“ከሚስቴ አፋቱኝ!!!”

Wednesday, 12 August 2015 12:33

እንደምን ሰንብታችኋል ውዶቼ!?. . . የዛሬ ጨዋታችን ወይም ቲኪ-ታካችን (ቲኪ-ታካ የስፔን ጋላክቲኮ ክለቦች የሚያሳዩት ምርጥ ጨዋታ እንደሆነ ከእናንተ የተሰወረ አይደለም) እናላችሁ ከሰሞኑ ለጆሯችን ደርሶ የደነቀን አስተዛዛቢ ዜና በመነሳት አንድ ወዳጃችን ነገሩን “ኮስሞ- ቲኪ ታካ” ብሎታል።

እኔ የምለው ሰምታችኋል አይደል? ባለፈው ሳምንት “ኤሜሬት 24/7” አስነበበን ሲል ሸገር ኤፍ -ኤም የነገረንን ድንቅ ዜና?. . . አልጄሪያዊው ሰው ወዷትና አፍቅሯት ያገባትን ሴት ፤ ገና ፊርማው ሳይደርቅ “በህግ አምላክ ከሚስቴ አፋቱኝ!” ማለቱ ተሰምቷል። ድንቅ የሚለው ምክንያቱ ነው፤ “ያገባኋት ሴት ያልኮስሞቲክስ ቅባቶቿ ፍፁም አስቀያሚ ናት” የሚል ነበር። ሌላው ዜናውን አስደናቂ ያደረገው ነገር ደግሞ የሰውዬው አቤቱታ “ከአፋቱኝ!” አልፎ “በኮስሞቲክስ አጭብርብራኝ እንዳገባት አድርጋኛለችና የሞራል ካሳ ይገባኛል” ማለቱ ነው።

“ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም” ማለት ይሄኔ ነው ጎበዝ!. . . ይህን ዜና ስሰማ ምን አይነት ወግ ትዝ አለኝ መሰላችሁ? . . . ሰውዬውና ሴትየዋ ለ20 ዓመታት በትዳር ኖረዋል። እርሷ ጨቅጫቃ፣ ተጠራጣሪና ቀናተኛ ናት፤ ግን ባሏን በጣም ትወደዋለች። እርሱም የዛሬን አያድርገውና በጣም ይወዳት ነበር። ነገር ግን ፀባይዋ እሳትና ውሃ እየሆነ ቢቸግረው ልቡ ቀስ በቀስ ተሸረሸረ።

አንድ ቀን ታዲያ የሚከተለው ታሪክ ተከሰተ። ሚስት እኩለሌሊት አካባቢ ከእንቅልፏ ነቃች። ባሏ ግን ከጎኗ አልነበረም። አንዳች ጥርጣሬ ብልጭ አለላትና ነገሩን ለማጣራት ቀስ ብላ ወደሳሎን ቤት ገባች። ባል በጨለማ ውስጥ ተቀምጦ መጠጡን እየተጎነጨ ነበር። በእንግዳ ድርጊቱ የተደናገጠችው ሚስት በዝግታ አጠገቡ እየተቀመጠች፣ “ምን ሆነሃል የኔ ውድ?” ጠየቀችው። ባል በደከመ መንፈስ ሆኖ፤ “ታሪክን የኋሊት” አይነት ነገር መተረክ ጀመረ። “ትዝ ይልሻል? ከዛሬ 20 ዓመት በፊት ገና ፍቅር ስንጀምር አንቺ የ16 ዓመት ልጃገረድ ነበርሽ። ፍቅር ሸፍኖን፣ ስሜት ተጭኖን በወጣትነት ትኩሳት ውስጥ ስንላፋ፣ ትዝ አለሽ?” ከመጠጡ መጎንጨቱን ሳይዘነጋ፤ አይኑን ዓይኗ ላይ እንደተከለ ጠየቃት።

“በጣም እንጂ የኔ ውድ! ያ የአፍላነታችን ጊዜ እንዴት ሊረሳኝ ይችላል። በተለይ ደግሞ ካንተ መኪና ኋላ ፍቅር ስንሰራ አባቴ ደርሶ የተናገረህን አልረሳውም” ስትል ሳቅ እየተናነቃት ተናገረችው። ባል ግን በሀዘን ተውጦ እንደተከዘ፣ “እኔም ዛሬ ላይ ቆሜ ያንን ዛቻቸውን አልረሳውም። ትዝ ይለኛል ፍቅር ስንሰራ ደርሰው፤ ሽጉጣቸውን ግንባሬ ላይ እንደደቀኑብኝ፣ “ለአቅመ ሔዋን ያልደረሰች ልጄን ተኝተሃታልና የግድ ታገባታለህ፤ አለበለዚያ ግን የ20 ዓመት እስራት ይጠብቅሃል ነበር ያሉኝ” ባል ይሄን ተናግሮ ለጥቂት ሰኮንዶች ዝም አለ። ሚስት ግን የነባሩ አመጣጥ አልገባትም ኖሮ፣ “ታዲያ ይሄንን ነገር ዛሬ በምን አስታወስኸው ነው እንዲህ የተከዝከው?” ብትለው ባል ምን ቢመልስ ጥሩ ነው? “ይሄኔ አባትሽ እንደዛቱብኝ ታስሬ ቢሆን ኖሮ ልክ በዛሬዋ ዕለት የ20 ዓመታት ግዞቴን ጨርሼ ከእስር ነፃ እወጣ ነበር” ብሎላችሁ እርፍ. . . ይህቺ ናት ጨዋታ ማለት ይሄኔ ነው ጎበዝ!

