ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ስታዲየምና የወጣቶች ማዕከል ምን አጠፋ?

Wednesday, 25 April 2018 12:59

 

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በወልድያ እና በፋሲል ከነማ ጨዋታ በተከሰተው ረብሻ ጋር ተያይዞ የወልድያ የሙሐመድ ሁሴን አሊ አልአሙዲ ስታዲየምና የወጣቶች ማዕከል ማናቸውንም ውድድሮች ለአንድ ዓመት እንዳያካሂድ መታገዱ ይታወሳል። ይህም ጉዳይ የስፖርት ቤተሰቡንና ጉዳዩ በቀጥታና በተዘዋዋሪ የሚመለከታቸው አካላትን ሲያወያይ ከርሟል። የወልድያ ስታዲየም ጥር 6 ቀን 2009 ዓ.ም ግንባታው በይፋ መመረቁና በዕለቱም ሼህ ሙሐመድ ላሳደጋቸውና ለወግ ለማዕረግ ላበቃቸው የወልድያ ሕዝብ የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በተገኙበት በስጦታ ማስተላለፋቸው የሚታወስ ነው። ስታዲየሙ ትልልቅ አገራዊና ዓለማቀፋዊ ውድድሮች ይካሄዱበታል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ነበር። ነገርግን ሰሞኑን ከእግር ኳስ ፌዴሬሽን የወጣው ቅጣት ከክለቦች አልፎ ስታዲየሙ እንዲዘጋ የሚያደርግ ውሳኔ መያዙ ብዙዎችን አሳዝኗል። ይህንን ጉዳይ መነሻ በማድረግ ከወልድያ ስታዲየም የምህንድስና ጥበብ ጀርባ ስማቸው በጉልህ የሚነሱት ዶ/ር አረጋ ይርዳው የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር ሚያዝያ 15 ቀን 2010 ዓ.ም በፃፉት ደብዳቤ ቅሬታቸውን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ ኃላፊዎች ገልጸዋል። የደብዳቤው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።

***          ***          ***

ለክቡር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት

አዲስ አበባ

ጉዳዩ፡    ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ስታዲየምና

የወጣቶች ማዕከልን ይመለከታል

ተጠቃሽ፡ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለወልድያ ከተማ ስፖርት ክለብ የተጻፈ ደብዳቤ ቁጥር፡ 25/ኢእፌአ9/034 ቀን 08/08/2010 ደብዳቤ

ከሁሉ አስቀድሜ የስፖርቱን ዓለም በማፍቀር በግላቸው፣ በመንግሥት ሥራ ኃላፊነታቸው፣ በቡድን መሪነታቸው፣ በክለብ አስተዳዳሪነታቸው፣ በተለያዩ የፌዴሬሽን ሥራቸው፣ በዜና ዘጋቢነታቸው ተግባር ተሰማርተው ለስፖርት ዕድገት በከፍተኛ ደረጃ ለሚደክሙ ሁሉ ከሚያገኙት ጥቅም ይልቅ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦና መስዋእትነት ከፍ ያለ መስሎ ስለሚታየኝ አድናቆቴ ከፍ ያለ ነው። ይህ ደብዳቤ እንደ አንድ ግለሰብ በተቆርቋሪነት የቀረበ መሆኑን ከወዲሁ መግለጽ እወዳለሁ። የተለያዩ የግል ድርጅቶችና የዩኒቨርስቲ የመምራት ኃላፊነቴ፣ ስፖርት ሥራን በህብረት በማሠራት፣ ደንበኛን በማርካትና ውጤታማ በመሆን ለሥራዬ ዓቢይ አስተዋጽኦ እንዳለው ከልብ አምናለሁ። በምመራቸው 25 የሚድሮክ ቴክናሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች ውስጥም የተለያዩ ክለቦች በማቋቋም፣ ዓመታዊ ውድድር ማድረግ ከጀመርን ከ13 ዓመት በላይ ሆኖናል። ስፖርት ህብረት ፈጥሮልናል፣ መልካም ሥነ ምግባርን እንድናበለጽግ ረድቶናል። ቆንጆ ስታዲየም የመገንባት ሙያችንንም አዳብሮልናል።

