዋል። በቀጣይም ማህበሩ መሰል መድረኮች በተደጋጋሚ እንደሚያዘጋጅ ጠይቀዋል።

የማህበሩ ፕሬዝዳንት ጋዜጠኛ ዮናስ ተሾመ የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ሙያዊ ሀላፊነታቸውን በብቃት ለመወጣት እንዲችሉ የሚያደርጉ መሰል መድረኮችን እንደሚያዘጋጅ አስታውቋል። የሁለት ቀናት ስልጠናው በስኬት እንዲካሔድ ድጋፍ ላደረጉ ለኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና ለአለምአቀፉ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር እንዲሁም ለአዜማን ሆቴል ምስጋናውን አቅርቧል።

በስልጠናው መድረክ ላይ የክብር እንግዳ ሆነው ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ተወካይ ወይዘሮ ሔሮዳዊት የስፖርት ጋዜጠኞች ሙያዊ አቅማቸውን ለማሳደግ በሚጓዙበት መንገድ የኦሊምፒክ ኮሚቴው ድጋፍ እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል። ከዚህ በተጨማሪም ጋዜጠኞች ከእግር ኳስና አትሌቲክስ ስፖርት ውጪ ላሉ ሌሎች የስፖርት አይነቶችም የዘገባ ሽፋን እንዲሰጡ ጠይቀዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
95 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us