ለካንስ ባል ትዳሩ የቁጭት እስር ቤት ሆኖበታል። ሚስኪኑ አልጄሪያዊ ግን የቸኮለ አልመሰላችሁም? እኔ የምለው ግን የምር- የምር እንነጋገር ከተባለ የኮስሞቲክስ ነገር አልበዛባችሁም እንዴ?. . . ደግሞ’ኮ የሚደብረው ኮስሞቲክስ በሴቶቻችን ፊት ላይ ብቻ ሳይሆን፤ በጋዜጦች ፊትም፤ በሬዲዮኖች ፊትም፣ በቴሌቭዥን ፊትም ይህውና በፈረደበት ፌስ ቡክም ፊት ቢሆን “ኮስሞቲካል” መልክና ወሬ እንደጉድ ሆኗል።

ድምጻዊት ዘሪቱ ከበደ እንዳለችው ሁሉ ነገር ከምር ይልቅ የአርቴፊሻል ክምር መሆን በዝቶበታል። በቲቪ የምናየው ምስልና የሚሰጠን የተስፋ ቃል በኮስሞቲክስ እንደተብለጨለጨ ጊዜያዊ ውበት ከሆነ ምን ዋጋ አለው። እንደክፉ ደላላ የውሸት ቃል ከሚገባ አለቃ፤ የውሸት ተስፋ ከሚሰጥ አለው ባይ፤ የውሸት ፍቅር ከሚያሳይ ወዳጅ፤ የውሸት ከሚስቅ አስመሳይ ሁሉ አንድዬ ይሰውረን አቦ። እዚህች’ጋ አንድ ፖለቲከኛና አንዲት የቡና ቤት ሴት አደረጓት የተባለችን ወግ ልጥቀስ። ሰውዬው አንድ ሁለቴ ከቀማመሰ በኋላ የእንትናዬን ጉንጭ እየደባበሰ “እኔ የምጠላው ምን እንደሆነ ታውቂያለሽ ውሸት ነው፤ አንድም ቀን ዋሽቼ አላውቅም” ሲላት “ለመሆኑ ስራህ ምንድነው?” ጠየቀችው “ፖለቲከኛ” ሰውዬው መለሰላት ይሄኔ እርሷ ሆዬ ምን ብትለው ጥሩ ነው፣ “አንተ ዋሽተህ አታውቅም ማለት እኔ ለዘመናት የቡና ቤት ሴት ሆኜ ድንግል ነኝ ማለት ነው” ብላላችሁ እርፍ። ቂ-ቂ-ቂ-

ስለፍቺ ካነሳን አይቀር ፌስቡክ ነክ ፍቺን እንጥቀስ እስቲ። በድረ-ገፆች ከአስቂኝ የፍቺ አይነቶች መካከል ገና በሁለት ወር የትዳር ዕድሜ ውስጥ ፍቺ የጠየቀችው ሴት ነበረች አሉ። ምክንያቷ ደግሞ ባሌ የፌስቡክ ግላዊ መግለጫውን (status) “ነጠላ ነኝ” የሚለውን “አግብቻለሁ” ወደሚለው ለምን አልቀየረም የሚል ነበር፡ ፍርድ ቤት የቀረቡት ሁለቱ ባልና ሚስቶች ብዙ መነጋገሪያ የሆኑ ሲሆን፤ ባል ይህን ለውጥ የረሳሁት በእጅጉ በስራ ተጠምጄ ነውና ይቅርታ ይደረግልኝ ማለቱም ተጠቅሷል። ዜናው አያይዞም ፌስ ቡክ በአለማችን ላይ ለፍቺ ምክንያት ከሚሆኑት አምስት ቀደምት ምክንያቶች መካከል አንዱ እየሆነ መምጣቱንም አስታውሷል። ጉድ አትሉልኝም ጎበዝ!

 እናላችሁ ማታ “አንቺ ልጅ ማሬ -ማሬ” ስንላት አምሽተን፤ ጠዋት ላይ “አፋቱኝ ወይኔ-ወይኔ” ከምታሰኝ “ኮስሞ” ስሪት ሴት፣ ኧረ! ምን ሴት ብቻ በኮስሞ ከሚብለጨለጭ ፍንዳታ ወንድ!. . . ይጠብቀን አቦ፤ ቸር እንሰንብት

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
3659 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 133 guests and no members online

Archive

« August 2018 »
Mon Tue Wed Thu Fri Sat Sun
    1 2 3 4 5
6 7 8 9 10 11 12
13 14 15 16 17 18 19
20 21 22 23 24 25 26
27 28 29 30 31    

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us