በአንድ ወቅት ከሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች የተውጣጡ ተጫዋቾች ያሉበት "የመቻሬ" እግር ኳስ ቡድን በአዲስ አበባ አቋቁመን ወደ ብሔራዊ ሊግ ገብቶ እንዲጫወት አድርገን ነበር። ይህ ቡድን በመንግሥትና በእግር ኳስ ፌዴሬሽን የተሰጡ ህጐችንና መመሪያዎችን እንዲያከብር ከማድረጋችን በላይ የራሳችን የውስጥ መመሪያ አውጥተን ቡድኑ በሥራ ላይ እንዲያውለው በማድረግና በየሜዳው ተገኝተን መከታተል ጀመርን። ከውስጥ የዲሲፕሊን መመሪያችን ውስጥ ጨዋታ ተመልካቹ በኩባንያዎቻችን ውስጥ የምናመርታቸው ምርቶች ገዥ በመሆኑ በደንበኛ (Customer) መልክ በጥንቃቄ በመያዝ ተገቢውን አክብሮት ማድረግ እንዳለብን፣ ተጫዋቾቹን አሳምነን ሥራ ጀመርን። የኩባንያዎቻችን ማልያ ማንነታችንን በአዎንታዊ መልኩ በህዝቡ ዘንድ እንዲያስተዋውቀን በማቀድ በጽኑ አምነን ሥራ ገባን። ሆኖም በየጨዋታው ቦታ ስንገኝ ብዙ በጆሮ ሊሰሙ የማይገቡ ቃላትና አልባሌ ሁናቴዎችን ብንመለከትም በጨዋታው ገፋንበት። ከዚህ በኋላ ተጫዋቾቻችን የውስጥ ደንባችንን መጣስ ጀመሩ። ከእነዚህ የውስጥ ደንቦች ውስጥ የዳኛን ውሳኔ አለማክበርና መጨቃጨቅ፣ በአንድ ጨዋታ ከአንድ በላይ ቀይ ካርድ ማግኘት ተቀባይነት እንደማይኖራቸው በደንባችን ውስጥ ስለነበር፣ ይህን በመተላለፍ ስነ-ስርዓት የጐደለው ሥራ በመሥራት፣ ሁለት ቀይ ካርድ ከገንዘብ ቅጣት ጋር ቡድኑ አገኘ። ማኔጅመንቱም ቡድኑ ምናልባትም በዲስፕሊን አቋሙ ከሚጠበቅበት ደረጃ እንዳልደረሰ በመገንዘብ ከፌዴሬሽን እንዲወጣ የራሳችን ውሳኔ ወሰድን። ሠራተኛው ከ"መቻሬ" ቡድን ይልቅ በየኩባንያዎቹ ቡድን አቋቁሞ የሠራተኞቹን የስፖርት ፍላጐት የማርካት ሥራ እንዲሠራ አደረግን። ይህን በማድረጋችን የጠቅላላው የቴክኖሎጂ ግሩፕ ሠራተኞችን የስፖርት ስሜት ሳንጐዳ በተሻለ መልኩ ስፖርቱ እንዲቀጥል አድርገናል። "የመቻሬ" ቡድን አጠፋ ብለን የስፖርቱ እንቅስቃሴ ከኩባንያዎቻችን ውስጥ እንዲጠፋ አላደረግንም። ማንም ጥፋተኛ በመመሪያና በህግ መሠረት ቅጣት ማግኘት እንዳለበት አምናለሁ። ሆኖም ቅጣቱ ፍትሐዊ መሆን ብቻ ሳይሆን ክለቡን፣ ቡድኑን፣ አጠቃላይ የስፖርት አፍቃሪውን የስፖርት ፍቅር በአሉታዊ መንገድ የሚጐዳ እንዳይሆን ጥንቃቄ ከመሪዎች/ከሀላፊዎች የሚጠበቅ ነው።    

ወደ ዋናው ጉዳዬ ስመለስ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ ሚያዝያ 03 ቀን 2010 ዓ.ም. በወልድያ ከተማ ቡድንና በፋሲል ከተማ ቡድን መካከል የተደረገውን የእግር ኳስ ጨዋታ አስመልክቶ ለተፈጠረው ችግር የሰጠውን ውሳኔ ኮፒ አግኝቼ መመልከት ችያለሁ። በዚህ ውሳኔ ላይ ቅጣት የተጣለባቸው የወልድያ ስፖርት ክለብ አሠልጣኝ፣ አንድ የወልድያ ስፖርት ቡድን ተጫዋች፣ የወልድያ ከተማ እግር ኳስ ቡድንን ያካተተ ነው። ከላይ የተጠቀሱት ላይ የፌዴሬሽኑን የዲስፕሊን መመሪያ አንቀጾች በመጥቀስ የተደረጉ ውሳኔዎች ላይ በጉዳዩ ጥልቅ እውቀት ስለሌለኝ ለባለሙያዎች በመተው ተገቢው ፍትሃዊ ውሳኔ እንደገና የማየት ሁኔታ ይደረግበታል የሚል ተስፋ ጽኑ እምነት አለኝ።

ይህ እንዳለ ሆኖ በውሳኔው ቁጥር 2 ላይ የቀረበውና የሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ስታዲየም አጠቃቀምን በሚመለከት የተወሰነው ውሳኔ ግን ፍትሃዊና ትክክለኛ መስሎ ስላልታየኝ ፌዴሬሽኑ በጥሞና እንዲመለከተው ትንሽ ልበል።

በመጀመሪያ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ስታዲየም እና የወጣቶች ማዕከል በለጋሹና በአንድየው የሀገር አጋር ሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ ተሠርቶ የተበረከተው ለወልድያና ለአካባቢው ህብረተሰብ መገልገያ እንዲሆን ታቅዶ ነው። ይህም ማለት ተቋሙ (ስታዲየሙ) የወልድያ የእግር ኳስ ክለብ ወይም ቡድን ሀብት አይደለም። በወልድያና አካባቢዋ፣ ከዚያም አልፎ በሀገር ደረጃ ለኢትዮጵያውያን ወገኖች ከአንድ ለእናት ሀገሩ ፍቅር ባለው ባለሃብት የተሰጠ መሆኑና በከፍተኛ ደረጃ ክቡር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር፣ በተገኙበት ተመርቆ ለህዝቡ የተበረከተ ተቋም ነው።

