ዳኞቹ ጥያቄያቸው ሳይመለስ ውድድሮችን እንዲያስቀጥሉ ጫና በዝቶባቸዋል

Wednesday, 09 May 2018 13:39

 

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ስታዲየም መከላከያ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ባካሄዱት ጨዋታ በእለቱ ጨዋታውን በመሩት ፌዴራል ዳኛ እያሱ ፈንቴ ላይ የደረሰው ጥቃት የእግር ኳሱን ችግሮች ይበልጥ አጉልቶ አሳይቷል። በዳኛው ላይ የደረሰው ጥቃት ከዚህ በፊት የተፈጸሙና ያልሻሩ ቁስሎች እንዲያገረሹ አድርጓል። ሙያተኞቹም የተጠራቀሙ ችግሮቻቸውን ሁሉ በምሬት አሰምተዋል። የእስካሁኑ ይበቃል፤ ከእንግዲህም እንዳንጎዳ በሚል በሙያ ማህበራቸው አማካኝነት የተስማሙበትን አቋማቸውን ይፋ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ የዳኞችና ታዛቢዎች ማህበር ሰሞኑን ባወጣው የአቋም መግለጫ ላይ የአባላቱ መብቶችና ደህንነት ለማስጠበቅ ሲል በቀነ ቀደብ እንዲሟሉ የፈለጋቸውን ጥያቄዎችን ነው ያቀረበው። ጥያቄዎቹ እስከ ግንቦት 20 ቀን 2010 ዓ.ም. የመፍትሔ ምላሽ ካላገኙ የትኛውንም የውድድር መድረክ ተገኝተው ጨዋታዎችን በዳኝነት እንደማይመሩ ነው ያስታወቁት።

ማህበሩ ባወጣው የአቋም መግለጫ ላይ ካስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች አንደኛው በሁሉም የሀገሪቱ የእግር ኳስ መድረኮችን ጨዋታ ለሚዳኙ አባላቱ ፌዴሬሽኑ የህይወት መድህን ዋስትና እንዲገባላቸው ሲል ያቀረበው ጥያቄ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞም ፌዴሬሽኑ በጨዋታ ላይ ጥቃት የተፈጸመባቸው ዳኞችን የህክምና ወጪ እንዲሸፍንና ካሳም እንዲሰጣቸው ጠይቋል።

ከዚህ በተጨማሪም ዳኞች ጨዋታዎችን ለመምራት በተለያዩ አካባቢዎች ሲጓዙ የአውሮፕላን ማረፊያ ባላቸው ከተሞች በሚካሄዱ ጨዋታዎች የአውሮፕላን መጓጓዣ ትኬት እንዲጓዙ እና በስታዲየም ውስጥም አስተማማኝ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ነው።

እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች እስከ ግንቦት 20 ቀን 2010 ዓ.ም እንዲሟሉና እስከዚያው ድረስ ግን ጨዋታዎችን እንደማይዳኙ ነው ያስታወቀው። ቅድመ ሁኔታዎቹ ካልተሟሉ ዳኞቹ ሙያዊ አልግሎታቸውን ያለመስጠት ተቃውሟቸው ከግንቦት 20 ወዲያም ሊራዘም እንደሚችልም ነው ያስታወቀው።

ይህን ተከትሎም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና ክለቦች ድምጻቸውን አሰምተዋል። ሁለቱም አካላት ግን አንደኛውንም የዳኞች ጥያቄን ሳይመልሱ ወደ ውድድር እንዲመለሱ ከፍተኛ ጫና በመፍጠር ላይ ናቸው።

በማህበሩ የተነሱት ቅድመ ሁኔታዎች ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እጅግ ፈታኝ ናቸው ተብሎ ባለመታመኑም በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሔ እንደሚያገኝ ነበር የተገመተው። ይሁንና በስራ አስፈጻሚ የምርጫ ጉዳይ የተወጠረው ፌዴሬሽኑ ተስፋ የሚሰጥ ምላሽ እንኳን መስጠት አልቻለም። ‹‹ስራችሁን እየሰራችሁ ጥያቄያችሁን ማቅረብ ትችላችሁ›› እና ‹‹ችግሮቹ ላይ እየተወያየን በሒደት የምንፈታው ይሆናል›› የሚል አስተያየት ከመስጠት እና፤ በስተመጨረሻ ላይ ደግሞ ማሳሰቢያ አዘል የሰብሰባ ጥሪ በማድረግ ዳኖቹ ወደ ጨዋታ እንዲመለሱ በመወትወት ላይ ነው።

ይሁንና በዚህ ጽሑፍ አቅራቢ እምነት ዳኞቹ ያቀረቧቸው የመብት ጥያቄዎች ለፌዴሬሽኑ የማይቻሉ አይደሉም። ዳኞቹም ለፌዴሬሽኑ የማይቻሉ ነገሮችንም አልጠየቁም። ተቋሙ ለብቻውም ሆነ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበርና በመስማማት ጥያቄዎቹን ሁሉ መመለስ ይችላል።

ለፌዴሬሽኑ ፈታኝ የሚመስለው የህይወት መድህን ዋስትና (Life Insurance) ጉዳይ ነው። ነገር ግን ይህም የማይቻልና ከባድ አይደለም። በፊፋም ሆነ በካፍ ዘንድ ተቀባይነት ያለውና መሰረታዊ ጉዳይ ነው። ፌዴሬሽኑ ዳኞች በሜዳ ውስጥ ለሚደርስባቸው ጉዳት የህይወት መድህን ዋስትና እንደተቋም ስምምነት ሊፈጽም ይገባል። ዋስትናውንም ከዳኞች ማህበር እና ከክለቦች ጋር ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ጋር እንዲሁም በመተባበር ሊያሟላ ይችላል። ከሌሎች አካላት ጋር ለመወያየት ደግሞ ጊዜ ብቻ ነው የሚፈልገው። ለዚህም ደግሞ ሒደቱን ለመጀመርና መስመር ለማስያዝ ጊዜ እንዲሰጠው መጠየቅ ይችላል።

የህክምና ወጪንና ካሳን በተመለከተም ፌዴሬሽኑ በቀላሉና በአጭር ጊዜ ውስጥ ማስተካከል የሚችለው እንደሆነ ነው የሚታመነው። ጉዳት የደረሰባቸው ዳኞች ተጠያቂ ወይም ኃላፊነት ያለባቸው ክለቦች ጋር ስምምነት በመፍጠር መፍትሔ መስጠት ይችላል።

ይሁንና ፌዴሬሽኑ ለአንደኛውም ጥያቄ ምንም አይነት ተጨባጭ ተስፋ እና መፍትሔ ሳያበጅ ዳኞቹ ጨዋታ መምራታቸውን እንዲቀጥሉ ለማድረግ የውይይት መድረክ የሚጋብዙ ደብዳቤዎችን በመጻፍ ቀናትን እየፈጀ ነው።

ከፌዴሬሽኑ ጋር ውይይት ያደረጉት የእግር ኳስ ክለቦችም ቅሬታ አዘል አስተያየታቸውን በመሰንዘር ዳኞቹ ያቋረጡትን የሙያ አገልግሎት እንዲጀምሩ ነው የጠየቁት። ብዙዎቹ የክለብ አመራሮች በዳኞቹ ላይ በደረሰው ጉዳት ከማዘንና ከመቆርቆር የበለጠ ጨዋታ ባለማድረጋቸው የሚደርስባቸውን የገንዘብ ኪሳራ አስልተው ነው ቅሬታቸውን የገለጹት።

ክለቦቹም ቢሆኑ ዳኞቹ ላቀረቡት ጥያቄ አዎንታዊ አሊያም አማራጭ መፍትሔ ማቅረብ አልቻሉም። ይልቁንም ዳኞቹ ወደ ስራ ካልገቡ ከጅቡቲ፣ ከሱዳንና ከኬንያ ዳኞችን በማስመጣት ውድድሮችን እንዲመሩ ማድረግ ይቻላል ሲሉም አማራጭ የሰጡ የክለብ አመራር አስተያየትም ተሰምቷል። በዚህም በብዙ የስፖርት ቤተተሱ ዘንድ ከፍተኛ ትችት ተሰንዝሮባቸዋል።

ይሁንና ክለቦች በሜዳቸው ዳኞችን ደህንነት ለመጠበቅ ተገቢውን ኃላፊነት መውሰድ የዳኞችን ችግሮች ለመፍታት አስተዋጽኦ የማድረግ ኃላፊነታቸውን መወጣት የሚችሉበት መፍትሔዎች አሉ። ለአብነት ያህልም ዳኞች ከደህንነታቸው ጋር በተያያዘ ላነሱት ጥያቄ ክለቦች ኃላፊነት በመውሰድ መልስ መስጠት ይችሉ ነበር።

ይኸውም በጨዋታ ወቅት ዳኞች ላይ ጥቃት ለመፈጸም የሞከሩና የሚሞክሩ የቡድናቸው አባላት ላይ ክለቦች የስነ ምግባርና ሌሎች የቅጣት ውሳኔዎችን ለማስተላለፍ ቃል መግባት ይችሉ ነበር። በተመሳሳይ ዳኞች ላይ ጥቃት የሚያደርሱ ደጋፊዎቻቸውን ወይም ሌሎች አካላትን ለይተው በማውጣት ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው የሚያደርጉ መሆናቸውንም እንዲሁ መግለጽ ይችሉ ነበር። ይህም ዳኞች ደህንነት ተሰምቷቸው ጨዋታዎችን ለመምራት እምነት እንዲያድርባቸው ያደርጋል።