ይህ መሆኑ ግልጽ ሆኖ እያለና ፌዴሬሽኑ ይህን ስታዲየም ለሀገርም፣ ለአህጉርም እንዲሁም ለዓለም ልዩ ልዩ ውድድሮች እንዲውል በማድረግ ያስተዋውቀዋል ብለን በምንጠብቅበት ወቅት፣ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ባለሀብት የሆነው የአካባቢው ህዝብ እንዳይገለገልበት ማድረግ ፍጹም አሳዛኝና ስሜታዊ እርምጃ ነው። የዲሲፕሊን ኮሚቴው ቁጥር 2 ውሳኔ እንዲህ ይላል፡-

"የወልድያ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ለጨዋታው ያስመዘገበው የወልዲያ ሼህ አላሙዲ ስታዲየም ክለቡ ጥፋት ከፈፀመበት ከሚያዚያ 03 ቀን 2010 ዓ.ም. እስከ ሚያዚያ 2 ቀን 2011 ዓ.ም. በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዲሲኘሊን መመሪያ ክፍል 2 ምዕራፍ 5 በአንቀጽ 43 መሰረት በወልዲያ ሼህ አላሙዲ ስታዲየም የሚደረጉ ጨዋታዎች የመጫወት መብት እንዲያጡ እና በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሚካሄዱ ማንኛውም የእግር ኳስ ውድድሮች እንዳይካሄዱ ተወስኗል።"

ይህ ማለት ስታዲየሙ ባለበት ዝግጁ ሆኖ እንዲገኝ የሚያስፈልገው የገንዘብ ምንጭ ሁሉ ተቋርጦ፣ ከአንድ ዓመት በኋላ ሸረሪት ጠረጋ ውስጥ እንዲገባ የማድረግ ሥራ ላይ እንዲጠመድ ማድረግ ይሆናል። ወልድያና አካባቢው ብሎም ኢትዮጵያውያን በሙሉ ይህን ለሀገር የተበረከተ ስታዲየም በአግባቡ መጠቀም ይፈልጋሉ። ተገቢውን ክልላዊና ፌዴራላዊ ድጋፍ እና አስተዳደር በማመቻቸት የሀገራችን ባለሃብቶች በስፖርቱ ዓለም በሰፊው እንዲሳተፉ ቀስቃሽ (insentive) ይሆናል ብለን ሂደቱን በመጠባበቅ ላይ ባለንበት ወቅት ግራ የሚያጋባና እጅግ ለምናፈቅራት ወልድያና አካባቢዋ የቱሪስት መስህብ በመሆንና የወጣቶቹንም በስፖርቱ ዓለም የመሳተፍ ስሜትና ፍላጐት እንዲያጐለብት የተሠራው ስታዲየም ላይ የተወሰነው እገዳ ፍጹም ፍትሃዊ ስላልሆነ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በአንክሮ እንዲመለከተው በአክብሮት ስጠይቅ፣ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ስታዲየም ምን አጠፋ? ለሚለው ጥያቄ መልስ ለማግኘት በመሻት ነው። ተቋሙ ብዙ ዓይነት የስፖርት መሥሪያ ያለው በመሆኑ ከተማዋና አካባቢው በስታዲየሙ መገልገል የሚፈልግ መሆኑን አግንዛቤ ማስገባት ለአካባቢው እንደሚጠቅም ፌዴሬሽኑ እንደሚረዳ እርግጠኛ ነኝ። ስለሆነም አስቸኳይ መፍትሄ ቢሰጥበት ሁላችንም ደስ ይለናል።

በተያያዘ መልኩ የምንወዳትን ወልድያ በባህል፣ በኢኮኖሚ፣ በትምህርት፣ በልማት ወዘት ወደፊት እንዳትራመድ አሉታዊ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ግለሰቦች፣ ቡድኖች የአመራር አካላት፣ ግለሰቦች፣ ወዘተ ሰከን ባለ መልኩ ለአካባቢው እድገትና ብልጽግና ቅድሚያ በመስጠት የተፈጠረውን አንገት የሚያስደፋ አሉታዊ ገጽታ (image) በያገባኛል ስሜት በህብረት ማስወገድ እንዳለብንና ለዚህም ወልድያ-ወዳዶች የሆን ሁሉ እንደምንረባረብ ከወዲሁ እየገለጽኩ፣ የሚቻለውን ሁሉ በማድረግ ወልድያ የሰዎች መገናኛ ሆና እድገቷን እንደምታፋጥን ሙሉ እምነትና ተስፋ በመሰነቅ ነው።

           ከአክብሮት ሠላምታ ጋር

አረጋ ይርዳው (ዶ/ር)

ቺፍ ኤግዝኪዩቲቭ ኦፊሰር/ፕሬዚዳንት

ሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ

         (ፊርማና ማሕተም አለው)

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
172 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 547 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us