ክለቦች መቀመጫቸውን ካደረጉበት የከተማ አስተዳደር አካላት፣ ከጸጥታ ኃይሎች እና ከፌዴሬሽኑ ጋር በመቀናጀት የስታዲየም ውስጥ ደህንነትን ማስጠበቅ በመስራት የዳኞችን የደህንነት ጥበቃ ማረጋጥ ይችላሉ። ይህንን ለማድረግ እንደ አዳማ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ያሉ ስምምነታቸውን ቢገልጹም አንደኛውን የዳኞች ጥያቄ መመለስ ይችሉ ነበር።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም ክለቦች ጥፋት ፈጻሚዎችን አጋልጠው ለመስጠት እንደሚሰሩ ቢያረጋግጡ ዳኞች የጥያቄያቸው ከፊል መልስ እንደተመለሰ ሊቆጥሩት ይችላሉ። ይህን ማድረግ ደግሞ ክለቦች ቢችሉ በዳኞች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን የማስቀረት ኃላፊነት ከመወጣታቸው ባሻገር በግጭቶች ሳቢያ በክለባቸው ላይ የሚጣሉ ቅጣቶችንም ማስቀረት ይችላሉ።

በአጠቃላይም የእግር ኳሱ ባለድርሻ አካላት ትብብር በመፍጠር የዳኞቹን መሰረታዊ የመብት ጥያቄዎች መፍትሔ መስጠት ይችላሉ። ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ የተዘፈቀውን እግር ኳሱንም ከተጨማሪ ውድቀት ይታደጉታል።

አሁን ለጊዜው ፈጣን ምላሽ የሚሻውን የዳኞችን የመብትና ፍትህ ችግሮችን ለመፍታት ከሚደረገው ጥረት ባሻገር በቀጣይነትም ለዘለቄታዊ መፍትሔውም መስራት ከእግር ኳሱ ባላድርሻ አካላት ይጠበቃል።

በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ እግር ኳስ አሰልጣኞች ማኅበር ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ጨዋታዎች የፊታችን ቅዳሜ እና እሁድ እንዲካሄዱ በሙሉ ድምፅ መወሰኑ ያስታወቀ ቢሆንም፤ እስከ ማክሰኞ ምሽት የዳኞችና ታዛቢዎች ኮሚቴ ባወጣው የአቋም መግለጫ ለማወቅ እንደተቻለው ያቀረቡት ጥያቄ መልስ ካልተሰጠው ጨዋታ ለመምራት እንደማይፈልጉ በአቋማቸው መፅናታቸውን ገልጿል።¾

አዲሱ አስመራጭ ኮሚቴ ተስፋ ተጥሎበታል

ለወራት ሲጓተት የቆየውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚ ምርጫን በገለልተኛነት ያስፈጽማል ተብሎ የታመነበት አስመራጭ ኮሚቴ ምርጫ ተከናውኗል። አሁን በስራ ላይ ባለው አመራር ጥቆማ የቀረቡ እጩዎች ላይ የጠቅላላ ጉባኤው አባላትን ከፍተኛ ድምጽ ያገኙት ናቸው የተመረጡት። በመገናኛ ብዙሀን ዘንድ ብዙም እውቅና የሌላቸው ግለሰቦችን ያሰባሰበው አስመራጭ ኮሚቴም ምርጫውን በፍትሀዊነት ያከናውናል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባለፈው ሳምንት በጠራው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ከፊፋ በተላለፈለት ትዕዛዝ መሰረት አዲስ አስመራጭ ኮሚቴ አባላት እንዲመረጡ አድርጓል። የኮሚቴ አባላቱ በገለልተኛነት ምርጫውን የሚያስፈጽሙ አካላት መሆን እንዳለባቸው ፊፋ በጥብቅ ማሳሰቡ ይታወሳል።

ለአስመራጭ ኮሚቴ ከቀረቡ መካከልም አብዛኛውን ድምጽ ያገኙት አቶ አስጨናቂ ለማ፣ ኢንጂነር ጌታሁን ሁሴን፤ አቶ መሐመድ ኑር አብዱልከሪም፣ ወይዘሮ ህይወት አዳነ እና አቶ ኢብራሂም አደም ናቸው። አቶ አስጨናቂ ለማ የአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢ ሲሆኑ፤ ኢንጂነር ጌታሁን ደግሞ ምክትላቸው በመሆን ይሰራሉ። ኮሚቴው ምርጫው የሚካሔድበትን ቀን መወሰንና እጩዎችንም አጣርቶ በመለየት ይፋ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴን የሚመሩ አካላትም ታውቀዋል። ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴውን አቶ ሽፈራው አመኑ የሚመሩት ሲሆን፤ አቶ ኦባንግ ሀባላ በምክትልነት ያገለግላሉ።

የአስመራጭ ኮሚቴ አባላቱ በርካታ ውዝግቦችን በማስተናገድ እግር ኳሱን ያመሳቀለውን የምርጫ ሒደት በታማኝነትና ያለመድልዎ ለማከናወን ቃል ገብተዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
47 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 607 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us